ሁለቱ ገጣሚዎች (ዳግማዊ ዳዊት እና ደሳለኝ በርሄ) ሙግታቸውን በግጥም እንደቀጠሉ ነው። ዳግማዊ “እርጉዟ ሚስቴ” ሲል ለገጠመው፤ ደሳለኝ “ተልባ ቢንጫጫ” ሲል ምላሽ ሰጥቶታል። እኛም “ክፍል ሦስት” ብለን ሁለቱንም ግጥሞች እንደሚከተለው አቀርበናቸዋል። (የቀድሞዎቹን ሙግቶች ለማንበብ ክፍል አንድ ወይንም ክፍል ሁለት ላይ ይጫኑ!)

 

እርጉዟ ሚስቴ

ዳግማዊ ዳዊት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. 

ቀረ አልቀረ ሚስቴ - በዚህ ወር አርግዛ

አማረኝ ትላለች - ፍትህ እንደዋዛ

ጠዋት ከእንቅልፍ ነቅታ - ምሬት ምሬት ሲላት

ምግብ አይበላት - ውሃም አይጠጣት

ምን ላቅርብ ምን ላምጣ- ብዬ ስጠይቃት

አንድነት ትላለች - ነፃነት በፍትህ

ብቻየን አልጥድህ - ፍትህ ከየት ላግኝህ?

 

“ሙያ ዱሮ ቀረ” ትለኛለች አዝና

ጠይቃኝ ሳላገኝ - ፍትህ እንደገና

 

“ያኔ ዱሮ ዱሮ - አባቴ ተረግዘው

እማሆይ አያቴ - ፉከራ ሲያምራቸው

ዘራፍ ሲሉ አባባ - የአባ ዳኘው አሽከር

ግርማው የአባ በዝብዝ - ሙያው ያምር ነበር

 

አንተማ የኔ ባል - ባሌ የተባልከው

ፍፁም አላየኸው - ሙያውን አታውቀው

ዘራፍ አትል አንተ - ፍፁም አልዋልክበት

እኔ ባለሁበት - አንተ እየኖርክበት

ማን ይበል ይፎክር - ዘራፍ ይበል ወንዱ

አብረን መዋላችን - አይደልወይ ገሃዱ

ትናንት ጀምሬ - ጠይቄ እርጉዝ ሚስትህ

አማረኝ እያልኩህ - ነፃነት በፍትህ

ሙያ በአንተ የለም - ባንተስ ወንድነትህ”

 

ብላ ወንድነቴን - ፈተና ከታው

ጉድ ሆኛለሁ ዛሬ - እንዴት ልወጣው?

እኔ ደካማው ባል - ጀግንነት የሌለኝ

ሚስቴ ያማራትን - ማቅረቡ ተሳነኝ።

 

የትናንት ጀግንነት - የአባቶች ወንድነት

መተባበር ነበር - መታገል በአንድነት

ዛሬ የኔ ትውልድ - አንድነት አቅሮት

ኑሮውን ይገፋል - በኀዘን በምሬት።

 

ማቅረብ እኔ እንድችል - ሚስቴ ያማራትን

ከሁላችን በፊት - ትቅደም ሀገራችን

ፍፁም አይጠቅመንም - መለያየታችን

እስኪ ሁላችንም - እኛኑ እንይና

ምን እንደሚጎለን - እንመርምርና

እንታገል ትግልን - አንድ እንሁንና።


 

ዳግማዊ ዳዊት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ነሐሴ 2001 ዓ.ም.

ተልባ ቢንጫጫ

ደሳለኝ በርሄ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

የሳጥናኤልን ሠራዊት

በአንድነት ቢያሰልፉት

አንድ መልዓክ አይመክት

እንደ ተቃዋሚዎች ቢሆንማ

ማን ይተርፍ ነበር? እኮ ማ?

 

ኢዴኃቅ አሉን ሲጀምሩ

አብረው አንድ ቀን ላያድሩ

አማራጭ አሉ እንደገና

አንድ ዓመት መች ቆዩና

ተጣልተው ሲለያዩ ዓይን ላፈር

ተመልሰው መገናኘታቸውም ባይቀር።

 

ሕብረት ብለው መጡ ሰነባብተው

ባይቀርም ቅሉ ጉንተላቸው

ሳይውል ሳያድር ሕብረቱ

ወጡ እንጅ ከአንድነቱ።

 

ትልቅ ዲያብሎስ ፈጠሩ

ቅንጅት ብለው ቀጠሉ

የዲያብሎስ መጨረሻው ጥፋት

አስከተለ ታላቅ እልቂት

የወገንን ሞት

የሀገር አንጡራን ውድመት።

 

ጉሮሮዬ እስኪነቃ

ብታደርቀኝም ልብ አውቃ

ብታረግዝም ሚስትህ

የጠብ ደቦ አማረኝ ብትልህ

የለህ ቁም ነገር አትሰጣት

እንደ አንድነታችሁ ሂደት

የጠብ ደቦ ከሆነው ሕብረት

አትለይምና በድርጊት

የእርጉዝ ሚስትህ አምሮት

የትም አያደርሳት።

 

እናንተና እናንተን መሳዮች

ሠላም የማይጥማችሁ ወገኖች

ብትተባበሩም እልፍ ጊዜ

በያዛችሁ አባዜ

ዓላማችሁ ፀረ-ሠላም ነውና

እድገት አይታየውምና

ከምላሴ ፀጉር

ትወስዳለህ ዘወትር

የአንተ ድል ቢበሰር።

 

የጀመርከውን ሙግት

ህዝብን በህዝብ ላይ ማነሳሳት

ማበሩን የሚሠራን ሰው ለማወክ

ሀገርን በሚጎዳ መልክ

አይጋ ፎረምን መነካካት

መቀለዱን በሀገር ሠላም አንድነት

አቁመው እወቅበት

ተማር ከሠላም ኃይሎች ቅንነት።

 

እልሃለሁ ዳግማዊ ወዲ ዳዊት

ቀቢፀ-ተስፋ ወልደ-ጥፋት

የተቃዋሚወች ሩጫ

ሁሌም ያው ተልባ ቢንጫጫ

አያልፍምና ካንድ ሙቀጫ።


 

ደሳለኝ በርሄ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!