Prof. Mesfin Woldemariamመስፍን ወልደማርያም (ፕ/ር) - ሚያዝያ 2000

ምርጫ የነፃ ሕዝቦች መግለጫ ነው፤ ነፃ ሕዝቦች የአገራቸውንና የመንግሥታቸው ባለቤቶች ናቸው፤ ስለዚህም ምርጫ የአገራቸውና የመንግሥታቸው ባለቤትነታቸውን የሚያረጋግጡበት ዘዴ ነው። በአንፃሩ ደግሞ ነፃ ላልሆኑ ሕዝቦች ምርጫ ለሕዝቡ ፋይዳ የሌለውና የገዢዎቹን ጅራፍ ለመጎንጎኛ የሚያገለግል እጅ መንሻ ነው፤ በአፍሪካ ምርጫ የሚባለው የሁለተኛው ዓይነት ነው።

 

በቅርቡ በአፍሪካ ምርጫዎች የሚባሉ እንቅስቃሴዎችን እየታዘብን ነው። በኬንያ፣ በዚምባብዌና በግብፅ። ስለኢትዮጵያ አልናገርም - በአንድ የጎንደሬ የሠርግ ዘፈን ልለፈው። የጎንደሬው የሠርግ ዘፈን አውራጅና ተቀባይ አለው፤ አውራጁ ባንድ ጎጆ ሲል ተቀባዮቹ እህ ዛዲያማ እያሉ ይገፋፋሉ፤ አንድ ቁርንጮ ይነጠፍና ብሎ ይቀጥላል አውራጁ፤ ተቀባዮቹ እህ ዛዲያማ! እህ ዛዲያማ! ሲሉት የሚቀጥለውን በማለት ይደመድምላቸዋል …

 

እህ ዛዲያማ ምን ልንገራችሁ፣

ታውቁት የለም ወይ በየቤታችሁ!

 

Prof. Mesfin Woldemariamበኬንያ የአፍሪካ ምርጫ ተካሂዶ በሥልጣን ላይ ያለው ቡድን የሕዝቡን ድምጽ በጉልበት ለወጠው ተብሎ ሕዝብ ተቆጣ፣ ቁጣው ወደ ጎሣ ግጭት ተለወጠ። ከአንድ ሺህ በላይ ሰዎች ተገዳደሉ፤ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ንብረት ወድሞ ስደተኞች ሆኑ። በረብሻው ጊዜ አንድ የቢቢሲ ጋዜጠኛ አንዱን ኬንያዊ ሲያነጋግረው “ይህ ኢትዮጵያ አይደለም፤ የሕዝብ ድምጽ አይዘረፍም” ሲለው ሰምቼ አፍሬያለሁ። ይህ ሁሉ ሲሆን አሸናፊነቱን ቀማ የተባለው ባለጉልበት አንዳችም መጠራጠር ወይም አንዳችም ጸጸት አላሳየም። የጋናው ፕሬዝዳንትና የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ወደ ናይሮቢ መጡ፤ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩዋ ተመላለሱ፤ የደቡብ አፍሪካ ታላላቅ ሰዎች ሊሸመግሉ ሞከሩ ሁሉም አልሆነም።

 

በመጨረሻ የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን የምዕራባዊያንን ሁሉ ጫና በሻንጣቸው ተሸክመው ደረሱና ትንሽ ወደማስማማቱ ያደረሷቸው መሰለ። ሰሞኑን የሚሰማው ግን ሁለቱ ተቀናቃኞች በሥልጣን ክፍፍሉ አለመስማማታቸውና የጎሣ ግጭቱ ሊያገረሽ እንደሚችል ነው። የሕዝብ ስቃይና መከራ፤ ኀዘንና ጭንቀት ዋጋ የለውም። የኬንያ ፖሊስና የጦር ሠራዊት በአጠቃላይ ሲታይ የግጭቱ ተካፋይ አለመሆኑ የሙያ ብቃቱን ያመለክታልና የሚያስመሰግናቸው ነው።

 

ቀጥሎ ደግሞ በዚምባብዌ ሌላ የአፍሪካ ምርጫ ተካኼደ። ሕዝቡ ግልብጥ ብሎ ወጣ፤ የምርጫ ኮሚሽን የተባለው ውጤቱን ለሕዝብ በመግለጽ ፈንታ እያንጠባጠበ መደልደል ጀመረና አብዛኛውን የተወካዮች ምክር ቤት ወንበር ተቀናቃኙ ቡድን ማሸነፉ ሲታወቅ ገዢው ቡድን መርበድበድ ጀመረ። ለፕሬዝዳንቱ ወንበር የተሰጠው ድምጽ ታፍኖ ለአንድ ሣምንት እንዲቆይ ተደረገ። ተቀናቃኙ ቡድን ለፍርድ ቤት አመለከተ፤ የፍርድ ውሳኔ ጊዜን ፈጀ። ሆኖም ገዢው ቡድን ገና የምርጫ ኮሚስዮኑ ውጤቱን ሳይገልጽ አንዳንድ የኮሚስዮኑን ሠራተኞች ለተቀናቃኝ ቡድኑ አድልተዋል በማለት እየወነጀለ ፕሬዚዳንታዊው ምርጫ እንደገና እንዲደረግ እየጠየቀ ነው። በዚህም ይፋ ያልወጣውን ውጤት ማወቁንና መሸነፉን የተረዳ ይመስላል። ጉዱ ገና ነው።

 

ሰሞኑን በግብፅ ሌላ የአፍሪካ ምርጫ እየተካሄደ ነው። ይህ ደግሞ ገና ከአጀማመሩ ለመራጭም ሆነ ለተመራጭ ግድ የሌለው መሆኑን እያሳየ ነው። አንዱን ተቀናቃኝ ቡድን ከሃያ አንድ በላይ ተመራጮችን እንዳያቀርብ ከለከሉት። … ከምጣዱ ያስታውቃል እንደሚባለው ነው።

 

እንግዲህ የአፍሪካ ምርጫ የሚባለው በአሜሪካና በአውሮፓ አገሮች ከሚደረገው ምርጫ ጋር ምንም የዘርም ሆነ የባህል ግንኙነት የለውም ማለት ነው። ምዕራባውያን የአፍሪካ ምርጫ የሚሉት እነሱ ከሚያደርጉት ምርጫ በዓይነትና በዘር የተለየ መሆኑን ለማመልከት ነው። የቀደመው የትኛው የዘር ልዩነት ነው፤ በአፍሪካውያንና በአፍሪካ ምርጫ መሀከል ያለው የዘር ልዩነት ይቀድማል የቀደመውን ቀጥሎ ለመጣው ምክንያት ማድረግ ከተቻለ የአፍሪካ ምርጫ ከሰዎቹ ዘር ጋር የተያያዘ ነው ለማለት እንገደድ ይሆናል። ይህንን ከተቀበልን አፍሪካውያን በተፈጥሮ ለጉልበት እንጂ ለነፃነት፣ ለእውነት፣ ለፍትህና ለእኩልነት ፋይዳ አይሰጡም ወደሚል መደምደሚያ ልንደርስ ነው። ይህ የነጭ ዘረኞች አቋም ነው፤ ምን ተጨባጭ እውነት ይዘን ነው ልንቃወመው የምንችለው፣ አሳፋሪ ነው።

 

የዘረኛ ነጮችን አስተሳሰብ ከመቀበል የሚያድነን አንድ ወልጋዳ ዘዴ ያለ ይመስለኛል። የአፍሪካ ሕዝቦችና ገዢዎቻቸው አንድ ዘር መሆናቸውን መካድ ይኖርብናል። ምን ጊዜም ቢሆን ክህደት አጉል ደባልነትን ይፈጥራልና ይህ ክህደት ከነጭ ዘረኞች ጋር አብረን እንድንቆም ያደርገን ይሆናል፤ ግን እኛ ተራ አፍሪካውያን ለጉልበት ሳይሆን ለነፃነት፣ ለእውነት፣ ለፍትህና ለእኩልነት ፋይዳ የምንሰጥ ሰዎች መሆናችንን ያረጋግጥልን ይሆናል። ልፋ ያለው በሕልሙ ዳውላ ይሸከማል ይባላል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!