ጥቁር አንበሳ

”አንተ ምን አለብህ ያለኸው እውጭ? የፈለከውን ትቀባጥራለህ! እዚህ ለእኛ ደግሞ ዕዳ ትሆናለህ። እዚያ ያለህበት አርፈህ ብትቀመጥ ለእኛም የመከራችን ቋት አትሆነንም ነበር። እባክህ ባትደውል ጥሩ ነው! አንተን ለመከታተል ብለው ስልካችንን ስለሚጠልፉት ያልሆነ ነገር አናግረኸን ታስጠረጥረናለህ? ተጠርጣሪ ደግሞ ተጣርቶ ፍርድ እስከሚሠጥ ድረስ ሊታሠር እንደሚችል ማወቅ አለብህ” ... - የስልክ ልውውጥ

 

”ሄሎ!” አለ ወፈር ያለ ድምፅ፡- በድምፅ አወጣጡ ከውጭ የተደወለ መሆኑን መገመት ይቻላል።

 

”ሄሎ! ደህና ነህ? ወንድም ዓለም?” አለ ተቀባዩ።

 

”ለጤናህ ሰላም ነህ? ቤተሰብ ሁሉ ደህና ናቸው?”

 

”አዎ ደህና ናቸው”

 

”እማዬም አባዬም?”

 

”ሁላችንም ሰላም ነን።”

 

”እንዴት ነው ይህ የኑሮ ውድነት እንዴት ይዟችኋል?”

 

”በል እንግዲህ ፖለቲካ አትናገር እኛ ሁላችንም ሰላም ነን፣ የኑሮ ውድነትን ማንሳት አያስፈልግም። እኔን ከመጠየቅም የኢትዮጵያን ቴሌቪዥን ተመልከት፣ እንደሌለብን ይነግርሃል።”

 

”እሱ ካልነገራችሁ እናንተ አታውቁም ማለት ነው?”

 

”ብናውቅስ ከእሱ እንበልጣለን እንዴ?”

 

”እኔ እኮ የጠየቅሁት ስለ እናንተ ነው። በዚያ ላይ ስለኑሯችሁ መጠየቅ የፖለቲካ ጉዳይ አይደለም።”

 

”ለምን አይደለም? አንተ የመንግስት ተቃዋሚ አይደለህም?”

 

”ብሆንስ ዲሞክራሲያዊ መብቴ እኮ ነው፤ ወያኔ እናንተን አፍኖ ማሰቃየቱ አንሶ እኔም ልታፈንለት?”

 

”ነግሬሃለሁ ፖለቲካ አትናገር፤ አንተ እዚያ ማንም አይነካኝም ብለህ የፈለከውን እየቀባጠርክ እኛ ላይ መዘዝ አታምጣብን? የዚህ ዓይነት ንግግርክን ካልተውክ ቶሎ ስልኩን እዘጋዋለሁ።”

 

”ቆይ! ቆይ! ሌላውን እንተወውና፤ እነ እማዬ እንዴት ናቸው? እማዬ! ይቆረጣጥመኛል የምትለው በሽተዋ ከታከመች በኋላ እንዴት ነች?”

 

”ደህና ለውጥ አላት። አሁን እንደ ልቧ እየተንቀሳቀሰች ነው። ሽት!”

 

”ምነው እናቴ ደህና አይደለችም እንዴ?”

 

”ኧረ! ደህና ነች፤ ሳላስበው ”የአሸባሪዎች” የሚመስል ነገር ስላናገርከኝ ነው እንጂ ”ሽት!” ያልኩት እሷ ደህና ነች አታስብ? ጥሩ ኦፖረሽን አድርገውላታል! ኤጭ! አሁንም እሳሳታለሁ?”

 

”ምን ሆነህ ነው?”

 

”በቃ እባክህ የሚያስጠረጥር ነገር አታናግረኝ?”

 

”ምኑ ነው የሚያስጠረጥረው?”

 

”’እንደልቧ እየተንቀሳቀሰች ነው’፣ ’ጥሩ ኦፕሬሽን አድርገውላታል’፣ ’በቃ!’፣ ... የሚሉትን ቃላቶችና ዐረፍተነገሮች ጠልፈው ከሰሙት እኮ! ሊያስሩኝ ይችላሉ። አታውቅም? ሽት! አሁንም መልሼ እደግመዋለሁ?”

 

”በእውነት ወያኔ በሕዝባችን ላይ እንዴት ተጫውቶበታል? በቃ ስለቤተሰብም ጉዳይ ነፃ ሆኖ ማውራት አይቻልም ማለት ነው?”

 

”አንተ ምን አለብህ ያለኸው እውጭ? የፈለከውን ትቀባጥራለህ! እዚህ ለእኛ ደግሞ ዕዳ ትሆናለህ። እዚያ ያለህበት አርፈህ ብትቀመጥ ለእኛም የመከራችን ቋት አትሆነንም ነበር። እባክህ ባትደውል ጥሩ ነው! አንተን ለመከታተል ብለው ስልካችንን ስለሚጠልፉት ያልሆነ ነገር አናግረኸን ታስጠረጥረናለህ? ተጠርጣሪ ደግሞ ተጣርቶ ፍርድ እስከሚሠጥ ድረስ ሊታሠር እንደሚችል ማወቅ አለብህ” ...

 

”ኧረ! እባክህ አትንቦቅቦቅ? ለመብትህ መታገል ነው ያለብህ? ጭራሽ ወያኔ እዚህም ለመብቴ እንዳልታገል፣ ከቤተሰቤም ጋር በስልክ እንዳልገናኝ ማዕቀብ ያደርግብኛ! አርፈህ ተቀመጥ የምትለው? አላወቅከውም እንጂ እናንተን በማስፈራራት እኛንም ውጭ ያለነውን በእናንተ ምክንያት በእጅ አዙር በማፈን ለመጨቆን ነው የወያኔ ዓላማው!”

 

”እንቢ ካልክ ስልኩን እዘገዋለሁ! በአንተ የተነሣ ቃሊቲ ገብቼ ልበሰብስልህ እንዴ? አሁን ቆይ ባለፈው አንዱ ጋዜጠኛ የአባቱ ዓይን ኦፕሬሽን በአጋባቡ መከናወኑን በጥርጣሬ መልክ በመግለፁ በአሸባሪነት ቃሊቲ እንደገባ ሳትሰማ ቀርተህ ነው? እኔን የምታደርቀኝ?”

 

”የመናገር ነፃነትን አጥቶ ከመኖር ቃሊቲ መታሠር አይሻልም?”

 

”ኧረ እባክህ? ዓይኔ እያየ እሥር ቤት ገብቼ ዕድሜዬን ልገፍግፍልህ?”

 

”አሁን ያለህበት ከመታሠር ምን ይሻላልና!”

 

”አንተ ምን አለብህ? ያለኸው ውጭ! ችግሩ የሚታወቀን ለእኛ ነው። እሺ በቃ አናግሪው! ውይ ሳላስበው ”በቃ!” የሚለውን ቃል አናገርሽኝ።”

 

የተናጋሪው እናት ናቸው መሰል ስልኩን ተቀብለውት ”ምን ትነዘንዘዋለህ! አንተ አርፈህ አትቀመጥምና አንድ የሚረዳኝ ልጄ ወህኒ ይግባልህ እንዴ?”

 

”እንደዚያ እኮ አይደለም እማዬ! ዝም ብሎ ነው የምናገራቸውንና የሚናገረውን ቃል ሌላ ትርጉም እየሰጠ የሚጨነቀው። ደግሞስ መጀመሪያ ሰላምታ አይቀድም እማዬ? እንዴት ነሽ ህመሙ ከታከምሽ በኋላ እየተወሽ ነው? ለውጥ አለው?”

 

”ደህና ነኝ!”

 

”አሁን እንደልብሽ መንቀሳቀስ ቻልሽ?”

 

”ደህና ነኝ አልኩህ!”

 

”እንዴት ነው ያደረግሽው ኦፖሬሽን ምንም ጉዳት አላደረሰብሽም?”

 

”ቆይ! አንዴ ጠብቀኝ!” ስልኩን አፍነው ነው መሰል ”አንተ ማሙሽ! ኦፕረሽን! አፕሬሽን! እያለ እየጨቀጨቀኝ ነው፤ እኔ ብነገረው ያስጠረጥራልኛል?” ብለው ለልጃቸው ሲጠይቁት ይሰማል።

 

ልጁም ”ኧረ! እማዬ አይገባሽም እንዴ? ስንት ጊዜ እነግርሻለሁ? ’ኦፕሬሽን ማድረግ’ የሚለውን ’ሽብር መፈፀም’፣ ’መንቀሳቀስ’ የሚለውን ’ሽብር ማከናወን’ ወይም ’የሽብር ተግባር የሚፈፅሙ ሰዎችን መመልመልና የሽብር ተልኮ ማስፈፀም’ ማለት ነው ብለው ይተረጉሙታል። እሱ ደግሞ ቀንደኛ ተቃዋሚ መሆኑን ማንም ያውቃል። ስለዚህ ከልጅሽ ተልኮ ተቀብለሽ ለማስፈፀም ስትንቀሳቀሺ ነበር ብለው ቢከሱሽ ከ15 ዓመታት ያላነሰ አንችንም እኔንም ሊቀፈድዱን ይችላሉ፤ እናም እናቴ ለእኔ ስትይ ቢቀርብሽ ይሻላል።” ብሎ ተናገረ።

 

ሆኖም አባትዬው ናቸው መሰል ”እባክሽ ይህንን ሴታ ሴት ልጅ ተይውና መነጋገር ያለብሽን በአግባቡ አነጋግሪው! እንዴት ወያኔ የሚባል ሽፍታ ስልክ አስጠልፎ በመስማት ሊያስረን ይችላል ተብሎ እናትና ልጅ ስለቤተሰብ ጉዳይ መወያየት ይፈራሉ? ወይ ዘመን ወይ ጊዜ?” አሉ በንግግራቸው የተበሳጩ ይመስላሉ።

 

”ኤዲያ ድሮም እርስዎ ነዎት ካልጠፋ ነገር ልጄን ስለፖለቲካ እያወሩ አሳድገው እውጭ እንኳን ሔዶ አርፎ በመቀመጥ ፈንታ ሥራውን ትቶ የፖለቲካ ፈትፋች በመሆን ለእኛም የኑሮ ሰቀቀን የሆነብን! አሁን ማን ይሙት ችግሩ ሳይገባዎት ቀርቶ ነው? የምንነጋገረውን ጠልፈው ከእሱ ጋር በስልክ ስለኦፖሬሽን እንቅስቃሴ በመነጋገር ተጠርጥራችኋል በማለት ብንታሰር በቀላሉ የሚለቁን ይመስሎዎታል?”

 

”በቃ እሺ አንቺ ከፈራሽ እኔ ስለሁሉም ነገር ላናግረው፤ ስጭኝ ስልኩን።”

 

”አልሰጥዎትም! እኛ የምንናገረው ያስጠረጥረናል እያልን? ለእርስዎ ሰጥቼ ”ወያኔ! አገር ሻጭ! ከኢትዮጵያ ካልነቀለልን ምን ሰላም አለን ብለህ ነው! እንድህ አደረጉ! እንደዚህ ተናገሩ! እንዲህ ማድረግ ነበር ወዘተ ወዘተ እያሉ” አውርተው! ስድበዎን አውርደው! አውርደው! ሁላችንም ተያይዘን እንግባለዎታ!” እያሉ ሲናደዱ ይደመጣሉ።

 

ከዚያም ወደ ስልኩ ተመልሰው ”ሄሎ!” አሉ።

 

”ሄሎ! ምንድን ነው የምታወሩት እማዬ? ምንድን ነው የሚያጨቃጭቃችሁ?”

 

”ምንም አይደለም፤ የቤተሰብ ጉዳይ ነው።”

 

”እየሰማኋችሁ እኮ ነው፤ ውይ! ውይ! ይህንን ያህል ታፍናችኋል ማለት ነው?”

 

”ለካ ስልኩን አላፈንኩትም፤ አዬ ጉድ እነሱም ሰምተዋላ! በቃ ቻዎ!”

 

”ምነው ስለደኅንነትሽ አልነገርሽኝም እኮ?”

 

”ደኅንነት! የምን ደኅንነት? ምንም ደኅንነት የለም።”

 

”እንዴ! እያመመሽ ነው ማለት ነው?”

 

”ኧረ! እንደዚያ ማለቴ አይደለም። ጤናዬንማ ደህና ነኝ፤ እየተሻለኝ ነው።”

 

”እንዴ እኔማ ከታከምሽ በኋላ አገርሽቶብሽ ያመመሽ መስሎኝ ደነገጥኩ።”

 

”ደኅንነት የሚለውን ቃል ስለተጠቀምክ ብዬ ነው።” መጀመሪያ በስልክ ሲያናግር የነበረው ልጅ ከስልኩ ርቆ ነው መሰል ”ኧረ! እማዬ ተጠንቅቀሽ አውሪ!” አላቸው።

 

”በቃ ደህና ሁን! ልጄ ለእኔ አታስብ ደህና ነኝ። ምንም አትጨነቅ፤ የቻልኩትን ያህል እንደልቤ መንቀሳቀስ ችያለሁ።” ካሉ በኋላ ”ወይ! አሳሳትከኝ፤ ባትደውል ጥሩ ነው።”

 

”ለምን?”

 

”አሁን ይኸ ጠፍቶህ ነው፤ አትደውል አልኩህ አትደውል! በቃ!” ብለው ደነገጡ መሰል ”በል ቻዎ!” ብቻ አሉ።

 

”እሽ! እስከ መቼ ነው የማልደውለው?”

 

”በቃ ቻዎ! አልኩህ አይደለም፤ የባሰ ነገር ልታናግረኝ ፈልገህ ነው እንጂ አሁን ይኸ ጠፍቶህ ነው?” አጠገባቸው ያለው ልጅም ”እማዬ እሱ አሸባሪ ከሚባሉት ጋር ግንኙነት ሊኖረው ሲለሚችል፤ አጠቃላይ ባይደውል ይሻላል፤ ያለበለዚያ እሱ በፈጠረው ግንኙነት የተነሣ እኛም ”በተዘዋዋሪ ከአሸባሪዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር” ተብለን ልንታሰር እንችላለን።” ሲላቸው ይሰማል።

 

የደወለው ልጅ ደግሞ ”እኮ! እስከመቼ ነው የማልደውለው እማዬ?” ብሎ በድጋሚ ጠየቃቸው።

 

”አሁን ይኸ ጠፍቶህ ነው? ያለው መንግሥት እስቲቀየር ነዋ!” ብለው አሁንም የባሰ ደነገጡ መመሰል ”ወይኔ ጉዴ! የባሰውን አናገረኝ!” ብለው ስልኩን ጠረቀሙት።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!