ስለ ዳኛ ብርቱካን ሚደቅሣ የክብር እንግዳነት ምርጫ የወሰደው ፖለቲካዊ አቋም

ዘውገ ፋንታ (የፌደሬሽኑ የቀድሞ ቦርድ አባል)

መግቢያ

በውጭ ያለው ማንኛውም የኢትዮጵያኖች ማህበራዊ ድርጅት፣ በሀገር ውስጥ እንዳለው ድርጅት ሁሉ በተዘዋዋሪ ወይም በቀጥታ በወያኔው መንግሥት ቁጥጥር ስር ካልሆነ በስተቀር ለመቀጠል እንዳይችል ውዝግብ እየተፈጠረ ስለሆነ ሕብረተሰቡ አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን መረዳት ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄዱት ጋዜጦች እንዲሁም ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ የሚተላለፉት የዜና ማሰራጫ መስመሮች መንግሥታዊ ድርጅት የሆነው የአሜሪካ ድምፅ ሳይቀር አምባገነኑ መሪ በአሜሪካ ምድር ቆሞ በድፍረትና በንቀት ያገዳቸው መሆኑን ለአሜሪካ ሕዝብ አሰምቷል። ኢትዮጵያኖች በየትኛውም ሀገርና ምድር የሕብረተሰብ ጉዳያቸውን ያለሁከትና ብጥብጥ ለማካሄድ ከማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል። የኢትዮጵያ ሀብት ለወገኖቿ ጥፋት ስራ በየሀገሩ እየተረጨ መሆኑ ግልጽ ነው። ወያኔ መጨቆኛ ሴራ-ድሩን ለማስፋፋት ሲል የኢትዮጵያ ወገኖችን ለሌላ ጨቋኝ ዘረኞች አሳልፎ እየሰጠ መሆኑንም መረዳት ያስፈልጋል።

 

የኢትዮጵያ ስፖርት ፌደሬሽን በሰሜን አሜሪካ ቦርድ የመጪውን ዓመት የክብር እንግዳ ምርጫ በስርዓቱ ፈጽሞ ክብርት ዳኛ ብርቱካን ሚደቅሣን እንደመረጠ ተገልጿል። ዳሩ ግን፣ ህገወጥ በሆነ ስርዓት የቦርዱን ምርጫና ውሳኔ ባልነበረና ባልተፈጸመ የፖለቲካ ሂደት አሳቦ የራሱን የፖለቲካ አቋም ተከትሎ የቦርዱን ውሳኔ ሽሯል። በዚህ ጉዳይ ላይ ያልተነገረና የቀረ ሀቅ ነገር የለም። ዳሩ ግን፡ አሁንም የሥራ አስፈጻሚው አካል ከፌደሬሽኑ ቋሚ አላማ ልምድና ስራ ፈንጠቅ ብሎ ይታያል። ስለሕጉ ያነሳውን መሸሻ የሕግ ዐዋቂዎች ግልጥልጥ አድረገው አስቀምጠውታል። አያሌ ተቆርቋሪ ወገኖችም በየመድረኩ የማይስተባበሉ ሀቆችን አሰተጋብተዋል። በዚህ ጽሑፍ የተባለውን ለመድገም ሳይሆን ለማይበገረው የፌደረሽኑ አካል አስፈላጊ ከሆነ አሁንም ጥፋቱን እስከሚያርምና ውሳኔውን እስከሚያስተካክል ድረስ ደግሞ ደጋግሞ ማስታወቁ የሚከብድ አይሆንም።

 

አባቶችና እህቶች የመሰረቱት ቅርስ

የኢትዮጵያ ስምና የሕዝቦቿ ታሪክ በፈተና ወቅት አዳዲስ ጀግና እና አርቆ አሳቢ ብልህ ሰዎች ይፈጥራል። ብልህ ወገኖቿ ዕንቁው ቅርስና ታሪክ ዘላቂነት እንዲኖረው በማድረጋቸው እዚህ ደርሰናል። በዓለም ላይ በስደት የተሰራጨው የኢትዮጵያ ወገን በሰፈረበት ቦታ ሁሉ በክብርና በስነስርዓት እንዲኖር ማምለኪያ ቦታውንና የመረዳጃ ድርጅቱን በመፍጠር ችግርና ተጽእኖ እንዳያጠቃው ተሰባስቦ በመረዳዳት መኖር ጀምሯል። ብልህና አርቆ አሳቢዎች የኢትዮጵያ ወገን ተሰባስቦ ቅርሱንና ባህሉን እንዲያከበር የኢትዮጵያኖች የስፖርትና የባሕል ፌደሬሽኑን መሰረቱ። ይህ ድርጅት ለስደቱ ወገን ዋና ቅርሱ ሆኗል። ፌደሬሽኑ ለኢትዮጵያኖች ያአደረገው አስተዋጽኦ መለኪያ የለውም። ይህን ያቋቋሙት ወገኖች ስማቸው ከታሪክ መዝገብ የሚኖር ይሆናል። ኢትዮጵያኖች በዕንቁ ባህላቸውና ውብ ገጻቸውንና ግሩም ባህሪያቸውን በዓለም ላይ እንዲያንጸባርቁ አስችሏል።

 

ይህ ድርጅት ያለትልቅ መስዋዕትነት አለተቋቋመም። በየጊዜው ድርጅቱን ሊያናጉና ሊያፈርሱ የተነሱትን ጠላቶች ተቋቁሟል። በ1991 በዓሉን ለማስቀረት የተደረገው ከባድ ሴራ፣ ኃላም በ1993 ድርጅቱን አዳክመው ከዚያም ገዝተው ለመውሰድ ያደረጉት ታላቅ ደባ ከሽፏል። ለድርጅቱ ቀጣይነት ትልቅ መስዋዕትነት ተከፍሏል። መስራቾቹ ከኪሳቸው ገንዘብ እያወጡና ጊዜአቸውን ከቤተሰባቸውና ከስራቸው እየሰረቁ ለድርጅቱ ዕድገትና በየዓመቱ ለሚደረገው በዓል ያደረጉትን አስተዋጽኦ ለመተመን አይቻልም። እስከ አሁን እያገለገሉ ያሉትብርቱ ወገኖች ሰብስቤና እንዳለ ሌሎችም ቢጠቀሱ ጸሐፊው እጅግ ደስ እያለውና በነሱም እየተማመነ ነው። ይህ ጸሐፊ ብዙ ወገኖች ለፈጸሙት በጎ ድርጊትና ወደር ለሌለው አስተዋጽኦ የአይን ምስክር ነው። በስደተኞች ለስደተኛው ወገን የተቋቋመው ፌደሬሽን አቋሙ ግልጽ ነው። አሁን የታየው ውዥግብ ግን አዲስ ሂደት ነው። ችግሩም የተጸነሰሰው በቦርዱ አባሎች ሳይሆን ብልህና አዋቂ መሪ ናቸው ብሎ ቦርዱ በመረጣቸው የስራ አስፈጻሚው አካል አባሎች ነው። አሁን የሚደረገው ጥረት ይህን ለማስተካከል ነው።

 

የስፖርትና የባሕል ቅርሶች

ፌደሬሽኑ የስፖርትና የባሕል ድርጅት ነው ሲባል ለስፖርትና ባህል ልማት የሚያገለግል ድርጅት መሆኑ ግልጽ ነው። ዳሩ ግን፣ ማናቸውም “የኢትዮጵያኖች” ድርጅት ተብሎ የተቋቋመው የሚሰራው “ኢትዮጵያ” የሚባለው ሀገርና ሕዝብ ሲኖር ብቻ ነው። “ኢትዮጵያ” የምትባለው ሀገር ሳትኖር በስሟ መሰብሰብ እንደ ኃይማኖትዕምነት የሚታሰብ ካልሆነ በስተቀር ምግባራዊ አይሆንም። በሶቪያት ዩኒየን ወይም በዩጎዝላቪያ ስም የሚሰበሰብ ርዝራዥ ሕዝብ አሁን የለም። ኢትዮጵያ ብትፈርስ አሁን በተዘጋጀው የጎሳ ክልል ስም እንጂ በኢትዮጵያ ስም መሰብሰብ አይቻልም። የዚህ ዋዜማ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአውሮፓና አሜሪካ በየከተማው በትግሬ፣ በኦሮሞ … ወዘተ ጎሣ ስም የተደራጀው ህብረተሰብ ሁናቴ ጉልህ አድርጎ ያሳያል። የወያኔ አምባሳደሮችም የአሜሪካንን ከተሞች ሲጎበኙ ስብሰባው ቅዳሜ ለትግሬዎች፣ እሑድ ለእከሌ እየተባለ ነው። በኢትዮጵያም ያለው ስፖርት ውድድር የሚካሄደው ትግሬው ከኦሮሞው ጋር ተጋጠመ፣ አማራው ከትግሬ ጋር ተወዳደረ፣ … ወዘተ እየተባለ ነው።

 

የስደተኞቹ የኢትዮጵያኖች ስፖርት ፌደሬሽን የኢትዮጵያኖችን አንድነት የሚጠብቅ ድርጅት ነው። ፌደሬሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ምግባሮቹ የኢትዮጵያውያንን አንድነት የሚያንጸባርቁ ናቸው። የስፖርት ፌደሬሽኑ ለዘመናት የታወቀውን የኢትዮጵያን ዕንቁ ባንዲራ እንጂ የወያኔን ከፋፋይ ባንዲራ አያውለበልብም። ይኽ ፖለቲካ አቋም ከሆነ የማይሻር የማይነካ ዕንቁ የፖለቲካ ኃይማኖታችን ነው። የወቅቱ ስራ አስፈጻሚ አካል የፌደሬሽኑን መንፈስ ባለማወቅ ወይም እያወቁ የተረከቡትን ቅርስ ለማናወጥ የተነሱ የተገፋፉ ይመስላል። ኢትዮጵያ በስሟ እስከቆየችና እስከጸናች ድረስ የፌደሬሽኑ ሕልውና ይቀጥላል። ኢትዮጵያ ከተፈረካከሰች ሌላውም አብሮ ይወድማል። ይኽ ደግሞ በጠቅላይ ሚንስትሩ አዕምሮ ያለና የሚታወቅ ዳሩ ግን ኢትዮጵያኖችን እጅግ የሚያስጨንቅ ጉዳይ ነው። ጠቅላይ ሚንስትሩ እንደገለጸው፣ “ኢትዮጵያ ከተከፋፈለች፣ አንድ ልትሆን ስለማትችል ነው“ ብሏል። ኢትዮጵያን የምትከፋፈልበትን መንገድ የቀየሰውና ያዘጋጀው ግን ይኸው መሪ ነው። ኢትዮጵያ በዚህ አፋፍ ላይ እንዳለች ለማንም ዕውቅ ነው። በጠንካራና ብልህ ወገኖች የተቋቋመው አሁንም በጠንካራ ወገኖች እጅ የሚካሄደው ‘የኢትዮጵያኖች የስፖርትና ባሕል ፌደሬሽን በሰሜን አሜሪካ’ የጎሣ ክፍፍልን ከብዙ ፖለቲካ ድርጅቶች አቋም ይበልጥ አጥብቆ ይጻረራል።

 

የክብር እንግዳ ምርጫ

ፕሮፌሠር አስራትን ፌደሬሽኑ ለዚህ ክብር ሲመርጣቸው የእሳቸውን ስም የጠቆመው ይህ ጸሐፊ ነበር። ዳሩ ግን ስማቸው ለዚህ ክብር እንዲጠቀስ አስቀድመው የጠቆሙ ሌሎች እንደነበሩ መግለጽ ይገባል። ያን ጊዜም አንዳንድ የቦርድ አባሎች ስፖርቱ ከፖለቲካ ጋር ተለወሰ ብለው ከፍተኛ ጩኸት አሰምተው ነበር። ይህ ጸሐፊ ቀጥሎ እንዲናገር ዕድል ተሰጥቶት ፕሮፌሰር አስራት ለምን መመረጥ እንደሚገባቸው ሲገልጽ፣ በመጀመሪያ ደረጃ በሕክምና ሙያቸው ለኢትዮጵያ ያደረጉትን ወደር የማይገኝለትን አስተዋጽዖ በመጥቀስ ነበር። ከዚያም ለኢትዮጵያ ሕልውና መቆማቸው ፌደሬሽኑ የሚያምንበትና የተቋቋመበት መንፈስ መሆኑ ሲገለጽ የቦርድ አባሎቹ`በጽሞና አዳምጠው ተወያይተው በምርጫ አጸደቁት። ፌደሬሽኑ ሲወጠን ጀምሮ በዚህ ኢትዮጵያዊ መንፈስ እነሆ ቀጥሏል። ዕድገቱም በየአቅጣጫው ሆነ። ሴቶችም እንዲሳተፉ በሩ ተከፈተ። ወ/ት የሀረርወርቅ ጋሻው ቀደም ብሎ የፌደሬሽኑ ልዩ የክብር እንግዳ ሆና በበዓሉ ላይ እንድትቀርብ አድርጎ ነበር። ወጣቶች እንዲሳተፉ የተለያዩ ፕሮግራሞች ማዘጋጀት ተጀምሮ እንዲሁ ቀጠለ።

 

ፌደሬሽኑ የፖለቲካ ድርጅት ያልሆነ ነው ሲባል፣ በፖለቲካ ሚና አንዱን የፖለቲካ ፓርቲ በመደገፍ ወይም የተለየ አስተዋጽዖ እንዳያደርግ ወይምበማናቸውም የፖለቲካ ድጋፍ ወይም ቅዋሜ እንዳያሰማና የፖለቲካ ሚና እንዳያካሂድ እንጂ፡ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለኢትዮጵያ ሕልውና የሚያበረክቱትን እንዳያከብር የሚያግደው መንፈስ የለም፡ ሊኖርም አይችል።

 

የክብርት ዳኛ ብርቱካን መመረጥ

ብልህ ወገኖች ክብርት ዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ ያሳየችውንና ያደረገችውን የላቀ አስተዋጽዖ ተገንዝበው ለክብር እንግዳነት እንድትመረጥ ማድረጋቸው እጅግ የሚያኮራ ድርጊት ነው። ይህን ሃሳብ መጻረር ግን የሚዘገንን ታሪክ ይሆናል። ክብርት ዳኛ ብርቱካን ማንም ሴት በዘመናችን ያልፈጸመችውን ፈጽማለች። ዳኛ ሁኜ በፍትሕ ወንበር ላይ ተቀምጨ ሕግ የጣሰውን ቀጥቻለሁል። ለተበደለውና ለበደለው ፍርድ ሰጥቻለሁ። ወንጀል ያልሰራውን ነጻ አውጥቻለሁ። ዕውነቱን ለመናገር የኔ ተራ ሲደርስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዕውነቱን እነግራለሁ በማለቷና በዕውነት ጸንታ በመቆሟ የደረሰባትን በደልና የከፈለችውን መስዋዕትነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን መላው የዓለም ሕዝብ ያየውና የሚያውቀው ጉዳይ ነው። ይኽን ወደር የሌለው ድርጊት ለኢትዮጵያ ሕዝብና ወጣት ትውልድ ግሩም አርአያ ነው። የዳኛ ብርቱካንን አርኣያነት ከፍተኛ ቦታ የነሳው ሰው ምን ጊዜምክብር የማይኖረው ከትንሽነቱም ዝቅ ያለ ፍጡር ነው። ክብርት ብርቱካንን ማክበር ራሱ ታላቅ ክብር ነው። የወያኔው መሪ ክብርት ዳኛ ብርቱካንን አስመልክቶ የስደቱን ወገን ማንም መሪና ሰው አድርጎት በማያውቀው ህሊናና አንደበትአሟርቶበታል። ኢትዮጵያኖች ተጠግተው የሚኖሩበትንሕዝብና የመንግሥት ስርዓቶችምዝቅ በማድረግ አፊዟል። የስድቱ የኢትዮጵያ ወገን እጅግ በተቋሸሸበት ወቅት የፌደሬሽኑ ስራአስፈጻሚ አካል ክብርት ዳኛ ብርቱካን ለክብሩ ቦታ ከተመረጠች በኋላምርጫውን ለመቀልበስ መሞከሩና ማድረጉ ድፍሮ መለስ ዘናዊን አላስደሰትኩም አይለንም። የፌደሬሽኑን ስርዓት ለማበላሸት ቆርጦ የተነሳ ካለ ከፌደሬሽኑ ከመቅጽበት ተገልሎ ወደ ቤቱ ቢላክ አጥጋቢና ተገቢ ርምጃ ይሆናል።

 

ምርጫው ይጽደቅ ስርዓት ይከበር

ቦርዱ በአደረገው ምርጫ የፌደሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ አካል አባሎችየወሰዱት እርምጃና ድርጊት ትልቅ ጠንቅ የሚያስከትል ነው። ዳሩ ግን የጣሱትን ሕግ ባለማዎቃቸው ደግመው ደጋግመው እንደ መከላከያ አድርገው ያቀርቡታል። ይህ እጅግ አሳፋሪና አሳዛኝ ጉዳይ ነው። የፌደሬሽኑ ባለሥልጣኖች የምርጫውን ትክክለኝነት እንዲህ ብለው ይገልጹታል። “… የመሐሙድ አሕመድ ስም ለምርጫ ተጠቆመ። ብዙ ጭብጨባ ተደረገ። አንድ ሌላ አባል ብርቱካንን ጠቆመ፣ ሌላ አባል ደገፈው። የቆዩት የቦርዱ አባሎች የብርቱካን መጠቆም ፌደሬሽኑ ፖለቲካዊ አቋም የያዘ ስለሚያስመስለው ከውድድሩ እንዳትገባ አጥብቀው ተከራከሩ። ከብዙ ጭቅጭቅ በኋላ በስነስርዓቱ መሰረት ምርጫ እንዲካሄድ ተደርጎ ብርቱካን 12 ለ10 አሸነፈች …” የቦርዱ ምርጫ ይህ ነበር። ቋሚና ወሳኝ ነው። ውሳኔው በአባሎች ይግባኝ ተብሎ እንደገና ለማየት አልቀረበም። ብዙ አባሎች ከምርጫው በኋላ ከስብሰባው እንደወጡ ተነግሯል። ዳግም ተደረገ የተባለው ምርጫ ቦታ የሌለው መነሳት የሌለበት እጅግ አሳፋሪ ጉዳይ ነው። የፌደሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ አባሎች ከዚህ የላቀ ዕውቀት አላቸው ተብሎ ይገመት ነበር። እስከአሁን ያሳዩት ብልኽነት የለም። የተሰጡት ምክሮች የሚያመጡት ለውጥ ይጠበቃል። አለበለዚያ አንዱ ትክክል ምርጫውን የተነሳው አባል የጠበቃ ያለህ ቢል መደናገጥ አይገባም።

 

መደምደሚያ

የፌደሬሽን የስራአስፈጻሚው ፖለቲካ እንጂ የዳኛ ብርቱካን ሚደቅሣ ፖለቲከኛነት ለዚህ ሁሉ ችግር መነሻ እንዳልሆነና እንደልነበረ የሆነው ድርጊትቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ከመለስ ዜናዊ ጠበቆችከነፓይፐር ሌላ ፌደሬሽኑንና የስደተኛውን ወገን የፖለቲካ ሰው አከበራችሁ ብሎ የሚከስ ሰው በዚች ምድር አይኖርም።


ዘውገ ፋንታ

(የኢትዮጵያ ስፖርት ፌደሬሽን በሰሜን አሜሪካ የቀድሞ ቦርድ አባል)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!