ፋሲካ (ፊልጶስ)
ፋሲካ
ፊልጶስ - ከሆላንድ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)
በጊዜ ሰንሰለት - በጊዜ ቀመር ወቅት
አልፈህ የምትመጣው ሁሌም ዓመት - በዓመት
የሙታን ትንሳዔ ታላቁ ዓውደ - ዓመት
”የኩዳዴ መፍቻ” እንዴት ነህ ፋሲካ
በአንተ ያፈረ አለወይ ወይስ የተመካ? ...
ለማን ዛሩ ወርዶ ሆነለት ’ጆከር’
ማንስ ተነጅሶ ዞረበት ’አኪር‛ …
እነማን አፍርሰው እነማን ጰጰሱ
እነማን ተሽረው እነማን ነገሡ
እነማን ተገለው እነማን ተርፍዋል
እነማንስ ጠፍተው እነማን ለምተዋል
እነማን ሄደው እነማን መ’ተዋል
እነማንስ ከድተው እነማን ታመኑ
ተጠየቅ ፋሲካ በዓውደ - ዓመት ዘመኑ? ...
ፎቅ በፎቅ ገብቶ
አዲስ ቪላ ሠርቶ
ወይም መርጦ ገዝቶ …
በአዲስ ልብስ አጊጦ
አምሮ ተሽቆጥቁጦ …
ሰንጋ ፍሪዳውን - በግ ዶሮውን አርዶ
ጮማ ሥጋ ቆርጦ - በጠጅ በውስኪ በጠላ አወራርዶ …
ስንቱ ሰው ፈሰክ በቀዬ ባድባሩ
ስንቱስ ጾም አደረ - ስንቱስ ተሳደደ በገዛ ሀገሩ።
ቤተሰቡን አ’ቶ - ቤት ንብረቱ ፈርሶ
በወገን ትዝታ ውስጥ ልቡ ታምሶ
በሰው ሀገር ምድር በስደት ‘ካምፕ’ ኑሮ
በኀዘን በመከራ - በእዬዬ - በእሮሮ
ስንቱ ውሎ አደረ የባዕዳ እጅ ልሶ
ዓውዳ - ዓመትህ እምባውን አፍስሶ።
ከሙያ ጉሮሮው - ከሥራው ተነስቶ
የጎጆ ቅልሱን የእጁን ተቀምቶ
‘በፕላስቲክ’ ጣራ በጎዳና ኑሮ
ስንት ወገን ፈሰከህ አ’ቶ ‘መናኛ’ ዶሮ።
እነማን ታስረው - በእነማን ተግዘው
ያለፍርድ ዘብጥያ - ከርቸሌ ወርደው
በዕለተ ፋሲካህ …
በዕለተ ዓውደ - ዓመትህ …
በሃሳብ በትካዜ በትዝታ ዋለ
በ’ውነት ትንሣዔ ነው - በዓል ነወይ እያለ።
የነማን አባቶች - የነማን እናቶች
የነማን ወንድሞች - የነማን እህቶች
የነማን ልጆች - የነማን ወገኖች …
በየስርቻው ... በየጎዳናው
ተንቀው ... ተዋርደው
ተረግጠው ... ተጥለው
ሲለምኑ ዋሉ በዕለተ ዓውደ - ዓመትህ
ማንስ ሆነ መጽዋች ዘካሪ በስምህ።
ፋሲካ ያ’መት ነህ
ብታልፍ ትመጣለህ
ምን ‘አኪር’ ይዘህ ነው
ምን ‘ካርታ’ ስበን ነው
ደ’ሞ የዛሬ ዓመት የምንገናኘው ??? ...
ፊልጶስ - ከሆላንድ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)