የደም ጎርፍ

በደም ጎርፍ - የፈዘዘ

ቁራጭ ሰይጣን - የደነዘ

ጤና ያጣ ዙፋን ያዘ።

 

የደም ጎርፍ - መጣ ደራሽ

የህዝብ ጥያቄ - ምላሽ።

የደም ጎርፍ - ጠራራጊ

ደርሶ አስማጭ አረግራጊ።

 

የደም ጎርፍ - ይኸው እዛም

መልሱ ለአህዛብ የሚያስገርም።

ተረሸነ በሀገሩ

ራበኝ ባለ ይሄ ኩሩ።

ተደለዘ ተወቀጠ

መንደር ቀዬው ተናወጠ።

ስላላቸው ‘በሕግ አምላክ!’

ሕግን ጥሰው አስያዙት ብርክ።

 

የደም ጎርፍ - እንደጅረት

ይንኳለላል በያለበት።

ተርቤያለሁ ዳቦ ባለ

ተረሸነ ተገደለ።

እንደራበው እንዳዛጋ

ወገናችን ወህኒ ፈጋ።

ልብላ ባለ - በለመነ

በአጋዚ ተረሸነ።

 

የደም ጎርፍ - የደም ፍሳሽ

መፍራት ቀረ ግፍን ጭራሽ።

 

የደም ጎርፍ - አብረቅራቂ

መላው ጠፋ አስታራቂ።

ባገራችን …

ግራር ጠፍቶ ላይን ጠላቂ

ጡንጅቶቹ ሆኑ አዋቂ።

 

የደም ጎርፍ - የደረቀ

ወርዶ ካፈር ተጣበቀ

ፍትህ ባለ - ህዝብ አለቀ።

 

የደም ጎርፍ - በየቀዬው

የጎሣ ጦር ያደባየው

የተፈታው ባፍ በወሬ

ጠፋው መላ አዬ ዛሬ።

 

የደም ጎርፍ - ከዚያ ካምባ

የህዝባችን ሲቃ እምባ

ቃላት የለው ልሳን አልባ

ባጋዚ ጦር ወህኒ ገባ።

 

የደም ጎርፍ - ግፍ በዛ

ደሃ አለቀ እንደዋዛ

‘መብቴን ስጡኝ፣ ልኑር’ ባለ

በያለበት ተገደለ።

 

የደም ጎርፍ - ሆነ ኩሬ

አጨቀየው ያንን አውሬ

ተነከረ በደም ጎርፍ

ህዝብ አለቀ ያለሰልፍ።

 

አልደራጅ እምቢ ይቁም

የጎሣ ጦር አያሻንም

ብሎ ባለ ከፋ ችግር

ተላለቀ ህዝቡ ካገር።

 

የደም ጎርፍ - ጡሩ ጠፋ

ኧረ የት ነው የኛስ ተስፋ?

ተወልጄ ባደኩበት

ልኑር ባለ ከተዳፋት

ካፋፍ ወስደው ገደል ላኩት።

 

የደም ጎርፍ - እዚህም እዛም

ደኅና ሁን በል ዘረ አዳም።

ነጠብጣቡ የማይለቀው

አዕምሮህን አጎደፈው።

 

የደም ጎርፍ - ከዚያ ካምባ

ካገራችን ሰይጣን ገባ

ወንድማማች ደም ተቃባ።

ቂም ነገሠ የለየለት

ቁርሾው ሊያይል ሊሆን ጥፋት

የታሰበው የዶለቱት

ዕውን ሊሆን ላንድ ምዕት።

 

ይሁን ባለ ምርጫው ደኅና

ባደባባይ በጎዳና

ወገን ሆኗል መቀጣጫ

ደሙ ጎርፏል ለቂም መውጫ።

 

አታፍኑን እንናገር

ብሎ ባለ መላው ሀገር

በቦምብ ናዳ ተጠበሰ

ያገሬ ሰው በደም ራሰ።

 

የደም ጎርፍ - በደም ጣባ

ወርዶ ረጋ ነጋ ጠባ

ልኑር ባለ - በታከተ

ያ ወገኔ አይሞት ሞተ።

 

የደም ጎርፍ - ባገራችን

በኢትዮጵያ እናታችን።

እየሰሙ ቅዱስ ቃሉን

የፈጣሪ የእግዚአብሔርን

አጋዩዋቸው ድንገት ገብተው

በመቅደሱ ቀሩ ሞተው

አየለብን ጥጋባቸው

እኒህ ሰዎች ወዮላቸው።

 

በደም ጎርፍ - በጠቆረ

ምድረ ወጣት ተሳከረ።

ተግቶ ላገር ስላደረ

ከሥራው ላይ ተባረረ።

ሀገር ወዳድ ተጥላላ

መግቢያ ጠፋው ጉዱ ፈላ።

ተቆርቋሪ ለሀገሩ

ስሙ ጠፋ ሞተ ክብሩ።

ተሰደደ ካገር ጠፋ

ነፍሱን ሊያድን ያዘ አካፋ።

 

በደም ጎርፍ - የፈዘዘ

ቁራጭ ሰይጣን - የደነዘ

ጤና ያጣ ዙፋን ያዘ።

 

ጩኸት በዝቷል የደማችን

ካምላክ ደርሷል ፈጣሪያችን

ይውረድልን ምህረቱ

ትታደገን ማርያሚቱ።


 

ሃዲዱ

01 አፕሪል 2007

 

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!