ግርማ ካሣ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

”ከፌዴሬሽኑ ጀርባ ልንሰለፍ ይገባል” በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ጽሁፍ፣ እጅግ በጣም በርካታ ምላሾች በኢሜል ደረሱኝ። ኢሜሎቹ በሙሉ የተቃውሞ ኢሜሎች ናቸው። አንዳንዶቹ ከመቃወም አልፈው ስድብና ዛቻም አዝለዋል።

 

“ይህን የፌዴሬሽኑ ውሳኔ የማልስማማበት እንደሆነ በቅድሚያ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ። አስፈላጊ ከሆነ ለምን እንደማልስማማ ወደፊት በሰፊው የምመለስበት ጉዳይ ሊሆን ይችላል …. ነገር ግን ፌዴሬሽኑን ከማውገዝና ከመክሰስ በፊት ማነጋገር፣ ያለውን ሁኔታ በሚገባ መረዳት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። የቀረቡትን ምክንያቶች በሰለጠነ መልኩ ቻሌንጅ በማድረግ፣ ነገሮች በተለየ ማእዘን እንዲታዩ ማድረግ ይቻላል። ሁሉም አሸናፊ የሆነበትን፣ የሁሉንም ቅሬታና ጥያቄ በሚመልስ መልኩ፣ ይህ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ዙሪያ የተነሳውን አለመግባባት በሰላምና በንግግር ማንፈታበት ምንም ምክንያት የለም። … ይህ ፌዴሬሽን፣ እስከነ ችግሮቹ፣ በሰሜን አሜሪካ ያለን ብቸኛ፣ ኢትዮጵያውያንን የሚያሰባሰብ አካል ነው። ልንከባከበው ይገባል። ከዳንኪራና ከስፖርት ባለፈ መልኩ፣ ኢትዮጵያውያንን ለቁም ነገር የሚያነሳሳ፣ በኢትዮጵያ የወገናችንን ሕይወት ለመለወጥ ትልቅ ራእይ ይዞ የሚንቀሳቀስ አካል እንዲሆን፣ ከዚህ ፌዴሬሽን ጀርባ ልንሰለፍ ይገባል። ይህ ፌዴሬሽን ብዙ ሊያደርግ የሚችል ፖቴንሻል ያለው አካል ነው። እንደግፈው እናጠናክረው እንጂ አናፍርሰው። … በዚህ አጋጣሚም በወሰዱት ውሳኔ ባልስማማም፣ መልሰው ውሳኔያቸውን እንደሚመርምሩ ያለኝን ትልቅ እምነት በመግለጽ፣ ለሁሉም የፌዴሬሽኑ ቦርድ አባላት፣ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ያለኝን ምስጋናና አክብሮት መግለጽ እወዳለሁ …“ (ከፌዴሬሽኑ ጀርባ ልንሰልፍ ይገባል ከሚለው ጽሁፍ የተወሰድ)

 

በዚህ ጽሁፍ አንዳንድ ወገኖች ምን ሊያስከፋቸው እንደቻለ በርግጥ ሊገባኝ አልቻለም። በሰለጠነው አለም እየኖርን የስድቡና የዛቻው ብዛት በርግጥ የሚያሳዝንና የሚያሳፋር ነው። ብዙዎቻችን ኢሕአዴግን እንቃወማለን እንላለን። ነገር ግን በምንሰራቸው ሥራዎችና ባሉን አስተሳሰቦች ከኢሕአዴግ ካድሬዎች በምንም አንደማንለይ እያሳየን ነው። በዳያስፖራ ያለው የመወጋገዝና ያለመቻቻል ፖለቲካ ኢሕአዴግ ከሚያራምደው ፖለቲካ ጋር እየተመሳሰለ ነው።

 

አንድ ሰው ከተሳሳተ፣ ወይንም ባይሳሳትም እኛ የማንፈልገው አስተያየት ከሰጠ፣ ያ ሰው ወዲያውኑ እንደ ጠላት ነው የሚቆጠረው። ”ወያኔ” ወይንም ”ሆዳም” የሚል ስም ይለጠፍበታል። ትላንት ለትግሉ ጥሩ ያበረከተው፣ ትላንት የሰራው መልካም ሥራ ተረስቶ ዛሬ በአደባባይ ይብጠለጠላል።

 

አንድ ጊዜ ነዋሪነታቸው በኒውዮርክ የሆነ፣ አቶ አባተ ካሳ የሚባሉ አንጋፋ ኢትዮጵያዊ በተለያዩ የአሜሪካ ከተሞች ሴሚናር ይሰጡ ነበር። በቺካጎ ያደረጉትን ሴሚናር ለመካፈል እድል አግኝቼ ነበር። በሴሚናሩ ከተማርኳቸውና ከማስታወሳቸው ጠቃሚ ትምህርቶች መካከል ስለ ”ስህተት” ያስተማሩት አንዱ ነበር። ”ስህትት የማይሰሩ በሶስት ሊመደቡ ይችላሉ። እነርሱም የማይሰራ ሰው፣ የሞተ ሰው እና እግዚአብሄር ናቸው” ሲሉ ሌላው ስህተት እንደሚሰራ ነበር አቶ አባተ ያስረዱት።

 

የሚሰራ ሰው ሊሳሳት እንደሚችል ብዙ ጊዜ እንዘነጋለን። አንድ ሰው ስህተት ከሰራ ”ሰው ነውና መሳሳቱን እንደ ትልቅ ነገር መቁጠር የለብኝም። ለምን ወንድሜን አልመልሰውም ? ለምን ቀስ ብዬ አላናግረውም ? ድንገት ያልተገነዘበው ነገር ይኖራል፤ ስህተት መሆኑን ካለኝ ልምድ አሳየዋለሁ። ሌላ ጊዜ ተመልሶ ድጋሚ እንዳይሳሳት እመክረዋለሁ” በሚል፣ ወንድማችንን ከስህተት ለማረምና ለማንሳት አንቸኩልም። ወዲያው በስሜት እንሞላና እራሳችንን ለንዴት፣ ለጥላቻ አሳልፈን እንሰጣለን።

 

ሌላው ያለብን ችግር በሌላው ጫማ ላይ ሆነን ነገሮችን ለማየት አለመሞከራችን ነው። ኢትዮጵያዊ ወገናችን ላይ ክስ ስናቀርብ፣ እኔ በርሱ ቦታ ብሆንስ ብለን አንጠይቅም። አንድ ሰው ከኔ አስተሳሰብ የተለየ ነገር ከተናገረ ”ለምንድን ነው እንዲህ ያለው ? እስቲ እንዲሁ በጭፍን ፍርድ ከምሰጥ እርሱ ባለው መልኩ ነገሮችን ላማዛዝናቸው” አንልም። ለፍርድ፣ ለወገዛ እንቸኩላለን።

 

ይህ በዳያስፖራ ያለው ያለመቻቻል ፖለቲካ፣ አላወቅነው እንጂ በተዘዋዋሪ መንገድ እንቃወመዋለን የምንለውን ገዢውን የኢሕአዴግ ፓርቲን እየጠቀመ ያለ ፖለቲካ ነው። አንድ ሰው የበለጠ በሰደብነውና ባወገዝነው ቁጥር፣ ከኛ እየራቀ ነው የሚመጣው። ብዙዎች፣ እኛ የዳያስፖራ ሰዎች ባለን ጽንፈኛና አክራሪ አቋም፣ የበለጠ እንዲያመሩ፣ ከትግሉ ሜዳ እንዲወጡ፣ ምናልባትም ወደ ኢሕአዴግ ካምፕ እንዲገቡ እየገፋፋናቸው ነው። የወዳጆችን ቁጥር እየቀነስን የሚቃወሙንን ቁጥር እያበዛን ነው። ይህ ደግሞ የሽንፈት ፖለቲካ ነው።

 

ወደ ፌዴሬሽኑ ጉዳይ ልመለስና ያለው ችግር በንግግር በውይይት ይፈታ ነው የምለው። አለመስማማቶች፣ አለመግባባቶች አሉ። በርጋት በቅንነት ከተነጋገርን፣ እንኳን ይችን ቀላል ጉዳይ ቀርቶ ሌላ ከባድ ትልቅ ችግር መፍታት እንችላለን። ”እገሌ ውሸታም ነው … እገሌ ወያኔ ነው..እገሌ ገንዘብ በላ … ወዘተረፈ” የሚል ትልቅን ሰው የማይመጠን አባባሎችን በጽሁፍና በድህረ ገጾች ባንወረወር ጥሩ ነው። ፌዴሬሽኑ የራሱ ሕገ ደንብ አለው። በደንቡም መሰረት ወሳኞቹ በተለያዩ ከተሞች ያሉ ቡድኖች የወከሏቸው የቦርድ አባላት ናቸው። የቦርድ አባላትም ለፌዴሬሽኑ ጥቅምና ሕልውና ሲሉ ጠቃሚውንና ኢትዮጵያውያንን የሚያቀራርብ ውሳኔ ይወስዳሉ የሚል እምነት አለኝ።

 

ብርቱካን ሚደቅሳ በዚህ በፌዴሬሽኑ ጉዳይ ምን እንደምታሰብ ብዙ አላውቅም። ነገር ግን እርሷ የመለያየትና የመወጋገዝ ምክንያት መሆን እንደማትፈልግ ግን መገመቱ አይከብድም። ማንም በባዶው፣ በፍርደ ገምድልነት ”ወያኔ፣ ሆዳም” ተብሎ እንዲሰደብ የምትፈልግ አይመስለኝም። አንድ ሰው ”ወያኔ ነኝ” እንኳን ቢል በኢትዮጵያዊነቱ መከበር ይገባዋል ብላ የምታምን ሴት ናት። የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ፖለቲካ የፍቅር፣ የሰላም፣ የአንድነት፣ የጨዋነት፣ የመከባበር ፖለቲካ ነው። ”ብርቱካን ሚደቅሳን እንወዳታለን፣ እናከብራታለን” የምንል ከሆነ እርሷ ለምትታገልለት፤ ለታሰረችለት የተከበረ አላማ መቆማችንን ማሳየት አለብን። በብርቱካን ስም ሌላውን ኢትዮጵያዊ እየሰደብንና እያወገዝን፣ ከኛ ጋር የማይስማማውን ሁሉ ”ወያኔ ነው” እያልን ለብርቱካን ሚደቅሳ ፍቅርንና አክብሮትን እገልጻለሁ ማለት ውሸት ነው።

 

ዳያስፖራው ለኢትዮጵያ እንደ ወርቅ መዓድን ነው። በአንድ ላይ ከተሰባሰበ ትልቅ ሥራ ሊሰራ የሚችል አካል ነው። በአንድ ላይ እንዲሰባሰብ ደግሞ መቻቻል ይኖርበታል። ዴሞክራሲን የሰለጠነ ፖለቲካን መማር አለበት። ከአሜሪካ ቀመስ ጄሪ ስፒንገር አስተሳሰብ ወጥቶ ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን ማንገብ ይጠበቅበታል።


ግርማ ካሣ

(This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

ጥቅምት 18 ቀን 2003 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!