ቅዳሜ ጁላይ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በምእራብ ካናዳዋ ውብ ከተማ ቫንኩቨር በተካሄደ የኢሳት የማስተዋወቂያና የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ከሚጠበቀው በላይ ድጋፍ ማግኘታቸውንና የተሳካ ዝግጅት ማድረጋቸውን የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ገለጹ።

 

በዚሁ ከቀኑ 3 ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት በተካሄደው ዝግጅት ላይ ከሰላሳ በላይ በአካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የተገኙ ሲሆን መቶ አስር የቶምቦላ ቲኬቶች መሸጣጨውንና 27 ሰዎችም በወር ከ10 ብር እስከ 30 ብር በማዋጣት መደበኛ የኢሳት ስርጭት ባለቤቶች ለመሆን መመዝገባቸውንና ቅጽ መሙላታቸውን አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

 

በዝግጅቱ ላይ ኢሳት ከዚህ በፊት ያስተላለፋቸውና ሌሎች ተያያዥ አጫጭር ቪዲዮዎች የቀረቡ ሲሆን፣ በዕለቱ ንግግር አቅራቢ የነበረው ተክለሚካኤል አበበም የተሸነፍነው በመገናኛ ብዙሀን እጦት ነው የምናሸንፈውም መገናኛ ብዙሀን መገንባት ከቻልን ብቻ ነው”በሚል ርእስ ስለሚዲያ ጠቀሜታ ሰፊ ንግግር አቅርቧል።

 

Teklemikael Abebeተክለሚካኤል አበበ የኬንያን የጀርመንን የኢትዮጵያንና የሌሎች አገሮችን ምሳሌ እያጣቀሰ ባቀረበው ንግግር ላይ “… በአመጽ ግዜ የቦሌው ከጦር ሀይሎች ጋር የመርካቶው ከኮተቤው ጋር የመገናኛው ከቃሊቴ ጋር አይገናኘም። ስለዚህ ተሸነፍን። የሽንፈታችንን የመገዛታችንን ሂደት ብንመለከተው ያጣነው ነጻና አስተማማኝ የመገናኛ ብዙኀንን አገልግሎት ነው። የሚያምጽ አላጣንም። የሚሰለፍ አላጣንም። የሚመርጥም አላጣንም። የሚከተለም አላጣንም። ያጣነው የሚከተለንንና የሚያምጸውን ርስ በርሱ የምናገናኝበትና የምናነቃበት መሳሪያ ነው። ሕወሀት/ኢህአዴግ ያሸነፈን በመገናኛ ብዙኀን ነው። የምናሸንፈውም በመገናኛ ብዙሀን ነው። ሰላማዊ ትግሉም ይሁን የጠብ መንጃው ትግል አስተማማኝ መገናኛ ብዙሀን ካላስቀደሙ ህዝቡም በየእለቱ ተስፋውን የሚያለመልምና ልቡን ወደኛ የሚያስከዳ፤ መተማመንን የሚፈጥርበት ተስፋን የሚመግበው መገናኛ ብዙሀን ካልገነባን ድል የለም።” ብሎ ተናግሯል።

 

ይሄንን ንግግር ተከትሎ በዝግጅቱ ላይ የተገኙ ኢትዮጵያዊያን ሰፊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፣ ሁሉም አስተያየት ሰጪዎች በኢሳት መወለድ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ኢሳትን እንደራሳቸው ልጅ በማየት መኮትኮትና ማሳደግ እንዳለባቸው ተናግረዋል። በተለይ ስሟ እንዳይጠቀስ የፈለገች አንዲት ሴት “እስካሁን በተግባር የሚታይ ስራ አንጡ ስንል ከርመናል ኢሳት አንድ የሚታይ እርምጃ ነውና የምግብ ችጋር ሳይሆን የመረጃና የነጻነት እጦት እየፈጀው ያለውን ህዝብ ለማስረደሰት ሁላችንም የበኩላችንን እናድርግ” ብላለች። ይሄንን ዝግጅት ኃላፊነት ወስዶ ያስተባብር የነበረው አቶ ኦሪዮን መንግስቱም ላልተወሰነ ግዜ የቫንኩቨርን የኢሳት ደጋፊዎች በአገናኝ መኮንንነት እንዲያገለግል ተወክሏል።

ነጻ ተመልካች ከቫንኩቨር ካናዳ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!