እንቁጣጣሽ

ከትንሣዔ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

መልካም ዘመን ይሁን ልበል እንቁጣጣሽ፣

ደህና ጊዜን ይዘሽ ደግሞ ደግሞ ያምጣሽ።

ድሮ እንደምናውቀው ፍቅር ነው ደመራ፣

ለምለም አበባ ነው እልልታ ጭፈራ።

አዝመራው አፍርቶ ሲታየን ጥጋቡ፣

መስከረም ተስፋ ነው ያባራል ዝናቡ።

እርቅ ነው ፍቅር ነው ውበት አዲስ ዘመን፣

ለእድገት እይታውም ተስፋ እሚያስጨብጠን።

 

ዛሬ ግና እኔኑ ሆዴን እየባሰው፣

በእህህታ በቁጭት እንዲህ ነው የምለው።

«ደግሞ ዞሮ መጣ አይታክተው መዞር፣

ቆሜ ስጠብቀው ፈቅ ሳልል ስንዝር።

ባምናው እከኬ ላይ መጣ ደግሞ ዞሮ፣

መከራ እንግልቴን ችግሬን ጨምሮ።

እንቁን አስቀርቼ ልበል እንጂ ጣጣሽ፣

ዘመናቴ ሁሉ ውርደት ሲሆን ርካሽ።

ዛሬ እንደምናየው ዘመነ ግርምቢጥ፣

አጉል ተሸንሽነን በጎሳና በጎጥ።

እፍኝ እንኳ ጠፋ ማንም አልጠገበ፣

ትግሬው ኦሮሞውም አማራም ተራበ።

ብድርም ፍለጋ አልሄድ ጎረቤቴ።

ከጦም አዳሪዋም አልጠይቅ ከእናቴ።

ወይ የዘመን ጥፉ እንዲህ የዘመመ፣

ትንሹ ትልቁ ቀረ እንደ ቆዘመ።»

 

መልካም ዘመን ይሁን ልበል እንቁጣጣሽ፣

ደህና ጊዜን ይዘሽ ደግሞ ደግሞ ያምጣሽ።

ድሮ እንደምናውቀው ፍቅር ነው ደመራ፣

ለምለም አበባ ነው እልልታ ጭፈራ።

ቴወድሮስ ካለበት ከቃሊቲ እንግባ፣

እርሱ እዲያዜምልን ኢዮሀ አበባ።

ኢትዮጵያ ቃሊቲ ቃሊቲም ኢትዮጵያ፣

ምን ልዩነት አለው እዚህ ሆንን እዚያ።

 

ለመጭው ዘመኔ የኔውስ ምኞቴ፣

ብፈራ ብሸሸግ ላይቀርልኝ ሞቴ።

አጠረ ቀጠነ ሳልልም ወፈረ፣

ጠይም ነው ቀይ ነው አልያም ጠቆረ።

ችግሬ ከገባው ችግሩ ከገባኝ፣

ወገኔ ከሆነው ብዬው እንጎዳኝ።

ወተትና ጓያ ደብልቄ ሳልበላ፣

የክፋት መንገድን ብለን መላ መላ፤

ነጻነቴን ለኔ ነጻነቱን ለርሱ፣

ፍቅርና ፍትህ ሕዝቤ እንዲቃመሱ።

የሰው እንጂ የዘመን ጥፉ የለምና፣

አረሙን ነቅለን የሚታረቀውን እንድናቀና

ወሬን በቁም ነገር ተንኮልን ደግሞ በስራ፣

ተስፋና በረከት እህሉም ሞልቶ በጎተራ፤

እንቁጣጣሽ ማለት ያኔ እልልታውና ጭፈራ።


 

መልካም አዲስ ዘመን ለሁላችሁ!   

ከትንሣዔ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )  

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!