ክንፈሚካኤል ገረሱ

ከዕለታት አንድ ቀን ስድስት ሰዓት ግድም፣
ገሚሱ ሲያሻቅብ ገሚሱ ሲያገድም።
አለቃ ደክሟቸው ወደ ቤት ሲያዘግሙ፣
አመሻሽ አዳሩን ሲቃኙ ሲያልሙ።
በሃሳብ ጅረት ባህር ሲቀዝፉ ሲዋኙ፣
ካንድ ከሚያውቁት ሰው ድንገት ተገናኙ።

ሰውዬውም፤

አለቃ ጥርስ ላይ ያየውን አየና፣
በነገር መጎንተል ማሽሞር ፈለገና።
“አለቃ ዛሬ ተልባ ስንት ስንት ዋለ?” ብሎ ጠየቃቸው በልቡ እየሳቀ፣
አለቃም ገብቷቸው ከልብ ተረድተው ምን እንዳጧጧዘ።
ቁመና አካሂዱን ተክለ-ሰውነቱን አስተዋሉትና፣
ያፉን ጠማማነት የግሩን ወረሃነት አገናዘቡና።
ሕሊናቸው ገብተው አንጎዳጎዱና ትንሽ ፈገግ ብለው፣
“ብዙም አልጨመረ እዚያው ገደማ ነው፤
ያው እንደ ሳምንቱ በጠማማ ቁና ስድስት ስድስት ነው።”
ብለው አስታጠቁት ከእግር እስከ እራሱ፣
አዋዝተው ገረፉት በሸረበው ጅራፍ በገዛ ምላሱ።


ክንፈሚካኤል ገረሱ
ኅዳር 11 ቀን 2009 ዓ.ም.
* ወደ ግጥም የተመለሰ የአለቃ ገብረሃና አባባል ወይም ተረት።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!