አብርሃም በየነ

የታጨደው ሳር ድርቆሽ ነው የከብቶች መኖ በመሆን

በበሬ ጫንቃ ድካም ጠግቦ አደር ያደረገን፤

የሞተው የግጦሽ ሳር ነው ጮሌ ፈረስ አሳድጎ

በጦር ሜዳ የድል ብሥራት ያቀዳጀን ጀግና ተዋጊ አድርጎ፤

የበሬውን ቆዳ ከበሮ የበሬውን አንጀት ጅማት

የፈረሱን ሞት በደል የሸንበቆውን ያካል ስብራት፤

የእንስሳቱን ሞት ከእሳሩ ሞት ጋር ስናዋድደው

ከሞት ምንጭ ነው ለካስ የደስታ ጅረት የሚወርደው።

የሞተ በሬ አንጀት ነው፤ የክራር ጅማት ሆኖ

ያሳለፍነውን ሕይወት ወደ ፊት አጠንጥኖ

መልሶ የሚያኖረን ያለፈውን ጊዜ ትዝታ

ሳናውቀው ለካስ ሞት ነው፤ የሚለግሰን ደስታ።

የሞተ በሬ አንጀት ነው፤ የክራር ጅማት ሆኖ

ልባችንን የሚያሸፍተው በቼ በለው ቅኝት ፋኖ።

የሞተ በሬ ቆዳ ነው፤ ከበሮ ሆኖ ተወጥሮ

ሲነረት ሲደበደብ ልዩ ቃና ድምጽ ፈጥሮ

ባጀቡት ዜማዎች ግነት ቅላጼውን አጉልቶ

መድረኩን ሲነቀንቀው ንዝረቱ ስሜት ነክቶ፤

የተሰበረው ሸንበቆ ነው፤ አካሉ ተበሳስቶ

በጣት ላይ ትንፋሽ ጨምሮ፤ የዋሽንት ድምጽ አፍልቆ

አዕምሮን የሚያብከነክን የሰውን ቀልብ ሰርቆ

የሞተ ፈረስ ጭራ ነው፤ የአዝማሪ ጥበብ ማሲንቆ

ደስታ የሚዘራብን ስሜታችንን ሰርቆ።

ከተገደለ እሳር፣ ከተገደለ በሬ፣ ከተሰበረ ሸንበቆ

ከሞተ በሬ አንጀት፣ ከሞተ ፈረስ ጭራ መረዋ ድምጽ ፈንጥቆ

ከሞተው ክርስቶስ ሕይወት፣ የምህረት ፀበል ፈልቆ

የአዳምን ልጆች ሁሉ በደሙ ዋጅቶ ያፀዳው

ከሞት ምንጭ ነው ለካስ፣ የሰው ደስታ የሚቀዳው።


*መታሰቢያነቷ የሥነ ሃሳቡ ምንጭ ለሆነው ከያኒ እሱባለው ይታየው

አብርሃም በየነ

መስከረም ፳፻፲ ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ