ሁለት የተለያየ እምነትና ሃሳብ ያላቸው ሰዎች ለረዥም ጊዜ ልዩነታቸውን አስመልክተው መከራከርና መወያየት በኢትዮጵያዊ ባህል አልተለመደም። በፖለቲከኞቻችን መሃል ብቻ ሳይሆን በጓደኛሞችም መሃል እንኳን ቢሆን እንዲህ ያለው ክርክርና ሙግት ብዙም አይዘልቅም። ብዙውን ጊዜ እንዲያውም ያጣላል፣ ያቃቅራል፣ ያራርቃል፤ ብሎም በጠላትነት ያስፈርጃል።

 

ዳግማዊ ዳዊት እና ደሳለኝ በርሄ የተሰኙት ሁለቱ ገጣሚዎች እስካሁን ሳይሰለቹ ሙግታቸውን ቀጥለው ክፍል አራት (፬) ላይ ደርሰዋል። እነሱ ሙግታችን በቃን ካላሉ በቀር፤ ኢትዮጵያ ዛሬ ልታስተናግዳቸው ፈቃዷ ነው። ገጣሚ ዳግማዊ ዳዊት “ጥጃ - ለዘመን መለወጫ” ሲል፤ ገጣሚ ደሳለኝ በርሄ ደግሞ “ለጥጃ - ጠመንጃ?” ሲል ይጠይቃል። ሁለቱንም ግጥሞች እነሆ! (የቀድሞዎቹን ሙግቶች ለማንበብ በቁጥሮቹ ላይ ይጫኑ! ፩ አንድ፪ ሁለት ወይም ፫ ሦስት)

 

ጥጃ - ለዘመን መለወጫ

ዳግማዊ ዳዊት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

በግንባሩ ወግቶ - ቢያጠቃኝ በርግጫ

ቢላ ቢላዋ አለኝ - ለዚህ ክፉ ጥጃ።

 

ዘመን ተለውጦ - ዘመኑ እስኪተካ

“ይወርዳል … ይለቃል” - ወሬ እንዳልተቦካ

ይኸ ጥጃ እምቢ አለ - አልሄድ ብሏል ለካ!

 

ሰፈሩን አመሰው - አጉል ተፈራግጦ

ሰዉ ግራ ገባው - በጭንቀት ተውጦ

እረኛ አይመልሰው - አዳኝ አያድነው

ሰውን እየጎዳ - ከአካል እያወጣው

ለህልፈት ሲዳርግ - እፎይታ ሲያሳጣ

ኑሮን ክፉ ትርዒት - ሲያበዛበት ጣጣ

ምን ጉዴ ሆነ እና ነው - ይህ የሰፈር ጥጃ

ጀግና የለም እንዴ - የሚያውቅ ጠመንጃ።

 

እናንት አድርባዮች - ዘመን ስትለውጡ

ከዚህ ክፉ ጥጃ - አብራችሁ አትውጡ

ብትቀሩ ይሻላል - እናንተስ አትምጡ።

እናንት ወገኖቼ - ከብት የምታረቡ

ይህን ክፉ ጥጃ - ከእናንተ አትደንቡ

እናንተ ተለዩ - ወደ ተራራው

ያ ክፉ ጥጃ ነው - ገደል የሚያምረው።

 

አጨደው ሰርዶውን - የሰፈሩን ሙጃ

ምላሱ መርዝ አለው - እግሩ የጦር ሳንጃ

ረሃብ ላይ ጣለው - ፍየልና በጉን

አጉልኛ ጠባት - ያች በግ እናቱን

ጀግና ምነው ጠፋ - የሚያድን ላሚቱን።

 

ቄራ ሠራተኞች - በግ የምታግዙ

እስኪ በዚህ ዓመት - ይህን ጥጃ ግዙ

ገበያ ውሰዱት - ለዚህ አዱስ ዓመት

አራጅ እንዲወስደው - ሁሉን የሚያውቅበት

አቅርበው ለሽያጭ - ሲራራው ነጋዴ

በሠላም ልተኛ - ይረፍልኝ ሆዴ።

 

ከሰሜን ከምስራቅ - ከምዕራብ ከደቡብ

ተሰባሰብና - ሁሉም ያገሬ ህዝብ

ደስ ብሎን እንድንውል - ዘመን መለወጫ

ጨፌ ጎዝጉዛችሁ - ቄጠማ ወይ ሙጃ

አንገቱ ላይ አርጉ - ቢላዋ ወይ ሳንጃ

ገላግለን በአንድዬ - ከዚህ ክፉ ጥጃ።


 

ዳግማዊ ዳዊት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

መስከረም 2002 ዓ.ም.

“ለጥጃ” ጠመንጃ?

ደሳለኝ በርሄ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ሒትለር ወሰይጣን ከጉድህ በአወጣን

ወይ የዛሬ ጣጣ

ደግሞ ምን አመጣ?

 

ይመኝ ጀመረ

ትናንት የነበረ።

 

ከሂትለር ምኩራብ

ኢድያሚን ድባብ

አክራሪ ሁቱ አምላክ

ለጥፋት የሚላክ

ኮሶቮ አሞራዎች

ሰው ተቀላቢዎች

ዳግማዊ አምሳያዎች

ሁሉም ሲቆጠሩ

በታሪክ ነበሩ።

 

ዳግማዊ አባ ሰይጣን

ዛሬ ደግሞ አስቆጣን

ለዚህ ትጉህ “ጥጃ”

ተመኘለት ሳንጃ

ቃሉ አልቀፈፈውም

ትናንት ቢለምደውም

ህዝባችንም ቢራብ

ህልም ቢሆን ምግብ

ሕፃናት ሲረግፉ

አዛውንት ሲገፉ

ሆኖ ከመ-ጤፉ

ግድ አለው እንዴ እርሱ

ከሞላለት ከርሱ?

 

ዛሬ በእርሱ ሚዛን

ሞልተን አልተገኘን

እርሱ ካልመራ ሀገር

ለእርሱ ሆኖ ሽብር

“ህዝብ ተቆጣ” አለ

ሐሰት ተናገረ

ከፈለግህ ተንጣጣ

“የግለሰብ ቁጣ”

ምንም አያመጣ።

 

ሀገር እያደገች

ዳዴ እያዘገመች

ለሚመራን መሪ

ታሪክም ዘካሪ

በመልካም ስም ጠሪ።

 

መሪዬን ብትጠላው

“ክፉ ጥጃ” ያልከው

አንተ ነህ ወራዳ

የተመኘህ እዳ

የሚያስተውሉቱ

ሁሉን የሚያውቁቱ

ዶክተር አሽብርን

የኢትዮጵያ ህዝብን

አትሰማ ደንቆሮው

መስማት ያልፈለግኸው

ዓይንህ የማያየው

የተጨፋፈንከው

ምላስህ መርዘኛ

የሆንከው ጉደኛ

በተመኘህለት በመሪዬ ፋንታ

ሞትህን ያቅርበው የላይኛው ጌታ።

 

እኛስ መሪያችንን

እንወደዋለን እናከብረዋለን

ለቀቅ አድርግልን።


 

ደሳለኝ በርሄ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!