ጠ/ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ, PM Hailemariam Desalegn(ምናባዊ)

ፊልጶስ

እናት ለልጇ ያላትን ፍቅር መለኪያ፣ ወሰን፣ ድንበርና ግዜ ይኖረው ይሆን? … በእግዚአብሔር ፈጣሪነትና ፈቃድ፤ ዘጠኝ ወር በመሀጸኔ ተሸክሜ፣ በጭንቅና በጣር አምጨ ወለድኩት። አርባ ቀን ሲሞለው እምነታችን በሚያዘው መሰረት ክርስትና አስነሳሁት። በክርስትና ስሙ ኃይለማርያም ብዬ ስም አወጣሁለት። ጡቶቼን እያጠባሁ፣ የምችለውን ሁሉ እያደረኩና የማይጠገበውን የእናትነትን ፍቅር እየመገብኩ አሳደኩት። ወደ ዘመናዊ ትምህርት ቤትም ላኩት። ልጄም ለቁምነገር በቃ። ከስልጣን ወደ ስልጣን ተሸጋገረ። ከትልቅ ደራጃም ደረሰ። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትርም ተባለ። ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ የኔ ልጅ።

 

 

መቼም የእናት ፍቅርና ስቃይ መሳ-ለመሳ ነው። ትልቅ ደረጃ ላይ መድረሱ የሚያስድስተኝን ያህል፤ ”ምን ይሆን? ወይስ ምን ይደርስበት ይሆን? ...” የሚለው የሌት-ተቀን ሀሳብና ጭንቀቴን እናት ብቻ ነው ሊረዳው የሚችለው። የጭንቀታችን አይነት ይለያይ እንጅ፤ ልጅ ኃይለማርያምም ለ'ኔ ይጨነቃል። ”እናቴ አልዳንሽም! … እጸልይልሻለሁ! …” እያለ።

 

የተማረውና ብዙ ያውቃል የምለውን ልጄ የሚለኝ ባይገባኝም፤ ዝም ብዬ አልፈው ነበር። እየዋለ እያደረ ሲሄድ ግን ”ጆሮ ለባለቤቱ ባ'ድ ነው!” እንደሚባለው ሆነና ከጉረቤቶቼ ”ልጅ ኃይማኖቱን ከድቶ”፤ ከባህር ማዶ በመጣ አዲስ ኃይማኖት እንደለወጠ ተነገረኝ። ደነገጥኩ። ተጠራጠርኩም። ተቆጣሁም። ተናደድኩም። ተገናኝተን እስካናግረው ድረስ ቀኑ 'ረዘመብኝ። ለነገሩ እስካገኘው ሁሌም ቀኑ እንደረዘመብኝ ነበር። ይህ ግን የተለየ ነው። እናም ”ምን ቢቃጠሩ ደረሰ ቀኑ!" ነውና ልጄን አገኝሁት። ነገር ግን ገና ሳየው ቁጣዬንና ንዴቴን ሁሉ ናፍቆቱ አጠፋብኝ። እንዴት አድርጌ ልቆጣውስ? እንዴት ብዬ ልናደድስ? ... ደስ ሲለው ደስ ብሎኝ፣ የከፋው ሲመስለኝ ከፍቶኝ፣ የራበው ሲመስለኝ እርቦኝ፣ የጠማው ሲመስለኝ ጠምቶኝ፣ ወ'ቶ እስኪመለስ ድረስ ”የሆነ ነገር ይደርስበት ይሆን?' እያልኩ ፈጣሪን እየተማጸንኩና ለአርባ አራቱ ታቦት እየተሳልኩ፤ መገቢያ በሩን እያየሁ በጭንቀተና በስስት ባሳደኩት ልጄ ለመናደድና ለመቆጣት የእናትነት ልቤ እንዴት ይፍቀድልኝ?። አሁን እንዲህ ትልቅ ሰው፣ ባለስልጣንና ባለሀብት ሆኖ እንኳ’ በልቶ የሚጠግብ፣ ለበሶ የሚያጌጥና ወ'ቶ በሰላም የሚመለስ ይመስለኝም።

 

የቤተሰብ ጉዳይ አንስተን ብዙ ስንጨዋውት ከቆየን በኋላ ግን፤ ስለሰማሁት ነገር ስፈራ ስቸር አነሳሁበት።

 

”ልጄ! ... ለመሆኑ የምሰማው ነገር እውነት ነው?”

 

“ምን ነገር ሰምተሽ ነው?”

 

”ጠፍቶህ ነው? ... ሀገሩ ሁሉ ስለ አንተ አይደለም እንዴ ሲያወራ የከረመው። መቼም አሮጊት እናት ምን ታመጣለች ብለህ ነው? ለነገሩማ እኔ ባይገባኝ እንጅ አንተማ ልትነግረኝ ሞክረህ ነበር።"

 

ሳላስበው እምባዬ በጉንጮቼ ላይ መፍሰስ ጅመሩ። ልጄ በድንጋጤ ”ምነው በደህናሽ ነው?" አለና አቅፎ ሊያባብለኝና ምክንያቴን ለማወቅ ተጠጋኝ።

 

”ለመሆኑ ልጄ …" አልኩ ለቅሶየን ለመግታት እየሞከርኩ። ”ለመሆኑ … ኃይማኖታችንን ከድተህ፣ ሌላ ኃይማኖት መከተል ጀምረሀል የሚባለው እውነት ነው?”

 

እንደመሳቅ አለና፤ መሀረም ከኪሱ አው'ቶ እምባዬን እየጠረገ፤ እኔ ወይም ሌላው ሰው እንደሚለው ኃይማኖታችን ሳይሆን የከዳ፣ ትክክለኛውን የክርስቶስን መንገድ እንደተቀበለና እኔም ብቀበል ዘላለማዊ ህይወት እንደማገኝ መከረኝ። የ'ኛ ወይም የ’ኔ ኃይማኖት ትክክል እንዳልሆነና ገና ያልዳንን መሆናችን ጨምሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል "እየጠቀሰ” ሊያስረዳኝ ሞከረ። ”እናቴ አልዳንሽም! ... እጸልይልሻለሁ! …” አለኝ። እኔም ሁሉ ነገር ግልጽ ሆነልኝ። ለግዜውም ቢሆን እምባዬ መፍሰሱን አቆመ። ልቤ ግን ያለቅስ ነበር።

 

በራሴ ሀሳብ ውስጥ ገባሁ። ልጄ እኔን ”አልዳንሽም!” ሲለኝ፤ ስለ እግዚአብሔር እናገራለሁ እያለ ”… በማንም ሰው ላይ አትፍረዱ! …” የሚለውን ህያው ቃል ዘነጋው ይሆን? ምን አልባት መጽሐፍ ቅዱሳቸው ከ'ኛ የተለየ ይሆን? ወይስ ፈረንጆች የ'ነሱን እምነት እንድንከተል ሆን ብለው አሳስተው ተርጉመው ልጄንም አሳሳቱብኝ ይሆን?

 

ልጄ ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር እንደሚለኝ ከሆነ፤ እሱ የሚከተለውን ኃይማኖት ያልተከተለ ሁሉ ”ያልዳነና የጠፋ ነው።” ታዲያ ይህን ሳስብ ልቤን ሀዘን ተሰማው። በማን እንዳዘንኩ ግን በትክክል አላወኩትም። አእምሮዬ በሀሳብና በጭንቀት ናወዘ። እንደሰማሁትና እውነት ከሆነ፤ ልጄ አሁን የሚከተለው ኃይማኖት ከተጀመረ ሶስትና አራት መቶ ዓመት ቢሆነው ነው። ታዲያ ከዚህ በፊት የነበረው የሰው ልጅና አሁንም ከ'ሱ እምነት ውጭ የሚከተለው የአምላክ ፍጡር ሁሉ የጠፋና ያልዳነ ነው። ይህ ደግሞ እንዴት ሊሆን ይችላል?

 

ኃይማኖት የግል ነው። ይህ የሰው ልጅ የተፈጥሮ መብቱ ይመስለኛል። የልጄ ኃይማኖታዊ ግንዛቤ በ’ኔ በእናቱ ”አልዳንሽም! ..." ብቻ ብሎ የሚያቆም አይመስለኝም። ፈረንጆች እምነታቸውን በዚች ሀገር ለማስፋፋት ስለሚጥሩ፤ ልጄ የያዘውን ስልጣን ከለላ በማድረግ በሌሎች ዜጎች ላይ ተጽኖ ላማሳደር እንዳይጠቀሙበት ፈራሁ። ”ያ'ገሩን በሬ ባ'ገሩ ሰርዶ!” አይደል የሚባለው። ”ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ይጋጭብኝ ይሆን?” ብዬ የእናትነት ነፍሴ ተጨነቀች። ጭንቀቴን ዋጥ አድርጌ ልጅን ቀና ብየ አየሁትና ሁሉንም ባይሆን የተወሰነውን ስሜቴን ልገልጽለት ወሰንኩ።

 

”እንደ አ'ተ የዚያን ከዚህ አጣቅሸ ማስረዳት ባልችልም 'የጠፋው በግ' ማለት አንተ ነህ። ከልጅነትህ ጀምሮ እንድትማር ሌት-ተቀን የደከምኩት እምነትክን አጥብቀህ እንድትይዝ፣ ወገንህን ከድህነት እንድታወጣና ሙያህን ለሀገርህ ህዝብ እንድታስተምር ነበር እንጅ፤ የራስህን እምነት ንቀህና ከድተህ እኔን እናትህን ደግሞ ለማስካድ አልነበረም። መዳን የሚያስፈልግህስ አንተና ያንተ ብጤዎች ናችሁ።"

 

እምባዬ እንደገና መፍሰስ ጀመረ። የተናገርኩት ልጄን ያስከፋው ይሆን ብዬ ጨነቀኝ። በጥፋተኝነት ስሜት ዓይን-ዓይኑን እያይሁ መለሳለስ ጀመርኩ።

 

”ዋናው ነገር ለ'ኔ ለእናትህ ኑርልኝ። ደህና ሁንልኝ እንጅ ደስ ያለህን አድርግ።" አልኩት።

 

እምባዬን እየጠረገ ”ደህንነት ከክርስቶስ ነው!” አለኝ።

 

የሆነ ነገር ብልጭ አለብኝ። ”እኔ ደህንነት ከድንጋይ ነው አልኩ እንዴ? በክርስቶስ ስለማምለክ ደግሞ ... ”ከ'ኛ ወዲያ ...።" አስቤ የተናገርኩት አይመስለኝም።” እናም በእናትና በልጅ መሀ’ል ዝምታ ሰፈነ። የኔ ልብ ግን ማንጎራጎር ጀመረ። ...

 

”ከሁሉ - ሁሉ፣ ጤፍ ታንሳለች

ከጭቃ ወድቃ ትነሳለች።” ...

እናት ምን ግዜም፣ እናታ'ለም ነች!

ሀገር ምን ግዜም፣ ሀገር ነች!

”ስልጡን” ኢትዮጵያዎያኖች ...

ዘመናዊ ”ልሂቃኖች” …

አምላካቸውን ዘነጉና

ለባእድ አምልኮ ተገዙና፤

ህዝብ-ወገናቸውን ‘ረሱና

ማንነታቸውን ናቁና፤ ...

”እኛ ብቻ እናውቃለን”

አጠፋን እንጅ፣ አላለማን

ለያየን እንጅ፣ አላፋቀረን። …

ተዉ! ተመከሩ ... ተመከሩ!

ከትላንቱ ተማሩ ... ተመራመሩ!

ኢትዮጵያ ግን፤ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች

እየነጋ እንጅ እየመሸ አይሄድም፣ በጽናት ለቆሙ ለአምላክ ልጆች።

 

የልቤን እንጉርጉሮ ስጨርስ፤ ልጄን አስተውልኩት። ያልጠበቀው ነበርና ድንጋጤና ሀዘን ፊቱ ላይ አነበብኩ።

 

"በል አሁን 'ይቅር በለኝና’ የእናትና የልጅ ወግ እናውጋ።" ስለው ወዲያውኑ እስታውን አሳየኝ። በውስጡ ግን ”እናቴ አልዳንሽም! ... እጸልይልሻለሁ! ..." የሚል መሰልኝ። በእርግጥ የኔም መንፈስ “የጠፋው በግ! ... የጠፋው ልጅሽ! ... " እያለኝ ነበር።

--------//--------

ፊልጶስ / ጥቅምት 2004

ለማንኛውም አስተያየት፡ e-mail: This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!