ግርማ ካሣ (ከቺካጎ)

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከቃሊቲ ከተፈታች ሶስት ሳምንታት አልፈዋታል። ከቤተሰቦቿ ጋር ለማሳለፍና በፓርቲዋ እንዲሁም በአገር ቤት ያለውን ሁኔታ የበለጠ ለመመርመር ይረዳት ዘንድ፣ ትንሽ የራሷን ጊዜ በመውሰዷ ለጊዜው ብዙ አንሰማትም።

 

እንደዚያም ሆኖ ግን በርሷ ዙሪያ የሚነሱ የተለያዩ ጉዳዮች ኢትዮጵያውያንን በማነጋገር ላይ ይገኛሉ። ለምሳሌ ያህል በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌዴረሽን፣ ከዘጠኝ ወራት በኋላ አትላንታ በሚደረገው ዝግጅቱ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ለመጋበዝ ከወሰነ በኋላ መሰረዙን ተከትሎ የተነሳውን ውዝግብ መጥቀስ ይቻላል። ፌዴሬሽኑ በድህረ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ ከፖለቲካ ነጻ እንደሆነ ገልጾ፣ የፖለቲካ ሰው ናት የሚላትን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ለመጋበዝ የፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንቡ እንደማይፈቅድለት ያስረዳል።

 

ይህን የፌዴሬሽኑ ውሳኔ የማልስማማበት እንደሆነ በቅድሚያ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ። አስፈላጊ ከሆነ ለምን እንደማልስማማ ወደፊት በሰፊው የምመለስበት ጉዳይ ሊሆን ይችላል። አሁን ግን አንዳንድ የማይጠቀሙ ነገሮች እያየሁ ስለሆነ በነርሱ ላይ ትንሽ ማተኮር እፈልጋለሁ።

 

ፌዴሬሽኑ በርግጥ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ የሚያሰባስብ ከፖለቲካ ፓርቲ ተጽእኖ ነጻ መሆን ያለበት ድርጅት ነው። ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የፈለገ የፖለቲካ አቋም ይኖረው፣ ፌዴሬሽኑ በሚተክለው የኢትዮጵያውያን ድንኳን የመግባትና የመሰባሰብ ሙሉ መብት አለው። በመሆኑም ፌዴሬሽኑ ይህንን የፖለቲካ ገለልተኛነቱን ለመጠበቅ፣ ኢትዮጵያውያኖችን ሁሉ ለማቀፍ የሚወስዳቸውን አቋሞችና እንቅስቃሴዎች መረዳት ያለብን ይመስለኛል። ቅንነት ይኑረን ማለቴ ነው።

 

ስም እየጠቀሱ፣ የፌዴሬሽኑ አባላት ለወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከበሬታ እንደሌላቸው መናገርና መክሰስ ተገቢ አይመስለኝም። የድል ቀን አርበኞች እንደሚባለው፣ ዛሬ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ስትፈታ የርሷ ተቆርቋሪና አጃቢ መስሎ ለመታየት ብቅ ብቅ ያሉ በበዙበት ጊዜ፣ አንዳችን ለብርቱካን ተቆርቋሪ፣ ሌላው ደግሞ የብርቱካን ጠላት እንደሆነ ማውራት ትንሽ የሚያስቸግር ይመስለኛል።

 

የፌዴሬሽኑ አባላት ከማናችንም ያልተናነሰ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ለከፈለችው ታላቅ መስዋዕትነት ትልቅ ከበሬታ ያላቸው፣ ከማናችንም ያልተናነሰ ለርሷ መፈታት በፊናቸው የጣሩና የሰሩ ወገኖቻችን ናቸው። ዛሬ የፌዴሬሽኑ አመራሮች ከፖለቲካ ገለልተኛ መሆን አለብን የሚለውን እምነታቸውን ከመለጠጣቸው የተነሳ ስህተት ቢሰሩም፣ ትላንት የሰሩት ጥሩ ሥራ ተሰርቶ ውርዥብኝ ሊወርድባቸው አይገባም።

 

ፌዴሬሽኑ እንደ ማንም ድርጅት ስህተቶች ይሰራል። ነገር ግን ፌዴሬሽኑን ከማውገዝና ከመክሰስ በፊት ማነጋገር፣ ያለውን ሁኔታ በሚገባ መረዳት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። የቀረቡትን ምክንያቶች በሰለጠነ መልኩ ቻሌንጅ በማድረግ፣ ነገሮች በተለየ ማእዘን እንዲታዩ ማድረግ ይቻላል። ሁሉም አሸናፊ የሆነበትን፣ የሁሉንም ቅሬታና ጥያቄ በሚመልስ መልኩ፣ ይህ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ዙሪያ የተነሳውን አለመግባባት በሰላምና በንግግር ማንፈታበት ምንም ምክንያት የለም።

 

ለወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መፈታት ብዙም ትሁን ትንሽ ጥረት ሲያደርጉ ከነበሩ አካላት መካከል አንዱ የብርቱካን ትፈታ ግብረ ኃይል ነው። ከዚህ ግብረ ኃይል ጋር የመስራት እድል አግኝቻለሁ። ግብረ ኃይሉ በሳን ሆዜ የኢትዮጵያውያን እግር ኳስ ውድድር ወቅት፣ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መታሰር የፖለቲካ ጉዳይ ሳይሆን የሰብዓዊነት ጉዳይ እንደሆነ ለፌዴሬሽኑ በማስረዳት፣ በዚያን ወቅት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲያደርግ እንደነበረ በስፍራው የነበሩ ሲመስክሩ ሰምቻለሁ።

 

ይህ የብርቱካን ትፈታ ግብረ ኃይል ከፌዴሬሽኑ ያልተቆጠበ ትልቅ ድጋፍ እንደተደረገለት፣ በርግጥ የፌዴሬሽኑ አመራር አባላት ለወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ትልቅ ፍቅር እንዳላቸው ያኔ በሥራቸው እንዳሳዩ ነው የሰማነው።

 

ሌላው መዘንጋት የሌለብን ነገር ደግሞ ፌዴሬሽኑ ማለት እኛ ማለት እንደሆነ ነው። የፌዴሬሽኑ ቦርድ አባላት በየከተማው ያሉ ቡድኖች የመረጧቸው ኢትዮጵያውያኖች ናቸው። በፌዴሬሽኑ ያለው ችግር የእያንዳንዳችን ችግር ነው። አንዳንዴ ስሜትና እልህ እየተጨመረ አንዳንድ ጥቃቅን አለመግባባቶቻችን ሊከሩ ይችላሉ። አንዱ ወደ ቀኝ ሌላው ወደ ግራ ሲጎትቱት፣ ገመዱ ይበጠስና ሁላችንም ልንጎዳ ስለምንችል መጠንቀቅ ያለብን ይመስለኛል።

 

ይህ ፌዴሬሽን፣ እስከነ ችግሮቹ፣ በሰሜን አሜሪካ ያለን ብቸኛ፣ ኢትዮጵያውያንን የሚያሰባሰብ አካል ነው። ልንከባከበው ይገባል። ከዳንኪራና ከስፖርት ባለፈ መልኩ፣ ኢትዮጵያውያንን ለቁም ነገር የሚያነሳሳ፣ በኢትዮጵያ የወገናችንን ሕይወት ለመለወጥ ትልቅ ራእይ ይዞ የሚንቀሳቀስ አካል እንዲሆን፣ ከዚህ ፌዴሬሽን ጀርባ ልንሰለፍ ይገባል። ይህ ፌዴሬሽን ብዙ ሊያደርግ የሚችል ፖቴንሻል ያለው አካል ነው። እንደግፈው እናጠናክረው እንጂ አናፍርሰው።

 

በዚህ አጋጣሚም በወሰዱት ውሳኔ ባልስማማም፣ መልሰው ውሳኔያቸውን እንደሚመርምሩ ያለኝን ትልቅ እምነት በመግለጽ፣ ለሁሉም የፌዴሬሽኑ ቦርድ አባላት፣ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ያለኝን ምስጋናና አክብሮት መግለጽ እወዳለሁ። «እየሰጣችሁት ላለው አገልግሎት እግዚአብሔር ያክብራችሁ፣ እግዚአብሔር ይስጣችሁ» እላለሁ። ኢትዮጵያውያን በያለንበት ልናበረታታቸውና ከጎናቸው ልንቆም ይገባል።


ግርማ ካሣ (ከቺካጎ)

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

ጥቅምት 15 ቀን 2003 ዓ.ም.

ኦክቶበር 25 ቀን 2010

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!