Artist Tilahun Gesesse (Photo Zethiopia)ጥላሁን ”የኦፔራ የወርቅ ማንኪያ ነክሶ የተወለደ ነው” ሲሉ ወዳጆቼ ይመሰክሩለታል። በተፈጥሮ ተስረቅራቂ ድምፅ ማግኘቱ፣ መልከ መልካምነቱ፣ በሚያውቁት ሁሉ ዘንድ ተወዳጅ መሆኑ ዕድለኛነቱን ይመሰክራሉ። በተለይም ጎላ ጎላ ያሉ ዓይኖቹን ወዲያና ወዲህ ሲያንከባልላቸው ግርማ ሞገሱን ከፍ ያደርጉለት ነበር። ”ቁልጬ” የሚል የቅጽል ስም አስገኝቶለታል። ተወዳጁ ልዩ ተሰጥዖውን የሚያሳይበት መድረክ ያለብዙ ውጣ ውረድ ማግኘቱ ለዕድለኝነቱ አንዱ ማሳያ ነው።

 

የ1943 ዓ.ም. የራስ ጎበና መድረክ ግን ልዩ ፈተና ነበረበት። አንድ ትልቅ እንግዳ ማስተናገድ ይጠበቅባት ነበር - ደጃዝማች ሀብተሥላሴ በላይነህን። በወቅቱ ደጃዝማች ሀብተሥላሴ የወሊሶ ከተማ ሀገረ ገዥ ተብለው በንጉሡ ይሾማሉ። የእሳቸው መሾም ከአቅሟ በላይ እንግዳ የመጣ ያህል የተሰማት ከተማ ግን አቀባበሉ ጭንቅ ጥብብ ብሏት ነበር። በምን መስተንግዶ ትቀበላቸው? ... ምጥ ነበር።

 

መፍትሔ ዘግይቶም ቢሆን አልጠፋም። በወቅቱ ለከተማዋ ”አንድ ለእናቱ” የነበረው ራስ ጎበና ትምህርት ቤት የመስተንግዶውን ኃላፊነት ይወስዳል። ያለምክንያት አልነበረም። ብቸኛዋን የከተማዋ ”ኦፔራ ሐውስ” በመተማመን ነበር። ”በኦፔራ ሐውስ” ውስጥ ደግሞ ቀልጣፋው እና ንቁው ጥላሁን ገሠሠ ይገኛል። ትምህርት ቤቱ የመስተንግዶውን ሙሉ ኃላፊነት ቢወስድም ሸክሙ የወደቀው በጥላሁን በሚመራው የመዝሙር ቡድን ላይ ነበር።

 

ጥላሁን ይህችን አጋጣሚ እንደ ቀላል አልተመለከታትም። ለወትሮውም ቢሆን ከመዝሙር ባሻገር ያለው ዓለም የማይማርከው አዳጊ፤ ሙሉ ትክሩቱን ”ኦፔራ ሐውስ” ውስጥ አደረገ። ልጆችን አደራጀ፣ አሠለጠነ፣ ለመድረክም ብቁ አደረጋቸው። የመዝሙር መምህርቷ በቀለች ይማም ድጋፍ ደግሞ ጥረቱን የሚያግዝለት ሆነ።

 

እንግዳው ይመጣሉ የተባሉበት ዕለት ልዩ ነበር። ከተማዋ ከወትሮው በተለየ ደምቃ ነበር። ”ኦፔራ ሐውስ”ም በከተማው ነዋሪዎች እና በደጃዝማቹ አንጋቾች ተወሮ ነበር። ደጃዝማች ሀብተሥላሴ የክብር ቦታቸውን ሲይዙ የሚጠበቀውን የአቀባበል ሥርዓት ፊቱን ወደ መድረኩ አዞረ። በቃ ”የመዝሙር ፊደሉ” ጊዜ ደረሰ። ከደቂቃዎች በኋላ ጋሻ እና ጦር ያነገተ በአስረቅራቂ ድምፅ የሚሸልል አዳጊ ከአጃቢዎቹ ጋር መጋረጃውን ገልጦ መታየት ይጀምራል። ጦሩን እየሰበቀ ጋሻውን እንደ ክንፍ እየወጠረ ይቀዝፈው ጀመር።

 

”ዘራፍ! ገለሌ ገለሌ ...

ደሞ ገለሌ

ገለል በል ገለሌ

ዘራፍ ዘራፍ ሲል ነው፤ የወንድ አብነቱ

ሴትም ትዋጋለች ከነጋ መሬቱ

ገለሌ ... ገለሌ ... ገለሌ

ደሞ ገለሌ! ዘራፍ ...”

ማለት ሲጀምር ከመድረኩ ፊት ለፊት የተቀመጡት ደጃዝማች ወኔያቸው ተቀጣጠለ። ”ባለ ዘራፉ” የአምስት ዓመታት የአርበኝነት ጊዜያቸውን ቀሰቀሰባቸው። ጊዜ አላጠፉም። ሽጉጣቸውን አውጥተው ወደ ላይ እየተኮሱ የእነ ጥላሁንን ሽለላ ይቀላቀላሉ። አጃቢ የነበሩት አዳጊ ልጆች እና ተመልካቹ ግን ተደናግጠው ከ”ኦፔራ ሐውስ” ይሸሻሉ። ”መድረኩ የሁለቱ ሸላዮች ብቻ ሆነ። ”እኛ ደንግጠን ከሸሸንበት የተመለስነው የተኩሱ ድምፅ ሲጠፋ ነበር” ይላሉ፤ በወቅቱ ጥላሁንን አጅበው በመድረኩ ይተውኑ ከነበሩት አንዷ ወ/ሮ በቀለች ማሱድ። አዳጊው ልጅ ግን ለመድረክ የነበረውን ፍቅር በድፍረት ገለፀ። ”በኦፔራ ሐውስ” የመድረክ አልጋ ወራሽነቱን አክሊል በመድፋትም ትልቁን ጉዞ ”ሀ” አለ። የመጀመሪያውን የክብር ሽልማት በደጃዝማች የ20 ብር ኖት አኀዱ አለ።

”አዲስ ነገር” ጋዜጣ ሚያዝያ 17 ቀን 2001 ዓ.ም.

ማስታወሻ

በሚያዝያ ወር 1960 ዓ.ም. የታተመው ”አዲስ ዘመን” ጋዜጣ የሕይወት ታሪካቸው እንደሚገልፀው ደጃዝማች ሀብተሥላሴ በላይነህ በአምስት ዓመቱ የፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ዘመን በጀግንነታቸው የታወቁ ታላቅ አርበኛ ነበሩ። በዚህ የአርበኝነታቸው ጊዜ ከገደሏቸውና ከማረኳቸው የጣሊያን መኮንኖች መካከል ጄኔራል ጋሊያኒ እና ጄኔራል አውግስትኒን ይገኙበታል።

 

በመጨረሻም የጣሊያን ጦር አዛዥ የነበረው ጄኔራል ናዚን ጐንደር ላይ በተደረገው ከባድ ውጊያ በኋላ ማርከውታል።

ሀብተሥላሴ ስለሺ (ጌቱ)

ፈረንሣይ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!