ተስፋዬ ገብረአብ

ሳቂታ ውብ ጥርሶችና ታማኝ አይኖች ያሏት ሸዋረጋ የምትባል አንዲት ልጅ ነበረች። ነዋሪነቷ ወሎ ላይ ነበር። ገና የስምንት አመት ህፃን ሳለች ወላጅ እናቷ ስለሞተችባት ለአንዲት አሮጊት በግርድና ለማገልገል ተቀጠረች። ይህች እድለቢስ ልጅ አባቷን አታውቀውም። እንጀራ ጋጋሪ ከነበረች ወላጅ እናቷ የተገኘ ውርስም አልነበራትም።

 

 

አሮጊቷ በበቅሎ ሲጓዙ፣ እየተከተለች ከበቅሎዋ እኩል መስገር ዋና ስራዋ ሆነ። ምሽት ላይ የአሮጊቷን እግር ታጥባለች። ማለዳ ቤት ትጠርጋለች። ገረድ እንደመሆኗ የታዘዘችውን ሁሉ ትሰራለች። በዚያን ዘመን ሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ልማዱ ነበር። ወታደሮች ወሎን እያቋረጡ ያልፋሉ። ወታደሮች ወደ ዘመቻ ሲሄዱና ሲመለሱ ማየት ለሸዋረጋ የእድገት ትዝታዋ ነው። አንዳንድ ጊዜ ስሜቷ እየተነሳሳ፣ የተቀጠረችበትን የግርድና ስራ በመተው ከወታደሮቹ ጋር ወደ ዘመቻ ትሄድ ነበር።

 

በዘመኑ አስተሳሰብ ለአቅመ አዳም እንደደረሰች ከምስራቅ ኢትዮጵያ ከመጡ ወታደሮች አንዱ ሸዋረጋን ወደዳት። ምንም እንኳ ችግር ያደቀቃት ገረድ ብትሆንም፣ ቁንጅናዋን በማስተዋል፣ ልበሙሉ ፈገግታዋን በማጤን ሚስቱ አደረጋት። እሷም ቢሆን ከግርድና ይልቅ የአንድ ወታደር ሚስት መሆን እንደሚሻል በማመን ሳታመነታ ወደ ትዳር አለም ገባች። ወታደሩም ግዳጁን ፈፅሞ ሲያበቃ ሚስት ይዞ ወደ ሃረርጌ ተመለሰ። እነሆ! ያቺ ተስፋ አልባ የነበረች ምስኪን ልጅ አሁን የተሻለ ህይወት መኖር ጀመረች።

 

አንድ ቀን ከባልዋ ጋር ሲጨዋወቱ፣

 

“ሸዋ! ምንድነው ይሄ አንገትሽ ላይ ያለው ድግምት?” ሲል እንደ ዋዛ ይጠይቃታል።

 

“ምንም” ትላለች።

 

“አለምክንያትማ አላንጠለጠልሽውም?”

 

መልስ ሳትሰጥ ዝም ትላለች፣

 

ባሏ ጠረጠረ። መስተፋቅር ሊሆን ይችላል ብሎ ስለገመተ ወደ ንስሃ አባቱ ሄዶ ሚስቱ አንገት ላይ ስለታሰረው ድግምት ይናዘዛል። ቄሱ ሚስትየውን ለማነጋገር ይፈቅዱና ባልየው በሌለበት እለት ወደቤት በመምጣት ሸዋረጋን ያነጋግሯት ጀመር።

 

“እንዲያው ይሄ አንገትሽ ላይ ያሰርሽው ምን ይሆን?”

 

ሸዋረጋ በልቧ የያዘችው ምስጢር ቢሆንባትም፣ ቄስ ጠይቆ መልስ መስጠት ግዴታ ነውና እናቷ ከመሞቷ በፊት የነገረቻትም ምስጢር ተነፈሰች፣

 

“እናቴ ናት ያሰረችልኝ …”

 

“ምን ይሁንሽ ብላ አሰረችልሽ ልጄ?”

 

“የማን ልጅ መሆኔ ተፅፎበታል ብላ ነገረችኝ …”

 

“ማናት እናትሽ? ወዴት አለች አሁን?”

 

“እንጀራ ጋጋሪ ነበረች። የሰባት አመት ልጅ ሳለሁ ሞተችብኝ …”

 

“እስኪ ወዲህ በይው ልጄ?”

 

ሸዋረጋ አንገቷ ላይ የታሰረውን ክታብ ፈትታ ለቄሱ አቀበለች። ቄሱ እያማተቡና አንዳች የማይሰማ ነገር እያጉተመተሙ የታሰረውን ክታብ በጥንቃቄ ፈቱት። የተጣጠፈውን ወረቀትም በርጋታ ዘረጋጉት። እናም አነበቡት። በማንበብ ላይ ሳሉ በድንጋጤ ብዛት ትንፋሻቸው ሊያመልጥ ምንም አልቀረውም። በተቀመጡበት ተፈንግለው እንዳይወድቁ፣ መከዳውን ደገፍ ብለው አቀርቅረው ቀሩ። ሸዋረጋ ከቄሱ ድንጋጤ ጋር አብራ ስለደነገጠች አባቷ ማን እንደሆነ እንዲነግሯት ተጣድፋ የጠቀች። ቄሱ ግን የተጠየቁትን በመመለስ ፈንታ መልሰው ለልጅቱ ጥያቄ ያቀርቡላት ጀመር፣

 

“እናትሽ ስላባትሽ ምን ነግራሻለች የኔ ልጅ?”

 

“ምንም አልነገረችኝም፣ እሷ ስትሞት ትንሽ ነበርኩ …”

 

“ምን ትዝ የሚልሽ ነገር አለ?”

 

“ምንም የለም።”

 

“መቼም ምንም አልነገረችሽም አይባልም። እስኪ አስታውሺ?”

 

“ምንም አልነገረችኝም አባቴ። ድሃ ነሽና ከሰው ተጠግተሽ እደጊ! ካደግሽ በሁዋላ ግን ይህን በአንገትሽ ላይ በቆዳ ሰፍቼ ያሰርኩልሽን ወረቀት ለምታምኛቸው ሰዎች አሳዪ’ ብላኝ ሞተች …”

 

“ከእናትሽ ጋር የት ነበራችሁ?”

 

 

“ወሎ ነበርን። እስላሞች ቤት …”

 

“እናትሽ እስላም ናት?”

 

“ለመኖር ብዬ ነው እስላም ቤት የገባሁት ብላኛለች።”

 

“እናትሽ ማንነበር ስሟ?”

 

“ደስላ”

 

ሸዋረጋ ልቧ ተሰቅሎ እንደገና ጠየቀች፣

 

“ወላጅ አባቴ ማነው?”

 

“አጤ ምኒልክ ናቸው የኔ ልጅ …”

* * *

እነሆ! ሸዋረጋ እና ባልዋ ከሃረርጌ ወደ አዲስአበባ ጉዞ ጀመሩ።

 

አንዲት መጠጊያ ያጣች ወላጅ አልባ ሴት ያገባ የመሰለው ወታደር ከንጉሰ ነገስቱ ሴት ልጅ ጋር ጋብቻ መፈፀሙን ማመን ቸግሮታል። ህይወት እድል ናት። እድል እያዋከበ ወስዶ የንጉስ ልጅ ባል አድርጎታል። በዚህ ምክንያትም ከንግዲህ ህይወቱ ይለወጣል። በርግጥም ሹመት እንደሚያገኝ አምኖአል። የልእልት ባል እንደመሆኑ ተራ ሰው ሆኖ ሊቀጥል አይችልም። ቢያንስ ደጃዝማችነት ማግኘት እንደሚገባው ሳያሰላስል አልቀረም። የንስሃ አባቱ የመከሩትና የነገሩትም ይህንኑ ነው፣

 

“እድለኛ ነህ። ከንግዲህ ኑሮህ ይለወጣል። ሚስትህን ወደ ንጉሱ ውሰዳት። የእሳቸው ልጅ ነች …”

 

ባላገሩ ወታደር ይህንኑ ጣፋጭ ህልም እያኘከ፣ ሸዋረጋ ምኒልክን ይዞ ከመናገሻዋ ከተማ አዲስ አበባ ገባ።

* * *

እቴጌ ጣይቱ በጥሞና ካዳመጡ በሁዋላ፣

 

“አስገቧቸው” ሲሉ አሽከራቸውን አዘዙ።

 

የተጎሳቀሉ ባልና ሚስት ባላገሮች ከንግስቲቱ እልፍኝ ገብተው ለጥ ብለው እጅ ነሱ። እቴጌ ጣይቱ ልጅቱን አተኩረው መረመሯት። የእናቷን ቁንጅና ይዛ መወለዷን ሳያስተውሉ አልቀሩም። ፈገግ ስትል ፀሃይ ብልጭ ያለ ይመስላል። አይኖቿ የአባቷን እንደሚመስሉም ታዝበዋል። እናቷ ከቤተመንግስቱ ስትባረር ይህች ልጅ የ7 ወር ፅንስ እንደነበረች ያስታውሳሉ። የተፈፀመውን ዝርዝር ነገር ሁሉ ያስታውሳሉ። አሁን ግን ፀፀት ቢጤ ልባቸውን ጫር ሳያደርገው አልቀረም።

 

በርግጥ በዚያን ዘመን፣ ቅናት በልምጩ ሸንቁጧቸው የነበረ ቢሆንም በጊዜ ብዛት አሁን ያ ስሜት ጠፍቶአል። ደስላ ከወሎ የመጣች ኦሮሞ ነበረች። አንገቷ እንደ ኪሊዮፓትራ ነበር። ደርበብ ሞላ ያለች በጣም ቆንጆ። አንድ ቀን ከአጤ ምኒልክ ገረዶች አንዷ እመኝታ ክፍላ ድረስ በመምጣት እንዲህ አለቻት፣

 

“የይሁዳው አንበሳ ፈልገውሻል”

 

“ምነው በዚህ ሰአት?”

 

ደስላ ገረዲቱን ተከትላ በጨለማ ውስጥ ወደ ንጉሱ የመኝታ ክፍል በመጓዝ ላይ ሳለች፣

 

“ንጉሱ ለምን ፈለጉኝ?” ብላ ጠይቃ ነበር።

 

“ወደውሻል! እድለኛ ነሽ” የሚል ምላሽ አገኘች።

 

ንጉሠ ነገሥቱ ከዚያን ቀን ጀምሮ ከዚህች ውብ የወሎ ኮረዳ ጋር የፍቅር ግንኙነት ነበራቸው። በመካከሉ ደስላ ፀነሰች። ማርገዟም ይታወቅ ጀመር። ሆኖም ፍርሃት ይዟት ለንጉሱ ሳትናገር ቀረች። በቤተመንግስቱ ዙሪያ የደስላ ማርገዝ በሹክሹክታ ይወራ ጀመር። ከአጤ ምኒልክ ልጅ መውለድ የሚመኙ ሁሉ፣ ደስላ ከንጉሱ በማርገዟ በቅናት ጦፈዋል። እቴጌ ጣይቱ በወቅቱ ይህን ሁሉ ዝርዝር ቢያውቁም፣ አንዳች ሊያደርጉት የሚችሉት ነገር አልነበራቸውም። ደስላ ማርገዟን ለንጉሱ ከመንገሯ በፊትም አጤ ምኒልክ ወደ ሰሜን ዘመቱ። ከዘመቻ ሲመለሱ ደስላ ቤመንግስት ውስጥ አልነበረችም።

 

… ርግጥ ነው፣ ደስላ ከቤተመንግስት ከተባረረች በሁዋላ አጤ ምኒልክን ፍለጋ ወደ ሰሜን ተጉዛ ነበር። በጉዞዋ ላይ ግን ወለደች። ህፃኗ የንጉሱ መሆኗን መናገር አደጋ ይኖረዋል ብላ ሰጋች። የጣይቱ ሰዎች ይህን ከሰሙ ከነልጇ እንዳያስገድሏት መፍራቷ አልቀረም። ስለሆነም፣ ለራሷም ሆነ ለልጇ ህይወት ስትል ንጉሱን በአካል እስክታገኝ ምስጢሯን በሆዷ መያዝ መረጠች። የምትጠጋበት ወገን ስላልነበራትም እንጀራ ጋጋሪ ሆና ማገልገል እጣ ክፍሏ ለመሆን በቃ። እንዳለመችው ግን አልሆነም። ታመመችና ህይወቷ አለፈ።

 

እቴጌ ጣይቱ ለአሽከራቸው ትእዛዝ ሰጡ፣

 

“ሰውነቷን ታጥባ ንፁህ ልብስ እንድትለብስ አድርጉ።”

 

ደጃዝማችንትን እያለመ ረጅም መንገድ የተጓዘው ወታደር ታሪክ ግን ከዚያ በሁዋላ ከምድረገፅ ጠፋ። ‘እኩያህን ፈልገህ አግባ’ ከሚል ምክር ጋር ለኑሮ የሚሆን ድጎማ ተሰጥቶት ተሰናብቶ ሊሆን ይችላል።

 

በዚያው ሰሞን አጤ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ እንደተለመደው እያወጉ ሳለ፣

 

“ያቺ ይወዷት የነበረች ገረድ ትዝ ትሎታለች?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

 

“የትኛዋ?”

 

“ወደ ሰሜን በዘመቱ ጊዜ እዚህ ትተዋት የሄዱት። ከዘመቻ ሲመለሱ እንኳ ‘የት ሄደች?’ ብለው ጠይቀው ነበር። ልናገኛት ስላልቻልን ግን ልናመጣልዎ አልቻልንም”

 

“አስታውሳለሁ። የወሎዋ ልጅ አይደለችም? ተገኘች እንዴ?”

 

“የርስዎን ሴት ልጅ በወለደች በሰባት አመቷ ሞታለች።”

 

አጤ ምኒልክ ክፉኛ አዘኑ። ልባቸው ሳይሰበር አልቀረም። መረር ባለ አነጋገርም ለእቴጌ ጣይቱ ትእዛዝ ሰጡ፣

 

“ያለፈው አልፎአል። ስለ እግዚአብሄር ብለሽ ልጄን ፈልጊልኝ?”

 

“ንጉሠ ነገሥት ሆይ! ደስ ይበልዎ! ልጅዎ ተገኝታለች”

 

እቴጌ ጣይቱ እልፍኙን ለቀው ወጡ። ሲመለሱም ስምንት ተመሳሳይ ልብስ የለበሱ፣ በተመሳሳይ እድሜ ላይ የሚገኙ ኮረዶችን አስከትለው ገቡ። አጤ ምኒልክ ድራማው ገባቸው። ከስምንቱ መካከል አንዷ ከዚያች በጣም ከሚያፈቅሯት የወሎ ኦሮሞ ወለዷት ልጃቸው ናት ማለት ነው። አጤ ምኒልክ ከዙፋናቸው ተነስተው እንደ እግር ኳስ ተጫዋቾች ቡድን በተርታ የተደረደሩትን ኮረዶች አንድ ባንድ ያስተውላቸው ጀመር። እየተጠጉ መረመሯቸው። እናም ጥቂት እንኳ ሳያመነቱ፣ ሸዋረጋ ምኒልክን ከሴቶቹ መሃል ለይተው እጇን ያዟት፣

 

“ልጄ ይህቺ ናት!” ሲሉም ጮኸው ተናገሩ። አያይዘውም ጨመሩበት፣ “… ጥርሶቿና ፈገግታዋ ቁርጥ የእናቷ ነው!...”

 

(ሸዋረጋ ምኒልክ ለወሎው ራስ ሚካኤል ተድራ ጥር 25፣ 1888 ወረሂመኑ ተንታ ውስጥ ልጅ እያሱ ሚካኤልን ወለደች። አጤ ምኒልክም ለሚያፈቅሯት ሴት የልጅ ልጅ የንጉሠ ነገሥትነት ሥልጣናቸውን አውርሰው አረፉ…)


ተስፋዬ ገብረአብ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!