ግርማ ካሣ - መጋቢት 2000 ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

ከአሥራ አራት ዓመታት ስደት በኋላ አገሬን ለማየት ግንቦት ሰባት 1997 ዓ.ም. አዲስ አበባ ገባሁኝ። የታሪካዊውን ምርጫ ሁኔት ለመከታተል ዕድል አግኝቼ ነበር። ዛሬ ስለ ምርጫው ማወራት አልፈልግም። ነገር ግን ከፒያሳ ወደ መገናኛ ለመሄድ ሚኒባስ ውስጥ ገብቼ ያጋጠመኝን ላጫውታችሁ እፈልጋለሁኝ።

 

 

አውታንቲው “መገናኛ፣ ኮተቤ፣ …” እያለ ተሳፋሪዎችን ይጠራል። ትንሽ እንደቆየን ሚኒባሱ ይሞላና ጉዞ እንጀምራለን። ከጎኔ አንዲት ወጣት ሴት ነበረች። ትንሽ እንደሄድን እንባ በዓይኔ መፍሰስ ጀመረ። ከዚህ በፊት ሰምቼ የማላውቀው፣ አይነት በሬጌ ቢት የቀረበና ልብን የሚሰበር ቃላት ያሉት ዜማ ሹፌሩ ያጫውት ጀመር። “ይሄ ማን ነው?” ብዬ ከጎኔ ያለችውን ወጣት ጠየቅኋት። በመገረም አይታኝ “ቴዲ አፍሮ ነዋ!” ብላ መለሰች። ብዙ ጊዜ መንፈሳዊ መዝሙሮችን ስለምሰማ ድሮ ከማውቃቸው ከእንደነ ነፃነት መለሰ - ‘አረንቻታ’ እና ከቴዎድሮስ - ‘ጉዱሮዬ’ ውጭ ብዙም የዘመኑ የኪነት ባለሞያዎችን አላውቃቸውም ነበር።

 

“ይቅር በለውና የበደለን ወቅሰህ

ምህረት አስተምረን አንድ አርገን መልሰህ

 

 

ዘጸዓት ለኢትዮጵያ ወደ ተስፋ ጉዞ

ባህር የሚያሻግር አንድ ሙሴ ይዞ

ቅርብ ነው አይርቅም የኢትዮጵያ ትንሳዔ

በአንድነት ከገባን የፍቅር ሱባዔ

 

 

ፍቅር አጥተን እንጅ በረሃብ የተቀጣን

አፈሩ ገራገር ምድሩ መች አሳጣን

ኦሲሳ ኦሲሳ ኦሲሳ ማንዴላ

ይቅር አባብሎ እንዳስጣለ ቢላ

በተስፋዋ መሬት እንዲፈጸም ቃሉ

ሞፈሩን ያዙና ይቅር ተባባሉ …”

 

 

እያለ ነበር ቴዲ አፍሮ የሚያቀነቅነው። (በቅርብ ያየሁት ፎቶግራፎቹ ፀጉሩን በአጭሩ ተቆርጦ ነው እንጂ የሚያሳዩት፤ አፍሮ ሆኖ አይደለም። በዚህ ምክንያት ለምን ቴዶ አፍሮ እንዳሉት እስከአሁን ሊገባኝ አልቻለም። እንግዲህ በፊት ፀጉሪን አፍሮ ያደርግ እንደነበረ አላውቅም)።

 

 

ትዝ ይለኛል በምርጫው ውዝግብ ወቅት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ይህን በኔ ግምት እንደ ኢትዮጵያ የሕዝብ መዝሙር ሊቆጠር የሚገባውን ዜማ እያዜሙ ነበር የምርጫው መሰረቅ ላይ ያተኮረውን ተቃውሟቸውን የገለጹት።

 

 

የዜማው መልዕክት ግልጽና ቀጥተኛ ነው። አገራችን ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብት ያደላት፣ ከማንም አገር በምንም የማትተናነስ እንደሆነች፣ እኛ ኢትዮጵያውያን የደኸየነውና የቆረቆዝነው ፍቅር በማጣታችንና ይቅር መባባል ባለመቻላችን ብቻ እንደሆነ ነው ቴዲ አፍሮ ደስ በሚያሰኝ ቃና የገለጸልን።

 

 

እርስ በርስ መገዳደል፣ እርስ በርስ መባላት አይበቃንም ወይ? ነው ያለን። እጅ ለእጃችን ከተያያዝን፣ አንድ ከሆንን፣ በዘር በኃይማኖይት ካተከፋፈልን፣ ከግል ጥቅማችን አልፈን ለወገናችን ካሰብን የኢትዮጵያ ትንሳዔ ቅርብ እንደሚሆንና እግዚአብሔር አምላክም እንደሚታረቀን ነው ያስተማረን። በዚህ ዜማ ኢትዮጵያዊነትን አይቻለሁ። ፍቅርንና መተባበርን አሽትቻለሁ።

 

 

ይህ ብቻ አይደለም። ወደ አሜሪካ ከተመለስኩኝ በኋላ አንድ ወዳጄ ቤት እራት ተጋበዝኩኝ። በርካታ ሰዎች ነበሩ። ለካ ሌላ ተመሳሳይ ዘፈን ቴዲ አፍሮ ከዚህ በፊት አውጥቶ ኖሯል፤ ቀልቤን የሳበ በቪዲዮ የተቀነባበረ ዜማ ለማዳመጥ ቻልኩኝ። በሲድኒ ኦስትራሊያ ኦሎምፒክ ወቅት ወገኖቻችን ያሳዩት አኩሪ ዉጤት ላይ ያተኮረና በምሳሌያዊነት የመያያዝንና የመደጋገፍን ጥቅም ለማሳየት የሞከረበት የዜማ ቅንብር ነበር።

 

 

አንጋፋው ኃይሌ ገብረሥላሴ እግሩን በመታመሙ ወደ ኋላ ሲቀር፤ ቀነኒሳ እና ስለሺ ወደ ኋላ እርሱን ሲመለከቱ ነው ቪዲዮው የሚያሳየው። ወንድማቸው ወደ ኋላ በመቅረቱ ውስጣቸው አዝኖ እግራቸው ወደፊት እየሮጠ ዓይናቸው ወደ ኋላ ይመለከት ነበር።

 

ኃይሌ ገብረሥስላሴ፡-

“… መርቆ ሸኝቶን አገር

አሲዞን ሰንድቅ ዓላማ

መርዶ ነው ለወገናችን

ማሸነፍ ካቃተንም

ብሰለፍ ሕመሜን ችዬ

እሮጬ ላሯሩጣችሁ

ትልቁን እምነት በናንተ

ጥለናል እንግዲህ አይዟቹህ …”

 

ሲላቸው ስለሺ እና ቀነኒሳ ደግሞ በተራቸው፦

 

“… እዮሃ ከባንዲራው ነው

እዮሃ ቃልኪዳናችን

እዮሃ አታፍርም በኛ

እዮሃ ኃይሌ አባታችን …”

 

እያሉ ኢትዮጵያን፤ እንዲሁም “አባታቸውን” ኃይሌን ሲያኮሩ እናያለን።

 

አንዱ ሲደክም ሌላው እያገዘ፣ አንዱ ሲወድቅ ሌላው እየተነሳ፣ በሕብረት፣ በወንድማማችነት፣ እርስ በርስ በመተያየትና በመያያዝ አገራችንን ከውርደት ማንሳት እንደሚቻል ነው የምንማረው። የኢትዮጵያን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ባንዲራ ከሌሎች አገራት ባንዲራዎች ከፍ ብላ እንድትውለበለብ ማድረግ እንደሚቻል ነው ቴዲ አፍሮ ለማሳየት የሞከረው። ምሳሌው ሩጫ ሆነ እንጂ በሁሉም መስክ ፍቅርና አንድነት ካለን ቀዳሚ የማንሆንበት ምክንያት የለም።

 

 

ታዲያ እንደዚህ ኢትዮጵያዊ የሆኑና የሚያነቃቁ፣ አገራችን ኢትዮጵያ ታላቅ ለመሆን ያላትን አቅም የሚያጎላ፣ የአንድነትን፣ የፍቅርን፣ የሠላምን፣ የይቅርታን፣ … መልዕክትን ይዞ የሚመጣን ወጣት ማሰርና ማንገላታት እጅግ በጣም የሚያሳስብና የሚያስቆጣ ድርጊት ነው።

 

 

“መንገደኛ በመኪና ገጭተሃል” በሚል ክስ ነው ገዥው ፓርቲ ይህን ወጣት በቁጥጥር ስር ያዋለው። በርግጥ መንግሥት መረጃ ኖሮት ነውን? ወይስ ቴዲ የገዥው ፓርቲ ሰዎች ህዝብ እንዲሰማ የማፈልጉትን መልዕክቶች በማቅረቡ? በርግጥ ሕግ የበላይ መሆን ስላለበት ነውን? ወይስ ሕግን እንደ ዱላ ተጠቅሞ የተቀየሙትንና የማይስማማቸውን ሰው ለማፈንና ለማስወገድ ስለተፈለገ ነውን? በኢትዮጵያ ፍትህ እንዲሰፍን፣ ሁሉም በሕግ ፊት እኩል ስለሆኑ ነውን? ወይስ በኢትዮጵያዊነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት? … መልሱን በቅርብ ጊዜ ውስጥ የምናየው ይሆናል።

 

እስከዚያው ግን ለዚህ ወጣት ያለኝን አድናቆት በመግለጽ እግዚአብሔር ባለበት ቦታ ጽናቱንና ብርታቱን እንዲሰጠው እፀልያለሁ። በዚህ አጋጣሚ ቴዲን ኢትዮጵያውያን ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ፣ እግዚአብሔር ለሚወደው ፍቅር ልባችንን እንድናስገዛ ላደረገውና ለሚያደርገው አስተዋጽኦ እግዚአብሔር ይባርከው! እለዋለሁ።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!