አፅም ይሰደዳል?

ከትንሣዔ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

(አሜሪካን ሀገር ላለችው ሉሲ/ድንቅነሽ የተገጠመ)

 

የኛ ነገር የኛ ስም ባገሩ ክብር አልባ፣

 

የኛ ነገር የኛ አጥንት ቀሊል ከገለባ።

 

ምልስ የማይል ሲጓዝ ሲሄድ ኖሮ፣

 

በስደት እንዲያልቅ በጉዞ ተጀምሮ።

 

ራሳቸውን ቢንቁ ቢመርጡስ እንኳ ቅሌት፣

 

አፅም ወዳገር እንጂ እንዴት ይሸኛል ስደት?

 

ከምድር ማኅጸን ተፈልቅቃ ብትሆነን አሻራ፣

 

መንከራተት ይሁን እንዴ የድንቅነሽ ወር ተራ?

 

ቡና አይደለች አበባ እስቲ በምንተዳዋ፣

 

”ላንቲካ” የቀረበው ድንቅነሽ ክቡር አጽምዋ።

 

አይደለች የክብር ዋንጫ የአሸናፊዎች ቅብብሎሽ፣

 

እንዴት ባሳብ ቢያንሱ ነው አንቺን ለስደት የዳረጉሽ?

 

ከርሳም ተውልዶም አይደል የልጅ ልጅ ገልቱ፣

 

ከቶ ቅር ማ’ይለው በአያቶቹ አፅም መጫወቱ።

 

ከቀመሰችው አፈር ከአቀፈችው በአፅምዋ፣

 

የተቀሰቀሰች በግድ ከዘመናት መኝታዋ።

 

እንዲህ ይሻቀጡባት ክብር የጠሉ ልጆችዋ?

 

እኛው እንጂ ወሽካቶች ተፈጥረን ወኔ አልባ፣

 

ውር ውር የምንል ባጉል እሰጥ አገባ።

 

መቀመጫ ሀገር ሳይኖር ለሁላችን እሚበቃ፣

 

ሁላችን የምንመኝ ልንሆን የሁሉ አለቃ።

 

አሳባችን እንደ እህላችን ፍሬው ትንሽ የቀጨጨ፣

 

ምኞታችን እንደ እድገታችን እልፍ የማይል የጫጨ።

 

መዳረሻ ግባችንን መርምረን በውል ሳናውቅ፣

 

የእኔ አውቃለሁ የመንገድ ምርጫ ነው የኛ ጭቅጭቅ።

 

ላሚቱ ሳትኖር በጥጃ ማሰሪያው ትንቅንቅ፣

 

በተረቱ እኛ ስቀን በእኛም ሌላው ይሳለቅ?

 

አንድ ሁለት እየቆጠርን ውርደታችንን ስንሸምት፣

 

እንኳንስ ለእኛ ለድንቅነሽም ይትረፍ ስደት?

 

እርስዋም እንደ ልጆችዋ የፈረንጅ ጉያ ልትሞቅ፣

 

ሄደች አሉን እንጂ ምንዋ እንደሚመለስ አናውቅ።

 

ግና ዳሩ የሁሉም እናት ሉሲም ይበሏት ድንቅነሽ፣

 

እኛ በክብር ካልያዝናት ካከበሯት ጋር ትምነሽነሽ።


ከትንሣዔ - መስከረም 2001

( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

(አሜሪካን ሀገር ላለችው ሉሲ/ድንቅነሽ የተገጠመ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!