ስየ አብርሃ

እሁድ ነሐሴ 10 ቀን 2001 ዓ.ም. አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) በጠራው ህዝባዊ ስብሰባ እንዲገኙ ከተጋበዙት የመድረክ ለዲሞክራሲ ምክክር በኢትዮጵያ (መድረክ) አባላት አንዱ በመሆን ወደ አዳማ ሄጄ ነበር። እንደ እኔ ሁሉ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ፕሮፌሠር በየነ ጴጥሮስ፣ አቶ ቢንያም ሄራቦ እና አቶ ሃዲ መሐመድ በእንግድነት ተገኝተዋል። የመድረኩ አባል የኾኑ ፓርቲዎች በሚጠሩዋቸው ህዝባዊ ስብሰባዎች እና ጉባዔዎች ስገኝ የመጀመርያዬ አይደለም። በተናጠል የሚደረግ ትግል ብዙ ርቀት እንደማያስኬድ፤ ገዢው ፓርቲ የሚያደርሰውን አፈና ተቋቁሞ ውጤታማ ሥራ መስራት የሚቻለው ትግልን አስተባብሮ በመሄድ ብቻ መኾኑን ከመገንዘብ የተፈጠረ መድረክ እንደመሆኑ የመድረኩ አባል ፓርቲዎች በሚጠሩዋቸው ህዝባዊ ስብሰባዎች ስገኝ ቆይቻለሁ ወደ ፊትም እቀጥልበታለሁ።

 

የአንድ ፖለቲካዊ ፓርቲ እንግዳ ኾኜ በአዳማ ስገኝ ይህ የመጀመርያዬ አይደለም። መጋቢት ወር 1992 ዓ.ም. ዓሥረኛው የኦሮሞ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዲድ) ምሥረታ በዓል ሲከበር የወቅቱ የድርጅቱ ሊቀ መንበር አቶ ኩማ ደመቅሳ ጋብዞኝ በበዓሉ ላይ ተገኝቻለሁ። በአዳማ የቀደሙት የትግል ጓደኞቼ - እነ አቶ ኩማ ደመቅሳ እና እነ አቶ አባዱላ ገመዳ - ያኔ የነበረውን የወዳጅነት አቀባበል ያደርጉልኛል ብየ አልጠበቅሁም። ይሁንና ከፓርቲያቸው ኦህዲድ/ኢህአዲግ ጋራ ባለ የፖለቲካ ልዩነት ምክንያት ነሐሴ 10 ቀን አንድነት በጠራው ስብሰባ ለመገኘት በአዳማ ማዘጋጃ ቤት የስብሰባ አዳራሽ ለተገኘነው እኔና ሌሎች ኢትዮጵያውያን የገጠመንን አይነት "መስተንግዶ" ያደርጉልናል ብለን ግን አልጠበቅንም ነበር።

 

አንድነት ሕጋዊ እውቅና የተሰጠው ሕብረ-ብሔራዊ ፓርቲ መሆኑ ይታወቃል። ፓርቲው ህዝባዊ ስብሰባውን ለመጥራት በጽሑፍ የሰፈረው ሕግ ካስቀመጠው ግዴታ በላይ እንዲያደርግ የተጠየቀውን ሁሉ አሟልቶ፣ ፈቃዱን ከሰጠው የከተማው መስተዳደር አደራሹን እንዲጠቀም ተፈቅዶለታል። ስብሰባውን የጠራው አንድነት ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን በዚህ ዳስ ውስጥ ለተጠራው የፖለቲካ ድግስ ባለቤቱ ፓርቲው ራሱ እንጂ ኦህዲድ ወይም ሌላ ሊሆን እንደማይችል አንድ እና ሁለት የለውም።

 

ስብሰባው እንደተጀመረ እንኳን ደኅና መጣችሁ በማለት የተያዘውን ፕሮግራም ያስተዋወቁት አቶ ብሩ ብርመጂ ናቸው። አቶ ብሩ የአንድነት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል፣ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የቢሾፍቱ አካባቢ ህዝብ ተመራጭ ሲሆኑ፤ ፈቃድ ማስገኘቱን ጨምሮ ለዚህ ስብሰባ ዝግጅት ሲያስተባብሩ ከከረሙት የአንድነት ፓርቲ ኃላፊዎች አንዱ ናቸው። በመክፈቻ ንግግራቸው፣ ለተደረገው ዝግጅት የአዳማ ከተማ መስተዳደር ያደረገውን ትብብር እጅግ በማመስገን ስብሰባው የተጠራበትን ዓላማ አስመልክተው መሪ ንግግር እንዲያደርጉ የአንድነት ፓርቲ ተቀዳሚ ም/ሊቀ መንበር ኢንጂንየር ግዛቸው ሺፈራውን ወደ መድረኩ ጋበዙ።

 

ኢንጂንየር ግዛቸው በጽሑፍ ያዘጋጁትን ንግግር ሲጀምሩ ከአዳራሹ በስተጀርባ ከተቀመጡት በኩል የማጉረምረም ድምፅ ተሰማ። ብዙም ሳይቆይ ወደ ጩኸት እና ፉጨት ተሸጋገረ። ድርጊቱ ስብሰባውን ለመረበሽ የታቀደ ፕሮግራም መሆኑ ግልጽ እየሆነ ሄደ። ኢንጂንየሩ ንግግራቸውን ለመቀጠል ቢሞክሩም ሰዎቹ ከተቀመጡበት ተነሥተው ወደ መድረኩ በመጠጋት ሁኔታውን በእርጋታ ሲከታተል የነበረውን ተሰብሳቢ በማወካቸው ንግግራቸውን ለማቋረጥ ተገደዋል። ሰዎቹን ለማረጋጋት ቢሞከርም ባለማሳካቱ ኢንጂንየር ግዛቸው፣ "ሕግና ሥርዓት ተከትለን የአዳማውን ስብሰባ ለማድረግ ጥረት ብናደርግም ኢህአዲግ ይህንን እንድናደርግ ስላልፈቀደ ስብሰባውን ለማቋረጥ ተገደናል" በማለት ስብሰባውን ዘጉ። ስብሰባውን ማወክ ዓላማቸውን አድርገው የመጡት ሰዎች በዚህ ያልተጠበቀ ሁኔታ የልባቸው ስለደረሰ ደስታቸውን በጭብጨባ ገልጸዋል። ከኢህአዲግ የተለየ አመለካከት ያለውን የአንድ ኢትዮጵያዊ ፓርቲ አመለካከት ለማስተዋወቅ ሕግንና ሥርዓትን አክብሮ የተጠራን ስብሰባ በማወክ እንዳይካሄድ ማድረግ እንደስኬት ተቆጠረና ጭብጨባ ተቸረው። ልቡና ላለው ሰው ግን በእጅጉ አሳፋሪ ድርጊት ነው።

 

አንድነት ኅዳር 17 ቀን 2001 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በጠራው የመጀመሪያ ህዝባዊ ስብሰባ ማግስት የፓርቲው ሊቀ መንበር ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን በዳግመኛ እስር መነጠቁ ይታወቃል። ከዚያ ወዲህ አዲስ አበባ ላይ ህዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ ቢጠይቅም አሁን ድረስ ፈቃዱን ለማገኘት አለመቻሉም ይታወቃል። ይህ በዚህ እንዳለ አዳማ ላይ የማዘጋጃ ቤቱን አዳራሽ ተጠቅሞ ስብሰባውን እንዲያካሂድ መፈቀዱን ስሰማ "ይህ ነገር የእውነት ነው?" ማለቴ አልቀረም። በዚሁ ጉዳይ ከአንድነት መሪዎች ጋራ አንዳንድ የቀልድ ቃላት የተወራወርንበት ሁኔታም ነበር። አቶ ብሩ ብርመጂ የከተማውን መስተዳድር እጅግ አድርገው ሲያመሰገኑ ስሰማ ውስጤ "መጨረሻውን ያሳየን" ማለቱ አልቀረም። ብዙም ሳይቆይ የሆነው ሆነ። በምርጫ 97 ወቅትስ ቢሆን ግንቦት ሰባት ቀን በመጨረሻው ሰዓት ላይ (ማታውኑ) አይደለም ጉዱ የወጣው።

 

ኢንጂንየር ግዛቸው ለመናገር ያሰቡትን የመስማት ዕድሉ ተነፍጎናል። ለማድመጥ ከቻልናቸው የመጀመርያዎቹ ዓረፍተ ነገሮች እንደተገነዘብሁት ም/ሊቀመንበሩ መጀመርያ ላይ ሊናገሩበት ያሰቡት ጉዳይ የሀገራችን ፖለቲካዊ ምኅዳር በሚመለከት ነበር። በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በገዢው ፓርቲ እና በተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች መካከል የስቱድዮ ውስጥ ክርክር ተካሂዶ ከፊሉ በቴሌቭዥን ቀርቦልናል። የኢህአዲግ ተወካዮች የፖለቲካ ምኅዳሩ አለመጥበቡን እየተቀባበሉ ሲደሰኩሩልን፣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ተዘረጉ ያሏቸውን አሰራሮች እና ሕጎች "ማሳያ ይሁኑላችሁ" ሲሉን አድምጠናል።

 

አቶ መለስ በያዝነው ዓመት ሰኔ ወር ላይ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ "... ባለፉት አራትና አምስት ዓመታት የዲሞክራሲያዊና ፖለቲካዊ ትግል ሕጎችን ዓለም አቀፍ ደረጃ በጠበቀ አኳኋን ለማሻሻልና ለማዳበር ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። … ያስቀመጥናቸው የዲሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ትግል ሕጎች ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቁ ዲሞክራሲያዊ ... የፖለቲካዊ ምኅዳሩን በየትኛው የዳበረ ዲሞክራሲ ባለው አኳኋን ዳር ድንበሩን የለዩ ሕጎች ናቸው" ብሎን ነበር።

 

በስቱድዮ እና በቢሮ ሆነው መግለጫ የሚሰጡት የኢህአዲግ መሪዎች የሚሉት እና እነሱ "አባል" "ፎረም" እያሉ የሚጠሩዋቸው እና ብዛታቸው ሚሊዮን ቤት ደርሰዋል የሚባልላቸው "ቪጂላንቴዎች" የሚሠሩት ለየቅል መሆኑን አዳማ አሳይታለች። አንድ ፖለቲካዊ ክንዋኔ ብዙ ሰዓታት ከፈጀ ዲስኩር በላይ ጮኾ ይናገራል። በሀገራችን ያለው የፖለቲካ ምኅዳር ለመጥበቡ ኢንጂንየሩ ሊገልጹ ከሚችሉት ቃላት በበለጠ የኢህአዲግ ተግባር ስለገለጸላቸው ድካም ቀረባቸው እንጂ ሥራ ተሰናከለባቸው ለማለት አይቻልም።

 

ከዚሁ የአዳማው ስብሰባ ቀደም ብሎ ሰኔ 21 ቀን 2001 ዓ.ም. አንድነት የጠራው ስብሰባ ደብረ ማርቆስ ላይ፣ በጥር ወር ዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ለሉዓላዊነት (ዓረና) የጠራው ስብሰባ መቀሌ ላይ ተካሂደው ነበር። በእነዚህ ከተሞች ኢህአዲግ ስብሰባዎቹን ለማሰናከል ተመሳሳይ ሙከራዎች አድርጎ እንደነበር ከወጡት መግለጫዎች ለመገንዘብ ችለናል። በሁለቱም ከተሞች ስብሰባ ለማካሄድ ተፈቅዶላችኋል ቢባልም ፓርቲዎቹ መኪና ተከራይተው በድምፅ ማጉያ የስብሰባ ጥሪ ሲያደርጉ በትራፊክ ፖሊስ ተከልክለዋል። በመቀሌማ ከዚያ በኋላ "ሕግ ወጥቷል" እየተባለ ነው።

 

እንደአዳማው ሁሉ ዓረና በጠራው ስብሰባ ላይም የህወሓት/ኢህአዲግ ባለሥልጣናት ፈቃዱን ከሰጡና አዳራሹን ካከራዩ በኋላ ወደ ስብሰባው በገቡት የፓርቲው ካድሬዎች እና አባላት በኩል ስብሰባውን በማወክ እንዳይካሄድ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት አድርገው እንደነበረ ሂደቱን አስመልክቶ ዓረና ካወጣው ይፋዊ መግለጫ ለመገንዘብ ችለናል። የመቀሌው ከአዳማው የሚለየው ነገር ቢኖር ተሰብሳቢዎቹ ኹከት ፈጣሪዎቹን "ጥያቄ ካላችሁ በሥነሥርዓት ጠይቁ፣ ጥያቄ ከሌላችሁ ደግሞ እንደሌሎቻችን የሚሰጠውን መግለጫ አዳምጡ እንጂ አትረብሹን። እኛ እንደሆነ ለመስማት እና ለመወያየት እንፈለጋለን" በማለት ችግር ፈጣሪዎቹን አደብ እንዲገዙ ማስገደዳቸው ነው። ደብረ ማርቆስ ላይ መጀመርያ ላይ እንቅፋት ከመፈጠራቸው በቀር ወደ ውስጥ ዘልቀው ስብሰባውን ለማወክ አልደፈሩም።

 

ውጤቱ ከቦታ ቦታ ይለያይ እንደሆነ እንጂ የኢህአዲግ ስልት ግን ከሞላ ጎደል ወጥነት ያለው ለመሆኑ ከነዚህ ምሳሌዎች ለመገንዘብ ይቻላል። ሰበብ እየፈጠረ ፈቃድ ይከለክላል፤ ያዘገያል። ፈቃድ ሰጥቶ ሲያበቃ ህዝቡ ስለ ስብሰባው እንዳያውቅ የማስተዋወቁን ሥራ ያስተጓጉላል። ይህ ሁሉ ታልፎ ስብሰባው ሲጀመር ደግሞ የስብሰባው ሂደት እንዲታወክ ያደርጋል። "ስብሰባ አልተከለከለም" ለማለት ፈቃድ ከሰጡ በኋላም ቢሆን ስብሰባው እንዳይሳካ ያደርጉና "ተቃዋሚዎች ህዝባዊ ስብሰሰባ የማያደርጉት በራሳቸው ችግር እንጂ መንግሥት በሚፈጥርባቸው እንቅፋት አይደለም" በማለት ይሣለቃሉ። አቶ መለስ ሰኔ ላይ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ "የፖለቲካ ውድድር ቀርቶ የእግር ኳስ ጨዋታም ቢሆን የራሱ ሕግ አለው። በእግር ኳስ እጅና እግር እየተጠቀሙ ጎል ማግባት አይፈቀድም፤ ... ፖለቲካም ከዚህ በላይ ነው" ቢለንም፤ በአንድ በኩል ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሕጎች አሉን እየተባለ ወረድ ብሎ ደግሞ በእግር እና በእጅ ጎል ላስገባ እያለ እያስቸገረ ያለው እርሱ ራሱ የሚመራው ፓርቲ ነው።

 

ለዚህ መልሱ አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት "ለሠላማዊ ትግል አመቺ ሁኔታ የለም" ብሎ መድረኩን ለኢህአዲግ መልቀቅ ወይም እኛም እንደነሱ በእጃችንም በእግራችንም ጎል እናስገባ ማለት አይደለም። የአዳማዎቹ ኹከት ፈጣሪዎች እኛ ያልነው ካልሆነ ብለው በኃይል ወደ አዳራሹ መድረክ ሲመጡ በአዳራሹ ውስጥ የነበሩት የአንድነት ደጋፊዎች አይሆንም ብለው ሰዎቹን ለማቆም ቢሞክሩ ኖሮ ግርግር መፈጠሩ አይቀሬ ነበር። ከዚያ በኋላ "ነውጥ" በመፍጠር የሚከሰሰው ማን እንደሆነ መገመቱ አይከብድም። ምስጋና ይግባቸውና በአዳራሹ የተገኙት የአንድነት ደጋፊዎች የሞራል ገዢ መሬቱን ለቀው ራሳቸውን አዋኪዎቹ ወደ አወረዱበት ደረጃ አላወረዱም። የመቀሌ፣ የደብረ ማርቆስ እና የአዳማ ድርጊቶቹ ኢህአዲግ ሠላማዊ ትግሉን ከትጥቅ ትግሉ በላይ እየፈራው ስለመሆኑ ግልጽ ማሳያዎች ናቸው። የተቃውሞ ኃይሎች መድረኩን እንደዚህ ምንችክ ብለው ይይዛሉ እንጂ ለኢህአዲግ አይለቁለትም።

 

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተስፋ ሳይቆርጡ ያቀዱትን ዳር ማድረስ፣ እንቅፋት አጋጠመ ብሎ ሙከራውን ከማቆም፤ ዛሬም ነገም ለምንጊዜውም መደጋገሙ ይልመድባቸው። እርስ በርስ መተባበር እና ተሞክሯቸውን እየቀመሩ በስልት ኢህአዲግን መብለጥና መቅደም ይልመድባቸው፤ ህዝቡም በሂደት በሰው ዳስ እየገቡ የሚያውኩትን ሰዎች መቀሌ ላይ እንደተደረገው "ከፈለጋችሁ በሥነሥርዓት የፖለቲካ ድግሱ ተካፋይ ሁኑ፤ አለበለዝያ በሰው ዳስ ገብታችሁ አትበጥብጡ" ብሎ አደብ ያስገዛቸዋል።

 

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይሁን መድረክ የኢህአዲግ መሪዎች ስትድዮ እና ቢሮ ውስጥ ሆነው አልጠበበም የሚሉት ምኅዳር ስለመኖሩ ደብረማርቆስ፣ አዳማ እና መቀሌ ላይ እንደተደረገው መሬት ወርደው መፈተሹን ሊቀጥሉበት ይገባል። የሀገራችን ጉዳይ ያገባናል ብለን በመታገል ብዙ ችግር እና ፈተና ያለፍን ሰዎች እንደመሆናችን ኢህአዲግ ወደ ስብሰባው የሚልካቸውን "ቪጂላንቴዎች" ፈርተን በስብሰባዎች ከመገኘት ወደ ኋላ እንደማንልም ሊታወቅ ይገባል። ሕግን እና ሥርዓትን አክብሮ መሄድ ያባት ነው። ይህን አልፎ ጉዳት ቢደርስብን ግን ኃላፊው ኢህአዲግ እና እርሱ የሚመራው መንግሥት መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያውቅ እንፈልጋለን።


 

ስየ አብርሃ - ነሐሴ 13/2001 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!