ክንፈሚካኤል ገረሱ

ግራም ኪሎ ሳይሆን የዕውቀት ሚዛኑ፣
ጠረፍ አድማስ ሳይሆን የዕውቀት ወሰኑ፣
ሦስት ነው ደረጃው የጥበብ እርከኑ።

አንድ
ዓይኑን ከመግለጡ ከጀመረ ጉራ፣
መስሎ ለመታየት በሜዳ ካጓራ።
ያለ እርሱ አዋቂ ፈፅሞ ካልታየው፣
ጥራዝ ነጠቅነት በቁም ካጠለቀው።
ባውቃለሁ ደንዝዞ ሕሊናው ከጦዘ፣
ከላይ ሲሽሞነሞን ውስጡ ከነቀዘ።
በባዶ ኮፍሶ የሚያቅበዘብዘው ማስተዋል የነሳው፣
ወፌ ቆመች ዳዴ የዕውቀት ሀ ሁ ነው።

ሁለት
ለመውጣት ሲጣጣር የዕውቀትን ማማ፣
ይዞ ሲያውለበልብ የክህሎትን አርማ።
ሲጓዝ ሲገሰግስ ለመድረስ ካለመው፣
በልፋት ጥረቱ ሲረካ ሕሊናው።
ባወቀ በገባው በተካነ ቁጥር፣
ሚስጥር ስንክሳሩን ማበጠር ሲጀምር።
ያቀደው ሲሳካ ትልሙ ሲሰምርለት፣
ይበልጥ የመመስጠር ጉጉት ካደረበት።
ውስጡ ተሰድሮ የሚወተውተው የሚጎተጉተው፣
የዕውቀት ርካቡ ካልዕ መደቡ ነው።

ሦስት
ጥበብን አሹሮ መፍትሔ ሲፈትልበት፣
ዝናው ሲያስተጋባ በየደረሰበት፣
በትሩፋት ግብሩ ዓለም ሲመካበት።
ሁሉ በእጁ ሳለ ጥነት ካልተሰማው፣
ብስለቱ ሕፀፁን ጉድለቱን ካሳየው፣
ይህ ነው አናት ቁንጮው የዕውቀት መቋጫው።


ክንፈሚካኤል ገረሱ
ታህሳስ 2፣ 2009 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ