ሆሳዕና Hosaenaእንኳን አደረስዎ!

ወለላዬ ከስዊድን

ሆሳዕና

ማቴዮስ .21፥1-17

(ግጥሙን በፒ.ዲ.ኤፍ. አስነብበኝ!)

ወደ እየሩሳሌም ወደ ቤተፋጌ

ደርሰው ነበርና ደብረዘይት ግርጌ

በዛን ጊዜ ጌታ ደቀ መዛሙርቱን

እንዲህ ብሎ አዘዘ ጠራና ሁለቱን

ከዛ ከፊታችሁ ከምትገኝ መንደር

አህያ ታስራለች ከውርጫዋ ጋር

ሂዱ ቅደሙና አምጡልኝ ፈታችሁ

ማንም ደግሞ በዚህ አንዳችም ቢላችሁ

በሉና ንገሩት ጌታ አስፈልጎታል

ይሄንን ሲሰማ ወዲያው ይሰዳታል።

 

ፅዮን ሆይ! ንጉሥሽ ባህያ ጀርባ ላይ

ይመጣል እንዳለው አስቀድሞ ነብይ

ደቀ መዛሙርቱም ሄደው አመጡለት

እንዳዘዘው ሆነ እንዲፈጸም ትንቢት።

ባህያ ተቀምጦ ኢየሱስም ሲደርስ

ከህዝቡ ብዙዎች እያነጠፉ ልብስ

ሌሎችም እንዲሁ ከዛፉ ጫፍ ጫፉን

ቆርጠው በመጎዝጎዝ ሸፈኑት መንገዱን

 

ቀድመው የደረሱ የተከተሉትም

ሆሳዕና ለዳዊት ልጅ ሆሳዕና በአርያም

የተባረከ ነው መጪ በጌታ ስም

እያሉ በመጮኽ ይናገሩ ነበር

አንድ ላይ በመሆን ካሉት በዛ መንደር።

 

እየሩሳሌምም ገብቶ እንደረገጠ

ማነው ይኼ እያለ አገር ተናወጠ

የመጣ ነው አሉ ከገሊላ ናዝሬት

ኢየሱስ የሚባል ነብይ ነው አሉት

 

ሁሉን አወጣና ገባና ከመቅደስ

ገዥንም ሻጭንም ተቆጥቶ ኢየሱስ

እንዲሁም አየና ገንዘብ ሚለውጡ

ወንበርም ዘርግተው እርግብ የሚሸጡ

መሆኑ ተጽፎ ቤቴ የጸሎት ቤት

የወንበዴ ጎሬ ዋሻ አረጋችሁት

አሁንም ጸሎት ቤት ይባላል አላቸው

ወንበሮቹን ጣለ ገለባበጣቸው።

 

ዕውሮች አንካሶች ነበሩና መቅደስ

ወደሱ ቀረቡ አረገላቸው ፈውስ

የካህን አለቆች ይሄንን አዩና

ደግሞም ለዳዊት ልጅ ሲባል ሆሳዕና

ድንቅ ድንቅ ሥራው አስቆጣቸውና።

ህዝቡ የሚለውን አትሰማም ወይ ሲሉት

ከህጻኖቹ አፍ ደግሞም ከሚጠቡት

ምስጋና አዘጋጀህ ለራስህ የሚሆን

የሚል ቃል እንዳለ በቅድሚያ መጻፉን

እንዴት አታነቡም ብሎ በመናገር

ቢታንያ አደረ ወጣና ከዛ አገር።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!