በዓለማየሁ ታዬ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. 

ረቡዕ አራተኛ ቀን ነው። እግዚአብሔር ባራተኛው ቀን የመዓልትና የሌት ብርሃናትን በየጽንፋቸው እንዲሰለጥኑ አዘዛቸው እነሱም ታዘዙት። በዚሁ አካሄድ ገጣሚው በሳምንቱ አራተኛ ቀን ትዝብቱን ቁጣውን ትግርምቱን ደስታውንና ሃዘኑን የሚያንጸባርቁ ሃሳቦችን በፈደል ዘር በግጥም ዘዬ እንዲሰለጥኑ አዘዛቸው እነሱም ታዘዙት።

ታዲያ ወለላዬ በሃምሳ ሁላት ርቡአት/እሮቦች/ ለወግ ማዕረግ ያበቃቸውን ግጥሞች /ልጆቹን/  ሳሙልኝ፤ መርቁልኝ፤ ገስጹልኝም ሲል ጋበዘ። ይሄው ግብዣ በኢሜል ከደረሳቸው ወገኖች መሃከል አንዱ እኔው ሆንኩና እነሆ አጭር ምልከታ:-

ወለላዬ በሃምሳ ሁላት ሳምንታት አርባ ባላራት፦ ስምንት ባለስድስት፦ ሁለት ባላምስት፦ አንድ ባለስምንት እና ተጨማሪ አንድ ባላስራሁለት መስመር ግጥሞችን አስነብቧል። በይዘት ደረጃ ግጥሞቹ ያለንበት ዘመን ያቀፋቸውን ሰብአዊ ጉዳዮች ዳሰዋል። ሃምሳ ሁለቱም ግጥሞች ወጥና በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ ገጣምያን አውቀውትም ሆነ ሳያውቁት በተመሳሳይ ጭብጥ ሁለት ሶስት ግጥሞችን ሲጽፉ እናስተውላለን። በዚህ ረገድ በሃምሳ ሁለቱም እሮቦች የተጻፉት ግጥሞች የተለያዩ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ማንሳታቸው ለገጣሚው የምንነቅስለት ብርታት ነው።

ቁጥር 6

ሲበርደን ኡኡታ

ሲሞቀን ኡኡታ

ስንጠግብ ኡኡታ

ስንጠማ ጩኸት

ስንፋቀር ጩኸት

ስንጣላ ጩኸት

በድለንም ለቅሶ

ሲበድሉን ለቅሶ

ግራ ግብት አለው

እግዜሩ ጨርሶ

በዚህ ግጥም ውስጥ የሰፈሩ ቃላት በሙሉ ተለማዷዊ ቀላላልና በእለት ተእለት ንግግሮቻችን የምንጠቀምባቸው  ናቸው። የየስንኞቹ ማሰርያ የሆኑት ኡኡታ ጩኸትና ለቅሶ ግን የአንድ ሃሳብ ማንጠርያ ሆነውም ተለዋውጠው መሰደራቸው ግጥሙን ከተራ የስድ ንባብ ተርታ አውጥተውታል፤ ድምቀትም ሰተውታል። ግጥምን አይሰለቼና ተነባቢ ከሚያደርጉት ነጥቦች አንዱ የተለመደውንና የዘወትር ክስተት የሆነውን ጉዳይ አንስቶ እንደአዲስ ሊያስገርመን ሊያዝናናን ሊያስቆጣንና ሊያመራምረን መቻሉ ነው። የተነበበው ግጥም ውስጥ ያለው ገጸ ሰብእ እራሱን በኪሩቤል መንበር ላይ አስቀምጦ ነው ትዝብቱን የሚያጋራን። የሥነ መለኮት ሰዎች እንደሚያብራሩት እግዚአብሔር አምላካዊና ሰብአዊ ባህርያትን አጣምሮ የያዘ አምላክ ነው። ታዲያ በዚህ ግጥምፈጣሪ ሰብአዊ ባህሪ ተጎናጽፎ የሰው ነገር ግራ ሲያጋባው እንታዘባለን ወዲያውም የየእለት ክስተት የሆነውና የሰው ልጅ በበጎውም በክፉውም የማጉረምረም ልምድ እንዲህ ስንኝ ተቋጥሮለት ትግርምታችንን ይዞ ሲያመራምረን ሲያሳስበን ፥እውነትም!፥ ሲያሰኘን እናስተውላለን።

ገጣሚ የሚያነሳው ፍሬ ሃሳብ ተደማጭና ያንባቢን ቀልብ የሚስብ ይሆንለት ዘንድ የተለያዩ ድምጸቶችን ይጠቀማል። 

ቁጥር 12

እሁድ ጠዋት ተጠራርተው

ጥቂት ሰዎች ተሰብስበው

ቁጭ አድርገው መርዶ አረዱኝ

ዘሃራ ቤይሩት ሞተች አሉኝ

እኔ ምንድን ነኝ ለዘሃራ

ብዬ ነገሩን ሳጣራ

ለካስ ልጄ ሳራ ብሩ

ሆና ኖሯል ዛሃራ ኑሩ

ይህ እንግዲህ አሳዛኝና አስደንጋጭ የሆነው የሞት ዜና እጅግ ለዛ ባለውና ኮርኳሪ ድምጸት /humorous tone/ የቀረበበት ግጥም ነው።

በተነጻጻሪ የሰይፉ መታፈሪያ ያይናለም ነጠላ እንዲሁ ሊያሳዝነን እና ከንፈር ሊያስመጥጠን የሚገባንን

ጉዳይ በተለየ ድምጸት አቅርቦ ነው ፈገግ የሚያሰኘን።

ያይናለም ነጠላ

ውሎዋን አሸርጣው

ሌሊቱን ደርባው

ያ ነጠላ ተጉላላ ላላ ላላ

ዘረዘረ

ክሩ ብቻ ቀረ።

ደግሞ ማሰብዋ

          ለጥብት

          ለጥምቀት

እንዶድ ማቅረብዋ፦

የልጃገረድ ነገር

                ቢያምራት

ማማር ማማር

እንደ ጓደኞችዋ

የድሜ አቻዎችዋ

ግን እንዴት ብላ

እስዋስ

ባንድ ነጠላ

ውሎዋን አሸርጣው

አረህ ላረህ

እንጨት ሰበራ

እንጀራ ብላ እንጀራ

እና ሌሊቱን ደርባው።

እሱ ለራሱ ላልቶ

ዘርዝሮ

ክሩ ብቻ ቀርቶ።

አረ እንዴት ይቻላል

ቀንና ሌሊት ማገልገል

ቅያሪ ሳይኖረው

በድንም ቢሆን ግፍ ነው።

የሁለቱን ግጥሞች ድምጸት ስንመረምር የወለላዬ የደመቀ ኮርኳሪ humorous ሳቅ

አጫሪ ድምጸት ያለው ሲሆን። የሰይፉ መታፈሪያ ግጥም ግን ከhumor በተጓዳኝ የተግሳጽ፦ የትዝብት

ቃናም ይደመጥበታል።

የወለላዬ ግጥሞች አብዛኞቹ ባራት መስመር የተቋጠሩ እጥር ምጥን ያሉ የዘመናችን መዝሙሮች የየእለት ህይወታችን ሂሶች ናቸው። ግጥሞቹ ግልጽና ቀጥተኛ ስለሆኑ አደናጋሪነት አይታይባቸውም። የየስንኞቹን ሃሳብ ለመረዳትም ጥልቅ ምርምርና ተመላልሶ ማንበብን አይጠይቁም። ገጣሚው እራሱ በቁጥር 23 ስንኙ እንዳመለከተው

ቁጥር 23

አስፍቼ እጽፋለሁ ብለህ ከመቀመጥ

ድርጊቱ እንዳይጠፋ አንተም እንዳታመልጥ

ሰብሰብ አጠር አርገህ በቆንጆ አማርኛ

የእለቱን በእለቱ ወርውርና ተኛ

ይለናል። ወዲያውም ስመጥሩው ባለቅኔ ደበበ ሰይፉ

ወርውር የእጅህን ዘገር

በትን ያሻራህን ዘር

ይዘኸው እንዳትቀበር። ብሎ የቋጠረውን ስንኝ ያስታውሰናል።

ሌላው በዚህ አጭር ቅኝት የምናነሳው ግጥም ቅልል ያለ የተለየ ምስጢር የሌለው ሆኖም ግን ውብ አጨራረስ የሚታይበት ነው

ቁጥር 43

እጃችሁ ከገባ ድንገት ብታገኙት

ሰይጣን የታባቱ ቀጥቅጡ ውገሩት

ነገር ግን ጨርሶ አይገባም መግደል

ጥፋት ስናጠፋ ማን አሳተኝ እንበል

ይህቺ ግጥም በተለየ አጨራረስ የተጻፈች /thought provoking/ ስራ ናት። ገጣሚው በፈቃዱ ሞረዳ

የትውልዱን መዝሙር ባቀነቀነበት መድበሉ ያኑርልን በሚል ርእስ ያቀረባት ግጥም ተመሳሳይ ያጨራረስ   ብልሃት ይታይበታል

ያኑርልን

ጦር መሳርያ ይውደም

ጦረኞች ይክሰሙ

ጦርነት ግን ይኑር

እያስፈራ ስሙ።

        ***

ድህነት ይገልበጥ

ባፍጢሙ ይደፋ

ደሃ ግን ይበርክት

ፍቅር እንዳይጠፋ።

ያለውን ያስታውሰናል። የወለላዬ ግጥሞች አብዛኞቹ ባላራት መስመር /Quatrain/

መሆናቸውን ደጋግመን ጠቅሰናል ታዲያ የባላራት መስመር ግጥም /አራቶ/ ነገር ሲነሳ ወደኋላ መለስ ብሎ የቀደምት ባለቅኔዎችንም ስራ ማጤኑ ግድ ነውና እስቲ  ከባህላዊ /traditional/ መዲናና ዘለሰኛ ግጥሞች ጥቂት ምሳሌዎች እንይ። የመጀመርያው አለቃ ተገኝ ተአምሩ ያማርኛ ሐረግ በሚል ርእስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው ያሰፈሩትን መዲና ግጥም ነው

የወልደ አምላክን እራቱን

ሳላሰናዳ ምናምን

በስጋ አደረ ትላንትና

ጌታ ሰው ሆኗልና።

ይህ እንግዲህ ሰምና ወርቃዊ ያማርኛ ህብር ቅኔ ነው። ከላይ ከላይ የምንረዳው ወልደ አምላክ ለተባለው ሰውዬ እራት እንዳልተዘጋጀለት እሱ ግን ጌታ/ሃብታም ሆኖ ስጋ በልቶ እንዳደረ የሚያትት ሲሆን ወርቁን ለመረዳት ምስጢረ ሥላሴን ማወቅን ግድ ይላል።

አቤ ጉበኛ ደግሞ መስኮት በተሰኘ ርእስ ባሳተመው የግጥም መድበሉ ያሰፈረው ዘለሰኛ ባላራት መስመር ግጥም እንደሚከተለው ይነበባል።

ሜዳ ሸለቆውን ዞትር ብናርስም፦

በጋራ ካላረስን እህል አንጠግብም።

ተበልቶ አለቀና የየሜዳው ጋሻ፦

በጋራ ሆነ አሉ ያሁን ዘመን እርሻ።

ወደወለላዬ ግጥሞች ስንመለስ ሌላው የዘመናችንን ሰው ስነልቦናዊ ሰብእና የተቸበትን ግጥም እናጢን።

መጨበጫም የለው መቼም የኔ ጣጣ

በአገሬም አልኖር ካገሬም አልወጣ

እዛ ስሆን እዚ ከዚ እዛ እያሰብኩኝ

ማደርያ የሌለው ከንቱ አሞራ ሆንኩኝ

ይህ እንግዲህ ብርቱ ሂስ ነው።  የጊዜው አሳሳቢ አደጋ ተብሎ የሚታሰበው ስደትና ከስደት ጋር ተያይዞ የሚመጣው ስነልቦናዊ ቀውስ በዚህች አጭር ግጥም ተጠቃሎ ተከትቧል።

 ባላራት መስመር ግጥም በግእዙ ቅኔ ባህልም የተለመደ ነው። የግእዙ አራቶ ክብር ይእቲ ይሰኛል። እስቲ ባለቅኔው ቦጋለ ዳኜ ከነማብራሪያው ከጻፉት ዕዝል ክብር ይእቲ ቅኔያት አንዱን ለምሳሌ እንመልከት

አልቦኑ ግእዛን በውስቴታ ለእንተ ሰማያት ጠፈር?

ፈላሲ ኮከብ ህልወ ዛቲ ሀገር፤

አኮኑ ተሰደ ሃበ ዝንሄሉ ምድር፤

ሠላመ ይርከብ በውስቴታ በደመ ክርስቶስ ክቡር።

 

ትርጉም

በሰማያት  ጠፈር ውስጥ ነጻነት የለም ወይ? በዚያች አገር የሚኖር ስደተኛ ኮከብ ክቡር በሆነው በክርስቶስ ደም  ሠላምን ያገኝ ዘንድ፤ ወደምንኖርበት ምድር ተሰዷልና።

ታሪክ

ይህ ቅኔ በክርስቶስ ስቅለት ጊዜ ኮከብ መውደቁን ለማሳየት የተቆጠረ ነው። ኮከብን  እንዸ  ስደተኛ ሰው፤ ጠፈርን እንደ ሀገር  በመውሰድ፤  ኮከብ ወደምንኖርበት ምድር የተሰደደው በጠፈር ነፃነት የለም ወይ? በማለት ይጠይቅና በክርስቶስ ደም ሠላምን ለማኘት ወደምድር መሰደዱን ይገልጻል። ይህም በክርስቶስ ደም በምድር ለሰው ልጅ (ለአዳም) ሠላም መውረዱን ለማመልከት ነው። ሰሙ ፤ ኮከብ የተባለው ሰው መሰደዱን ሲያሳይ ወርቁ ኮከብ ጌታ በተሰቀለ ጊዜ መውደቁንንና በጌታ ደም የሰው ልጅ ነፃ መውጣቱን  ለማመልከት ነው።

QATRAIN በእንግሊዝኛ በፈረንሳይኛ በፋርስ እና በሌሎችም ቋንቋቆዎችም የሚዘወትርና ተወዳጅ የግጥም ቤት ነው። እስቲ ከእንግሊዝኛ ባላራት ቤት ግጥሞች አንድ እንመልከት። ይህ  አራቶ በ W.H. Auden የተጻፈ ነው።

The sense of danger must not disappear:
The way is certainly both short and steep,
However gradual it looks from here;
Look if you like, but you will have to leap.

እንደ ተጨማሪ ምሳሌ ደግሞ በፈረንሳይኛ ተጽፎ ወደእንግሊዝኛ የተተረጎመ ትንቢታዊ ባላራት መስመር ግጥም እነሆ። ገጣሚው ኖስትራዳመስ ነው። ኖስትራዳመስ በአጠቃላይ 942 ባላራት መስመር ግጥሞችን በመጻፉ በሥነ ግጥሙም ዓለም ተጠቃሽ የ QUATRAIN ገጣሚ ነው።

 

   Enormous-promontories on fire in the center of the mainland

   Will cause trembling in the towers of the City of New York;

   Two great rock-monoliths continuously will be attacked,

   This is when air-vessels will turn-around to a new course.

 

ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ የኖስትራዳመስ  ጉዳይ ከተነሳ ኢትዮጵያዊው ሼህ ሁሴን ጂብሪልም አብዛኞቹን ትንቢታዊ ግጥሞች የጻፈው እንዲሁ በግጥም ነውና ዶክተር ጌቴ ገላዬ ከሰበሰባቸው የሼህ ሁሴን ግጥሞች አንድ ባላራት መስመር ምሳሌ (የሼህ ሁሴን አብዛኞቹ ግጥሞች ባላምስት ቤት መሆናቸውን አንዘንጋ)

 ቁጥር 202

አሁን ያልኩህ ዘመን ናት የነዚያ ወራት

ወታደር መንግስቱ የሚሾምበት

አገር ቤት ሹመቱ የሚገባበት

ወንድ ሴት ልጅ አዋቂ ሁር ባርያ እኩል የሚባልበት

 

በዚህ ጽሁፍ ስለ አራት ቤት ግጥሞች ጠቅለል ያለ ቅኝት ቢደረግም ማጠንጠኛው ወለላዬ ነውና እስቲ ከወለላዬ ግጥሞች አንድ ተጨማሪ እንመልከትና ወደ ፋርሳዊው ባለቅኔ እናምራ፤

ቁጥር 26

ሕይወትን በዘዴ ጥፎና ለጥፎ

ገበናውን ከድኖ ሰው ቢኖርም አርፎ

ከውስጥ ወይ ከውጭ የሚጠዘጥዘው

የራሱ የሆነ ሁሉም ህመም አለው ።

 

 በአረቡ ዓለም ባላራት መስመር ግጥም ሲነሳ አብሮ ስሙ የሚነሳው ኡመር ኻያም ነው። ከኡመር ኻያም አራቶ / RUBAIYAT/ የኤድዋርድ ፊዝጄራልድን ትርጉም እነሆ

Rubai 4

Now the New Year reviving old Desires,

The thoughtful Soul to Solitude retires,

Where the White Hand of Moses on the Bough

Puts out, and Jesus from the ground suspires

መልክአ ዑመር በተሰኘው የተስፋዬ ገሠሠ መጽሃፍ ሩባይ አራት እንደሚከተለው ተተርጉማለች

ሩባይ 4

አዲስ አመት መጥቶ አሮጌውን እሾት

ሲያክክ ሲደሳስስ

መቁዋሚያውን ይዞ ሙሴ ሲያለቃቅስ

ከከርሰ መቃብር የሱስ ሲተነፍስ

ይህን ሁሉ ታንኪር የምታደምጪ ነፍስ

ተከርቸሚ ገዳም!

 ሳትቀውሽ ቀስ በቀስ !!

የወለላዬ ግጥሞች መነሻ ሆኑኝና ብዙ መንገድ ተጓዝኩ አንባቢንም አሰለቸሁ? አሁን ግን መሰነባበት አሰኘኝ በደጋጎቹ አባቶቻችን አንደበት ሠላም ለኩልክሙ ብዬ ከመሰናበቴ በፊት ግን የወለላዬን ቁጥር

52 እነሆ

የረቡዕ ግጥም ሃምንቱ ሲሰላ

ሃምሳ ሁለተኛው ድፍን አመት ሞላ

እኔም ከቀኑ ጋር እየሮጥኩ አብሬ

በዚህ አበቃሁኝ ስራዬን ቋጥሬ።

እንደገና ሠላም ለኩልክሙ!!   

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!