Ethiopian national literacy campaign during Derg regime.

በደርግ ሥርዓት መኃይምነትን ለመቀነስ በተደረገው የመሰረተ ትምህርት ዘመቻ የተሳተፉ

ዘጌርሳም

በሕይወት ላይ ብዙ ገጠመኞች አሉ፤ አብዛኞቹ ሲረሱ አንዳንዶቹ ደግሞ ሁልጊዜ አብረው ይኖራሉ። ትዝታዎች ጥሩም መጥፎም ሲሆኑ ገጠመኝ የራስ ወይም የሌሎች መታሰቢያ ነው። በሕፃንነት ዕድሜ ጭቃ አቡክቶ፣ ውኃ ተራጭቶ፣ ተኮራርፎና ተደባድቦ፤ ተመልሶም ጓደኛ በመሆን በክፉ ወይም በበጎ የሚታሰቡ ሆነው በትምህርት፣ በስፖርት ተወዳድሮ መሸነፍና ማሸነፍ ራሱን የቻለ ገጠመኝና ትዝታዎች ናቸው።

የታሪክ ትረካዎችም እንደ አቅራቢው ይለያዩ እንጅ፤ የማይረሱና የሕይወት ተጓዳኝ በመሆን ይቀጥላሉ። የታሪክ ትረካ ተሰጥዖ ይጠይቃል። የራስን ወይም የሌሎችን ገጸ ባህሪያት ለመግለጽ፤ ሥነ ጥበባዊ ስጦታ ይሻል። ጥርስ የማያስከፍተውን ትረካ አሳምርው በማቅረብ ሕይወት እየሰጡ የሚያዝናኑ ተራኪዎች የመኖራቸውን ያህል፤ የደመቀ ሕዝባዊ ትዕይንት የሚወጣውን ትረካ ባለቤቱን በማጣቱ አንገሽጋሽ የሚሰኙ በርካቶች ናቸው። ሥነ ጥበብ መስታወት ነችና ባለቤት ትፈልጋለች።

የትምህርት ቤትና የሥራ ባልንጀራዬ የነበረና በጣም የቀረበ ግንኙነት የነበረን፤ በየጊዜው እኔንም ሆነ ሌሎች የጋራ ጓደኞቻችንን እያሳቀ ካዝናናን ትረካዎቹ መካከል አንዷንና ዘመን ተሻጋሪ ነች ብየ ያሰብኳትን ላካፍላችሁ።

ስዩም ይባላል፤ ግን በሕይወት የለም። ተወልዶ ያደገው በወቅቱ ምርጥ ሥጋና የፍራፍሬ ጭማቂ አላፊ አግዳሚውን በምታስተናግደው ዱከም ከተማ ሲሆን፣ ዱከምን ለማታውቁ በአዲስ አበባና ደብረ ዘይት መካከል የምትገኘው ትንጥዬ ከተማ ነች። ምንም እንኳን ደብረ ዘይትና ዱከም በአሁኑ ወቅት የገጠሙ ቢሆንም።

ታሪኩ እንዲህ ነው፤ በዘመነ ደርግ የዕድገት በሕብረት ዘመቻ ተቋርጦ በምትኩ አስራ ሁለተኛ ክፍልን የጨረሱ ተማሪዎች ለጎልማሶች በመሰረተ ትምህርት አስተማሪነት ሲያገለግሉ ስዩም ተወልዶ በአደገባት ከተማ ዱከም ይመደባል። የስዩም ተማሪዎች አብዛኞቹ የጓደኞቹ እናቶችና እርስ በርሳቸው የሚተዋወቁ ስለነበሩ፤ በተገናኙ ቁጥር አበክረው የሚወያዩት ስለ ኑሮ ውድነት፤ ምን ተወደደ? ምን ረከሰ? በሚሉት ዙሪያ ነው። ተማሪዎቹ ሁሉም እናቶችና ልጅ የሌላቸውም ካሉ ሁሉም ትልልቅ ሴቶች ነበሩ። ትምህርት ቤት መግባት የተገደዱት ከቀበሌ ሱቅ ለሚገዙና ለሚሸመቱ የምግብ ቁሳቁሶች የፈቃድ ወረቀት ለማግኘት ሲሆን፤ ዋጋውም በጣም የረከሰና ከግል ነጋዴው ዋጋ ጋር ሲነፃፀር እጅግ የሚስብ ኹኖ በመገኝቱ አጋጣሚውን ለመጠቀም ነው። ታዲያ ይህን እድል ለማግኘት ደግሞ ”በእርጅና ቁንጅና” እንዲሉ ተማሪ ሆኖ ከመመዝገብ በተጨማሪ የፈተና ውጤት ማስረጃ ማቅረብ ግድ ይል ነበር። የተማሪዎቹ ስብጥር ከወጣት የቤት እመቤት እስከ ዕድሜ ጠገብ እናት ያካተተ ከመሆኑ አንፃር፤ አስተማሪዎቹም ለብዙዎቹ ተማሪዎች ልጅ፣ ለዕድሜ ጠገቦቹ ደግሞ የልጅ ልጅ በሚሆን የዕድሜ ልዩነት የነበራቸውና ከሁለቱም ፆታዎች የተውጣጡ ነበሩ።

የስዩም ተማሪዎች አብዛኞቹ ትልልቆችና ሴቶች ብቻ ሲሆኑ፤ ሥራውን በተገቢ ሁኔታ ለማካሄድ ይቸገር ነበር። እሱን በማዳመጥ ፈንታ እርስ በእርሳቸው ስለቀበሌው ሱቅ፣ ስለጉልት ገበያውና ስለሌሎች የገበያ ቦታዎች ቡና እየጠጡ እንደሚያወሩት በሚመስል ያወራሉ። ከእናት ተማሪዎች መካከል በዚህ ፀባይ የታወቁት እትዬ አበበች የተባሉት ሲሆኑ፤ ሌሎቹ አድማጫቸውና አድናቂያቸው ነበሩ። ብዙ ጊዜ ስዩም ተማሪዎቹን የሚያነጋግራቸው በአክብሮትና በፍርሃት ስሜት ነበርና፤ አንድ ቀን በዚህ ሁኔታ መቀጠሉ ተገቢ መስሎ ስለአልታየው ትንሽ ጠንከር ባለ አቀራረብ የክፍሉን ፀጥታ ለማርገብ በማሰብ፤ ሙከራውን እንዲህም በማለት ይጀምራል፣

ስዩም፤ “ዛሬ ትምህርታችንን የምንጀምረው በአማርኛ ትምህርት ነው”

እትዬ አበበች፤ “ወይ ጉድ ’እግር ሂዶ ሂዶ የማይደርስበት የለም’ ደግሞ አንተ ሆንክ እኔን አማርኛ የምታስተምር?! እኔ አበበች አንተ ገና በእናትህ ሆድ ውስጥ ሳትረገዝ ነው አማርኛ የማውቀው”

ሌሎች ተማሪዎች ክፍሉን በሳቅና በጩኽት አደመቁት።

ስዩም፤ “እትዬ አበበች እዚህ እኮ የመጡት እማራለሁ ብለው ነው”

እትዬ አበበች፤ “ተወኝ ወዲያ! ትምህርቱ እንኳን ለኔ ለአንተም አልጠቀመ፤ ተማርን ያላችሁትም ስታውደለድሉ ከመዋል ያለፈ የሠራችሁት የለም፤ ሂድና የኔን ልጆች ጠይቅ፤ ... ወንዱም ሴቷም የአልጋ ሽቦ ሲያረግቡና ሶፋ ሲያለፉ ነው የሚውሉት”

ስዩም፤ “ታዲያ ሊማሩ ካልሆነ ለምን መጡ?”

እትዬ አበበች፤ “አይ የኔ ልጅ! ስኳርና ዘይት ለመግዛት የምችይው ስትማሪ ብቻ ነው ብሎ የእናንተ አለቃ ተብዬዎቹ የቀበሌ ተመራጮች ስለአስገደዱኝ ነዋ! አይደለም እንዴ? እስኪ ሁላችሁም እውነቱን ተናገሩ! ...”

የክፍሉ ተማሪዎች፤ “ትክክል ነው” በማለት አጉተመተሙ።

ከተማሪዎች አንዷ፤ ”እውነቱን ነው ፍርጥ አርገው የተናገሩት፤ እኛማ እንደ እርስዎ አንችል፤ እንዲህ አርገው ያቅምሱልን እንጅ”

ከተማሪዎች ሌላኛዋ፤ እኛማ ብንናገር አይደለም የቀበሌዎቹ ተመራጮች፤ ባል ተብየዎቹ ሳይቀሩ አያስቀምጡንም። የነሱን ቁጣና ፍጥጫ ለመራቅ ብለን ነው ከዚህ ተጎልተን የምንውለው፤ ከዚህ በኋላ ምን ልንሆን?! ድሮስ፣ ወጉ አልቀረም።

ከእትዬ አበበች በስተኋል የተቀመጡት፤ አዳሜ ተማርኩ ሠለጠንኩ ብሎ ሲቦጠጥና ሁሉም ሥራ ሲያጣ ቀበሌና ካድሬ ብቻ ሆኖ አይደል የቀረው!! እኔ እንደሁ ጦሜን አድራለሁ እንጅ ካድሬ ኹኘ ወገኔን ሳስለቅስ አልኖርም

ስዩም ውይይቱ መስመር በመልቀቁ ስጋት ውስጥ ስለከተተውና አድማ አነሳሽ ሆንክ የሚለውን ተጠያቂነት ለማስወገድ ሲል ርዕሱን ለመቀየር ተገደደ። “እሺ እትዬ አበበች የአማርኛ ትምህርቱን እንተውና ሌላ ነገር እንማር” ሲል፤

እትዬ አበበች፤ “ድሮስ እኔ አልጠየኩህ አንተው አመጣኸው እንጅ፤ ደግሞ ሌላ ምን ልታመጣ ይሆን?! ቀደም ብየ እንዳልኩህ አማርኛ አንተ እንደማታስተምረኝ ተግባብተናል፤ በዚህ የተነሳ አይደለም የቀበሌ ሱቅ ሽመታ የመርካቶ ገበያም ይቅርብኝ። ሳልሞት ደግሞ አንተ እኔን አማርኛ ላስተምርሽ! ደፋር!

ይህ ደግሞ የአስተዳደግ ጉድለት ነው፤ ብትፈልግ ሂድና ለአለቃህ አበበች እምቢ አማርኛ በአንተ አፍ አልማርም ብላለች ብለህ አቃስጥና ሁሉን ነገር ይከልክሉኝ ”ኩራት እኮ እራት ነው” አንተ!

ስዩም፤ “እትዬ አበበች አይቆጡ አባከዎት፣ እኔ የተሰጠኝ ትዕዛዝና መመሪያ ነው ካስቀየምኩ ይቅርታ!

እትዬ አበበች፤ “ኤዲያ! መመሪያ የምትለኝ እኔይቷ አበበች ዓይነ ስውር መሰልኩህ ወይስ መንገድ ጠፋኝ አልኩህ። ታዝዠ ላልከው ግን ድሮስ አንተ ከመታዘዝ ሌላ ምን ልታደርግ ኑሯል! ምን አቅም አለህና ሌላ ምን ልትሠራ አሰብክ? ይህም ሲበዛብህ ነው አልገባህም እንጅ፤ አንተንስ ማዘዝ የሚያቅተው ማን አለና፤ አሁን ዕድሜ ለጌቶችህ በልና ቀረ እንጅ ክፉ ልታናግረኝ አይደል! የዛሬ ዘመን ልጆች ሳይነካኳችሁ ትነካኩና አገር ታቃጥላላችሁ የሰው ጠባይም ታስገምታላችሁ፤ አንተ ብዙ አታናግረኝ ይህችን ቀን ብናልፋት ይሻላል፤ ለመሆኑ እናት የለህም አንዴ! ጥሎባቸው እንዲህ ዐይነቱን ደፋርና ዓይን አውጣ ልጅ ከሚሰጠኝ መክኘ ብቀር ይሻለኛል ...

ስዩም፤ ይቅርታ እኮ ጠይቄያለሁ እትዬ አበበች፤ ካጠፋሁ እንደገና ይማሩኝ ብሎ ወደ ጉልበታቸው ደፋ ማለት ሲጀምር፤

ከተማሪዎቹ አንዷ፤ ወይ ጉድ አንተ ምን አቅም ኑሮህ ልጀ ታዘህ እንጅ፤ ይበሉ እርስዎም ምርር ብለው አይዘኑበት፣ ለልጆችዎ ግፉ እንዳይደስ የእናት አንጀትዎን ፈታ ያርጉት ሲሏቸው፤

እትዬ አበበች፤ “ውይ ምን አረኳችሁ እንዲህ ዐይነቱስ በልጆቸ አይድረስ ጠልዩልኝ፤ በያመቱ የምዘክረው ቅዱስ ሚካኤልስ ምን ይሠራል። ይህ ልጅማ ምን አድርጎ መታዘዙንማ እኔም አውቃለሁ በምንስ አቅሙ ይህን ማድረግ ይችላል ተብሎ ይታሰባል! እንዲያው ነገሩ ቢበዛብኝ እንጅ። አውቃለሁ ማረር መትከኑ ለኔ ብቻ የመጣ አይደለም፣ የአገራችን የቤት እመቤትና ሴት ወይዛዝርት ሁሉ ስቃዩን እያየ አይደል! ለማን አቤት ይባላል! ካድሬና ቀበሌ እንደሁ የቀን ጅብ ሁኗል፤ መዝረፍ ማስጨነቅ እንጅ። ለመሆኑ እናትና እኅት ያላቸው ይመስላሉ! ይህ ምስኪንማ በምን አቅሙ። እንደቤት ውሻ የሰው እጅ አይቶ የሚያድር አይደል” በማለት ስዩምን በኀዘኔታ እየተመለከቱ የውስጥ ብስጭቱን ከአበረዱለት በኋላ፤ “በል ልጀ ባልወልድህም ልጀ ነህና የታዘዝከውን አስተምረን ግን አማርኛን ተወው፤ በሱ አንስማማም” በማለት አረጋጉት።

ስዩም፤ “አመሰግናለሁ! እትዬ አበበች። አማርኛውን ትተን ሂሳብ እንማር” ሲላቸው ደስታ የተሞላበት ይሁንታ አሳዩትና በል እሱ ጥሩ ነው ለኛም ይረዳናል፤ እኔ እንዲያውም ይህን ዐይነቱን ትምህርት ድሮ ጀምሬ እፈልገው ነበር። መርካቶ ገብያ ሂጀ መልስ ሲሰጡኝ ሁልጊዜ ሳልጣላና ሳልጨቃጨቅ ተቀብየ አላውቅም፣ ብዙዎችም ያታልሉኛል። ምንም እንኳን ሱቅ ከፍቸ ትርፍና ኪሳራ ባላሰላም መቀነቴ ላይ ያለውን ገንዘብ እንኳን በደንብ መቁጠርና ማስላት ያስፈልገኛል። የኔ ልጆች ሁልጊዜ ማዕድ ቤት ሁኘ ስሰማችው ሂሳብ ሲያሰሉ እሳት የላሱ ናቸው፣ በተለይ ሴቷ ልጀ ስሌቱን በአየር ላይ ነው የምትቀልበው፤ ወንዱ እንኳን ትንሽ እንዳንተ ፈዘዝ ያለ ስለሆነ፤ ሂሳቡን ቢችለውም ትብት ብሎ በፍጥነት እንደ እኅቱ አይናገረውም። በል አንተ አሁን እኛንም ፈጣን አስሊዎች እንድንሆን አስተምረን። ይህን ካደረክ ምርቃታችንም ለትልቅ እንጀራ ያበቃሃል፤ የተመረቀ ልጅ ረደኤት አይለየውም ...

ስዩም፤ “በሉ አሁን ትምህርቱን እንጀምር” አለ፤ ወቅቱ አርባ ፆም የሚፆምበት ወቅት ነው፤ በመቀጠልም እንዲህ አለ፣ “አበበ ገብያ ሂዶ አስራ ሰባት ዕንቁላል ገዛ” ሲል፤

እትዬ አበበች፤ “ስብሃት ለአብ፣ ስብሃት ለወልድ፣ እመቤቴ ደግሞ ምን ልታሰሚኝ ነው!” በማለት ማጉረምረም ጀመሩ፤ ሌሎች ግን በፅሞና ያዳምጣሉ፤ እትዬ አበበች ንግግራቸውን ቀጠሉ፤ “ጀሮ አይሰማው የለ፣ ጉድ እኮ ነው! እንደ እናት ዶሮ ታቅፎ ጫጩት ሊቀፈቅፍ ነው፣ ደግሞስ ሁዳዴ ፆም መሆኑን ረሳው! አቡዬ ገብረ መንፈስ ቅዱስ አባክዎ ክፉ አያሰሙኝ” በማለት ዝም አሉ።

ስዩም በመቀጠልም፤ “ከአስራ ሰባቱ ዕንቁላል ውስጥ ሁለት ወድቆ ተሰበረበት” ሲል

እትዬ አበበች፤ “ከርፋፋ ተጠንቅቆ አይዝም ነበር”

ስዩም፤ “ሦስቱን ለጓደኛው ለከድር ሰጠው

እትዬ አበበች፤ “ደግሞ እሱስ ምን ሊያደርገው ይሆን፤ ከአበበ የባሰም አለ ለካ

ስዩም፤ “አራቱን ሸጠ

እትዬ አበበች፤ “ለከስካሳ በሱ ቤት ሥራ መሥራቱ ነው፤ ይልቅ ሌላ ለወንድ ልጅ የሚስማማ ሥራ ሠርቶ አይበላም! ሥራው ተሠርቶ ተሙቷል! ”ሌባ ለአመሉ ዳቦ ይልሳል” ይባል የለ ...

ስዩም፤ “ሁለቱን ቀቅሎ በላ ሲል

እትየ አበበች፤ ትዕግስታቸው ወሰን አጣና ኡ! ኡ! ብለው እየጮሁ “አቤት! አቤት! ... የጉግ ማንጉግ ጊዜ፣ የጌታ ቃል ታጥፎ በአርባ ፆሙ ዕንቁላል የሚበላበት ጊዜ ደረስን። ፈረንጅ ነኝ ሊለን ይሆን! አፈር ያስበላህ! ምኑን አሲድ በሆዱ ቀበረበት፤ ስንት በፆም ጊዜ የሚበላ እንደ ድንች፣ ጎመን፣ ሽሮ፣ ክክ፣ ምስር፣ ሱፍ፣ ተልባ፣ ኑጉ፣ ባቄላው፣ ... ስንቱ ተዘርዝሮ የባለሙያ ሴት እጅ ይቁጠረው እንጅ። ውሻ ይመስል የተገኘው ሁሉ የሚለቀምበት ጊዜ፤ አቤት! አቤት! ፈጣሪ አምላክ ስንቱን ልታሳየን ነው፤ እረ ግፉና መዋረዱ በዛ፤ በቃ በለን! ምግብ ሳይጠፋ ዕንቁላል በፆሙ ምድር ይበላል! ለመሆኑ ይህ ጉድ በራዲወን ተነግሮ ያገራችን ሕዝብ ቢሰማው ምን የሚያስከትል መሰለው። ይህ ሁሉ ጉድ የመጣው ይህ የቀበሌ ሱቅ የቀበሌ ጉድ ቢሉት ይሻል ነበር ... የሚባል ከመጣ በኋላ እንጅ፤ ይህን ያህል ዕድሜዬን ስኖር ይህን የመሰለ ጉድ ጀሮየን አሰምቶት አያውቅም። ምን ይደረግ የራሱን ንጉሥ ገሎ የሰው አገር ንጉሥ የሚያወድስና የሚያከብር ጉግ ማንጉግ ጥሎብን። ላደለው ምዕመናን በየገዳሙ እየዞሩ ሱባዔ በሚገቡበት ወቅት ካልሆነም እንደ አባት አደሩ በባቄላ አሹቅና ንፍሮ መሬት ላይ እየተኙ ማረኝ ማረኝ የሚባልበት ጊዜ ነበር። ታዲያ ምን ይደረግ አንድየም ሰለቸን መሰል አልሰማ አለ፤ እሱማ ምን ያርግ የኛ ኃጢያታችን ስለበዛ ስንቱን ይታገሰን?! ...

ስዩም፤ “ይበሉ የሂሳብ ጥያቄው ይህን ይመስላልና በመጨረሻ አበበ ስንት ዕንቁላል ቀረው?” ብሎ ሲጨርስ፤ ሁሉም ተማሪዎች እጃቸውን አወጡ።

እትዬ አበበች፤ አሁን ይበልጥ ተናደዱና ወደ ሌሎቹ ተማሪዎች ዞር በማለት “የት ነበራችሁ እስካሁን! እያንዳንድሽ እንደቆረበ ሰው አፍሽን ይዘሽ እንዳልነበር፤ አበበችን ደንቆሮ ለማሰኘት ነው ይህ ሁሉ ማስመሰልና መጣደፍ! እኔ እኔ ማለት እስኪ እናንተን ምን አገባችሁ! መልሱን ነገራችሁ እንዴ! ወይንስ እያንዳንድሽ አፏን እንደዘጋች ቤቷ ተመልሳ ሄደች የምላችሁ መስላችሁ! ሲሆን እኔና እሱ ስንጣላ መገላገል ሲገባችሁ ከንፈራችሁን ስትመጡ ውላችሁ፤ አሁን እኔ እኔ ትላላችሁ፤ ለአበበች መልሱ ጠፋት ያላችሁ ማነው፤ ያውም እኔይቷ አበበች ከእናንተ አንሸ! እንኳንስ የአስራ ሰባት ዕንቁላል ስሌት አንድ ዶንያ ጤፍ ብታመጡ እንኳን ቆጥሬና አስልቸ መስጠት እችላለሁ። ሌላው ቢቀር እሳት የላሱና በቃላቸው ትምህርቱን የሚያነበንቡ ልጆች አሉኝ፤ ደግሞ ብዙዎቻችሁ ልጅ እንኳን አሳድጋችሁ አታውቁም፤ አጉል አለሁ ለማለት ግን ማን ቀድሟችሁ። እግዚአብሔር ያሳድገውና ልጁ ጥያቄውን የጠየቀው እኔን ነው፤ ግን የናንተን መውለብለብ ምን አመጣው! እስኪ ከመካከላችሁ ጥያቄው ለእኔ ነው የሚል አለ? አልገባችሁም እንጅ መኖራችሁን እንኳን ያስታወሰ አይመስለኝም። ምነው ሚካኤል ሻማህን እንኳን አብርቸልህ ነበር፤ የቀብሌው ሱቅ ሽመታ ይቅር እንጅ የማንም መቀለጃና መለማመጃ ልሆን አልመጣሁ። ልጁ እንኳን ጥፋቱን ተረድቶ ይቅርታ ጠይቆኛል፤ እንዲያው ገና ለገና ከአንድ የግዳጅ ትምህርት ወንበር ላይ አብረን ተቀመጥን ተብሎ እንዲህ ይደረጋል እንዴ!! ለነገሩማ ይበለኝ ክብራቸውን የወደዱት ጓደኞቸማ ምኑም ምኑም ይቅርብን ብለው ከጎረቤቶቻቸው ጋር ደግ ደጉን እያወጉ ቡናቸውን እየተጠራሩ ሲጠጡ ይውላሉ፤ እኔ ግን ልጅ አሳድጋለሁ ብየ ለውርደት በቃሁ። እኔ ተምሬ አገር አልገዛ፣ መሃያ አላስቆርጥ፤ ለስኳርና ዘይት ብየ ራሴን ላዋርደው! ብለው ምርር ባለ ስሜት ሲናገሩ

ስዩም፤ ቀበል አደረገና፤ “ወደ ሌሎቹ እየተመለከተ ጥያቄውን ያቀረብኩት ለእትዬ አበበች ስለሆነ፤ እናንተ አዳምጡና እሳቸው ካልቻሉት እናንተ ትሞክራላችሁ

እትዬ አበበች፤ “አንተ ልጅ ተወኝ ብየሃለሁ ጤና የለህም እንዴ! ማንኛዋ ነች ለኔ አቅቶኝ እሷ ትመልሰዋለች የምትባለዋ፤ ለብሰውና ተሽሞንሙነው ስላየሃቸው ሊቅና አዋቂ መሰሉህ እንዴ! አንተማ ምን ታደርግ! ልጅ አሳድጋለሁ በየ እንዲህ ወድቄና ተጎሳቁየ አይተኸኝ፤ ነበርኩ ማለት አይጠቅምም እንጅ ከዚህ ከፊትህ ከምታያቸው ሁሉ የበለጥኩና አንች የተባልኩ የቆንጆዎች ቁንጮ ነበርኩ። እንዲህ ጎስቁዬ እያየኸኝ እንኳን ”የጥሩ ሸክላ ምስክሩ ገሉ” ነው እንዲሉ አስተውሎ ለተመለከተኝ ውበቴ አሁን ድረስ ማንንም የሚያስንቅ ነው።

አሁን አንተን የምጠይቅህ የሂሳብህን መልሱን ይዠዋለሁ፤ እኔ ስናገር ጣልቃ እየገቡ ማደናቀፉን እንዲያቆሙ ንገርልኝና መልስህን አንድ ባንድ ምንዝርዝር ብጥርጥር አድርጌ እነግርሃለሁ፤ ተግባባን! ሲሉ

ስዩም፤ “በሉ እባካችሁ ሁላችሁንም በአክብሮት የምጠይቀው የእትዬ አበበችን መልስ በፅሞና አብረን እናዳምጣቸው” ሲል ሁሉም ዝም አሉ።

እትዬ አበበች፤ ስዩምን አመስግነው፤ “በሉ ሁላችሁንም የምጠይቀው አስቀይሜያችሁ ከሆነ በእመቤቴ ስም ይቅርታ እየጠየቅሁ መልሴን በደንብ ስሙልኝ፤ አንተም ብትሆን መልስህን ካገኘህ በኋላ ሳትውል ሳታድር ቢቻል ዛሬውኑ ለሁላችንም ካልሆነ እኔን በተመለከተ ጠቅላላ ትምህርቱን ሂሳብ የምትሉትን ሳይቀር በደንብ ስለቻለችው ከቀበሌው ሱቅ የምትፈልገውን ሁሉ መሸመት እንድትችል ይፈቀድላት ብለህ፤ ሲሆን በጥሁፍ፤ አለዚያም በቃልህ እንድትነግርልኝ ነው የምፈልገው። ይህን ስልህም እንደልመና እንዳትቆጥረው መብቴንና ችሎታየን አውቀዋለሁ። ዲፕሎሙንም ሰኔ ወር ድረስ የምጠብቅበት ምክንያት ስለሌለ፤ ደግሞስ አንተው ለምትጥፈው ነገር ያን ያህል የሚያስጠብቀኝ አይመስለኝም፤ የጎደለ ካለም ወደፊት ማስተካከል አያቅተኝም። ሰው በዱቤ ዕቃ ይገዛል የለ! እንደዚያ አርገህ ቁጠረው። ዛሬውኑ ሰጥታችሁ ብታሰናብቱኝ ለእናንተም ረፍት ነው፤ የሚቀርባችሁ ከእኔ ጋር ጭቅጭቁ ብቻ እንጅ የሚጎልባችሁ ነገር የለም። እኔ ብጎልባችሁ እንኳን ሌሎች የሚፈልጉና የምትናገሩትን ሳያላምጡ የሚውጡላችሁ ሞልተዋልና ለእኔ በሰላም ዲፕሎሜን ሰጥታችሁ አሰናብቱኝ። ይህን የምልህ ደግሞ በነፃ ስጡኝ ሳይሆን፤ አሁን የጠየከኝን ከባድ የሂሳብ መልስ በደንብ አርጌ ከመለስኩልህ በኋላ ነው፤ እኔ እንደሁ ከዚህ ወዲያ ተጨማሪ ትምህርት አያስፈልገኝም። ዩኒበርሲቲ አልገባ ወይም ፓርላማ ምረጡኝ ብየ አላስቸግር፤ እኔይቷ አበበች እንደሁ ስሜንና የቤተሰቤን ስም እስከ አያት ቅድመ አያታቸው ድረስ ቁልጭ አድርጌ መፃፍ ችያለሁ። ቀበሌ ስብሰባ ላይ ግራ እጃችሁን አውጡ የሚለውን አስቸጋሪ ትምህርት እንኳን ቀኝ እጀ እንዳያስቸግረኝ በመቀነቴ ከወገቤ አስጠግቸ በማሰር ግራ እጀን ብቻ አለማምጀ ዛሬ ስንቱ ሴት ወይዛዝርትና መኳንንት በእጅ ማውጣት ሲደናበር እኔ ብቻ ያለችግር በመቻሌ ሰብሳቢዎቹ ሳይቀር ስሜን ከሕዝቡ ፊት አጉልተው እየጠሩ አመስግነውኛል። ስለዚህ ዛሬ ለእኔና ለአንተ የመጨረሻ ቀናችን ስለሆነች የጥያቄህን መልሶች በጥሞና አዳምጥ፣

  1. አበበ ገብያ ወጥቶ አሥራ ሰባት ዕንቁላል ገዛ ላልከው

መልሱ አቤት አቤት ያሰኛል፤ በጣም የሚያሳፍር ሰው ነው። ካልጠፋው ንግድ ያውም በሁዳዴው ፆም ሰው የዕንቁላል ነጋዴ ይሆናል! አይ አለመታደል አሳዳጊውን አሰዳቢ፤ ለመሆኑ እናትና አባት ይኖረው ይሆን! ምናለበት ጥራጥሬውን ነግዶ ቢሆን! በዚያውም የፆመኞቹ ፆምና ጸሎት ምህላው ተጨምሮለት ረድዔቱ ይደርሰው ነበር።

  1. ሁለቱን ለከድር ሰጠው ለምትለው የዛሬ ልጆች ከውሸት ሌላ ስላልተማራችሁ አንተው አይቻለሁ ብለህ የለመድከውን የውሽት ምስክርነት ስጥ። እኔይቷ አበበች እንኳንስ በሁዳዴው ፆም ጊዜ የፋሲካ ዕለት እንኳን ባይ ሲሰጠው አይቻለሁ ብዬ አልመሰክርም፤ ለመሆኑ ከድር እኮ የራሱ የፆም ጊዜ አለው፤ እንዳንተም የሚዋሽ አይመስለኝም። ደግሞስ ይህን ዐይነቱን ቀልማዳ ወሬ የሂሳብ ትምህርት ብለህ ትጠራዋለህ! የመቀላመጃና የኃጢያት ትምህርት ብትለው በተሻለ ነበር። ሌላው ቢቀር በፆሙ ምድር የዕንቁላሉን ስሙን እንኳን ስትጠራ ኩነኔ እንደሆነ ይገባሃል! በየሻይ ቤቱ እየዞሩ ያንንም ይሄንንም መቅመስና መላስ ቁምነገር መስሎህ ነው! ምን ዐይነት ዘመን ላይ ደረስን፤ በመሆኑም መልሴ ሲሰጥም ሲቀበልም አላየሁም፤ እረካህ!
  2. አራቱን ሽጦ በላ ብለሃል

እንዲህ ነው ነጋዴ! የሐረር ሰንጋ ነጋዴ! የጅማ ቡና ነጋዴ! የአዳ ነጭ ጤፍ ነጋዴ! የጎጃም ማር ነጋዴ! አቤት አቤት! ወጉ አልቀረም እሱም ከነጋዴዎች ቁጥር ሊገባ ፈለገ አይደል! የዕንቁላል ቱጃር ነጋዴ እንበላዋ! ያውም የአራት ዕንቁላል ነጋዴ!! ተነግዶና ተከብሮ ተሙቷል፤ ለመሆኑሳ አያፍርም!

ስለዚህ መልሴ ሲሸጥም ሲለውጥም አላየሁ፤ ባይ እንኳን ያሳፍረኛል፤ ”ሌባ ለአመሉ ዳቦ ይልሳል” እንበለው እንዴ! እኔ አንተን ብሆን ይህን ጥያቄ ብየ አላቀርብም፤ ለመሆኑማ አንተስ በሌሎች መጠሪያ አስተማሪ ተብልህ አይደል!

  1. ስንት ቀረው ላልከው

የኔ መልስ ስንት ኑሮት ስንት ሊቀረውስ ይችላል! አሥራ ሰባት ዕንቁላል ቁም ነገር ሆኖ ነበረኝ ይባላል እንዴ! ምን ዐይነት ሃፍረተቢስ ነው።

ተሰበረብኝ፣ ለጓድኛዬ ሰጠሁ፣ ስንት ቀረኝ! አሁን ይህ ጥያቄ ተብሎ ከሰው ፊት ይቀርባል!

ለአንተ ዐይነቱ በቀጣፊ ሥርዓት ለአደገና በውሸት ትምህርት አንጎሉ ለደነዘዘ በሬ ወለደ እያለ የወሬ ታናሽና ታላቅ ብልት ለሚያወጣ ጤናማ ጥያቄ ሊመስል ችሏል፤ ለእኔ ለአበበች ግን ከወሬ ድሪቶነት የሚያልፍ አይደለም፤ በመሆኑም ለጥያቄህ መልሱ ያለው ከራስህ ከአንተ ጋር ስለሆነ ከአለቆችህ ጋር ተወያይተህ በለመደው የአሉባልታ ልምዳችሁ በየስብሰባው እሰጥ አገባ እያላችሁ እንድትደሰኩሩ እየመከርኩ ጠቅለል ያለው መልሴ፣

ሲወድቅበት አላየሁ፣

ማበደሩን አልሰማሁ፣

ሲሸጥም አላዋዋልኩ፣

የተረፈው እንዳለ የማይታሰብ፣ መሆኑን ፍርጥም አርጌ ልነግርህ እወዳለሁ ሲሉ በመመለስ፤ በስዩምና በእትዬ አበበች መካከል የነበርው የሐሳብ አለመጣጣም በዚህ ተቋጨ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ