ክንፉ አሰፋ (ከአምስተርዳም)

“በዋሽንግተን ዲ.ሲ. እየተካሄደ ያለው የኢትዮጵያውያን ስፖርትና ባህል ፌዴሬሽ በዓል ሦስተኛ ቀኑን ይዟል። እኔ እዚህ አለሁ፣ ተጫዋቾቹም እዚሁ አሉ፣ ግን ህዝቡ የት እንደገባ ለማወቅ ጓጉቻለሁ።” ስትል ነበር አሜሪካዊቷ ጋዜጠኛ አሊሻ ፔተርሰን የ2008ቱን የዋሽንግተን ዲ.ሲ. የፌዴሬሽኑን ውድቀት የዘገበችው። ፔተርሰን “ሰው ሁሉ የት ገባ?” ብላ ለጠየቀችው ጥያቄ ምላሽም በዘገባዋ አካትታለች። በዓሉ ከኢህአዴግ መንግሥት ጋር ቁርኝት ባለው በሼክ አላሙዲ ስለተደጎመ በህዝቡ “ቦይኮት” እንደተደረገ በቪዲዮ የተደገፈ ምስል ጋር ቀርቧል።

 

የኢትዮጵያ ስፖርትና ባህል ፌዴሬሽን በሰሜን አሜሪካ እ.ኤ.አ. በ2008 ዓ.ም. ከሼክ አላሙዲ ሦስት መቶ ሺህ ዶላር በመቀበሉ ምክንያት በዋሽንግተን ዲ.ሲ. ላይ ብዙ ዋጋ መክፈሉ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። በወቅቱም እንደተዘገበውም ይህ ተቋም ለሦስት መቶ ሺህ ዶላር ሲል ሦስት መቶ ሺህ ህዝብ ነበር ያጣው። ፌዴሬሽኑ 25ኛ ዓመቱን በዋሽንግተን ዲ.ሲ. ሲያከብር ዝግጅቱ ምን ያህል ደማቅ ሊሆን እንደሚችል የገመቱት በርካታዎች ነበሩ። ዲ.ሲ. ኢትዮጵያውያን በብዛት የሚኖሩበትና በዓሉ የብር ኢዩቤልዩ በመሆኑ በቀን ቢያንስ መቶ ሺህ ሰው ተጠብቆ ነበር።

 

እውነታው ግን እንደዛ አልነበረም። ሜዳው ባዶ ነበር ማለት ይቀላል። ከሰሜን ጫፍ እስከ ደቡብ፣ ከም እራብ እስከ ምስራቅ እንደጨው የተበታተነውን ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሚያሰባስበውን ይህን ማእከል በብር እዩቤልዩ ክብረ-በዓሉ እንደዚያ ተዳክሞ ስናየው ብዙዎችችንን እጅግ በጣም አሳዝኗል። 25ኛውን የብር ኢዮቤልዩ በዓል በዚያ እጅግ በተዳከመ ሁኔታ ካከበረ በኋላ ፌዴሬሽኑ በታዳሚውም ሆነ በበዓል ዝግጅቱ እየቀዘቀዘ ከመምጣቱ አልፎ ዛሬ ከምንገኝበት፣ የብዙሃኑ ድምፅ በሁለትና ሦስት ግለሰቦች የሚሻርበት ደረጃ ላይ ደርሷል።

 

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ወይዘሪት ብርቱካን በአትላንታ ለሚደረገው ዝግጅት የፌዴሬሽኑ የክብር እንግዳ ለምን አልሆነችም? የሚለውን ጥያቄ ላማንሳት ውይንም ለመከራከር አይደለም። በርግጠኝነት ላመናገር በፌዴሬሽኑ በክብር እንግዳነት መጋበዟ ለብርቱካን የሚጨምርላት አንዳች ነገር የለም። አለመጋበዝዋም ምንም አይቀንስባትም። የአውሮፓ ህብረት የሳካሮቭ እጩ ተሽላሚ ያደርጋት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጩ ዓለም ታላቅ ዝናንና ክብርን የተቸረች የህዝብ መሪ ናት ብርቱካን። ይልቁንም ወ/ት ብርቱካን በአትላንታ ተጋብዛ ብትገኝ ኖሮ ለፌዴሬሽኑ ታላቅ ክብር ይሆናል።

 

የአብዛኛው ድምፅ ከሦስት በማይበልጡ በአንባገነኖች ሲገለበጥ ዝም ብሎ የማየት ሞራል ግን ሊኖረን አይገባም። በፌዴሬሽኑ አባላት አጠቃላይ ጉባኤ በአብዛኛው ድምፅ ያለፈው ውሳኔ በግለሰቦች ከተሻረ በኋላ በፌዴሬሽኑ ድረ-ገጽ ላይ የተለጠፈው መግለጫ ደግሞ የበለጠ የሚያበሳጭ ነው። አስቸኳይ ብሎ ፌዴሬሽኑ በድረ-ገጹ የለጠፈው መግለጫ በከፊል እንዲህ ይነበባል፣ “There was a nomination on the floor, a vote was taken and Judge Birtukan’s nomination narrowly passed.” "ዳኛ ብርቱካን በእጩነት ቀረበች፣ ድምፅ ተሰጠ፣ ቤቱ በጠባብ ድምፅ ብልጫ ብርቱካንን አሳለፈ።" ይላል እንግሊዝኛው በወጥ ሲተረጎም። መግለጫው ይቀጥልና የተውሰኑ የፌዴሬሽኑ ቀደምት አባላት ውሳኔው እንዲቀለበስ ባቀረቡት ሃሳብ መሰረት ውሳኔው መሻሩን ይገልጻል።

 

ይህ የሰሜን አሜሪካ ተቋም ላለፉት 27 ዓመታት ሲተዳደርበት የነበረው ደንብ፣ ሥርዓትና በአብላጫ ድምፅ የተደገፈ ውሳኔ እንዲህ እንደዋዛ በሁለትና በሦስት ሰዎች ሲፈርስ ዲያስፖራውን በእጅጉ አስቆጥቷል። ይህን መሰል መግለጫ በፌዴሬሽኑ ድረ-ገጽ ላይ መለጠፉ ደግሞ አባላቱን ብቻ ሳይሆን ታዳሚዊንም ህዝብ መድፈርና መናቅ ነው መስሎ ነው የታየው።

 

እዚህ ላይ የበለጠ ትኩረት የሳበው ደግሞ የብዙሃኑ ውሳኔ በግለሰቦች መቀልበሱ ብቻ ሳይሆን ፌዴሬሽኑ በተደጋጋሚ ሲታማበት የነበረው ጉዳይ ገሃድ መውጣቱ ነው። በብዙሃን ድምፅ የጸደቀ መመሪያን ሁለት እና ሦስት ሰዎች ማፍረስ ከቻሉ ተቋሙ ከጅምሩም በተደጋጋሚ ሲባል እንደነበረው በሙስና የተዘፈቀና ዲሞክራሲያዊ ያልነበረ መሆኑን ነው የምንረዳው።

 

“ፌዴሬሽኑ ለበርካታ ዓመታት ኦዲት ተደርጎ አያውቅም። … ከቀድሞ አመራሩ ቢያንስ ሁለቱ ግድያ ሙከራ በማድረግ ወንጀል የፈለጋሉ” ... ወዘተ የሚሉትን ዘገባዎች ለግዜው እንተዋቸውና የብዙሃን አባላቱ ድምፅ በነዚሁ ተጠርጣሪዎች መረገጥ ጉዳይ ላይ እናተኩር።

 

ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ በሚል ስም ከላይ የተጠቀሱት ግለሰቦች ድርጊትን በመደገፍ ሲጽፍ ለመከራከሪያ ያቀረበው የህግ አነቀጽ እንዲህ ይላል፣

 

“Under the Internal Revenue Code, all section 501©(3) organizations are absolutely prohibited from directly or indirectly participating in, or intervening in, any political campaign on behalf of (or in opposition to) any candidate for elective public office. Contributions to political campaign funds or public statements of position (verbal or written) made on behalf of the organization in favor of or in opposition to any candidate for public office clearly violate the prohibition against political campaign activity.

 

ይህ በጥቅል ሲተርጎም “በሃገር ውሰጥ ገቢ አንቀጽ ቁጥር 3 ክፍል 501 መሰረት [ድርጅቱ] በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ማንኛውንም ፖለቲካዊ ቅስቀሳ ማድረግና ጣልቃ መግባት አይችልም ... ለፖለቲካ ስራ ገንዘብ ማዋጣት ፈጽሞ የተከለከለ ነው። ..." ይላል።

 

ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ ጽሑፉን በመቀጠልም እንደ ወ/ት ብርቱካን አይነት የፖለቲካ ሰዎችን መጋበዝ የተቋሙን ፈቃድ ሊያስነጥቅ እንደሚችልም ሊነግረን ይሞክራል። ነገሩ ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ መሰለ። ፖለቲካዊ ቅስቀሳ ማድረግ ወይንም በፖለቲካ ጉዳይ ጣልቃ መግባትና የመብት ተሟጋችን የክብር እንግዳ አድርጎ መጋበዝ እንዴት ነው የሚመሳሰሉት? በቃ ይኸው ነው? ሌላ የለም? ሌላ ከሌለ ይህ አንቀጽ እንደ ወ/ት ብርቱካን ያሉ እውቅ ሰዎችን እንዳይጋበዙ የሚከለክል አንዳች ሐረግ የለውም።

 

“ፌዴሬሽኑ የሚመራበት ደንብ ነው” የሚሉን እንደዚህ ያሉ ሰዎች የሚያቀርቡት የህግ አንቀጽና ትንተና የራሳቸውን ደገፊዎች እንኳን ማሳመን የማይችል ደካማ ምክንያት ሆኖ ነው ያገኘነው። ለሰው ልጅ መብት መከበር ሲሉ ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ ሰዎች እና በሰብአዊ ፍጡር ላይ ወንጀል እየፈጸሙ ባሉ መካከል ያለውን ልዩነት ያለማገናዘብ ችግር አለ እንበል?

 

ይህ ቁንጽል ሃሳብ በጥቅሉ የሚለን “ወ/ት ብርቱካን የፖለቲካ ፓርቲ መሪ ነች” ነው። የፊፋ ክብር እንግዳ በመሆን የተጋበዙት ኔልሰን ማንዴላም 'ኮ የኤ.ኤን.ሲ. መሪ ነበሩ።

 

ፊፋ የ91 ዓመቱ ኔልሰን ማንዴላን የዓለም ዋንጫ መክፈቻ ላይ የክብር እንግዳ አድርጎ በመጋበዝ ብቻ አላበቃም። ማንዴላ የተጋበዙበትን ምክንያት ሲገልጽ - ፊፋ እንዲህ ነበር ያለው፣ "He inspired millions with his determination to crush apartheid. Nelson Mandela will be part of another historic moment."

 

ወደ አማርኛው ሲመለስ፣ አፓርታይድን ለመደምሰስ የነበረው ቁርጠኛ አቋሙ ሚሊዮኖችን በማንቃት ተምሳሌት ሆኗል። ኔልሰን ማንዴላ አሁን እንደገና የሌላ ታሪካዊ ወቅት አካል ይሆናል። እንደማለት ነው።

 

ፊፋ አትራፊ ድርጅት አይደለም። ፊፋ የፖለቲካ ደርጀት አይደለም። የኃይማኖትም ተቋምም አይደለም። ቀደምት የደቡብ አፍሪካ መሪዎችን አይደለም የክብር እንግዳ ያደረገው ፊፋ። ‘ማንዴላ ለምን ተጋበዙ?’ ብሎ የተናገረ ሰው ነበር እንዴ? ካለስ የሞራል ብቃት ይኖረዋል?

 

ማንዴላ የክብር እንግዳ ሲሆኑ ይህ የመጀመሪያቸው አልነበረም። እጅግ በርካታ የፖለቲካና ፖለቲካዊ ባልሆኑ ስፍራዎች ላይ የክብር እንግዳ ሆነው ተገኝተዋል። እንደ ማንዴላ ያሉ ለሰው ልጆች ነጻነት ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ ታላላቅ የፖለቲካ መሪዎችም በበርካታ ማህበራዊ ስብስቦች በክብር ተጠርተው እንደተገኙ የእነ ጋንዲ፣ እነ የጄሲ ጃክሰን፣ የእነ ፕራቲያ ሃል፣ የእነ ሁርታ ዶሎርስ … ማህደር ይነግረናል። ጋንዲ ለሰው ልጅ ንጻነት ራሰቸውን አሳልፈው የሰጡ የፖለቲካ ሰው እንጂ የኃይማኖት መሪ አልነበሩም። ጄሲ ጃክሰንም እንደዚሁ። …

 

ወደ እኛ ስንመለስ፣ ፕሮፈሠር አስራት ወልደየስ በአንድ ወቅት የፌዴሬሽኑ የክብር እንግዳ ነበሩ። ለዜጎች መብት መከበር ሲሉ ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ መሪ። በአንጻሩ ደግሞ የሼክ አላሙዲን ጉዳይም አለ። ሼኩ በፌዴሬሽኑ የክብር እንግድነት ከመሆንም አልፈው የክብር አባል ሆነው ተመርጠዋል።

 

በኢንተርኔት የተለቀቀ አንድ ቪድዮ፣ አላሙዲን በትግራይ ልማት ማህበር ስብስብ ላይ በመገኘት ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል “ለመጀመሪያ ጊዜ ኢህአዴግ እንድሆን ያጠመቀኝ አምባሳደር ተወልደ ነው። ለንደን ከተማ ኢህአዴግ በገባ በሁለተኛው ወር ከአሰፋ ማሞ ጋር በመሆን ቤቴ ድረስ መጥተው አጠመቁኝ።”

 

ሼኩ እንዴትና መቼ እዚህ ዘረኛ ድርጅት ውስጥ እንደገቡ ያብራራሉ። እኝህ ሰው ኢህአዴግ መሆናቸውን በአደባባይ እየተናገሩ፣ ገንዘብ ስለሰጡ ብቻ የፌዴሬሽኑ የክብር አባል ሆነው ተመርጠዋል። ይልቁንም በዓለም ዓቀፍ ሰብአዊ ድርጅቶች እየተከሰሰ ያለ ድርጅት (ኢሕአዴግ) ቀንደኛ አባልን መጋበዝ በሞራልም ሆነ በፌዴሬሽኑ ደንብ የሚያስጠይቅ ይሆናል።

 

ፌዴሬሽኑ እንደነዚህ አይነቶችን የሚገድብ መመሪያ አለው የሚሉን ታዲያ ይህ ለምን አልታያቸውም?

 

አንዳንዶች ደግሞ ለፈለጉት ወገን የሚሰራ ለማይፈልጉትን ደግሞ የሚገድብ ደንብ የሚሉት አባዜ አላቸው። በደፈናው ብቻ ደንብ … ደንብ ... እያሉ ሊያደነቁሩን ይፈልጋሉ።

 

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት DEMOCRACY AND REGULATION በሚል ርእስ የወጣ አንድ ጥናታዊ ጽሑፍ አስቀድመው የተደነገጉ ደንቦች ተግባራዊ መሆን እንዴት እንዳልቻሉ ይተነትናል። የአብዛኛውን ህዝብ ዕለታዊ ፍላጎትና የውቅቱን ሁኔታ ማያንጸባርቁ ከሆኑ ደንቦች ተግባራዊ አይሆኑም ይለናል ዘገባው። በዚህም የተነሳ በተለይ በዩናይትድ ስቴትስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚተዳደሩት ቀድሞ በረቀቁ ውስጠ-ደንቦች ሳይሆን እለት-ተዕለት በሚከናወኑ የህዝብ ውይይቶችና ይህንንም በመንተራስ የአመራር አካላት በሚሰጡት ውሳኔዎች ነው ይላል።

 

ለማጠቃለል ያህል የወይዘሪት ብርቱካን በአትላንታ የክብር እንግድነት መጋበዝ በፌዴሬሽኑ ደንብ መሰረት ስናየው የሚጻረር ነገር አላገኘንበትም። ከዲሞክራሲ አንጻርም በአብዛኛው ህዝብ ድጋፍ ያገኝ ጉዳይ ነው። ታዲያ ውሳኔው ሊቀለበስ የቻለበት ምክንያት ምን ይሆን?

 

ልንክደው የማንችለው አንድ እውነታ አለ። ፌዴሬሽኑ የወያኔ ነው ብሎ የመደምደሙ ጉዳይ ውሃ አይቋጥርም። በድምፅ አሰጣጡ ላይ በግልጽ እንዳየነው አብዛኛው የፌዴሬሽኑ አመራር አባላት ጠንካራና ለመርህ የቆሙ ናቸው። ነገር ግን ወያኔ ይህንን ቢያንስ በይዘት ግዙፍ የሆነ ተቋም በከፊልም ቢሆን ለመቆጣጠር ትናንሽ ጣቶቹን በውስጥ አሰርጎ አላስገባም ማለት የዋህነት ይሆናል። "አክራሪ" ዲያስፖራውን ለመቆጣጠር፣ አልያም ለማጥፋት በሚሊዮኖች በጀት የመደበው ህወሃት ይህንን ተቋም በምን መልኩ ሊያየው እንደሚችል ጠንቅቀን ማወቅ ይኖርብናል።

 

ወያኔዎች ቢቻላቸው ተቋሙን ማጥፋት ይመርጣሉ። አሁን እየታየ ያለው አዝማሚያ ያን ይመስላል። ይህ እንዳይሆን ግን ሁላችንም መረባረብ ሊኖርብን የግድ ነው። "ቦይኮት" የሚባል ነገር ፈጽሞ መታሰብ የለበትም። የተቋሙ ጠላቶች የሚፈልጉት ይህንን ነው። አብዛኛው ወገን ራሱን እያገለለ ሲሸሽ አናሳዎቹ ፌዴሬሽኑን በቁጥጥር ስር ለማድረግ ሰለሚሹ "ቦይኮት"ን እንደሚደግፉት አትጠራጠሩ።

 

ይህ ተቋም ለነጋዴው፣ ለጥበብ ሰው፣ ለኃይማኖት መሪዎች፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ... ወዘተ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ መድረክ እየሆነ የሚያገለግል የዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ተቋም ነው - ፌዴሬሽኑ።

 

መፍትሄ የሚሆነው ወደሚያሰባስበን ተቛማችን በመሄድ የአጠቃላይ ጉባኤውንና የአብዛኛውን ህዝብ ውሳኔ ተግባራዊ እንዲሆን ማስገደድ ነው። አሜሪካ እንደ ዛሬዋ ኢትዮጵያ ህግ የሚቀለድባት ሃገር አይደለችም። ማንም ሰው ከህግ በላይ አይደለም። ያለው ብቸኛ አማራጭ በብዙሃኑ ድምፅ አንገዛም የሚሉትን ማሳመን፣ እንቢ ካሉ ደግሞ በህግና ሥርዓት ማስወገድ ይሆናል።


ክንፉ አሰፋ (ከአምስተርዳም)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!