Ethiopia ZareAlemayehu Dibabaዓለማየሁ ዲባባ ከስዊድን (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

ላለፉት ፶፪ ሣምንታት ዘወትር ረቡዕ ገጣሚ ማትያስ ከተማ (ወለላዬ) ”የረቡዕ ግጥም” በሚል ቋጠሮ ሃምሳ ሁለት ግጥሞችን በኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ላይ ሲያስነብበን ቆይቶ፤ የመጨረሻውን ቁጥር ፶፪ን ባለፈው ሣምንት ረቡዕ አስነብቦናል። በግጥሞቹ ላይ አንባብያንና ባለሙያዎች ያላቸውን አስተያየት ይሰጡ ዘንድ ተጋብዘዋል። በተለይም የሥነግጥም ሃያስያን መድረኩን ይጠቀሙበት ዘንድ የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ዝግጅት ክፍል በአክብሮት እየጋበዘ፤ የዓለማየሁ ዲባባን አስተያየት ፩ በማለት ታነቡ ዘንድ ይጋብዛል።

 

Ethiopia Zareገጣሚ ማትያስ ከተማ በተለያዩ መድረኮች እንዲሁም በየድረ ገጹ፤ በተለይም በኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ሣምንታዊ ግጥሞቹን በማስነበብ ይታወቃል።

 

አንድ የግጥም ግምገማ ላይ ፕሮግራም መሪ ሆኖ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘሁት ዕለት ሌላም ተሰጥዖ እንዳለው አይቼለት ነገሬዋለሁ። የአንድ ሰውን ተሰጥዖ የሚያዩት ሌሎች ናቸው እንደሚባለው መሆኑ ነው። ማትያስ ጥሩ የመተረክ ችሎታና ለትረካ የሚሆን ጥሩ ድምፅም አለው። ከዚያ በኋላ ያዳመጥኩለት ንባቦቹና ትረካዎቹ ይህንኑ ችሎታውን ማሳያ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ። ብዙዎች ይህንኑ ምስክር እንደሚሰጡ ስለማምን ወደፊትም ብዙ እናዳምጥለታለን ብዬ ተስፋ አድርጋለሁ።

 

”የረቡዕ ግጥም” ለምን ተባለ? አጫጭር ግጥሞችን፤ ”ወለላዬ” የሚለውን የብዕር ስምስ ለምን መረጠ? ወደ ገጣሚነት እንዴት ገባ? ሌሎችንም ጥያቄዎች አስመልክቶ የጀርመን ድምፅ ራዲዮ ላይ የሰጠውን ቃለምልልስ አድምጣችሁም ይሆናል። (ቃለምልልሱን ለማዳመጥ እዚህ ይጫኑ!)

 

ከአንድ ሣምንት በፊት በስልክ ሽቦ የድምፅ መልዕክቱ በኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ላይ ያስነብበን የነበረውን የግጥም ሥራ አንድ ዓመት መሙላቱን ምክንያት አድርጎ እንደሚያቆም ሲነግረኝ እንደ ኃዋርያው ጳውሎስ ሩጫዬን ጨርሻለሁ ባለው ቃና ነበር።

 

ቁጥር ፶፪

የረቡዕ ግጥም ሣምንቱ ሲሰላ

ሃምሳ ሁለተኛው ድፍን ዓመት ሞላ

እኔም ከቀኑ ጋር እየሮጥኩ አብሬ

በዚህ አበቃሁኝ ሥራዬን ቋጥሬ

 

የሃምሳ ሁለተኛ ቁጥር ግጥሙም ይህን አመላካች ነው።

 

ይህ ሥራው ይቁም እንጂ በቀጣይ ግጥሞቹ ላይ ትኩረት ያደረጉ የግምገማ ጽሑፎች እንደሚወጡ ሲገልጽልኝ፤ የመጀመሪያው ሣምንት የግምገማ ጽሑፍ የእኔ እንዲሆንለት ፍላጎቱ እንደሆነም በደስታ ነበር።

 

በእርግጥም የግምገማ ጽሑፍ እሠራባቸዋለሁ ብዬ በፕሮግራም ከያዝኳቸው ዝርዝር ውስጥ የማትያስ ግጥሞች ቢኖሩም፤ እንዲህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብሎም ባለኝ እጅግ የተጣበበ ሁኔታ ውስጥ ይሆናል ብዬ አልገመትኩም።

 

በሌላ ጊዜ ተጨማሪ ሰፋ ያለ ግምገማ ልሰጥበት አሊያም ለሌሎች መነሻና ማጣቀሻ ሊሆን የሚችል አጭር የግምገማ ጽሑፍ አዘጋጅቻለሁና እንሆ!

 

ጥያቄ በማንሳት ልቀጥል …

 

ለመሆኑ አጭር ግጥም የሚባለው የቱ አይነት ነው?

 

ብዙ አይነት መልስ እንደሚሰጥ ስለምገምት መጠይቄን መሰረት ያደረገ ትንሽ ፍተሻ አዘል ንባብና ጥናት ካደረኩበት ጉዳይ ላይ ካሰፈርኩት ቀንጭቤ ላካፍላችሁና ወደማትያስ ግጥሞች ግምገማ አመራለሁ።

 

ለመጠይቁ የእኔ ምላሽ አጭር ግጥም የሚባል የለም የሚል ነው።

 

ግጥሞች በይዘትና ቅርጻቸው፤ አይነትና ግጥማዊ ዘያቸው ስያሜ ስላላቸው አጭር ግጥም ይሄኛው አይነት ነው ለማለት አይቻልም።

 

አንዳንድ ጽሑፎችና ለመጠይቁ ምላሽ የሚሰጡ ለሙያው ቅርበትም፤ ፍላጎትማ ያላቸው ሰዎች የሓይኩን የግጥም አይነት ከግጥም አይነቶች አጭሩ ነው የሚሉ አሉ።

 

ነገር ግን ስንኝ በማጠሩ ከሆነ አጭር ግጥም የሚባለውን ስያሜ የሚውስድ ሌላ አይነት የግጥም አይነት እንዳለ ማሳየቱ ለብዙዎች ጥሩ ግንዛቤ ሰጪና ትምህርታዊም ይሆናል ብዬ አምናለሁ።

 

በሁለት ስንኝ ላይ ብቻ ተመስርቶ በማለቂያቸው ላይ በተመሳሳይ ቤት እንዲመታ እየተደረገ የሚጻፈው የኮፕሌት (couplet) የግጥም አይነት በማሳያነት ይቀርባል። ይህ የግጥም አይነት በአጻጻፉም ስልት ቀላል የሚባለው ነው።

 

ይህን የእንግሊዘኛ ግጥም በምሳሌነት መመልከት ይቻላል።

 

Grandmother sits in her old rocking chair.

She rocks and she rocks all day there.

 

በአማርኛም ግልጽ የሆነ ምሳሌ ለመስጠት ያህል የግጥም አይነቱ እንደ አንዳንድ ሕዝባዊ/የወል ግጥሞች፤ ወይም አገር ቤት በመንገድ ላይ እየተነበቡ የሚሸጡ ግጥሞችን አይነት ያመላክታል።

 

ምሳሌ፦

ልጄን፤ ልጄን ስትል እናት እንደ ሻማ

በርታ ትቀልጣለች አልቃ ተንጠባጥባ

ዓዲ

 

የሓይኩ (Haiku) ግጥም ደግሞ በመሰረታዊው ጃፓንኛ በ17 የቀለማት ክፍልፋይ ተወስኖ በሦስት መስመር ላይ ቆሞ እናገኘዋለን። ይህ የ5/7/5 ቀለማት ድምር በእንግሊዘኛ ስልት የቀለማት ብዛቱ ላይ ያለውን የድምፅ ክፍልፋይ ቃና እንዲጠብቅ በማድረግ በ11 ቀለማት እንደሚጻፍም ነው።

 

የእንግሊዘኛው የሓይኩ አጻጻፍ ስልት 5/7/5 ቀለማትን በሦስት መስመሮች ላይ የሚመሰርት ቢሆንም፤ በቀለማት ቁጥር ብዛት አጠቃቀም ላይ ለጸሐፊው የተወሰነ ነፃነትንም ይሰጣል። ይሁን እንጂ በሦስት መስመር ላይ መሰደሩ ግን የግድ ነው።

 

ሓይኩ ተፈጥሮን እንደየሁኔታው የመግለጽ ይዘቱን መጠበቅ ይኖርበታል። አስገራሚ የሃሳብ አገላለጽ ኃይሉን ለማሳየት በሁለት ከግማሽ የተከፈለም ነው።

 

ሓይኩን በአማርኛ ለመጻፍ ቃላቶቹ በቀለማት የደመቁ በመሆናቸው የ5/7/5 ስልትን እንድንከተል ሊያስገድደን አልቻለም።

 

በመሆኑም በሁለት መሰረታዊ ነጥቦች የሓይኩን የአጻጻፍ ስልትና ይዘት ሳይለቅ በአማርኛ የሚጻፍበትን ዘዴ ማስተዋል ይቻላል።

 

አንድም በእንግሊዘኛው የሓይኩ አጻጻፍ ስልት ላይ በቀለማት ቁጥር ብዛት አጠቃቀም ላይ ለጸሐፊው የሚሰጠውን የተወሰነ ነፃነት በአግባቡ በመጠቀም፣

 

ሁለትም በመሰረታዊው የጃፓንኛ ሓይኩ ላይ ያለውን የ17 ቀለማት ክፍልፋይ የድምፅ ቃና ርዝመትን በመጠበቅ በእንግሊዘኛው የአጻጻፍ ስልት የ5/7/5 የቀለማት ክፍልፋይ የድምፅ ቃናውን መጠን እንዲተካ በማድረግ መጻፍ እንደሚቻለው፤ በአማርኛም ይህን ሥርዓት መሰረት አድርጎ ሓይኩ ይገጠማል።

 

ከዓለማየሁ ታዬ የሓይኩ (bilingual) መጽሐፍ ላይ የእንግሊዘኛ እና የአማርኛ ሓይኮችን ቀጥሎ በምሳሌነት ማየት ይቻላል።

 

Womb of deep darkness

Gives birth to a blessed fall

Replenishing earth

 

ተሲአት

አፍ ላፍ ገጥመው በቀቀኖች

ፀሃይን ያማሉ

 

እንግዲህ ከዚህ ማሳያ ትንታኔ መገንዘብ እንደሚቻለው ስንኝ እየተቆጠረ አጭር ወይም ረዥም ግጥም የሚባል ስነጽሑፋዊ ስያሜ እንደሌለ ነው።

 

መነሻ ባደረኩት መጠይቅ ላይ አጭር ትምህርታዊ ትንታኔ መስጠት ያስፈለገኝ የማትያስ ግጥሞችን እርሱም ሆነ ብዙዎች አጫጭርና የረቡዕ ግጥሞች በሚል ስያሜ ስለሚጠሯቸው አንድም ግንዛቤ ለመስጠት ሁለትም ግጥሞቹ ከየትኛው የግጥም አይነት እንደሚመደቡ ማስረዳት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን በማመን ነው።

 

የማትያስ ሣምንታዊ የኢትዮጵያ ዛሬ የድረ ገጽ ግጥሞች እንደ አንድ ግጥም አይነት በይዘትና ቅርጻቸው ስያሜ እንጂ በአጭር እና በረቡዕ ግጥም ስያሜ ሊጠሩም አይገባቸውም እላለሁ።

 

አጭር ግጥም የሚባል እንደሌለ ከላይ ባቀረብኩት ማሳያ ትንታኔ እንደምንረዳው ሁሉ የረቡዕ ግጥም ብሎ ነገርም የለም። ወዳጄ ማትያስ በጀርመኑ የዶቼ ቬሌ ራድዮ ጣቢያ ላይ ይህን አስመልክቶ የሰጠውን ማብራሪያ አዳምጫለሁ። የሰጠውን ገለጻና ማብራሪያ እንደ ነፃ የራሱ አስተያየት እንውሰደው እንጂ በስነጽሑፍ ዕይታ ቦታ ስለሌለው ብዙ አልሄድበትም።

 

ከእሱ ይልቅ ግጥሞቹ ምን አይነት ስያሜ ያላቸው ናቸው? ቅርጽና ይዘታቸው እንዲሁም መልዕክታቸው ላይ በማተኮር ግጥሞቹ እንዴት ባለ የግጥም አይነት ውስጥ ሊካተቱ ይችላሉ የሚሉትን መጠይቆች ለመመለስ አጠር ያለ ትንታኔ ልሰጥ እፈልጋለሁ።

 

ማትያስ በኢትዮጵያ ዛሬ የድረ ገጽ ላይ ያስነበበን ሁሉም ግጥሞች አንድ አይነት የሆነ የግጥም አጻጻፍ ስልት የተከተሉ ናቸው። አብዛኛዎቹ ባለ አራትና ባለ ስድስት መስመር ስንኞች ሲሆኑ፤ በማለቂያቸው ላይ በተመሳሳይ ቤት እየመቱ የሚጻፉትን የሪይሜ (Rhyme) የግጥም አይነት ስልት ይዘዋል።

 

ሀሀበበ

ሀሀበበቀቀ

 

አይነት ማለት ነው።

 

ምሳሌ፦

ቁጥር ፲፪

እሁድ ጠዋት ተጠራርተው

ጥቂት ሰዎች ተሰባስበው

ቁጭ አድርገው መርዶ አረዱኝ

”ዘሃራ ቤይሩት ሞተች” አሉኝ

እኔ ምንድነኝ ለዘሃራ

ብዬ ነገሩን ሳጣራ

ለካስ ልጄ - ሣራ ብሩ

ሆና ኖሯል - ዘሃራ ኑሩ

 

ቁጥር ፵፰

ከበደኝ ብላቸው የኑሮዬ ሸክሙ

ተቀላቀል አሉኝ ግባ ከሲስተሙ

ምንድነው የሚባል ይሄ በአማርኛ

ሲስተም ተከትለን አድገናል ወይ እኛ?

 

ሁሉም ግጥሞች የዚህ አይነት ስልት ብቻ መከተላቸው ካልቀረ [ማለትም በማለቂያቸው ላይ በተመሳሳይ ቤት እየመቱ የሚጻፉትን የሪይሜ (Rhyme) የግጥም አይነት ማለት ነው]፤ በተመሳሳይ ከዚህ ጋር ተቀራራቢነት ያላቸውን የኳትሬይን (Quatrain) እና የላይምሪክ (limerick) የግጥም አይነቶችን ስልት መደባለቅ ቢችል ኖሮ ከመልዕክቱ በተጨማሪ በግጥም አይነት የአጻጻፍ ስልትም ተጨማሪ ያማረ ጉራማይሌ ይሆንለት ነበር።

 

እንደዚህ አይነት የግጥም አይነቶች ማሳየቱ የበለጠ ግምገማዬን ግልጽ ያደርገዋልና እንዲህ ይቀርባል።

 

የኳትሬይን (Quatrain) የግጥም አይነት እንደማትያስ አብዛኛዎች ግጥሞች አራት ስንኞች ያሉት ሲሆን፣ ቤት አመታቱ ላይ ግን ይለያያል። ቤት ሲመታ አንድ መስመር እየዘለለ ነው። ይሁን እንጂ ሁለተኛው እና አራተኛው መስመሮች የግድ ቤት መምታት አለባቸው። አንደኛውና ሁለተኛው መስመር ግን ቢመቱም ባይመቱም የግድ አይለም።

 

ሀለሓለ

ወይም

ሀለሀለ

 

እንደማለት ነው።

 

የላይምሪክ (limerick) የግጥም አይነት ስልት ደግሞ ባለ አምስት መስመር ስንኞች አሉት። የአንደኛው፣ የሁለተኛው እና የአምስተኛው መስመር ስንኞች በተመሳሳይ ቤት የሚመቱ ሲሆን፤ ሁለተኛው እና ሦስተኛው መስመር ስንኞች ደግሞ እንዲሁ በተመሳሳይ ቤት ይመታሉ።

 

ሀሀለለሀ

እንደማለት ሲሆን፤ በምሳሌ ድምጻዊ ቃና ቤት ሲደፉ ለመረዳት ቀጣዩን ማየት ወይም ማንበብ ይቻላል።

 

ዳ ዱም ዳ ዳ ዱም ዳ ዳ ዱም(ሀ)

ዳ ዱም ዳ ዳ ዱም ዳ ዳ ዱም(ሀ)

ዳ ዳ ዱም ዳ ዳ ዱም(ለ)

ዳ ዳ ዱም ዳ ዳ ዱም(ለ)

ዳ ዱም ዳ ዳ ዱም ዳ ዳ ዱም(ሀ)

 

በግጥም ዙሪያ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በአጻጻፍ ስልት፤ ቅርጽ፤ ይዘትና መልዕክታቸው ላይ ትኩረት ያደረጉ ትንታኔዎችን መሰረት ባደረገ ስነጽሑፋዊ ማብራሪያ ከ60 በላይ የግጥም አይነቶች አንዳሉ ነው።

 

በዚህ መሰረት የማትያስ ግጥሞች አንድም በመልዕክታቸው በጣም ጥሩ የመባላቸውን ያህል ሁለትም ተመሳሳይ የሆነ አንድ አይነት የሪይሜ (Rhyme) የግጥም ስልትን ብቻ ተከትለው መጻፋቸው እንደ ጉድለትም አይቻቸዋለሁ።

 

በግጥም አይነቶችና አጻጻፍ ስልቶች ላይ በሰፊው ትንታኔ እንዳልሰጥበት ቢገድበኝም መልዕክታቸውን መሰረት ባደረገ እንዲሁም ቀረቤታ ካላቸው የሌላ አይነት የግጥም አጻጻፍ ስልቶች ጋር የቀረቡትን በማመሳሰል ምሳሌዎችን እየሰጠሁ አንዳንዶቹን ለመመልከት ችያለሁ።

 

የማትያስ ግጥሞች በመልዕክት ይዘታቸው ደግሞ በሁለት የግጥም አይነቶች ውስጥ ይመደባሉ።

 

የመጀመሪያው ታሪክ፤ ወግና ድራማ አዘል ሆነው፤ በጣም ትኩረት የሚሰጣቸውን ሁሉን አይነት ጉዳዮችን ከሚዳስሰው የበርልስኪዩ (Burlesque) የግጥም አይነት ውስጥ ነው።

 

ምሳሌ፦

ቁጥር ፴፪

ደግ መሃል ገብቶ ”ር” ተወትፎ

ደርግ አደረገብን ይህ የፊደል መጥፎ

አሁን ደግሞ ይሄው ”ያ” ክፉ ሸፋፋ

ወኔ መሃል ገብቶ ሀገርን አጠፋ

እኛ ባንቸኩል ዘመኑም ባይከዳን

ቀስ መሃል ሆኖ ”ኃ” ነበር ሚሻለን

 

ይህን ግጥም ለየት የሚያደርገው ሁኔታም አለ። ቃላቶቹ ለናሙና ተወስድው በጥልቅ መመርመራቸውን ልብ ይሏል።

 

እንዲህ ያለ ዕይታና ማስተዋል ገጣሚንና ግጥምን ቦታ ያሰጣቸዋል። አንድን ስያሜ ወይም ቃልን ከቀጥታ ትርጉሙ ባሻገር መፈልቀቅና መፍተል እንደሚቻል ማሳያ ሆኖ አግኝቸዋለሁና፤ ማትያስን በዚህም አይነቱ የግጥም አጻጻፍ ስልትም ግፋበት ለማለት እወዳለሁ።

 

በአንድ ግለሰብ ሕይወት ላይ እያጠነጠነ ለሌላው ማሳያ እያደረገ የሚያቀርበው የቢዮ (Bio) የግጥም አይነት ደግሞ ሁለተኛው ነው።

 

ምሳሌ፦

ቁጥር ፩

አሁንስ በዛ የኔ ችግር

መነጽር ፍለጋ ሌላ መነጽር

ይህስ አልመሰለኝም የዓይን

ሰውሮኝ ነው ህሊናዬን

 

አንድ ዓመት ባስቆጠረው የሃምሳ ሁለት ሣምንት ፶፪ ግጥሞቹ ሁላችንንም በጋራ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሲያስተምር፣ ሲወቅስ፣ ሲታዘብ፣ ሲያጽናና፣ እንዲሁም ሲቀኝ፣ ሲቋጥር፣ ሲፈታ ብሎም ሲፈላሰፍ አንብበነዋል። ብዙዎቻችን የምንጋራቸው ጉዳዮች የመኖራቸውን ያህል የእርሱ የማትያስ ብቻ የሆኑ ሃሳቦች፣ እምነቶች፣ ሕይወቶችና ራዕዮች መንጸባረቃቸው አልቀረም።

 

ማትያስ የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ላይ “የረቡዕ ግጥም” ሥራዬን አበቃሁ ይበል እንጂ፤ ይህን መነሻ አድርገው በቀጣይ በሚቀርቡ ግምገማዊ ጽሑፎች ላይ በመመስረት ግጥሞቹን ጥለት እያበጀላቸው ለብዙ አንባቢያን በመጽሐፍ መልክም እንዲያዳርስ ወዳጃዊ መልዕክቴን በዚሁ አጋጣሚ በማስተላለፍ፤ ጅማሬ የሆነውን አጭር የግምገማ ጽሑፌን በዚሁ አበቃለሁ።

 

ሠላም ሁኑ!


ዓለማየሁ ዲባባ ከስዊድን (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!