ዘነበ በቀለ

ርዕሱ ብዙዎችን ያሳስታል ብዬ አልገምትም። የሁለቱንም ዘፋኞች ሙዚቃ አገናዝቦ መረዳት የሚቻል ነውና። አሪታ በልጅነት ዘመኗ ”ሬሰኩዩሚ” እያለች ያቀነቀነችው ሙዚቃ በአንድ በኩል የሙዚቃው ርዕስ ጭንቀቷን ገላጭ ቢመስልም፤ በሌላ በኩል ደግሞ የድምፅዋን ልክ ያሳየችበት ዕፁብ ድንቅ የሆነ ዜማዋ ነው። ኢትዮጵያዊቷ አሪታ ፍራንከሊን ደግሞ በባህላዊ መንገድ ችግርን አምቆ መያዝ እንጂ ለአደባባይ አስጥቶ ማሳየት የተለመደ አይደለምና ሁሉን ቻይ ሆና መከራዋን የምትገፋው ድምፃዊቷ ማሪቱ ለገሠ ነች።

 

ማሪቱ ከአሪታ ጋር የምትመሳሰልበትና የምትለያይበት ጉዳይ አለ። የምትመሳሰለው በድምፅ ገደቧ ማለትም የሶፕራኖ ድምፅን ገደብ ሙሉ በሙሉ አጠናቃ የምትጫወት መሆኗ ሲሆን፤ የምትለያየው ደግሞ አድኑኝ በማለት እንደ ማሪታ አለመጠየቋ ነው። ማሪቱ በሀገራችን ውስጥ የሶፕራኑ ድምፅ ገደብን ጠብቃ የምታቀነቅን ምንም አይነት የፎልሴቶ አዘማመር ጠባይን የማትከተል በይበልጥም የጉሮሮ አዘማመር ባህርይን የያዘች ብቸኛ ዘማሪ ነች። ከሷ ጋር ተመሳሳይ አዘማመር ባህርይ የምትከተለው ብዙነሽ በቀለ ስትሆን የዜማ ስኬል ገደባቸው አንድ ቢሆንም ባሠራር ቴክኒክ ይለያያሉ። ብዙነሽ የመተላለፊያ ዜማዎችን በትናጋ፤ በራስና በላንቃ አዘማመር ፈሊጥ አስቸጋሪውን ቦታ ስታልፈው፤ ማሪቱ ግን ልክ እንደ አሪታ ፍራንክሊን ፊት ለፊት ተጋፍጣ ድምፅ የምትፈጥረው ያለምንም ቮይስ ማስክ መሆኑ በ”አምባሰል” ሙዚቃዋ ላይ ይንፀባረቃል። ማሪቱ የባህል መገለጫ ናትና አምባሰልን ስትዘምር በትክክለኛ ቶንና ስሜት ነው። ያም የሆነው አምባሰል ቅኝት የሚቃኘው በብሩህ ተስፋ አመላካችነት ስሜት ላይ በመሆኑ የማሪቱ ድምፅ ከርቀት ሆኖ የሚጣራ የተስፋ ምልክት ድምፅ ነው። ከዚህ ሌላ ቃላቶቿ ግልፅና ተደማጭ መሆናቸው ከአሪታ ጋር ያመሳስላታል።

 

ያለመታደል ሆኖ በሀገራችን ውስጥ የተፈጠሩ የሙያው ሰዎች ምንም ጊዜ በሙያቸው ተጠቅመውበት አያውቁም። ነፍሱን ይማረውና ታዋቂው የክቡር ዶ/ር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ የልጅነት ዘመኑን በሙሉ ሰውን በማዝናናት ሲያሳልፍ ለሕይወቱ የሚበጀው ሀብት አልሰበሰበም ነበር። ታምራት ሞላ፤ አለማየሁ እሸቴ፤ መልካሙ ተበጀ፣ ሙሉቀን መለሰ፣ ... ወዘተ በሕይወታቸው ገንዘብ ለማበጀት አልሮጡም። ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ስጦታ ያላቸው አርቲስቶች በትምህርት ዕውቀታቸውን የገነቡ አርቲስቶች ሁሉም አይነት አሏት። ነገር ግን አንዳቸውም በሙያቸው ተጠቃሚ ሆነው አያውቁም። ለምን እንዲህ ሆነ? ብሎ መጠየቅ ይቻል ይሆናል፤ ገንዘብ ባለመፈለጋቸው? ሁኔታው ስላልተፈጠረላቸው? መልስ ለመስጠት የራሱ ጥናት የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው። አንዳቸውም ተጠቃሚ አለመሆናቸው ግን ያለ ሐቅ ነው። ሻለቃ ሳህሌ ደጋጎን ያህል አቀናባሪ የትም ተጥሎ የሽምግልና ዘመኑን በችግር እየገፋ ላለፉት ሰባት ዓመታት ከአልጋ ሳይወርድ መጋቢት 5 ቀን 2002 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም ለአንዴና ለዘለዓለሙ አጥተነዋል። በኃይሉ እሸቴ በሕመም ሲሰቃይ ነበር ሲባል ሰምተናል። ታላቁ ደራሲ ተስፋዬ ለማንስ ከምን ላይ እንደሆን የሚያውቅ አለ? ጌታቸው ካሣስ? አረ ስንቱ! ...

 

ይህ የሆነበት ምክንያት ታላላቅ የሙያው ጠበቆች እንደ ፕሮፌሠር አሸናፊ ከበደ አይነቶቹ ባለመታደል ለሀገራቸው መሬት ሳይበቁ ያለፉ ናቸው። ሆኖም ግን በኖሩበት ዘመን ሁሉ የሙዚቃን ደረጃ ከፍ ለማድረግ ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም። ያ! ጥረት ሰምሮ ቢሆን ኖሮ ዛሬ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ቢገፉት የማይነቃነቅ ሙያዊ ማኅበር በሆነ ነበር። ያለ ሙያ ማኅበር ደግሞ መብትን ማስከበር የሚታሰብ አይሆንም። ውጤቱ ለአንዳንድ አጭበርባሪዎች ሲሳይ ሆኖ መሰንበት ነው። በመጨረሻም ለሕመሙም ሆነ ለእርጅናው ዘመን የሚደርስለት ለአርቲስቱ ሁሉ የራሱ እንጉርጉሮ ሆኗል።

 

ሙዚቀኛ የህዝብን ጭንቀት ተጋሪ በመሆኑ፤ ከህዝብ ጭንቀትን ከሀገር ባህልን ይወርሳል። ስለሆነም በበሽታ የመጠመጃው ዕድል ከፍተኛ ነው። ልክ እንደማሪቱ በተፈጥሮ ፀጋቸው ያለምንም ፎርማል የድምፅ ልምምድ ተፈላጊው እርከን ላይ የደረሱ ጥቂት አይደሉም። አሪታ ፍራንክሊን በቤተክርስቲያን ዘማሪነት ያዘማመር ፈሊጥን አውቃለች። የኛዎቹ ለማ ገብረህይወትና ማሪቱ ለገሰ ከከፍተኛው የድምፅ አወጣጥ ደረጃ ላይ ያሉ ናቸው። ግን አስተማሪያቸው ምናልባትም ለማሪቱ የጦሳ ተራራ፣ ለለማ ገብረሕይወትም የቡልጋ ተራራ ሊሆን ይችላል። በገደል ማሚቱነት የተባበራቸው (reciprocal በሆነ አቀራረብ የተባበራቸው)።

 

በሀገራችን ሙዚቃ ላይ የየራሳቸውን ስታይል ትተው ያለፉም ያሉም ሙዚቀኞች በርካታ ናቸው። ለምሳሌም ያህል፦ ማሪቱ ለገሠ፤ ብዙነሽ በቀለ እና ለማ ገብረሕይወት የሶል ሙዚቃ ስታይል፤ ዓለማየሁ እሸቴ - ”ኢትዮ ሮክንሮል”፤ ጌጡ አየለ፣ መልካሙ ተበጀ፣ ትዕግስት ፋንታሁን እና አበባ ደሳለኝ - ”ካባሬት ሙዚቃ”፤ ባህታ ገብረሕይወት፣ ሙሉቀን መለሰ እና አስቴር አወቀ - ”ሪዝም ኤን ብሉስ”፤ እማሆይ ፅጌ ማርያም ገብሩ - ”ኢትዮ ክላሲካል ፒያኖ” በተለይም የሜንዶልሰንና የሹበርትን አጨዋወት ስልት የተከተለ፤ አሸናፊ ከበደ - ”ሲምፎኒክ ፖየም” ለፍሉትና ለስትሪንግ መሣሪያዎች፤ ነርሲስ ናልባንዲያን - ኳየር፤ ከዚህ ሌላ በየጨዋታዎቹ ላይ የየራሳቸውን ችሎታ ያበረከቱ በርካታ ናቸው ለመጥቀስ ያህል ጌታ መሳይ አበበ በትዝታ ላይ፤ ጌታቸው ካሣ እና በዛወርቅ በትዝታ ላይ፤ የግጥም አጠቃቀምን ከባህላዊው የወል ግጥም ስሪት ወጣ ባለ መልኩ አዲስ ስታይል በማቅረብ ያበረከቱ ደግሞ ንዋይ ደበበ፣ ቴዲ አፍሮ፣ ጎሣዬ ተስፋዬ፣ ፍቅር አዲስ ነቅዓጥበብ እና ትዕግስት በቀለ ሲሆኑ፤ ተሾመ ምትኩ፣ መልካሙ ተበጀ እና ፍሬው ኃይሉ ትሩባዱር ስታይልን በማስተዋወቅ፤ ... ወዘተ ይገኙበታል። ጥላሁን ገሠሠ፤ ታምራት ሞላ፤ መሐሙድ አህመድ እና ዓለማየሁ እሸቴ በሶል፤ በጃዝ፤ በሪዝም ኤን-ብሉስ እና በሮክንሮል ውስጥ በርካታ ጨዋታዎች አሏቸው።

 

ባጠቃላይ ሙያቸው ሌላውን እንጂ እራሳቸውን ያልጠቀመ በሕይወት ያሉና ያለፉ በርካታ የሙያው ሰዎች መኖራቸው የማይታበል ነው። ካሣ ተሰማ ክራሩን በየሄደበት ከተጫወተ በኋላ ይሰብር ነበር። ሲጠየቅም ”እኔ ቧምቧ ሰሪ እንጂ ሙዚቀኛ አይደለሁም” የሚል መልስ ነበር የሚሰጠው። ብስጭቱ ምን እንደሆን ግን ሳይታወቅለት ነው ያለፈው። አስናቀች ወርቁ በክራር፤ አሰፋ አባተ በመሰንቆ፤ የመጀመሪያውን ያገር ባህል ኦርኬስትራ የመራው እዩኤል ዮሐንስ በድርሰትና በዝማሬ። መዲናና ዘለሰኛ ይጥና ታደገኝና አለማየሁ ፋንታ፤ ገረርሶ ወሰኑ ዲዶ በመሰንቆ፤ አርጋው በዳሶ በዝማሬ፤ በኦሮሞኛና በአማርኛ አቀላጥፎ የሚጫወተው አበበ ተሰማ በዋሽንት መላኩ ገላውና አፈወርቅ ወደር አይገኝላቸውም። ሁሉም ለዚህ ሙያ ከፍተኛ አሰተዋጽዖ ያበረከቱ የሙያው ሰዎች ነበሩ። ናቸውም። በሙያቸው ተጠቅመውበታል? አይመስለኝም። የሙዚቃ ጥበባቸውን እንደዘሩ ሳይሰበስቡት ያለፉም በሕይወት ያሉም አሉ። ይህ ችግር በቀጣይነት የሚዘልቅ ለመሆኑ አሁንም ያለው የሙያው ሰዎች አለመሰባሰብ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደርጋል። ስለዚህም ስቶክሆልም የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሙዚቃና ድራማ ግሩፕ ሁሉም በያለበት ተደራጅቶ የጋራ ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ማኅበር እንዲመሰረት ጥሪውን ያቀርባል። ተመሳሳይ ግንዛቤ ካለዎት አስተያየትዎን በሚቀጥለው አድራሻ ያድርሱን።

የኢትዮጵያ ሙዚቃና ድራማ ግሩፕ

www.kitabethiopia.com

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!