አብርሃም በየነ

ጥምል እየዞረ በሰማዩ ማገር
በመሬቱ ዙሪያ ዕውነት የሚናገር
ጠባሳው ያልጠፋ የታሪክ አሻራ
መሬቱ መሰለኝ ጠላት የሚያፈራ።

ሀገር በቀል ይሁን የሰው ሀገር ባዕዳ
ዓይን እየማረከ የሚጋብዝ እንግዳ
ከጥንት ጀምሮ እንደ ሚታወቀው
ጠላት የሚያፈራ ለምለሙ መሬት ነው።

ለምለሙ መሬት ነው ጦርነት አብቅሎ
ቤት አልቦ ያስቀረኝ ከቀዬ አፈናቅሎ።

ለም መሆኑ ቀዬ አፈረ - መሬቱ
ጠላቶቸን ጋብዞ ዛሬም እንደ ጥንቱ
ኮሪያው ይሁን ሕንዱ ወይ የዐረቢያው ጉምቱ
እንዲያፈናቅለኝ ገፍትሮ በሀብቱ
ምክንያት የሆነኝ ጫካውና ዱሩ
ጠላቴ ተግሬ ነው መባቀያ አፈሩ።

አያበቅሉ አብቅሎ አያፈሩ አፍርቶ
የሚያፈናቅለኝ ተጎጆየ አውጥቶ
ተግሬ ነው ጠላቴ ተቆምኩበት ምድር
ለምለሙ መሬቴ ገዳይ በሰናድር።

ማጣት ዕርዛቴን ሞቴን እንዲፈጥር
ተፈጥሮው አድርጎት የቆምኩበት ምድር
ልምላሜ ለብሶ ሜዳ እስከ ተራራ
ዓይን እየማረከ ጠላት እያፈራ
ለሙ መሬቴ ነው ኧረ እናንተ ሆዬ
የሚያፈናቅለኝ ካደግሁበት ቀዬ።

ከፍ ያለው በሥልጣን በደሉ የከፋ
ዝቅ ያለው የመሬት በጉልበት ዘረፋ
ጠላቴ ተግሬ ነው በልፅጎ የፋፋ።

ጠላቴ ተግሬ ነው ተቆምኩበት መሬት
ተተክሎ ያደገ ገድሎ የኔን ሕይወት።

ወፍ ዘራሽ አቃቅማ እንደ አሸዋ አፍሶ
ባገረ መሬቱ እሾህ አልከስክሶ
መቆሚያ መሄጃ መራመጃ ነስቶ
ጠላቴ ተግሬ ነው የወጋኝ ተነስቶ።

ወደ ኋላ ዞሬ ስቃኘው ታሪኬን ከዘመናት ጋራ
በግብጽና በቱርክ በጣሊያን ወረራ
ከጥንት ጀምሮ ለክብሬ መደፈር
ጠላቴ ተግሬ ነው ሁሌም ያ ለም አፈር።


አብርሃም በየነ - This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ሰኔ 2003

መሬቶቻቸውን ተነጥቀው፣ ተቀያቸው ተነቅለው፣ ስደተኝነትን ለተዳረጉት ለጎንደሮች፣ ለጋምቤሎች፣ ለቤናሻንጉሎች፣ ለአፋሮች፣ ለኮንሶዎችና ለኦሮሞ ገበሬዎች መታሰቢያ ትሁን።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ