ቦጋለ ዳኜ - ከካሊፎርንያ

ቅኔ፤ ግጥምና የተለያዩ ድርሰቶች ባጠቃላይ ሲጠሩ 'ሥነ ጽሑፍ' ይባላሉ። ሥነጽሑፍ የሚለው ሐረግ ጥሬ ትርጉም 'የጽሑፍ ውበት' ማለት ነው። ለሥነጽሑፍ ይህ ስያሜ የተሰጠበት አንዱ ምክንያት ድርሰቶች ሲጻፉ በቃል አመራረጥ ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ መሆኑን፤ ሥነ ጽሑፍ መዋብ እንደሚገባው ለመግለጽ ጭምር ይመስለኛል።

 

ቃል፤ በተለይ ባገራችን አያሌ ቋንቋዎች ስላሉ፤ ባንዱ ቋንቋ አንድ ትርጉም ሲኖረው ይኸው ቃል በሌላው ቋንቋ ሌላ ትርጉም የሚይዝበት አጋጣሚ አለ። ያም ቃል ንባቡን እንዳያጠፋ በቃል አመራረጥ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።

ለምሳሌ በቅኔ ቤት 'ወገረ' የሚለው የግዕዝ ቃል በትግርኛ ሌላ ትርጉም፤ ማለት ከሴት መገናኘትን ያመለክታል ስለሚባል ቃሉ በቅኔ ውስጥ ከገባ ጸያፍ ነው ይባል ነበር።

ሌላ ምሳሌ፤ 'በዳዳ' ለሚለው የኦሮምኛ ስም 'ደ' የሚለው ያማርኛ ሆሄ ድምፅ የኦሮምኛውን ድምፅ በትክክል እንደማያሰማ ይታወቃል። ነገር ግን ስለቸገረን ለተባለው ድምፅ ይህንኑ ሆሄ በመጠቀማችን ሌላ የቃል መመሳሰል አስከትሏል። ትክክለኛውን የኦሮምኛውን ድምጽ ካልን ግን የተባለው መመሳሰል አይኖርም።

እዚህ ላይ ለፊደሉ እንደ 'ቨ' ሌላ ሆሄ ከመቅረጽ ሌላ፤ ስም በሌላ አይተካም። ልክ 'በ'ን ወደ 'ቨ' እንደቀየሩ 'ደ' አናት ላይ ሰረዝ በማድረግ ለምን አዲስ ሆሄ በፊደላችን ላይ እንደማይጨምሩ አይገባኝም። ይህን ነገር በልጅነቴ ያየሁት ይመስለኛል። ለምን እስከ ዛሬ እንዳላዳበሩት ወይም ለተባለው ድምፅ ሌላ ሆሄ እንዳልተቀረጸለት አይገባኝም። ሰረዙ ከ'ደ' አናት ላይ ቢደረግ ከ'ጀ' ጋር ስለሚመሳሰል ከ'ደ' ግርጌም ቢያደርጉት ችግር ያለው አይመስለኝም። ለማንኛውም ነገሩ መደረግ ያለበት በጥናት ስለሆነ እግረ መንገዴን ለባለሙያዎች ጥቆማ ለማድረግ ነው።

በልጅነታችን 'ቁራ ቆላ ወረደ'፤ 'በቅል ጥሬ ኳኳ' የመሳሰሉትን ሐረጎች ቶሎ ቶሎ ደጋግማችሁ በሉ እየተባልን በሚያስከትለው ሌላ ትርጓሜ በታላላቆቻችን ይሳቅብን ነበር። እንዲህ ያለው የምድጃ ዳር ጨዋታ እንደ እንቆቅልሹና ተረት ተረቱ ሁሉ ማታ ማታ በጊዜ የሚመጣውን እንቅልፍ ስለሚያበርርልን እንወደው ነበር። ጨዋታው ግን ቃላት ሲከታተሉ ሌላ ትርጉም የሚያመጡበት ጊዜ ስላለ ጥንቃቄ እንድናደርግ ትምህርትም ይሰጣል።

ቃልና ቃል ሲናበቡም (ሲገናኙም) ሌላ ትርጉም ያስከትላሉ። አሁንም በቅኔ ቤት 'ልብ' የሚለው ቃል 'ዳዊት' ከሚለው ስም ጋር አይናበብም። በሌላ አነጋገር 'ልበ ዳዊት' (የዳዊት ልብ) አይባልም። ከተባለም ሌላ ትርጉም ያስከትላል።

በደርግ ጊዜ አንድ አቀንቃኝ (ስሟን ዘነጋሁት) ርዕሰ ብሔር መንግሥቱ ኃይለማርያምን ለማወደስ ይመስላል፤ '... ልበ ደንዳና' እያለች ስትዘፍን በሬዲዮና በቴሌቪዥን እንሰማ ነበር። በተለይ ወደ ዘፈኑ መጨረሻ ይህን ሐረግ ደጋግማ ስትዘፍነው እሷ ልብ ያላለችውን ቃል ስሰማ "ይቺ ሰው ሃይ የሚላትም የለ?" እል ነበር። ግጥሙን ያዘጋጀው ሌላ ሰው ከሆነም በዚህ በኩል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገው ነበር። የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎቹም አውቀው ይሁን ሳያውቁ ዝም ብለው ያዘፍኑት ነበር። ምናልባት አውቀው ከሆነም እገዳም ቢያደርጉ ውዳሴውን ከሚፈልጉት ወገኖች ጣጣ እንዳይመጣባቸው ፈርተው ይሆናል።

ከዚሁ ከቃል ማናበብ ሳንወጣ አሁንም በቅኔ ቤት 'እም' የሚለው የግዕዝ ቃል 'ፍጥረት' ከሚለው ቃል ጋር አይናበብም። በሌላ አነጋገር እምፍጥረት አይባልም። እንደዚህ ብሎ ከተቀኘም ቅኔው ላይ ንፍጡን ተናፈጠበት ተብሎ ቅኔው ይነቀፋል። በሌላ አነጋአገር 'እምፍ' ብሎ ተናፈጠበት ማለት ነው። አሁንም 'እም' የሚለው የግዕዝ ቃል ከ'ስ፣ ሥ' ሆሄያት ጋር አይናበብም። ለምሳሌ 'እም' የሚለው የግዕዝ ቃል ከ'ሥጋ' ጋር አይናበብም። በሌላ አነጋገር 'እም ሥጋ' አይባልም። ከተባለም ሌላ አነጋገር ወይም ቃል ብቅ ይላል። የዚህ ዓይነት ሌሎችም አሉ።

እንግዲህ የቀደሙ አባቶች (በተለይ የቅኔ መምህራን) በሥነጽሑፍ ባሕላቸው፤ ንባብን ለማሳመር ምን ያህል እንደሚጠነቀቁ አየን። ቅኔ የሚያስደስተው በይዘቱና በምስጢሩ ብቻ አይደለም። በቃላት አሰካኩም ጭምር እንጂ!

ባማርኛ አነጋገራችንም፤ ባህል ስለሚያስገድደን እነዚህን ከፆታ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ቃላት በግልጽ ላለመጥራት 'አባለ ዘር፤ ብልት፤ ሩካቤ ሥጋ፤ ፍትወተ ሥጋ፤ ተገናኘ፤ አወቀ፤ ወዘተ ...' በማለት አነጋገራችንን እናሳምራለን። እንደነ አቶ ሰሎሞን ዴሬሳ ያሉ ዘመናውያን ገጣሚዎች ደግሞ እነዚህን ድብቅ ቃላት በግልፅ እንድንጠራቸው ድፍረቱ እንዲኖረን በግጥማቸው ቃሉን እየጠሩ ያደፋፍራሉ። ተከታይ ካገኙ መልካም ነው። ነገር ግን ይህ አካሔድ በኛ ሕብረተሰብ ከባህል ያፈነገጠ ይመስለኛል። እንደእምነታችንም አዳምና ሔዋንም ራቁትነታቸውን ሲያውቁ ቶሎ ብለው በቅጠል የሸፈኑት እነዚህኑ አባለ ዘራቸውን ነው። ካልጠፋ ቃል ቃሉም በቃል ቢሸፈን ጥሩ ይመስለኛል።

ይድረስ ከአቶ ቦጋለ ዳኜ፣
ከላይ ባቀረቡት ጽሑፍዎ ላይ የኦሮምኛውን ቃል "በዳዳ" በግዕዝ/አማርኛ ፊደል መጻፍ ይቻላል። እርስዎ የጠቀሷት የኦሮምኛ ድምፅ በአብዛኞቹ ዩኒኮድ የኮምፒዩተር ፊደላት ውስጥ ተካታለች። ፊደሏም እርስዎ እንዳሰቧት በ'ደ' አናት ላይ ቅጥያ በመስራት የተፈጠረች ነች። ከተፈጠረች ረዘም ያሉ ዓመታትን አስቆጥራለች፤ ምናልባትም ከ12 ዓመታት በላይ አልፈዋል። ፊደሏና ዘርዎችዋም የሚከተሉት ናቸው፤ ዸ ዹ ዺ ዻ ዼ ዽ ዾ። ከላይ የጠቀሱትን ስም 'በዻዻ' ብሎ በመጻፉ ትክክለኛውን ድምፅ ማውጣት ይቻላል።

ለአንባብያንም ግር እንዳይል ከዚህ በታች ተመሳሳይ የሆኑትን ፊደላት (ደ፣ ዸ፣ ጸ እና ጰ)ን ልዩነታቸውን አጉልቶ ለማሳየት አቅርበናቸዋል።


ደ ዱ ዲ ዳ ዴ ድ ዶ
ዸ ዹ ዺ ዻ ዼ ዽ ዾ
ጸ ጹ ጺ ጻ ጼ ጽ ጾ (ሁለተኛዋ ፀ)
ጰ ጱ ጲ ጳ ጴ ጵ ጶ

የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!