ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ

ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ

ክንፉ አሰፋ

"ዋሸሁ እንዴ?" (ነን ሶቤ) ሲል ይጠይቃል፣ ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ። ይህንን ጥያቄ የሚያቀርበው ለታዳሚው ሕዝብ አይደለም። በአስር ሺዎች የታደሙበት የኮንሰርት አዳራሽ ውስጥ ከታዳሚው ፊት-ለፊት ለተቀመጡት ለእነ አባዱላ ገመዳ፣ ወይንም ደግሞ ለእነ ለማ መገርሳ ይመስላል። ከፍ ሲል ደግሞ ኮንሰርቱን በቀጥታ ሥርጭት እየተከታተሉ ላሉት የአድዋ ባለ ግዜዎች የቀረበ ጥያቄ ነው።

ይህ ድምጸ-መረዋ ወጣት በምርጥ ቅላፄው ያንጎራጎረው ፉከራ እና ዜማ እጅግ ያስደምማል። ማስደመሙ እውነትን በመድረክ ላይ መዘርገፉ አይደለም። ከራሱ ደህንነት ይልቅ የወገኑን ስቃይ እና ሰቆቃ በማስቀደሙ ነው። እንዲህ አይነቱ እውነትን አደባባይ ወጥቶ በድፍረት የመናገር ገት የነበረው ቴዲ አፍሮ ነበር። ይህንን በማድረጉም በአንባገነኖቹ ጥርስ ውስጥ ገብቶ ብዙ ቢያስከፍለውም፣ ከሕዝብ ልብ ውስጥ ሊወጣ አልቻለም።

በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ፣ ትላንት ምሽት የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመርዳት የኦሮሞ ሙዚቀኞች ማኅበር ባዘጋጀው "ወገን ለወገን" ኮንሰርት ላይ ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ መድረኩን ጠቆጣጥሮት ነበር። የሕዝቡን ስሜት እየኮረኮረ፣ ብሶቱን በአደባባይ ዘርግፎታል። ጠንከር ባሉ ቃላት የተቃኘው ስንኝ ከውብ ድምጽና ቀስቃሽ ዜማ ጋር ታጅቦ ሲቀርብ ልዩ ስሜትን ፈጥሮ ነበር። ይህ ዜማ በቀጥታ ሥርጭት ሲተላለፍ በአዳራሹ የነበረው ድባብ እጅግ ይደንቃል። ሃጫሉ ይጠይቃል፣ ታዳሚው ስሜቱን በጩኸት ይገልጻል። የኦሮሞኛ ቋንቋ ባልችልና የሚለውን ነገር ባልረዳ ኖሮ ይጸጽተኝ ነበር። ይህ ወጣት ድምጻዊ መድረኩን ተቆጣጥሮ ይዞ እንዲህ ይል ነበር፤

Geerar geerar naan jettuu

Dhiirri geeraree hin quufne

Hidhaa qaallitti jiraa

Dhiirri geeraree hin quufne

Hidhaa qilinxoo jiraa

Dhiirri geeraree hin quufne

Hidhaa karchallee jiraa

Karchallee Amboo jiraa...

ይህ ስንኝ በከፊል ወደ አማርኛ ሲመለስ፤

 "ሸልል ሸልል ይሉኛል

ምኑን ልሸልል እኔ

ቂልንጦ አይደለም ወይ

ቃሊቲ አይደለም ወይ

ከርቸሌ አይደለም ወይ

አምቦ ከርቻሌ አይደለም ወይ ...

መኖሪያው የወገኔ ...

የፈረሶቻችንን ዝና፣

የጀግኖቻችንን ዝና

አድዋ ላይ ይንገረና!

መቀሌ ላይ ይነገር!

አብሮ መኖር ይሻላል ብለን …

መከባበር ይሻላል ብለን …

እስከዛሬ ታግሰናል …

ከእንግዲህ ግን ይበቃናል!" ይለል ሃጫሉ።

እስር ቤቱ ሁሉ አፋን ኦሮሞ ይናገራል ሲሉ እነ ስዬ አብርሃ እንኳን የመሰከሩለት ጉዳይ በመሆኑ ይመስላል ሃጫሉ በመሃል እንደ አዝማች፣ "አይደለም እንዴ? ዋሸሁ እንዴ? (ነን ሶቤ?)" የሚለው የዓለምዬ ጌታቸውን ስንኝ የሚያክልበት። በቃሊቲ፣ በቂሊንጦ፣ በከርቸሌ፣ ... እየማቀቁ ያሉ የሕሊና እስረኞች ጉዳይ ከራሱ ደህንነት በላይ ስላስጨነቀው ይህችን አጋጣሚ መጠቀም ነበረበት።

ይህ የጥበብ ሰው ከርቸሌን በወሬ ሳይሆን በተግባር ያውቃታል። የአድዋ፣ የመቀሌ የሚላቸው ጥጋበኞች አምቦ ላይ አስረውት ለሁለት ዓመት አሳቃይተውታል። ለእስር እና ለዱላ ያበቃው ወንጀሉ መብቱን ማወቁ ነበር። በወሩ መጨረሻ ላይ በጊዮን ሆቴል ያዘጋጀው ኮንሰርትም በወያኔ ካድሬዎች ተሰርዞበታል።

ተከባብረን አብረን እንኑር ያሉ የኦሮሞ መሪዎች፤ እነ ፕ/ር መረራ ጉዲና፣ እነ በቀለ ገርባ በአድዋ ልጆች የግፍ ብትር እየተመቱ ነው። አድዋዎቹ ይህንን መከባበር እንደፍርሃት ከወሰዱት፣ መከባበሩ ካሁን በኋላ ያበቃል የሚል መልዕክት ነው ሃጫሉ ያስተላለፈው።

ይህ የሃጫሉ ሥራ፣ አትሌት ለሊሳ ፈይሳ በኦሎምፒክ በመድረክ ከፈጸመው ጀብዱ አይተናነስም። እርግጥ ነው። አትሌት ሌሊሳ ዓለም አቀፍ ትኩረትን ስቦ ነበር። ሃጫሉ ግን መልዕክቱን ሲያስተላልፍ በአንባገነኖቹ ጉያ ሆኖ፣ ሊመጣበት የሚችለውን ነገር ሁሉ ተጋፍጦ ራሱን ለመሥዋዕትነት ያዘጋጀ ጀግና ነው።

ይህንን አድርጎ ቢታሰርም፣ ታሪክ ሠርቷልና ምን ግዜም አይቆጨውም። የግዜ ጉዳይ እንጂ አንባገነኑ ሥርዓት ይሄዳል፤ የሃጫሉ ሥራ ግን ምንግዜም ይዘከራል።

ሙዚቃውን ለመመልከት ይህን አስፈንጣሪ ይጫኑ፣ https://youtu.be/bH61mCEclSw

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ