ከዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማሪያም

1. መነሻው

አንድ ማኅበረሰብ እንደ ማኅበረሰብነቱ እንዲቀጥል ከተፈለገ በረቀቀ መልኩም ይሁን በግርድፉ የህዝብ መስተጋብሮችን የሚያስተናግዱ፣ የሥራ ኃላፊነትንና ድርሻን የሚያደላድሉ፣ መሠረታዊ ፍላጎቶችን የሚያሟሉ ሕጎች መኖር የግድ ይላል። በመሆኑም እንደ አንዳንድ ጥንታዊ የዳበረ ኅብረተሰብ ኢትዮጵያዊያን ያለ ሕግ የኖሩበት ጊዜ የለም ማለት ይቻላል። ከዚያም አልፎ ዛሬ ሕጎቻቸው ዳብረው፣ ፍትሕ ሰፍኖባቸው፣ ህዝቡ መብቱ ተከብሮለት፣ ነፃነቱ ተጠብቆለት የምናያቸው ብዙዎቹ የዓለም መንግሥታት ባልተፈጠሩበት ዘመን በኢትዮጵያ በጽሑፍ የሰፈሩ የህዝቡን መስተጋብር የሚያስተናግዱ፣ የነገሥታቱና የባላባቱ ሥልጣን ስፋትና ወርድ ዳር ድንበሩን የሚከልሉ፣ በዳይን የሚወቅሱ፣ ተበዳይን የሚክሱ ሕግጋት ነበሩ።

 

ከእነዚህም ሕጎች መካከል በ16ኛው ምዕተ ዓመት አርቆ አስተዋዩ ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ “ህዝቤ ያለ ሕግ መኖር የለበትም” በማለት ዲያቆን ጴጥሮስን ወደ ግብጽ ልከው ያስመጡት የግብጽ ክርስቲያኖች (ኮፕቶች) ይተዳደሩበት የነበረው ፍትሐ ነገሥትን በዋናነት መጥቀስ ይቻላል። ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ እራሳቸው ጽፈውታል የሚባለው መጽሐፈ ምዕላድም አንዳንድ የወንጀልና የፍትሐ ብሔር አንቀጾች እንደነበሩት ይወሳል። ፍትሐ ነገሥቱ ከዓረብኛ ወደ ግዕዝ ተተርጉሞ ቢያንስ በሰሜኑ ኢትዮጵያ በዙፋን ችሎት (የንጉሡ ችሎት) በሥራ ላይ እየዋለ እስከ ዐፄ ምኒልክ ዘመን ዘልቋል።

 

ኢትዮጵያ ከብዙ አገሮች ቀድማ መጽሐፍ ቅዱስንና ቅዱስ ቁርኣንን ተቀብላ እነዚህ ቅዱሳን መጻሕፍትም የሁለቱ ኃይማኖቶች የእምነት መሠረቶች ቢሆኑም በህዝቡ ዓለማዊ ሕይወትም ላይ ከፍተኛ ጫና እንደነበራቸውና እንዳላቸውም አይካድም።

 

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ይተዳደሩባቸው የነበሩ ዛሬም ቅሪታቸው ያልጠፋ በኦሮሞው ገዳ፣ በአማራው ሸንጎ፣ በጉራጌ ቂጫ፣ በትግሬ ሽማግሌ ዓዲ፣ … በሌሎች ብሔረሰቦችም ዘንድ በተለያዩ ስሞች የሚታወቁ የባሕል ሕጎች የሰዎችን ግንኙነት ዳር ድንበር ከልለው ህዝቡ ተቻችሎ እንዲኖር አድርገዋል።

 

እነዚህ ጥንታውያን ሕጎችም ሆኑ የባህል ደንቦች አገሪቱ የደረሰችበት የእድገት ደረጃ፣ ጊዜውና ወቅቱ የሚጠይቀው ዘመናዊ የሆነ የፍትሃዊነት መሥፈርት እንደሚያሟሉ በመረዳት ከ1950ዎቹ ጀምሮ ዐፄ ኃይለሥላሴ እጅግ በተፋጠነ ሁኔታ ቁጥራቸው የበዛ ዘመናዊ ሕጎችን አስቀርጸው በሥራ ላይ እንዲውሉ አድርገዋል። ዐፄ ኃይለሥላሴ በረጅሙ ዘመነ መንግሥታቸው ሠሯቸው ከሚባሉት በጎ ተግባራት ከዋነኞቹ አንዱ እነዚህን ዘመናዊ ሕጎችን አስቀርጾ ማውጣትና በሥራ ላይ ማዋል መሆኑ ብዙ ኢትዮጵያውያን አይረዱም።

 

በየትኛውም ጥንታውያን አገሮች እንደነበረው ሁሉ በኢትዮጵያም በሕግ ከለላ የተሰጣቸው፣ በህዝቡ ላይ ከፍተኛ በደል ያደረሱ እንደ ባሪያ ንግድና እንደ ባለርስትና ጭሰኛ የመሳሰሉ አጸያፊ ሥርዓቶችና ሕጋዊ ግንኙነቶች እንደነበሩ አይካድም። ይህም ሆኖ ግን ጥንታውያን ሕጎች፣ የኃይማኖት ድንጋጌዎችና ባህላዊ ሕጎች መኖርና በሥራ ላይ መዋል በጥቅሉ በሀገራችን ፍትሃዊነት በህዝብ አዕምሮ እንዲሰርጽ አድርገዋል። ህዝቡ ለሕግ ከበሬታ እንዲኖረውና ግፍና በደልን እንዲጠላ፣ በጠቅላላው ፍትሃዊነት እንደ አንድ ብርቅዬ ዕሴት እንዲቆጠር በህዝብ እምነት ውስጥ ተቀርጿል።

 

ህዝቡ ለሕግ ከፍተኛ ከበሬታ እንደነበረው የሚገልጹ አያሌ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። ሁለት ባላጋራዎች መንገድ ላይ ቢገናኙ ተበደልኩ ባዩ ምንም ኃይል ሳይጠቀም “በሕግ አምላክ ቁም!” በማለት ብቻ ባላጋራውን አስቁሞ የነጠላዎቻቸውን ጫፍ ቋጥረው (ተቆራኝተው) ያለ ፖሊስ አጃቢ ወደ መረጡት ዳኛ ዘንድ ሄደው ፍርዳቸውን ይቀበሉ ነበር። ለዚህም ነው እስከዛሬ “በቆረጥከው ዱላ ብትመታ፣ በመረጥከው ዳኛ ብትረታ” እንዲቆጭህ አይገባም የሚባለው። “በሕግ አምላክ!” ሲባል ውሃ እንኳን ይቆማል ይባል ነበር።

 

በአገራችን የዳኝነት ሥራ በጣም የተከበረና ዳኞች የተለዩ ፍጡራን ሆነው ይታዩ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። የዳኝነት ሥራ እንደ መንፈሣዊ ተግባር ተቆጥሮ ከዳኛው ነፍስ ጋር ትስስር ነበረው። ፍርደ ገምድል ዳኛ በቀጥታ ወደ ገሃነም እንደሚወርድ ይታመን ነበር። ለዚህም ነው “ፍረድ ለነፍስህ፣ ብላ ለከርስህ” ይባል የነበረው። ስለዚህ ዳኞች በገንዘብ፣ በእጅ መንሻ እንዳይታለሉ ኅሊናቸውና ፈሪሃ እግዚአብሔርም ይገድባቸው ነበር። ጉቦና እጅ መንሻ ቢቀበሉም እንደ ዛሬው የባለጉዳይ ቆዳን ገፍፎ በአንድ ጀምበር ቱጃር የሚያደርግ ሳይሆን፤ ከአንድ ጉንዶ ማር ወይም ከአንድ ሽንጥ ጥሬ ሥጋና ጠርሙስ አረቄ የሚዘል አልነበረም።

 

2. ዛሬ ለሕግ ያለው ከበሬታ ወይም ንቀት

ዛሬ በአገራችን የፍትህ ሥርዓቱ ተሰብሯል ማለት ይቻላል። ለሕግ የነበረው ከበሬታ እየተሸረሸረ፣ ሕጉ ነፃነቱን ተገፍፎ፣ በፖለቲካ ተቀፍድዶ ህዝቡ ለፍትህ ያለው እምነት እየተሟጠጠ ነው። የሕግ ከበሬታ እያሽቆለቆለ የመጣው በዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት መገባደጃ ነው ቢባል ስህተት አይሆንም። በሀገራችን ቀርቶ በአፍሪቃም ተወዳዳሪ የማይገኝለት የቀይ ሽብር “ነፃ እርምጃ” አካብቶት የነበረው ሕጋዊነትና የፍትሕ ዕሴት ከህዝቡ ኅሊና ጠራርጎ አወጣው። እመቤት ሕግ ዓይኗን የተሸፈነች፣ በአንድ እጇ ሚዛን፣ በሌላው ሰይፍ ያነገተች ሳትሆን፤ ዓይኗን ብልጥጥ አድርጋ እየመተረች፣ ሰይፉ አድሃርያንን መርጣ የምትቀላበት መሣሪያ ሆነ። ሰው ሁሉ በሕግ ፊት እኩል ነው የሚለው ዓለማቀፋዊ መርኅ ተሽሮ ሕግ አንድን የኅብረተሰብ ክፍል (መደብ) መመንጠርያ መሆኑ በገሃድ ተሰበከ፣ በሥራ ላይም ዋለ። ከጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ ጊዜ አንስቶ ደም የሚገበርለት ዛር ውላጅ ያለ ይመስል በዚች ሀገር ያለ ፍርድ በፈረቃ፣ በየጎዳናዎች የፈሰሰው የንጹኀን ደም ቤቱ ይቁጠረው። አንዲት ከአሜሪካ ለእረፍት ሀገርዋ የመጣች ኢትዮጵያዊት ስልክ ደውለው 'ኢትዮጵያ ውስጥ ምን ርካሽ ነገር አለ?’ ብለው ቢጠይቋት 'ርካሽ ነገር ቢኖር የሰው ሕይወት ብቻ ነው' ማለቷ በራሱ ብዙ ይናገራል።

 

በአገራችን የፍትህ ሂደት በተለይ ደረቅ ወንጀል በሚባሉት እንደ ፖለቲካ ወንጀሎች የመሳሰሉት የኋሊት ሄዷል ማለት ይቻላል። ሕግ ተበዳይን መካሻ፣ በዳይን መውቀሻ፣ የተሳሳተውን ማረሚያ ሳይሆን፤ ቂም መውጫ፣ ተቃራኒን ማስወገጃ ሆኗል ማለት ይቻላል። ለቂም መውጫ በአንድ ሌሊት ሕግ ወጥቶ ያድራል። ከሕገ-መንግሥቱ ጋር ቢጣረስም ምንም አይደለም። በሕግ ማላገጥ፣ ሕግን የፖለቲካ መሣሪያ የማድረግ መጥፎ አርኣያነቱ ለሌሎች አፍሪካ አገሮች ሁሉ ተርፏል። ኡጋንዳ፣ ዛምቢያ፣ ዚምባብዌ የኢትዮጵያን አርኣያነት በመከተል የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎችን በሀገር ክህደት ወንጀል መክሰሳቸው ይታወሳል። ሆኖም ግን በቅኝ ግዛት ሥርዓት ወቅት ሕጎቹ ኢ-ፍትሃዊ ቢሆኑም ዳኞቹ ሕጉን በትክክል የመተርጎምና አለአድልዎ በሥራ ላይ የማዋል ባህል ቅኝ ገዢዎቹ ትተው ስለሄዱ እነዚህ ዳኞች መንግሥታቱ ቢቃወሙም መሪዎቹን በነፃ ለመልቀቅ ወኔው አልገደዳቸውም። ዛሬ በዓለም ኅብረተሰብ በተቸራቸው ክብር ተወዳዳሪ የማይገኝላቸው ኔልሰን ማንዴላ በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ መንግሥት በሀገር ክህደት ወንጀል ተከስሰው ተፈርዶባቸው ነበር። ክሳቸው በኢትዮጵያ ቢሆን ኖሮ እኚህ ትልቅ ሰው ዛሬ በሕይወት ይኖሩ ነበር ወይ? የሚለው ጥያቄ አግባብነት ያለው ነው።

 

ዛሬ በሀገራችን አንድ ሰው ወይም ድርጅት ጦር ሳያሰልፍ፣ በእጁ አንድ ሴንጢ ሳይኖረው፣ ወረቀት በጻፈ ወይም ንግግር ባደረገ መንግሥትን ለመገልበጥ ሞክሯል ወይም የሀገር ክህደት ወንጀል ፈጽሟል ተብሎ ይከሰሳል። አንድ ጋዜጠኛ በጻፈው ጽሑፍ ወይም አንድ ፖለቲከኛ ባደረገው ንግግር "እገለበጣለሁ" የሚል መንግሥት ምን ዓይነት የህዝብ ድጋፍ ያለው መንግሥት ቢሆን ነው? የሚል ጥያቄን ያጭራል። በአንድ ወቅት አንድ የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለሥልጣን “የሾላ ፍሬ መሰልናችሁ እንዴ በድንጋይ የምታወርዱን” ያሉት ትክክለኛ አባባል ነው። በተጨማሪም የወንጀሎች ሁሉ ቁንጮ በሆነው በዘር ማጥፋት ሙከራ ወንጀል በዓለም እስከ ዛሬ ክስ የተመሠረተው በሀገሩ መንግሥት ስሌት ከአንድ ሚሊዮን ህዝብ በላይ በተጨፈጨፉባት ሩዋንዳ ቢሆንም ተመሳሳይ ክስ የተመሠረተው በዘሩ ወይም በኃይማኖቱ ምክንያት አንድም ሰው ባልሞተባት ሀገራችን ነው።

 

በሀገራችን በዚያ በአሰቃቂው የቀይ ሽብር፣ የግድያ፣ ፈንጠዝያ (Orgy) ወቅት እንኳ አንድን ዘር ወይም ኃይማኖት ተከታዮችን ለማጥፋት ተብሎ የተካሄደ ጭፍጨፋ የለም። የጭፍጨፋው መንስኤ የፖለቲካ ልዩነት ሲሆን፣ ይህ ደግሞ የዘር ማጥፋት ወንጀል (Genocide) ሳይሆን በቅጣት ደረጃ ልዩነት ባይኖራቸውም በሰው ዘር ላይ የሚፈጸም ወንጀል (Crime Against Humanity) ነው። የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ከዓለም አቀፍ የዘር ማጥፋት ወንጀል ኮንቬንሽን ጋር እንደሚጣረስ ጠቅሰን እናልፈዋለን። ቀደም ሲል አለቃዬ የነበሩት የሩዋንዳና የዩጎዝላቪያ ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ዋና ዓቃቤ ሕግ ወ/ሮ ሉዊዝ አርቡር በቃሊቲ ‘ቆይታዬ’ ጊዜ ሊጎበኙኝ ቃሊቲ ድረስ መጥተው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን አግኝተው ተመስርቶብን የነበረው የዘር ማጥፋት ሙከራ ወንጀል ክስ ምን ያህል አስቂኝ (በራሳቸው ቋንቋ “Ludicrous”) መሆኑን እንደነገሯቸው አጫወቱኝ።

 

እነዚህን ሁሉ ልጠቅስ የፈለግሁት እንደዚያ ይከበር የነበረው ሕግና ዳኝነት እንዴት እንደተዋረደ፣ ፍትሃዊነት እንዳሽቆለቆለ ለማስገንዘብ ነው። ይህም ሲባል ዛሬም ቢሆን ለኅሊናቸው የተገዙ፣ የተሰጣቸውን ክቡር ኃላፊነት ተገንዝበው ሕጉንና ማስረጃ ብቻ በማገናዘብ ፍርድ የሚሰጡ ዳኞች የሉም ማለት አይደለም። በአንፃሩ ደግሞ ኅሊናም ሆነ ፈሪሃ እግዚአብሔር የማይገድባቸው፣ እግዚአብሔርን በገንዘብ፣ ኅሊናቸውን ደግሞ በበላይ ትዕዛዝ የሸጡ ዳኞች ፍርድ ቤቶችን እንዳጣበቡ ይነገራል።

 

በአገራችን ከብዙ ጊዜ ጀምሮ ተጠራቅሞ ቆይቶ የነበረው ፍትሃዊነትና ሕግን ማክበር ተንኖ የጠፋው በዋናነት ባለሥልጣናቱ ለሕግ ባላቸው ንቀትና በዳኞች ንቅዘት ቢሆንም፤ ለሕግ የሚሰጠው ደንታ ቢስነት መላው ኅብረተሰቡን እያጥለቀለቀው ነው። በሙስና እንደተጥለቀለቀች የሚነገርላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እንኳ ሌላ ሌላውን ትተን ሙስና ኃጢኣት መሆኑን አስገንዝባ አታውቅም።

 

በየቀኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የህዝብ ገንዘብ ሲዘረፍ፣ በዓለም ተመሳሳይ የማይገኝለት በብሔራዊ ባንክ የተቀመጠ ወርቅ ብረት ሆኖ ሲገኝ፣ ይሉኝታ ነውርና ሃፍረት ጠፍተው ሰዎች የቀለበት መንገድ ብረት እየቆረጡ ቢላዋ ቢሠሩ ምን ይደንቃል?

 

3. መደምደሚያ

ሀ. የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል ህዝቡ በሕግ ላይ አመኔታ፣ በዳኞች ላይ እምነት፣ በጠቅላላው ፍትህ እንደሚገኝ ማመን አለበት። ይህም ማለት ህዝቡ በጠቅላላውና የበታች ባለሥልጣናት በመንግሥት ላይ አመኔታ እንዲኖራቸው ይገባል ማለት ነው። ይህ ማለት መንግሥትና የመንግሥት ባለሥልጣናት ንጹሕና ሐቀኛ ሕግ አክባሪ መሆን ብቻ ሳይሆን መስለውም መታየት አለባቸው። በፍትህ ላይ ያለው እምነት በመሟጠጡ “ተጣጥሮ ተከሳሽ መሆን ነው” የሚል የምጸት ቃል ሰዎች ሲናገሩ ይደመጣል ወይም በቶሎ የህዝብን ገንዘብ ቦጨቅ ቦጨቅ አድርጎ ከሀገር መውጣት ወይም ከመንግሥት ሥራ መላቀቅ ነው። በተለይ በመንግሥት ላይ እምነት ከሌለ አስር ፀረ-ሙስና ሕግ ቢያዥጎደጉዱ ጠቀሜታው እምብዛም ነው።

 

ለ. በስብርባሪው የፍርድን ሥራ ስንገመግም የዳኞች ሥነ-ምግባር ወሳኝነት እንዳለው ግልጽ ነው። ምግባረ ብልሹ ዳኛን ለኅሊናውና ለሕግ እንዲገዛ ማድረግ በጣም አስቸጋሪ ነው። በመሠረቱ አንድን ሰው ሐቀኛነት፣ ጨዋነትና እውነተኛነትን ማስተማር አይቻልም። እነዚህ እሴቶች ከአስተዳደግ፣ ከቤተሰብ፣ ከአካባቢው የሚገኙ ቢሆንም እሴቶቹ በመኖራቸው ግን ማስተማር ይቻላል። ስለዚህ የወደፊት ዳኞች ሕግ በሚማሩበት ወቅት የሕግ ሥነ-ምግባር (Legal Ethics) በካሪኩለም አካትቶ የመልካም ሥነ-ምግባር እውቀትን ማስታጠቅ ይገባል።

 

ሐ. ሰዎች የግሪኩ ፈላስፋ አሪስቶትልን “መቼ ነው በአቴና (ግሪክ አገር ውስጥ) ፍትሕ የሚኖረው?” ብለው ጠየቁት። አሪስቶትልም “በአቴና ፍትሕ የሚኖረው ያልተበደለው ሰው ልክ እንደተበደለው ሰውዬ ጥቃቱ ሲሰማው ነው” ብሎ መለሰላቸው። ስለዚህ በሀገራችን ፍትህ እንዲኖር ከተፈለገ ‘በእኔ አልደረሰም’ ብሎ በመንግሥት፣ በፍርድ ቤቶች፣ በግለሰቦች ሕግ ሲጣስ ችላ ማለት “ነገ - በእኔ” ከመሆኑም በላይ በጠቅላላው ሥርዓተ አልበኝነትና ወንጀል ይስፋፋል።

 

መ. የኢትዮጵያ ህዝብ ኃይማኖተኛ ነው። በቤተክርስቲያንም ሆነ በመስጅድ የሚነገሩ ነገሮች ከፍተኛ ክብደት ይሰጣቸዋል። ስለዚህ ቤተክርስቲያናትና መስጅዶች እራሳቸውን ከብልሹ ተግባር አጽድተው ባለሥልጣናቱ ከሙስናና ከአድሏዊነት እንዲታቀቡ መስበክ ይገባቸዋል።

 

የፍትህን ጉዳይ ወዲህ ብንንጠው ወዲያ ሕግ እንዲከበር ከተፈለገ መሠረታዊ ቁልፉ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መሥርቶ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ነው። መንግሥት በህዝብ ተቀባይነት እንዲኖረው ማድረግ ነው። ህዝብ በፈቃዱ ሳይገደድ የመረጠው መንግሥት የሚያወጣው ሕግ በግድ ከተጫነበት ሕግ በላይ በህዝቡ ተቀባይነት እንዳለው የሚያከራክር አይደለም። አንድ ምሳሌም መጥቀስ ይቻላል። በምርጫ 97 መባቻ ብዙ ሰዎች የቅንጅት አመራሮችን በአካል እየቀረቡን “በምርጫ ያሸነፋችሁትን አዲስ አበባን ተረከቡ። ኢህአዴግ የአዲስ አበባ የገንዘብ ምንጭ ወደ ሌላ የመንግሥት አካል ቢያዘዋውርም እኛ ቀረጥ እጥፍ ከፍለን እናካክሰዋለን” ይሉን ነበር። የህዝብ ፈቃድ ካለ ተራራን መናድ ይቻላል። ተደርጓልም።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!