ፍቅር ይበልጣል

ከአንድ ደደብ ለአንድ ደደብ የተጻፈ አጸፋ

የቴዲ አፍሮን ልበም ለመግዛት ያየሁትን አበሳ አውቃለሁ። አልበሙን ለመግዛት የቋመጥኩትም ቴዲን በኢትዮጵያዊነት አርአያነቱ ከልቤ ስለማፈቅረው እንጂ ዘፈኑን - ገና ያላዳመጥኩትንና ያላጣጣምኩትን - ዘፈን በገና ለገና ወድጄ ወይም አፍቅሬ አይደለም። ይሁን እንጂ የቴዲን ዘፈን - ዘፈን ብቻም አይደለም ሙሾም ቢያወጣ - ተሸቀዳድሜ ኦሪጂናሉን እንደምገዛ ለራሴ ቃል ከገባሁ ቆይቻለሁ - ከመታሰሩ በፊት።

 

 

ዛሬ ከዘመድ የፋሲካ የራት ግብዣ መጥቼ ኢንተርኔት ስመለካከት በኤሊያስ ክፍሌ ድረ ገፅ የተመለከትኩት በፍቃዱ ዘ ኃይሉ “የቴዲ አፍሮን አልበም ያልገዛሁባቸው 5 ምክንያቶች” በሚል ርዕስ የጻፈው መጣጥፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ አስከፋኝ፤ አስኮረፈኝም - ማኩረፍን በቅጡ አላውቅም እንጂ። በዚህ አስደንጋጭ ‹መጣጥፍ› የተነሳ በይደር ያስቀመጥኩት የቴዲ ጉዳይ ተቀሰቀሰብኝ። (የበፍቃዱ ዘ ኃይሉን ጽሑፍ አስነብበኝ!)

 

በፍቃዱ ዘ ኃይሉ የተባለ ስሙን መጥራት የማይገባኝ አቃቂረኛ ቴዲን እንዲያ ሲወርድበት መመልከት ለቴዲ ሳይሆን ለእኛ ለአድናቂዎቹ የሞት ሞት ነው። በመሠረቱ ለእንደዚህ ዓይነቱ ወያኔ መልስ መስጠት ለወያኔ ክብር እንደመስጠት እንደሚቆጠር አጥቼው አይደለም። ነገር ግን ከግብዣ የመጣ ሰው ውሻ ሲጮህበት ወግድ እንደማለት ሊቆጠር ስለሚገባው አትፍረዱብኝ። እናም እውነቱን ልንገረው። በዚህም ላይ ኤልያስ ክፍሌን ከልብ ስለምወደው - ቅዱስ ሚካኤልን - እንደዚህ ዓይነቱን ጽሑፍ በቀናነትና በዲሞክራሲያዊ መብት ማስተናገዱን አስታውሶ ሌሎች ይህን መሰልና የኔን ዓይነት ሞልፋጣና መደዴ መጣጥፎችን ለወደፊቱ ለማስተናገድ ቃል እንዲገባልኝ ለመማጠን በመፈለግም ጭምር ነው።

 

ሐፊው ከምር ደደብ ነው - እንዲያውም ደደብ እሚለው ሠነፍ ቃል ያንሰዋል፤ ግን ምን ይደረግ የቋንቋ ሰዎች ከዚህ የተሻለ ገላጭ ቃል አላቆዩልንም። የዚህን ሰው ደደብነት በአሥር ጣቴ ላረጋግጥት እወዳለሁ - በአመክሮ ከደደብ ይነስለት ከተባለም ለሆዱ ያደረ ‹አድር ባይ መሠሪ› መባል ይገባዋል - ‹ጅብ ከሚበላህ በልተኸው ተቀደስ› በሚለው የሳይቀድሙህ ቅደም ራስ ወዳድ ዘይቤ የሚመራ። በነገራችን ላይ የምጽፈው በዴስክቶፔ ነው - አጠገቤ ከላፕቶፔ ላይ ከኢንተርኔት የወረደውን ግም ወያኔያዊ የኤልያስ ማለትም የበፈቃዱን ጽሑፍ እያጣቀስኩ ነው የምጽፍላችሁ - እውነቱንና እውነቱን ብቻ።

 

ከኢፍትሃዊ እሥር ቤት የወጣውን ብላቴና ዳግም ለማሰር ባይችሉ ወይም ቢያቅታቸው በሙያው ሊመጡበት ፈለጉ። እናም አልበሙ ገና ከመውጣቱ ሊዘምቱበት ቋመጡ። እንደማይቻላቸው እንነግራቸዋለን፤ ከኢትዮጵያዊነት የጨዋ ባህል አንጻር ነውር መሆኑንም ጭምር። ቴዲ ማለት የኛ ሳን ሱቺ ነው። ቴዲ ማለት የኛ ማህተመ ጋንዲ ነው። ቴዲ ማለት የኛ ማርቲን ሉተር ኪንግ ነው። ቴዲ ማለት የኛ ቴዎድሮስና ምኒሊክ ነው። ቴዲ ማለት የኛ ማዘር ቴሬዛ ነው። ቴዲ ማለት የኛ ኔልሰን ማንዴላ ነው። ባጭሩ ቴዲ ማለት የኛ ክርስቶስ ነው-። …

 

ኢትዮጵያ ከወሮበላ በስተቀር ጀግና ማፍራት ስላቆመች እንጂ ትንሹ ቴዲ ለኛ የመልካም ሥራ አርአያችን ነው። ትልቅ ትንሹ አቅሉን ስቶ በገንዘብ ፍቅርና በወሲብ ንዳድ እየታመሰ ባለበት ወቅት ይህ ብላቴና ገለጋ ዕድሜው ጀምሮ ለሀገርና ለወገን መቆርቆሩ ለስድብ ናዳና ለዋልጌዎች ሽሙጥ ሊዳረግ አይገባም። በኢትዮጵያ ባህል በስድብና በነቀፌታ መሞላለጭ እንጂ መሞጋገስና መልካም ጠባይን መመስከር እንደነውርና እንደተዓብዮ ስለሚቆጠር የምለው ነገር ከመጤፍ ላይቆጠር ይችል ይሆናል - ግን የምለው እውነት መሆኑን በሕያው እግዚአብሔር ስም በማልሁ ነበር - መማል ቢፈቀድ ኖሮ። (የምናውቀውን የነእስክንድርንና አንዱዋለም አራጌን እንዲሁም የሌሎቹን የሚዲያና የፖለቲካ ሰዎችን እንግልት ትተን) ማንኛችን ነን እንደቴዲ ለዚህች ሀገር የተሰቃየን? እውነት እንነጋገር - የታሪክ ሽሚያም ውስጥ አንግባ።

 

ዳንስ ቤት መጨፈርና ማስጨፈር እየቻለ፣ ለቁጥር የሚያታክቱ ጉብሎችን ሲያሻው ባንዴ ሳያሻው እያፈራረቀ አቅፎ መዋልና ማደር እየቻለ ለዚህች ሀገር ሲል በውርዝትናው ዘመን ከርቸሌ የወረደ ቴዲ አይደለም ወይ? በኪነ ጥበባዊ ሀገራዊ አስተዋፅዖው የርሱን ያህል የተንገላታ ማን ነው? ለምንድን ነው ጀግና መውለድን እንጂ ማሳደግንንና መንከባከብን የማንወደው? ምቀኞች ስለሆን ይሆን? ቀናተኞች ስለሆን ይሆን? ባንጠጣው እናደፍርሰው ባዮች እንሆን ይሆን? ጀግና ከኔ በላይ፣ ታሪከኛ ከኔ በላይ፣ ታጋይ ከኔ በላይ፣ ታታሪ ከኔ በላይ፣ ዐዋቂ ከኔ በላይ፣ ላገር አሳቢና ተቆርቋሪ ከኔ በላይ፣ ትግል ከኔ በላይ፣ መስዋዕትነት ከኔ በላይ፣ ባለዝና ከኔ በላይ … በሚሉት መድሓኒት የለሽ ደዌያት ተለክፈን ይሆን የሌሎች ሰዎች ዕድገትና ሙገሣ የሚያንገሸግሸንና በተፃራሪው የሚያቆመን? እናስብበት! በሰባት ሳይሆን በሰባት ጊዜ ሰባት ጠበሎች እማይለቅ ኢትዮጵያዊ በሽታ አለብን - ብዙዎቻችን። ለዚህስ ወጣት የኪነ ጥበብ ሰው ወሮታው በሞልጣ ብዕር መሰደብ ሊሆን ይገባው ነበርን? ያን መጣጥፍ አንብቡና ፍረዱ። ወያኔና ወያኔያውያን ግን ይህ ስለሚያንገበግባቸው ቴዲን ይቅርና ቴዲን የምንወድ ዜጎችን ያበሻቅጡናል፤ ብሎም ቢሆን ዝም አንልም። እውነቱን እንናገራለን እንጂ።

 

ቀድሜ ተናግሬያለሁ - እኔ ራሴ ከዚህ ቅጥረኛ የባስኩ ደደብ ነኝ - የምበልጠው ግን እኔ የኅሊናየ ቅጥረኛ እንጂ የቴዲ አለመሆኔ ነው። ቴዲ ራሱን ችሎ ለነገይቷ ኢትዮጵያ መድረሱ ለኔ ትልቅ ወሮታ ነው። አያውቀኝም አላውቀውም። ከዓለማዊ ነገር ጋር በተገናኘም እንዳውቀውና እንዲያውቀኝ አልመኝም። ፈጣሪ ይክበር ይመስገን ራሴን ችዬ የምኖር ሰው ነኝ። እንደደደቡ መጣጥፈኛ ለምሥጋና ወይ ለሹመት የምጽፍ አይደለሁም። እናም በቀጥታ ወደደደቡ መጣጥፈኛ እንሂድ። ጉደኛው ተንታኝ እንዲህ አለ - ‹አልበሙ የአማርኛ መሆኑን ያወቅሁት ከሰማሁት በኋላ ነው። ምክንያቱም በየቦታው የተለጣጠፉት ግባብዲያ ማስታወቂያዎች በሙሉ ‹Tikur Sew, Get ready, A feast of soul, Teddy Afro ምናምን ይሉና፤ ለሳቅ ለጫወታ ማን እንደሜታ ይላል!› ከዚህ ጠማማ አባባል በኋላ በመሠረቱ የዚህን ሰው ጽሑፍ ማንበብ አስፈላጊ ባልነበረ። ነገር ግን እጽፋለሁ የሚል ሰው አፍንጫውን በመሀረብ፣ ጆሮውንም በጨርቅ ጠቅጥቆ የጀመረውን ንባብ መጨረስና መልስም መስጠት አለበትና እየገማኝም ቢሆን ጨረስኩት። የታዘብኩት ግን እውነቴን ነው ኤልያስ ክፍሌን ነው። ‹ያመኑት ፈረስ ጣለ በደንደስ›ዓይነት ነው የሆነብኝ። ግን ኤልያስን ምን ነካው? በዚህ ዓይነት ጽሑፍ ድረ ገጽ አይገማም ብሎ ይሆን? አይምሰለው ይገማል! ቴዲ የማንም ጠላት አይደለም! ጠላትነቱ የፀረ-አንድነትና ፀረ-ሰላም ኃይሎች ነው። እነዚህም በወርዳና በቁመት የታወቁ ሳይሆኑ በነቢባዊ ኀላዌ በምናብ በየአእምሮኣችን የሚመላለሱ ፍጡራን ናቸው።

 

የዚህን መጣጥፈኛ ነገረ ሥራ ሁሉንም ዝግንትል መዳሰሱ ጊዜ ማጥፋት ነው። ነገር ግን የቴዲን አልበም ለማግኘት ያደረግሁትን ጥረት ልናገርና ላብቃ።

 

አልበሙ የወጣው ቅዳሜ ነው - የቀዳም ሥዑር ዕለት። በኪሴ የያዝኩትን ገንዘብ ጨርሼ ከአዟሪዎች ለመግዛት 25 ብር አጣሁና የሚያበድረኝ ሰው ብፈልግ ማግኘት አቃተኝ። በአቅራቢያየ ከሚገኝ ባንክ በኤቲ ኤም አውጥቼ ግን በዕለቱ ገዝቼ በፍቅር ጉያየ ውስጥ ሸጉጬ ወደቤቴ ገባሁ። ቀድሜ እንዳልኩት የቴዲን ዘፈን ሳይሆን የወደድኩት እሱን - ቴዲን - ነው፤ ብዙዎች ታላላቆች ለከርሳቸው ሲሉ እንደኤሣው ብኩርናቸውን (በምሥር) በቁራሽ እንጀራ ሽጠው በጠፉባት ምድር ይህ ብላቴና መከራውን ያየባትን ይህችን የግፉኣን ሀገር ባንዴራ በጭንቀት ዘመኗ ያውለበለበውን ቴዲን ነው የወደድኩት። ይህን ብዙዎች ለሆዳቸው ሲሉ ገሸሽ ያደረጉትን የመስዋዕትነት ገድል ነው ቴዲ ነፍስ የዘራበት። ይህን ታሪካዊ ገድል ነው እንግዲህ እነኤሊያስና በፍቃዱ በቅናትም ይሁን በተልዕኮ ሊያስተሃቅሩት የቋመጡት - ላይቻላቸው። ቃየል አቤልን ተመቅኝቶታል። ተመቅኝቶም አላበቃም፤ ገደለው። የመጀመሪያው ግድያም በዚያን ወቅት ተመዘገበ።

 

ቴዲ ምን አጠፋ ተብሎ ነው እንዲህ የሚወረድበት? ምቀኝነት ለከት ቢኖረው ምን አለበት? ደደቡ ሲፈልግ አልበሙን አይግዛ - የራሱ ጉዳይ። ግን ለምንድነው ሰዎች እንዳይገዙ በኤሊያስ ክፍሌ በኩል የዘመተበት? ለነገሩ አልበሙ በሠልፍ እንደተሸጠ ሰምቻለሁ። ነጋዴውና አከፋፈዩ ግን በስሙ ለመጠቀም መሞከራቸው አግባብ አልነበርም፤ አይደለምም። ለመሆኑ ቅጅ መግዛቱስ ወንጀል መሆኑን ደደቡ ዘነጋው ወይ? በአሁኑ የኑሮ ውድነትና የዕቃ ዋጋ ንረትስ በእውነት እንነጋገር ከተባለ አንድ ሲዲ ለማሳተም በርግጥ 5 ብር ብቻ ነው ወይ የሚፈጀው? ፍርድ ከራስ መባሉ ለመቼ ነው? ደደቡ ሰው፣ ሰው መሆን ያለበት ደደብነቱ እስኪነገረው መሆን አለበት ወይ - ሊያውም ከተሳካ? ኧረ ሰውን ምን ነካው ምዕመናን? እንዲህ ያስጮኸኝን ገልቱ ጽሑፍ ከኢትዮፒያንሪቪው ማንበብ ትችላላችሁ - መቼም የዚህችን መከረኛ ሀገር ስም እያነሳ ድረ ገጽ ያልከፈተ ሰው የለም። ይህን ስል በአንድ አጋጣሚ ብቻ ተነስቼ ትልቅ መጥፎ ፍርድ እንደበየንኩ አላጣሁትም - ከይቅርታ በላይ ምን ልል እችላለሁ? መቻቻል ነው እንግዲህ። ባይን ሲመጡበት የማይወራጭ የለም - ቢሆንም ከኤሊያስ ክፍሉ መልስ እፈልጋለሁ - ብሳሳት እንዲያርመኝ - ቢሳሳት እንዲታረም። በመሠረቱ አንድ ዐይና ሰው በጥንቃቄ ነው መጓዝ ያለበት። ብዙዎች አርቲስቶቻችን የወያኔ መናጆ ሲሆኑ አንድ ፍሬ ልጅ ቢገኝ እሱንም ሞራሉን ቀንድ ቀንዱን በማለት ንድህሪት ኮድኩዶ ወደወያኔው ጉያ ለመወተፍ የሚደረግ ጥረትን በምንችለው ሁሉ መቃወም አለብን። ኤሊያስ ደግሞ ለዚህ ፍጻሜ የቆመ አይመስለኝም። ተሳስቼ ሊሆን ይችላል - ግን ለመታረም በጣም ዝግጁ ነኝ። በተለይ … የምን በተለይ ነው። ይቅርብኝ።

 

የገንዘብ ፍቅር ብዙዎቻችንን አንጎላችንን ስላናወጠው የ25 ብሩን አልበም እስከ 50 ብር ድረስ በመሸጥ ከፍተኛ ትርፍ ለማጋበስ የሞከረ ነጋዴ አልጠፋም - ማግኘት ውሉን ላይስት ሰው በገንዘብ ፍቅር አብዷል። ይህን አጋጣሚ የመጠቀም ይሁዳዊ በሽታ ከተጠናወተን ቆየት አለ። በዚህ ግን ቴዲ ሊወቀስ የሚገባው አይመስለኝም። ቴዲ አልበሙን ለአከፋፋይ ነጋዴ ሸጠ፤ በቃ። አልበሙ ገበያ ከወጣ በኋላ ግን በመቶ ብር ይሸጥ በነጻ ይከፋፈል ቴዲን የሚመለከተው ጉዳይ አይመስለኝም፤ አይደለምም። ይሄ ደደብ ግን - አሁንም እንደኔው ደደብ መሆኑን ሳልክድ - ቴዲ በየግሮሠሪውና በየባቡር መንገዱ እየዞረ የሚሸጥ ይመስል ‹30 ብር ለአንድ አልበም?!› (አልበዛም? ማለቱ ነው!) እያለ ቴዲን ሊያሳጣ ይሞክራል፤ ነውረኛ የወያኔ ቅጥረኛ! በቅዱስ ሚካኤል ይሁንባችሁ ከኢትዮፒያን ሪቪው ያን ጠንቀኛ የምቀኛ ጽሑፍ አንብቡት!

 

በመሠረቱ መብቱን ሊያስጠብቅ የፈለገ እንደኔ ዓይነቱ ደንበኛ በ25 ብር መግዛት ይችላል። ቅጂ ደግሞ በበኩሌ አልሞክረውም - በቴዲም በሌላም፤ አርትን መግደል ነው። ደደቡ ግን አጭበርባሪ መሆኑን በጽሑፉ ገልጦልናል ‹ በየትኛውም ቴክኖሎጂ ቢሰራ ኮፒ ማድረግ እንደሚቻል ስለማውቅ፣ ኮፒ አድርጌ ተጠቅሜያለሁ።› በማለት። ይህን አባባል ኤልያስ አላየውም ማለት ይከብደኛል። ይህን ዓይነት ሕግ አፍራሽ ጽሑፍ በሕጋዊ ድረ ገጽ ማስተናገድም ምን ዓይነት ግምት ሊያሰጥ እንደሚችል ኤሊያሰ አያውቅም መላት ያስቸግራል። ምነው ኤሉ? ስናምንህ? ሀገር ግንባታ ላይ የተሰማራ ሰው ማጭበርበርን እንዴት ያበረታታል? ‹ኤዲት› ማድረግ ባይቻል ‹ዊዝሆልድ› ማድረግ እንዴት ያቅታል? ለማንኛውም ደደቡ ሰውዬ ለወደፊቱ ይህን መጥፎ ጠባዩን ያስተካክል። ቆሻሻ ባሕርይ ያለው ሰው ደግሞ ማስተማር አይችልም። በተውሶ ደግሞ የሰውን ዘፈን መተቸት ግምት ውስጥ ይጥላል።

 

ሰውዬው በጥቅሉ ወያኔ ነው ቢባል ቢያንስ በከፊል ያስኬዳል - እንዲያውም ሙሉ በሙሉ። እናም ደደቡ ወንድሜ እባክህን ከቴዲ ራስ ወረድ በልና ሌላ የፈለግኸው ራስ ላይ ቁጢጥ በል። ቢቻልህ ወደራስህ ውስጥ ግባና ራስህን መርምር። ብዙ ልትታወቅባቸው የምትችልባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ስላሉ በነዚያ ላይ እንደልብህ ጻፍ። ቴዲን ግን ለኛና ለኢትዮጵያ ተወልን - እንፈልገዋለን። በሰልፍ አልበሙን የገዛነው አንተ በምቀኝነት እንደምትወርድበት ጠርጥረን አልነበረም። ባንገዘው ደግሞ ብዕርህን አታነሳም ነበር። የኛ መግዛት ግን አንገበገበህ - ምን እናድርግ? ማንስ አለን? ከፈለግህ በነሠራዊት ፍቅሬ ላይ ለምን አትጽፍም? እነሱማ ወንድሞችህ ስለሆኑ - የዓላማ አጋሮችህ ስለሆኑ - የመደብ ሼሪኮችህ ስለሆኑ ለመተንከፍ ታፍራቸዋለህ ትፈራቸዋለህም። ባይ ባይ ወንድማለም። ልድገመው - አደራ ቴዲን ተውልን። በዚህ ጉዳይ አልመለስም። አንተም አደብ ግዛ።


ፍቅር ይበልጣል This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!