በቃኝ! 

ብርዞ ከፍራንክፈርት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

በቃኝ! እኔ በቃኝ! አዎ! በቃኝ! በቃኝ! ...

በደል ግፍ ስሰማ እኔን መሰል ስቃኝ

አልንበረከክም እጄንም አልሰቅልም

ህሊና አስገድሎ ሆድ ማዳን አይቀልም

ውርስ ላይሆን ከቶ ለትውልድ ለሀገር

ነፃነት አይሸጥ መብት አይመነዘር

 

ቆንጥሩ ቢወጋኝ አፈር ልሼ ብውል

ቢደክመኝ ባልጠጣ ባጣ ጥሬ እህል

መብቴን ነፃነቴን አጥቼ ከምኖር

አይቀሩን ሞት ልሙት ለሀገሬ ክብር

 

ባልዋን ልታስጥለው ባያስችላት ሆድዋ

በግፈኛ አጋዚ ወደ እስር ሲነዳ

ለአቤት ባይዋ መልሱ ጥይት በደረትዋ

ደጅ ላይ ተደፍታ ምስኪንዋ እናትዋ

ቅንጅት ገደላት ብለሽ ካልፈረምሽ

አስከሬን የለም እዚህ እንዳትደርሽ

የተባለችው ልጅ ወገን ያለህ እያለች

በራድዮ ስትለን ፍረዱኝ ወገኖች

ይህንን የሰማን የኢትዮጵያ ልጆች

ልባችን ተሰብሮ አንገታችንን ደፍተን

እንባ ከዓይን ሲያመልጥ በኀዘን ተውጠን

ነበረ ውላችን ይህን ግፍ መመከት

ዕድሜውን ማሳጠር የወያኔን እብሪት

አራት ዓመት አልፎት ግፍ እየበረታ

አስሮ እየገረፈ አፍኖ እየመታ

ጠመንጃ ደግኖ ረግጦ በጉልበቱ

ፊታችን ላይ ፈጧዋል ተራዝሞ ሕይወቱ

 

በቃኝ! እኔ በቃኝ! አዎ! በቃኝ! በቃኝ! ...

በደል ግፍ ስሰማ እኔን መሰል ስቃኝ

 

 

ፍትህ ለሁላችን ብንል በአቤቱታ

’በሕግ አምላክ!’ ብለን መልስ ለቅሬታ

18 ዓመት ሀገር ህዝብ ተጎድቶ

አዲሱ ሲቆስል የቆሰለው ደምቶ

ሲቆስል የደማው የደማውም ሞቶ

መቅበር ብቻ ሆነ ሌላ መላ ጠፍቶ

 

’አያያዙን አይተህ ጭብጦውን ቀማው’

ያሉት ትዝ ይበለን ድሮ ከጥንት አበው

አብራካችን ብለን ፍትህን ስንጠብቅ

ነጣጥሎ እያጠቃን እጁ ስንወድቅ

ገልብጦ ሲገርፈን ጨለማ ወርውሮ

እንደወጡ መቅረት የትም ተሰውሮ

ቤት ይቁጠረው እንጂ መች ያልቃል ተቆጥሮ

የሠላም አፀፋው ይህ ነው ውሎ አድሮ

 

መልስ የሚፈልገው በአንደበቱ አቅጣጫ

ወያኔ ዘረኛው የሚያምን በጡጫ

በያዘው መሣሪያ በጀሌው ቢመካ

የህዝቡን ጨዋነት በፍርሃት ከለካ

ውርደቱ ይሆናል የታሪክ ስህተት

ብሶት ጀግና ወልዶ ’በቃኝ!’ የሚልበት

ነፃነት እስትንፋስ እስትንፋስ ነፃነት

ሊነካ ሊታገድ የማይሞከር መብት

ሕይወት ለሕይወት ሲል ነዶ የሚያልፍለት

የቁም ሞትን አጋጅ የኢ-ሰባዊነት

ለሕግ ያልተገዛ ተመክሮን ያጣ

ሰልፍ ቢከለክል አፋኝ ሕግ ቢያወጣ

ሁሉም በያለበት በነቂስ ወጥቶ

ለፋሽስቶች ሳይበገር ሳይበተን ጸንቶ

ሚሊዮኖች እንነሳ ኢትዮጵያን እናድን

ኅብረ-ፀረ-ወያኔ አንድነት አጎልብተን

እጃቸው ተይዞ እንዲቀርቡልን ለፍርድ

’በቃ! በቃ!’ እንበል ሁላችንም እንደ አንድ


 

ብርዞ ከፍራንክፈርት This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!