ሄለን ነገራ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. 

ሰሞኑን በአዳማ ከተማ የአንድነት ፓርቲ የጠራው ስብሰባ በድንኳን ሰባሪዎች ተገለበጠ ተብሎ የተለያዩ አስተያቶችን እያነበብን ነው። እውነቱን ለመናገር ለኔም ሆነ ለጓደኞቼ ምንም የሚደንቅም የሚያናድድም ዜና አልነበረም። ወያኔም ያንን አስመልክቶ በአቶ በረከት ስምዖን በኩል የተለመደ የውሸት ማስተባበያውን መስጠቱም አልደነቀኝም። ይልቁንም እኔን የገረመኝ ያንን ክስተት አስታከው የቀድሞ የወያኔ ቁንጮ ባለሥልጣን አቶ ስየ አብርሃ የሰጡት መግለጫ (ጽሑፍ) ነው።

 

በእርግጥ ማንኛውም ሰው በመረጠው መንገድ መታግልም ሆነ ማታገል መብቱ ነው። ነገር ግን አቶ ስየ ሰሞኑን “እውነትም መንገድም እኔ ነኝ” አይነት መፈራገጥ በሚዲያዎች ላይ አበዙብኝና አላስቻለኝም። በሠላማዊ ትግል ስም ያዙኝ ልቀቁኝ እያሉ ሲወራጩ ደግሞ ያንን ዘረኛ መንግሥት በጥርስም በእጅም እታገላለሁ ብሎ የቆረጠውን አብዛኛውን የኢትዮጵያ ህዝብ እየተራገጡ ስለሆነ፤ እግሮችዎን ሰብስቡልን ማለት ፈለኩ። የአንድነት ፓርቲም አውቆ በድፍረት - የማይበጀውን፤ ሳያውቅ ደግሞ በስህተት - በሬ ካራጁ እንዳይሆንበት መጠቆሙ ተገቢ መሰለኝ።

 

እውነተኛ ሠላማዊ ትግል ለማድረግ የቆረጡትንም ሆነ ትግሉን ራሱ እንደ ትግል በፍፁም የማልቃወም መሆኑን አንባቢዎች እንዲረዱልኝ እየጠየቅኩ፤ ይህችን አጭር አስተያየቴን ታጣጥሙልኝ ዘንድ እነሆ! (የአቶ ስየን ስብዕና ሳይሆን የሚያራምዱትን አቋም ብቻ የመተቸት መብቴን መጠቀሜን ልብ በሉልኝ)።

 

አቶ ስየ ማናቸው?

እጅግ በጣም በትንሹና በጥቅሉ ለማስተወዋቅ ያህል አቶ ስየ ማለት፤ የወያኔን ዘረኛ መንግሥት (አሁን መሬት ወርደው ከሚወነጅሉት ሀገር አጥፊ ቡድን ጋር) አብረው የተከሉ፤ ከጥቂት ዓመታት በፊት ከነቤተሰባቸው አሁን ወያኔ የሚፈጽመውን ግፍና በደል (ምን አልባትም በባሰ ሁኔታ) ሲፈጽሙ የነበሩ፤ አክራሪ የትግራይ ዘረኞች ቡድን ውስጥ የሚመደቡ፤ ከእስር በኋላ በይቅርታና በንስኀ የእጃቸውን ያላፀዱ፤ እናም ጨለማው እስኪገፍ ፍትህ በጉጉት እጆቿን ዘርግታ የምትጠብቃቸው ሰው ናቸው ብል ማጋነንም ጥላቻም አይሆንም። ህዝባችን በጨዋነቱ፤ አንዳንዱ ደግሞ “ቂምህን አትርሳ፣ የወደቀን አንሳ” በሚል አቅፎ የያዛቸው ግለሰብ እንጂ የህዝብን ትግል እንዲመሩና እንዲያስተባብሩ የአቅምም የሞራልም ብቃት ያላቸው ሰው አይመስሉኝም።

 

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የሠላማዊ ትግል ሐዋርያ ሆነው ቀርበዋል። ሀገራችንን እሳቸውና የሳቸው ሰዎች ከዘፈቁበት የመከራ አረንቋ ለማውጣት ብቸኛውና ብቸኛው አማራጭ ሠላማዊ ትግል ነው እያሉን ነው። ምንም እንኳን የአቶ ስየ የረጅም ግዜ ተሞክሮ ጦር ሜዳ ቢሆንም (ምናልባት እዛም ሠላማዊ ትግል ሲያካሂዱ ነበር ካልተባለ) ሠላማዊ ትግል ያዋጣል ማለታቸው ምንም ችግር የለውም። ጥፋቱ በሠላማዊ ትግል ማመናቸው ወይም እሱን መስበካቸው አይደለም። እንደማንኛውም ዜጋ የፈለጉትን አቋም ማራመድ መብታቸው ነውና ይግፉበት። ችግሩ ወያኔ ካስቀመጠልን ሠላማዊ ትግል ውጪ (አሁን እየተደረገ ያለው አይነት ማለት ነው) አማራጭ የለህም አርፈህ ተቀመጥ ሲሉን ነው። ነኀሴ ፲፫ ቀን 2001 ዓ.ም. “ምኅዳር በስቱዲዮ እና ምኅዳር በአዳማ” በሚል ርዕስ የበተኑት ጽሑፍ አስረግጦ የሚነግረን ይሄንን ነው። ይህ ጽሑፍ ሲጨመቅ መልዕክቱ ሁለት ነው - “ሠላማዊ ትግል ብቸኛ አማራጭ ነው” እንዲሁም “የወያኔ ጉድ በአዳማው ስብሰባ ተጋለጠ!” (የአቶ ስየ አብርሃን ጽሑፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)

 

ሠላማዊ ትግል ነው ወይስ በሠላም እንኑርበት ተዉን ነው የሚሉን?

አቶ ስየ ደጋግመው የትግል አማራጮቹን ከነጭና ከጥቁር (ሠላማዊ ትግል ወይስ ጦርነት) አድርገው ያቀርባሉ። እውነታው ግን እሳቸውም በደንብ እንደሚገነዘቡት ያ አይደለም። ጭቆና ያንገፈገፈውና ብሶት ያስመረረው ህዝብ አንገቱን ከደፋበት ቀና ሲል በማንኛውም መንገድ እራሱን ይከላከላል። ወያኔን እያስፈቀደ ሳይሆን በትክክለኛው ሠላማዊ ትግልም ጭምር ይተናነቃል። ህዝቡም በዚህ ደረጃ ለመታገል የቆረጠ መሆኑን ለማሳየት አንድ ወዳጄ እንደቀልድ የሚለኝን መጠቆሙ በቂ ነው፤ “አካፋና ዶማዬን ወልውዬ በጉጉት እየጠበቅኩ ነው!” - በርግጥ ቀልዱን ይሁን እውነቱን እርግጠኛ አይደለሁም። እርግጠኛ ሆኜ መናገር የምችለው ግን አብዛኛው ህዝብ ማንኛውንም መንገድ ተጠቅሞ ፲፰ ዓመት እንደመዥገር ደሙን ሲመጠው ከኖረ ጠላት መላቀቅ ይፈልጋልም፤ ያደርገዋልም!

 

እንደውም በጽሑፋቸው አንድ ቦታ ላይ ኢህአዲግ ከመሣሪያ ትግል ይልቅ የሠላማዊ ትግሉን እንደፈራው አስረግጠው ይነግሩናል። ለኔ ይሄንን አባባል ቀና በሆነ መልኩ ስረዳው እየነገሩን ያሉት የተገላቢጦሹን ነው። ካልሆነ ግን ያው እንደተለመደው ማላገጥና የወያኔን ፍላጎት ማራመድ ነው የተያዘው። ወያኔ እንቅልፍ አጥቶ የሽብርተኛ ሕግ የሚያወጣው፤ ጄኔራሎቹን ሰብስቦ የሚያስረውና የሚያባርረው፤ ሕፃን አዋቂ ሳይል እስር ቤት የሚያጉረው፤ … “መድረክ” የሚባል ሠላማዊ ታጋይ ድርጅት አስጨንቆት አይመስለኝም። ቀን እንደ ጥላ፣ ሌት እንደቅዠት የሚያስበረግገው ኦነግ እንጂ ኦፌዲን ወይም ኦብኮ አይመስሉኝም። “የቃሊቲ እስር ቤት ኦሮምኛ ይናገራል” ያሉት አቶ ስየ አይደሉምን? እስረኛው በሙሉ ኦነግ ባይሆንም የእውር የድንብራቸውን ንጹኅ የኦሮሞ ልጆችን እያፈሱ የሚከቱት ግን ኦነግን ፍራቻ ብቻ ነው!

 

ከዚህ ቀደምም ቪ.ኦ.ኤ. ላይ፣ “ረጅም ጊዜ ይወስዳል እንጂ ሠላማዊ ትግል ብቸኛው መፍትሔ ነው” ብለውን ነበር። የጊዜ ስሌታቸውን ግልጽ ባያደርጉትም ከአነጋገራቸው ግን ምናልባት አስርት ዓመታትን በትዕግስት አዝግሙ፣ ታገሱ ይመስላል። ጥቂት ሰዎች ጠግበው እየተፉ ሌላው ግን በረሃብ እያለቀና በገዛ ሀገሩ ሁለተኛ ዜጋ ሆኖ እየኖረ፤ በሠላም እንኑርበት ተዉን ካልሆነ አሁን የተያዘው ቀልድ ሠላማዊ ትግል ነው ማለት ዘበት ነው። የተመቻቸው ጥቂቶች ለዘለቄታው ከነግፋቸውና ከነወንጀላቸው በሠላም እንዲኖሩ መታገል ለኢትዮጵያ ህዝብ ሠላማዊ ትግል ሊሆን አይችልም።

 

ውርደት እንደ ገድል

አንዳንድ ጊዜ ወያኔን እያስፈቀዱ የሚታገሉት ሰዎች ያስቁኛል። ባብዛኛው መብታቸው የሆነውን ነገር እንኳን ወያኔ አይፈቅድላቸውም። እሺ ብሎ የፈቀደላቸውም ጉዳዮች ላይ እንኳን አዋርዶ ያባርራቸዋል። እንደኔ እንደኔ እነዚህ ሰዎች አሁን አሁን ሠላማዊ ትግልና ሠላማዊ ውርደት ተምታቶባቸዋል። እንዲህ አይነቱን ክስተት ነው እንግዲህ አቶ ስየ እራስን በሚያሞኝ መልኩ፣ “ወያኔ አዳማ ላይ ጉዱ ወጣ” የሚሉን።

 

ለነገሩስ የቱ ጉድ ይሆን የወጣው? አቶ ስየ ብዙውን ጊዜ ሥልጣን ላይ ሆነው ጉድ ሲሠሩና ቀሪውንም ጊዜ እስር ቤት ስላሳለፉ አላዩ ይሆናል እንጂ፤ ወያኔ የተደበቀና አዲስ ጉድ የለውም። ለትምህርት ከቤቱ የወጣን ታዳጊ ወጣት በጠራራ ፀሐይ ግንባሩን በጥይት በርቅሰው፤ “ሲዘርፍ ገደልነው” ብለው የሚፎክሩ ወንበዴዎች ባሉበት ሀገር፤ ነጋሶ ተገፈተረ፣ ግዛቸው ተኮረኮመ ብሎ የሚደነቅ ማነው? ራሱ የአዳማ ህዝብ ኦነግ ነህ እየተባለ በየቀኑ እየታሰረ፤ እየተገደለና እየተሰደደ አይደለምን? በዚህ ወቅት የስብሰባ መቋረጥን እንደጉድ ማውራት ራሱን የቻለ ጉድ አይሆንም? እሺ ይሁን አቶ ስየና ራሱ ድርጅቱ እንዳለው ጉድ ታየ ብለን አደነቅን - “ስብሰባ በጭበጨባ ተቁዋረጠ” ከዛስ ምን ይሁን? በስፍራው የነበሩ አመራሮችን ሰብስቦ እስር ቤት ቢወረውራቸውስ ኖሮ ምን ታደርጉ ነበር? ለጀግናዋ እህታችን ብርቱካን ሚደቅሳ ከወሬ ያለፈ የናንተ ሠላማዊ ትግል ምን ፈየደላት? ይሄ ብቻ ነው ትክክለኛው አማራጭ ብሎ መስበክ ደግሞ የበለጠ የጉድ ጉድ ይሆናል።

 

ወያኔ ተጎንበሱ ሲል እሺ፤ ቀና በሉ እሺ፤ ተንበርከኩ እሺ … ማለት ሠላማዊ ሊሆን ይችላል። ትግል ግን ሊባል አይችልም። ለምን አዳራሽ ውስጥ አንባጓሮ አልተፈጠረም እያልኩ አይደለም። ሲጀምር ግን ያ እንደሚመጣ ይታወቃል፤ ምናልባትም ከዛ የባሰ። እንዲህ አይነት የሕፃን ጨዋታ አቁሞ ለውጥ ወደሚያስገኝ ትግል ራስን ማስገባት ነው ጀግንነት። የኢትዮጵያም ህዝብ የዓለምም መንግሥታት ጠንቅቀው የሚያውቁትን ነገር ማጋለጥ ምንም አይገባኝም - ምኑን፣ ለማንና እስከመቼ የሚሉ ጥያቄዎችን በአግባቡ አይመልስምና።

 

የአቶ መለስን የቀልድ አባባል (metaphore) በመጥቀስ አቶ ስየ፣ “እኛ እንደ ኢህአዲግ በእጅም በእግርም ጎል አናስቆጥርም” ሲሉም ጽፈዋል። ሲጀመር እኮ ስለ ኳስም ስለ ጎልም የሚወራው ኳስ ሜዳ ነው። ጦር ሜዳ ውስጥ ቁጭ ብሎ ህዝብ እየተቃጠለ ስለ ማኖ ማውራት አሁንም ፌዝ ነው። በጽሑፋቸው መጀመሪያ አካባቢ ኦህዲዶች (እነ አባዱላና ኩማ) “በዚህ መልኩ ከአዳማ ያባርሩናል ብለን አልጠበቅንም ነበር” ይሉናል። በርግጥ እንድምታው እነርሱ እራሳቸው ጠፍጥፈው የሠሩት ኦህዲድ በራሱ የቆመና በራሱ የሚወስን ድርጅት አድርጎ ማቅረብ ነው። ከአዳማ ያባረረን ኦህዲድ ነው እያሉን ነው። ያሉትን ባልቀለም “ወደሽ ከተደፋሽ፣ ቢረግጡሽ አይክፋሽ” ለማለት ግን እገደዳለሁ።

 

ዞሮ ዞሮ ህዝብንም ራስንም እያዋረዱ መቀጠል በምንም መለኪያ ትግል ሊሆን አይችልም። ሌላው ቢቀር ብቸኛው ትግል ይሄ ብቻ ነው እያሉ ማሳሳት ያንገፈግፋል። አንድም የህዝብን የስቃይና የብሶት መጠን አለመረዳት ነው፤ ካልሆነም በሰው ቁስል ላይ እንጨት መስደድ ይሆናል። በአሁኑ ወቅት ህዝቡ የሚፈልገው ውርደትን እንደ ድል እያሞካሸ የሚያላምድ ሳይሆን፤ ለውጥ የሚያመጣ አመራርን ብቻ ነው። ምኅዳር ጠበበ፣ ምኅዳር ሰፋ፣ ቪጂላንቴ፣ … ምንትሴ እያሉ ቃላት መፈብረክና መተረክ ጠቀሜታም የለውም፤ አዋቂም የሚያሰኝ አይደለም። ከስብሰባ ተግፍትሮ መባረር ውርደት ነው እንጂ፤ ገድል ወይም ጀግንነት አይደለም። ውርደትንም መደጋገም ይለመዳል እንጂ ለውጥ አያመጣም።

 

ለውጥ ወዲህ ቂም በቀል ወዲያ

አንዳንድ ግዜ የአቶ ስየ ችግር የኢትዮጵያ ህዝብ መከራና ስቃይ ወይም ሀገሪቱን የበከላት የዘረኝነት መርዝ ሳይሆን ችግራቸው አቶ መለስ ብቻ ይመስለኛል። የሚገርመው ነገር ሁልጊዜ አቶ ስየ ሲጽፉም ሆነ ሲናገሩ የማይዘነጉትና ልዩ የሚያደርጋቸው ነገር፤ አቶ መለስን “አንተ” ማለታቸው ብቻ ነው። በርግጥ ድፍረት አይሁንብኝና የውስጥ ሱሪያቸውን አውልቆ በሙስና ጅራፍ እየጠበጠበ እስር ቤት ስለጣላቸው ቂም ይዘው ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የህዝብን ትግል እየደፈጠጡ ቂም በቀል ለመወጣትና በውስጥ ችግር ያጡትን ሥልጣን ለመያዝ ማድባት ትርፉ ትዝብት ነው።

 

እኔ እንደሚመስለኝ ህዝቡ ከሳቸው የሚጠበቀው ቂም መወጣታቸውን ወይም የሠላማዊ ትግል ሐዋርያነታቸውን አይደለም። እንደሚወራላቸው ጀብድና እሳቸውም ለመምሰል እንደሚሞክሩት ሆኖ መገኘት በፍፁም የቻሉ አልመሰለኝም። ሐቀኛ የሠላም ታጋይ ከሆኑ የወያኔን ወንጀሎችና ስስ ብልቶች ጠንቅቀው ስለሚያውቁ እሱን ማጋለጥ ነው። በድፍረት መናገርና መጻፍ፤ ያለበለዛ “መቀመጫውን የተወጋ ምንትስ እንደልቡ አይጮህም” እንዲሉ፣ ፍርሃት ከያዛቸው ደግሞ ወጣ ብለውም ለትግሉም ለታሪክም የሚጠቅም አስተዋጽዖ ማበርከት ይችላሉ። እዚህ ጋር ተስፋዬ ገ/አብን መጥቀስ በቂ ነው። እሱ የአቅሙን በትክክለኛው ቦታና መንገድ ለትግሉ አስተዋጽዖ እያደረገ ነው። የአዳራሽ ስብሰባ በጭብጨባ መቁዋረጡን ሳይሆን፤ የደራራ ከፈኔን የግፍ አሟሟት ማወቁ ለትግል የሚያበረታን የውስጥ ኃይል ፈጥሮልናል።

 

በመጪው ምርጫ ከሁለት ወያኔዎች መካከል አንዱን ይምረጡ?

አንዳንድ ሰዎች እነ አቶ ስየ መጪውን ምርጫ በሁለት ወያኔዎች መካከል ለማድረግ በቆረጣ የገቡ ተቃዋሚዎች ናቸው ይላሉ። “ቀን ከህዝብ፣ ሌት ከጅብ” እንደሚባለው አሁን አሁን እርምጃውን በደንብ እያየን ስለሆነ ይሄ ተራ ጥርጣሬ ነው ብሎ ማለፍ የዋህነት ነው። ሲጀመር ከአሁን በኋላ የወያኔን ምርጫ የሚጠብቅ ናፋቂ የለም። ቢገደድም ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዓረናና ከህወሓት ይመርጣል ብሎ ማሰቡ (በርግጥ አቶ ስየ እስካሁን ነፃ የመድረክ አባል ናቸው) ዓይናችሁን ጨፍኑና ላሞኛችሁ ይሆናል።

 

በመጨረሻም በጣም እንደማሽላ ያሳቀኝንና በጽሑፋቸው በስተመጨረሻ ያስቀመጡትን አንድ ነጥብ ቃል በቃል ጠቅሼ ላቁም። የሠለማዊ ትግል ድርጅቶችን ሲመክሩ ነው፣ …

 

“… እርስ በርስ መተባበር እና ተሞክሯቸውን እየቀመሩ በስልት ኢህአዲግን መብለጥና መቅደም ይልመድባቸው፤ ህዝቡም በሂደት በሰው ዳስ እየገቡ የሚያውኩትን ሰዎች መቀሌ ላይ እንደተደረገው "ከፈለጋችሁ በሥነ ሥርዓት የፖለቲካ ድግሱ ተካፋይ ሁኑ አለበለዝያ በሰው ዳስ ገብታችሁ አትበጥብጡ" ብሎ አደብ ያስገዛቸዋል። …”

 

በማለት ይቀልዳሉ የቀድሞ የወያኔ ባለሥልጣንና የአሁኑ የሠላማዊ ትግል ሐዋርያው አቶ ስየ አብርሃ። እኛም እሰይ! የመቀሌ ህዝብ አበጀህ! ጀግና! ብለናል፤ የአዳማና የደብረማርቆስ ህዝብ ነው እንጂ ወኔ የሌለው። ድንኳን ሰባሪዎችን አደብ የማስገዛት ወኔ ከመቀሌ ህዝብ መማር እንዳለብን በርግጥ ልብ ብለናል።

 

ሲጠቃለል

ባጭሩ የዚህ ጽሑፍ መልዕክት ሁለት ነው። የመጀመሪያው፦ እናንተ ከፈለጋችሁ አዳማም፣ መቀሌም፣ ደብረማርቆስም ደጋግማችሁ ተሰብሰቡ። እርሶም ቪጂላንቴዎችን ፈርተን ከስብሰባ አንቀርም ብለዋል እሰየው ይበርቱ! ህዝቡን ግን ሌላ አማራጭ የለህም እያላችሁ አታምታቱ። ሁለተኛው ነጥብ፦ አንድነት ፓርቲ ከማን ጋር እና እንዴት እንደሚሠራ ደግሞ ደጋግሞ ቢያስብበት የተሻለ ነው እላለሁ። መርኅ የሌለው መሞዳሞድ ሩቅ አያስኬድምና!!!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!


ሄለን ነገራ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!