ልጅ ተክሌ ነኝ ከቫንኩቨር ካናዳ

“ኢትዮጵያውያን (በተለይ አማሮች) ቢኖሩ አይጠቅሙንም፤ ቢጠፉም አይጎዱንም” ህወሓት1975 ዓ.ም.

እየተጓዝኩ ነበር። ከቦታ ቦታ። ከቢሲ እስከ ዲሲ የታዘብኩትን፣ የከነከነኝን፣ ሆዴን የበላውን እጽፋለሁ እያልኩ ስዘገጃጅ በዚህ መሃል ነው ገብሬን ሲናገር የሰማሁት። ገብረመድህን አርኣያ። የሱ ወግ ጊዜ አልሰጠኝም። ሌላው ይቆይ። የቀድሞ የህወሓት አባልና ገንዘብ ቤትን ወግ ላወጋችሁ ፈቀድኩ።

 

የፓልቶክዋ “ሙያዬ ምስክር” ወይም “ብዙ ወንድማገኘሁ” አንዳንዴ ልብ ሰቃይ ቅጽበቶች ላይ እየገባች ብስጭት ብታደርገኝም፤ እየጎረጎረች፣ እየሰረሰረች ደግሞም እየፈለፈለች የምታወጣቸውና የምታናዝዛቸው ሰዎች ያስደስቱኛል። ባለፈው ቅዳሜ ገብረመድህን አርኣያ አስደሰተኝ። አስደመመኝ። አሳቀኝ። አሳዘነኝ። እንደወረደ ይናገራል። እንደመጣ ይሰይማል። ጣጣ የለውም። አብርሃም ያየህ እሱንም አበሳጭቶት ኖሮ “ዋይ! እሱ ‘ኮ ጭልፊት ነው! ጭልፊት ታውቃላችሁ? ... ጭልፊት። ቆሻሻ ነው። ሌባ ነው። የማይረባ።” ለብቻዬ ነበር የምሰማው። ቤቴ እስኪታዘበኝ ሳቅኩኝ። ተንከተከትኩኝ። ሁለት ሦስት አራት በሳቅ የሚያንፈቀፍቁ ቅጽበቶች ነበሩ። በዚያ ባለፈው እሁድ ኦገስት 23 ቀን 2009 እ.ኤ.አ. በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች መወያያ መድረክ እንግዳ ሆኖ የቀረበው አቶ ገብረመድህን አርኣያ በሰጠው ቃለ ምልልስ ላይ።

 

ገብሬ ማነው? ገብረመድህን አርኣያ የዛሬ 36 ዓመት ኣካባቢ ነው መንገድ ላይ ሲሄድ ወይንም እርሻውን ከሚያርስበት መጥተው የማገብት ሰዎች የያዙት። ማኅበረ ገስግስቲ ብሔረ ትግራይ። ምንም የፖለቲካ እውቀት አልነበረኝም ይላል። ብሔር ብሔረሰብ፣ ብሔርተኝነት፣ የብሔር ጭቆና፣ ... ምናምን የሚባል ነገር አያውቅም ነበር። በዚያ ምንም በማላውቅበት ጭንቅላቴ ገብተው የነሱ ተከታይ አደረጉኝ አለ ገብረመድህን። በወቅቱ ማገብት፤ በኋላም ተሀህት፣ ከዚያም ህወሓት እስካሁንም ድረስ ትግላቸው በሦስት ዋና ዋና መርሆች ላይ የተመሰረተ ነበር። ኤርትራን ማስገንጠል ወይንም የኤርትራን ቅኝ ግዛትነት መቀበል። የቀይ ባህር የኢትዮጵያ አካል አለመሆን መቀበልና አማራውን ጠላት አድርጎ መቀበል። ሦስተኛውን ረሳሁት። ስለዚህ ከመጀመሪያውም ህወሓት ኢትዮጵያን ለመበታተን ኤርትራን ለማስገንጠል የተፈጠረ ቅጥረኛ ድርጅት ነው ይለናል ይህ ሰው። ከኢትዮ ሚድያው አብርሃ በላይ ጋር ይስማማሉ እዚህ ጋር። አብርሃም ይሄንን ነው የሚለው ከኢካድ ፎረም ጋር ባደረገው ቃለምልልስ። (ቃለምልልሱን ለማየትና ለማድመጥ እዚህ ይጫኑ!)

 

ስለኢኮኖሚ ምንጫቸው፣ ስለዓላማቸው ተጠየቀ

ገብረመድህን አርኣያ እንዳስቀመጠው፤ ባጭሩ የህወሓት የኢኮኖሚ ምንጭ ዘረፋ ነው። ህወሓት መጀመሪያ የትግራይ ዜጎችን አስሮ እየገረፈ ይዘርፍ ነበር። ጎን ለጎን አማራው የትግራይ ህዝብ ጠላት ነው ብሎ ተነሳ። ኤርትራም ቀይ ባህርም የኢትዮጵያ አካል አይደለችም ብሎ ተዋጋ። በዚህና በሌሎችም ምክንያት ህወሓት በትግራይ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት አልነበረውም። በዚህም ምክንያት ብዙ የትግራይ ኢትዮጵያዊያን ተገድለዋል። አቶ ገብረመድህን ብዙ ስም ጠራ እነ ክቡር ፊታውራሪ ምናምን። እነ ደጃዝማች እከሌ። እነ ክቡር ደጃዝማች እንቶኔ። ብዙ የላይኛውን አማራውን ጠላት አድርጎ የመነሳትና ኤርትራን የማስገንጠል የህወሓት ዓላማ የተቃወሙ የትግራይ ኢትዮጵያዊያን ተገድለዋል። መቼም ታሪክ ስለሆነና አቶ ገብረመድህን ስላለው ላንሳው እንጂ፤ ዛሬ የኤርትራ እጅ እንደሚያስፈልገን የማምነው ሰው ይሄንን መዘገብ አልነበረብኝም። ግን እሱ አቶ ገብሬ አለ።

 

ስየ መጣብኝ። ስየ አብርሃና ገብረመድህን አርኣያን በሁለት የተለያዩ ቅርንጫፎች ላይ የሚያስቀምጥ ነገር ብዙ ነው - ከዚህ ቃለ ምልልስ እንደተረዳሁት። የዛሬ ዓመት ከምናምን አቶ ስዬ ከእስር እንደተፈታ ከዚያም በኋላ በተካፈለባቸው ስብሰባዎች ላይ ሲናገር አዳምጫለሁ። ሌሎች ስለሱ የጻፉትንም ተመልክቻለሁ። ስየ ፍንክች አላለም። ምንም ኃጢያት ሠራን አይልም። ገብሬ ግን እኔ ኃጢያተኛ እያለ ንስኀ ይገባል። አሁንም ስየ በመድረክ በኩል ከአንድነት ጋር ወግኖ በመሥራት ህወሓትን ለመደምሰስ ይረዳናል ብዬ ብመኝም፤ ልክ እንደኤርትራው ጉዳይ የተባለውን እንደተባለ ከማቅረብ አልቦዝንም። ለነገሩ ይሄ አቶ ስየን ምላሽ እንዲሰጡ ያነሳሳ ይሆናል እንጂ አይጎዳም።

 

ዌል! ገብረመድህን አርኣያና ስየ አብርሃ በሁለት ዓለም ውስጥ ያሉ፤ አንዱ ባውሮፓ አንዱ በኢትዮጵያ በተለያየ ምክንያት ከህወሓት የተገለሉ ወይንም የወጡ ሰዎች ናቸውና ባንድ አይነት ቋንቋ እንዲነጋገሩ ወይንም እንዲመሰክሩ መጠበቅ የለብንም። ግን ልዩነታቸው እጅግ በጣም የተለያየና የሰማይና የምድር ያህል የሰፋ ሆነ። አንዱ (ገብረመድህን) ህወሓትን በኃጢያት ተጸንሶ፣ በኃጢያት ያደገ፣ በኃጢያትም ሕይወቱን የሚገፋ የመርገምት ድርጅት ያደርገዋል። ሌላው ደግሞ (አቶ ስየ) ህወሓትን በርግጥም ለቅድስና የቆመ፤ ነገር ግን በኀጥዓን የተነጠቀ የቅድስና ድርጅት ያደርገዋል። ለስየ ህወሓት ጥቂት ሰዎች ከተወገዱ መታደስ የሚችል ምንም ወንጀል ያልፈጠመ ድርጅት ነው። ለገብረመድህን ደግሞ ወያኔ ለፍርድ መሰቀል ያለበት የጥፋት ድርጅት ነው። አንዳንዱ የአቶ ገብረመድህን ምስክርነት ለኔ ራሱ የሚዘገንን ነው። ሀገር የወጉ። ሀገር የሸጡ። ህዝብ ያስጨረሱ። ህዝብ ያደሙ። ወገን በረሃብና በመሣሪያ የፈጁ ያደርጋቸዋል ገና ሲፈጠሩም።

 

የጋሽ ገብሬ ምስክርነት ይመች ነበር። ማንም ሊያደምጠው ይገባል። የምግባረ ሰናይ ድርጅት ያቋቋምነው በ1975 ነው አለ። ከዚያ በፊትም በኋላም ግን እንዘርፍ ነበር። እስኪ አቶ ገብረመድህን ሲናገር እንስማው። “እኔ ያኔ ሱዳን ውስጥ እርዳታ የመቀበሉንና ገንዘብ የመቀበሉን ሥራ እሠራ ነበር። ብዙ ፈረንጆች ይመጡ ነበር። እርዳታ ለመስጠት። ኋላ ላይ አለቃዬ ስብሃት ነጋ ጠራኝና ገበሬ ወይንም ነጋዴ መስየ እንድቀርብ አደረገኝ። አንዴ ሐኪም እንድሆንም ተደረግኩ። እኔ ገብረመድህን አርኣያ ሐኪም መሐመድ እንድሆን ተደረግኩ። ቁርዓንና መቁጠሪያ እንዲሁም ጥምጣም ተሰጠኝ። አንድ ታጋይ ሚስትም ተመርቆልኛል አለ ገብረመድህን።

 

“እንግሊዘኛ በፍጹም እንዳልናገር አስጠነቀቁኝ። ማሽላ መሸጥ ነው የኔ ሥራ። ግን የቀረበው የእርዳታ ገንዘብ መጠንና የማሽላው ብዛት አይገናኝም። ስለዚህስ? ከተከዜ አሸዋ እየተጫነ መጣና ማሽላ እንዲመስል ተደረገ። ከፊት ከፊት ማሽላ በጆንያ። ከኋላ አሸዋ የተሞላ ጆንያ ተቀምጦ አንድ ግዜ ሠላሳ ሁለት ሚሊዮን ሌላ ጊዜ አርባ ስድስት ሚሊዮን ዶላር ሸጥን” አለ። ይህቺ ናት ጨዋታ! ... ይህቺ ናት ብልጠት። ብሩን ስብሃትና መለስ ወሰዱት አለ። ከዚህ ምን እንማራለን? ብዙ ነገር። ለምሳሌም፦

 

ሁለት ነገር ታየኝ እዚህ ጋር። ዋናው ነገር ወያኔዎች እየዘረፉና እያጭበረበሩ እያምታቱ ሀብት መሰብሰባቸው ነው። ግን ትንሽም ቢሆን ጠላትን ማድነቅና ከጠላትም መማር አለብን። እንደው ጥሎብን ከጠላት መማር አልለመደብንም እንጂ በዚያን ዘመን ጭንቅላታቸው ይሄንን ያህል ብልጠት ከሠሩ እንደው መድኃኔዓለምን ነው የምላችሁ ትንሽም አደነቅኳቸው። በዚያ መልኩ ነው ማለት ነው ጄኔራሉንና ሀገሩን ሁሉ እየገዙ እዚህ የደረሱት? ያስብላል። ያ ብቻ አይደለም እኛም እነሱ የደረሱበት ለመድረስ ይሄንን ያህል መጓዝ ይጠበቅብናል ማለትም ይመስላል። አሸዋ እንደ ስንዴ መሸጥ አለብን አይነት ነገር።

 

በሚቀጥሉት ቀናት ስለገብረመድህን አርኣያ ሌሎች ምስክርነቶች እጽፍላችኋለሁ። ለምሳሌ እሱን ስለዘገነነውና አሁንም ድረስ ቋቅ ስለሚለው ያልተለወጠ የ1975 የህወሓት መፈክር። እሱ እንዳለው “To keep the Ethiopians is not benefit, to kill them is not loss” አባባል። ይሄንን እሱ እንዳለው ነው ያሰፈርኩት። ኢትዮጵያውያን በተለይ አማሮቹ ብናቆያቸው አይጠቅሙንም ብናጠፋቸውም አይጎዱንም። “አፈር ያርገኝ” ትላለች እናቴ ስትምል። እኔም ልበላችሁ። እንደወረደ ገብረመድህን አርኣያ እንዳለው ነው ያሰፈርኩላችሁ። በዚህ ፖሊሲ እጅግ ከማዘኑና አሁንም ድረስ ከመፀፀቱ የተነሳ ገብረመድህን ይሄ በዓለም ላይ በየትም የሌለ እንደው በካምቦዲያም ያልተፈጸመ ጸያፍ ፖሊሲ ነው ይለናል ደግሞ ደጋግሞ።

 

ስለገብሬና ቃለምልልሱ የምለው ይቀጥላል። እስከዚያው ግን ሙሉ ቃለ ምልልሱን www.ecadforum.com ላይ መጠበቅና ማዳመጥ አለባችሁ። ያልተናገረበት ርዕስ የለም። ከኀውዜን እስከ ሱዳን፣ ከአዜብ ጎላ እስከ አብርሃም ያየህ፣ ከዚህ በኋላስ እንዴት መጓዝ አለብን በሚለው ርዕስ ላይ ጥሩ ተናግሯል። እንደው ምንም አላውቅም ይላል እንጂ ብዙ ያውቃል ሰውዬው።


 

ልጅ ተክሌ ነኝ ከቫንኩቨር ካናዳ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!