ወለላዬ ከስዊድን

(ግጥሙን በፒ.ዲ.ኤፍ. አስነብበኝ!

ፍቅር ታሞ ከርሞ አልጋ ላይ እንደ ሰው

ብዙ ዘመን ሆነ ሞቶ ከቀበርነው

ይሄ ሆኖ እያለ ሞቱን እያወቅን

ለአያሌ ዓመታት ዘፋኞች በዘፈን

አሁንም እንዳለ ሕይወት እስትንፋሱ

ጨርሶ እንዳልሞተ እንዳልወጣች ነፍሱ

አድርገው ሲዘፍኑ ሲያቀብሉን ውሸት

ነገሩን ዋጥ አድርገን አብረን ጨፈርንበት

 

ከሁሉ ‘ሚገርመው የሚደንቀው ነገር

አለ የሚባለው የአሁን ዘመን ፍቅር

ገንዘብን ውሃልክ አ’ርጎ ተመስርቶ

በዓይናችን እያየን መካካዱ ከፍቶ

ዘፋኙ ተነስቶ ሲለን ፍቅር ፍቅር

በሆታ በስክስታ የኛ አብሮ ማጫፈር

 

ከ«እማትበላ ወፍ»፣ «እዘበናኝ» ድረስ

ሆዴ አንጀቴ እያለ ተሸክሞ እንደ ውርስ

ወጣቱም ያንኑ ሲያማስል ሲያቁላላ

ስለከረመበት ሳይቀይር በሌላ

ያወጣው ሙዚቃ ሳይሰማ ጣፍጦ

ዘፈኑ ይሞታል ዘፋኙ ተቀምጦ

ይህ ሁሉ ሲሠራ ይህ ሁሉ ሲፈጠር

እስከ ዛሬ ቆየን ምንም ሳንናገር

ስለዚህ ወደፊት ትዝብት እንዳናተርፍ

ሌላው ቢቀር እንኳን መልዕክት እናስተላልፍ

 

እንግዲህ ወጣቱ ድምጽህን ተጠቅመህ

ዘፈን ስታወጣ ሙዚቃ አቀናብረህ

የሌለች አይነት ሴት የሌለ አይነት ፍቅር

ለዘፈኑ ሲባል ሃሳብ ከምትፈጥር

የምድሪቷን ፀጋ የተፈጥሮን ውበት

የሰውን ባህሪ ክፋት ከደግነት

ስለእናቶች ሙያ ስለአባቶች ገድል

ስለቀለበት ሠርግ ዓመታዊ በዓል

ስለህጻናቶች ጨዋታ ፍንደቃ

ስለ‘ምታጅብህ የማታ ጨረቃ

የጥሩ የመጥፎን የዘመን ትዝታ

የወዳጅ የዘመድ የናትን ውለታ

የሕይወት ገጠመኝ አስደናቂ ውሎን

በጣፈጠ ዜማ ይቻልሃል መዝፈን

እነ «ተማር ልጄ»፣ «ቀጠሮ ይከበር»

ምሳሌዎች ናቸው ላነሳሁት ነገር

ስለዚህ በወደድኩ የውሸት ወከባ

ተጨማሪ ሆነህ ተራ ከምትገባ

የራስህ የሆነ ልዩ ጥበብ ገንባ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!