Mulatu Astatkeክንፈ ሚካኤል ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

ታላቁ መራሔ ሙዚቃ፣ አቀናባሪና ደራሲ ሙላቱ አስታጥቄ ባለፈው ወር መባቻ ላይ እንደ ዓመተ እግዚእ ከግንቦት 1 - 3 ምሽት እዚህ ሜልበርን ተዘጋጅቶ በነበረው ዓለም አቀፍ የጃዝ ሙዚቃ በዓል ላይ ተጋብዞ ለሦስት ቀን ከመክፈቻው ዕለት ግንቦት ቅዳሜ 1 ቀን 2 ሰዓት ገደማ ጀምሮ እሁድና ሰኞን ምሽት ጣዕም ያላቸውን የመሣሪያ ቅንብሮቹን ለታዳሚው አቅርቦ አስደስቷል።

 

 

በዚህ አጋጣሚም ከልጅነቴ ጀምሮ የማደንቀውን ታላቅ ሰው ባይነ ስጋ ለማየት በመብቃቴ እጅጉን ደስ ብሎኛል። ትዝ እንደሚለኝ ከሆነ ከውጭ ገብቶ ሥራውን ሲጀምር በየክ/ሀገሩ እየዞረ ሙዚቃውን በማሰማት ራሱንና ሥራውን ላገሬ ህዝብ አስተዋውቋል። በዚያን ጊዜም ሐረር በሚገኘው ራስ ሆቴልም አንድ ምሽት ተዘጋጅቶ ስለነበር ተበትኖ የነበረውን ማስታወቂያ (ፓስተር) አግኝቼ ለማየት ጓጉቼ እንደነበር ትዝ ይለኛል። ዛሬ በስተርጅናም ሳዳምጠው ትዝታው በተመስጦ በሐረር በኩል ጽርኅ አርያም አውጥቶኝ እየመለሰ አጅጉን ደስ አሰኝቶኛል።

 

በዕለቱ የተጫወታቸው ጥዑም ቅንብሮች አብዛኛዎቹ የ፷ቹና የ፸ቹ ሲሆኑ፤ የቅርቦቹንም ለምሳሌ ላስናቀች ወርቁ በስሟ የሰየመውን ቅንብር አሰምቷል። በዚህ ዓይነት ምሽቱን ሲያዝናናን ቆይቶ ከተሰናበተን በኋላ በታላቅ ጭብጨባና ፉጨት ተመልሶ መጥቶ ሁለት ቅንብሮችን ካሰማ በኋላ የምሽቱ ዝግጅት በዚሁ ተጠናቋል። አጅቦት የነበረው የሙዚቃ ቡድን እዚሁ ሜልበርን የሚገኝው የጥቁር እየሱስ ክበብ ነበር።

 

በዚህ ዝግጅት በትክክል ቁጥራቸውን ባላውቀውም ብዙ ኢትዮጵያውያን ታዳሚዎች በቦታው ተገኝተው ድጋፍና አድናቆታቸውን በከፍተኛ ስሜት ሲያሳዩ አምሽተዋል። ያገር ልጅ የማር እጅ እንዲሉ ሁላችንም መኑ ዝንቱ ብለን ማድነቃችን ተገቢ ነው።

 

ወደ ቤታችን ለመሄድ ስንወጣ በሩ አካባቢ አንድ ወገን ከመድረኩ ኋላ ከሙላቱ ጋር አብሮ ምስል መቀረጽ ይቻላል ብሎ ነግሮን የሰማነው በሙሉ ወደዚያው አመራን። ስንደርስ ከኛ በፊት የነበሩት አብረው ሲነሱ ደርሰን እኛም ዕድሉን አግኝተን አጅበነው ተነስተናል። መጀመሪያ የእንኳን ደህና መጣህ ሠላምታችንን አቅርበን ጉዞው እንዴት እንደነበር ጠያይቀን በበኩላችንም ዝግጅቱን ግሩም ድንቅ እንደሆነ ስናወሳ እግረ መንገዱንም የጥቁር እየሱስን አጃቢዎች ያሠለጠናቸው ሁለት ቀን ብቻ እንደሆነ ሲነግረን አድናቆቴም ኩራቴም እጅግ በጣም ከፍ ብሎና ግሎ ተሰምቶኛል።

 

አጋጣሚውንም በመጠቀም ሜልበርንን ለማሳየት ጋብዘነው እንደማይችል ነገረን። ምክንያቱም ለሊቃቶ[1] ተማሪዎች ገለፃ እንዳለበትና ማክሰኞ እንደሚመለስ ነግሮን በዚሁ ታላቁን ሙላቱ አስታጥቄን ተሰናብቼያለሁ። የማይገኝ ዕድል ከማይገኝ ሊቅ ጋር አፍታዋን አሳልፌ የዘመን እድሳት አትርፌአለሁ።

 

በቸር ይግጠመን አቦ!

[1] ሊቃቶ ማስተርስ ለማለት የቋንቋው ሊቅ መስፍን አረጋ የፈጠረውን ነው የተዋስኩት


ክንፈ ሚካኤል

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ግንቦት ፲፭ ቀም ፪ሺህ ፪ ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!