ቴዲ አፍሮ

ከትንሣዔ - ነኀሴ 2000 ዓ.ም. (በፒ.ዲ.ኤፍ. አስነብበኝ)

 

የኮራ ባገር የተዋበ፣

ሀቅ ያወቀ ቀልብ የሳበ።

ያገር ኩራት የአንድነት ፈርጥ፣

የእናቴ ልጅ የሕዝቤ ጌጥ።

 

በመረዋ ድምጽህ ፍቅር በሚሰብከው፣

ባለ ቅኔው ብዕርህ እውቀት የሚያፈልቀው።

በዜማ ቅኝትህ ነብስ በሚዘራ፣

የፍቅር ላምባዲና ደምቀህ የምትበራ።

አልሞላለት ላለው ቀን ከሌት ለለፋ፣

ኑሮ ለታከተው የምትሆነው ተሥፋ።

ኩራዝ ሻማ ፋና ቀንዲል፣

የጥበብ ሰው ምጡቅ ጸዳል።

ንዋይ ንቀህ ሕዝብ አክብረህ፣

"አበባ አየሁ" ስትል "ለምለም" ባልንህ፤

የቂም ጦር ሰብቀው ሊያሳንሱህ፣

የቅጥፈት ምላሳቸውን ቢያሾሉ፤

አንተ ሥርየትን ለማኝ ለሁሉ።

 

ያገር ኩራት የአንድነት ፈርጥ፣

የእናቴ ልጅ የሕዝቤ ጌጥ።

የሰላም ምልክት ዘንባባ፣

የፍቅር አርማ ነህ አበባ።

የሆዴን አውቀህ የልቤ እንዲደርስ፣

እንባ ጉንጨን እስኪያርስ።

ልብህን ነክቶ የስደት ጦስ፣

ያዜምክልኝ «ምን ይዤ ልመለስ»።

ይቅር እንድትለኝ እማማ፣

ሀዘኔን የከፈልህ በዜማ።

 

ባልና ሚስት ሁለት ከፍሎ፣

ቢለያያቸው የቀን ጎዶሎ፤

ቃልን ማን ሊነጥለው ችሎ።

ፍቅርዋን ከውሻ ላሳነሱባት፣

የተስፋ ቃልን የሰጠሀት።

ብሶቴን የውስጤን የጮህክልኝ፣

ብለህ ላልከዳሽ ቃል አለብኝ።

እኔም ላልከዳህ የቃል ውል ገባሁ፣

ምን ኩራት ሊኖረኝ መከታዬን ካጣሁ።

 

ቴዲ ወንድሜ አለኝታዬ፣

ያገር ጌጤ መኩሪያዬ።

አገር ሙሉ ነህ እልልታ፣

ሕዝብ አጃቢህ ሕዝብህ መከታ።

በቂም ቋያም ብትቃጠል፣

የነርሱ መንገድ ያንተ አይደል።

 ቢጎበኛቸው የምህረት ዓይን፣

ለነርሱም ስርየትን ለምን።

 

የኮራ ባገር የተዋበ፣

ሀቅ ያወቀ ቀልብ የሳበ።

ያገር ኩራት የአንድነት ፈርጥ፣

የእናቴ ልጅ የሕዝቤ ጌጥ።

አንተ ባገር ሙሉ ነህ በመንደሩ፣

ራሳቸውን በአጋዚ ጦር ያሰሩ፣

ያፈሩ እነርሱ ናቸው ዐይን የፈሩ፤

ቴዲ ፍቅር ነህ የልጅ ጠቢብ፣

በሼመንደፈርህ የምትስብ።

የእስላም የክርስትያኑን ህብር፣

እውነቱን ይፋ እምትናገር።

 

በጥፋት ጅራፍ እየተነዱ፣

የክህደት ቁልቁለትን የሚወርዱ።

እርባና ቢስ ሸንካላ የሀሳብ ቆማጣ፣

ጠቋቁመው የመጡ የዘር የጎጥ ቁምጣ፤

የትውልድ ዝቃጮች ናቸው የረከሱ፣

የሰው ቅማሎች አገር የሚያኮስሱ።

 

እንዳይሆን ብትፈራ ጅብ ከሄደ ውሻ፣

ኡኡታ ስታሰማ ቢሆነን ብለህ መነሻ።

አሳብህ ከአንተ ገዝፎ ቢፈሩ፣

ግዑዝ አካልህን ቃሊቲ አሰሩ።

አልሰማ ብዬ አረግሁህ እንጂ ባለተራ፣

ኡ ኡ ብለህ ነበር ወጥተህ ከተራራ።

አዎ እኔን ብትቀየምም በጥፋቴ፣

ቢወቅጡት እምቦጭ ውሀነቴ።

እለት በእለት አገር ያሉትን እየለቀሙ፣

አንድ ባንድ ሲያፍኑ ሲኮረኩሙ።

"አገር ትቼ መኖር እፈራለሁ፣

ታድያ እስከመቼ እችላለሁ"።

ብለህ በሆንክልን የፍቅር መብራት፣

ጨመሩህ አንተን ጭለማ ቤት።

በስምህ ስም ተጋርቶ፣

ልቡ ከሌላ ሸፍቶ።

ሰው ሆኖ ሰው ያልወደደው፣

እርሱ እንጂ ነው የታሰረው።

 

ቴዲ ኩራት ነህ የአንድነት ፈርጥ፣

የኢትዮጵያ ልጅ የሕዝብህ ጌጥ።

የሰላም ምልክታችን ዘንባባ፣

የፍቅር አርማችን ነህ አበባ።


 

ፍቅር፣ አንድነት፣ ነፃነትና ሰላምን መዘመር ወንጀል በሆነባት ሀገር በመፈጠሩ ፍዳውን ለሚቆጥረው ወጣት

ኢትዮጵያዊ ወገናችን ለቴዲ አፍሮ የተጻፈ።

 

ከትንሣዔ - ነኀሴ 2000 ዓ.ም.

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!