ያሬድ አይቼህ

የኢትዮጵያ አገራዊ ፖለቲካ ላይ ገንቢና ጠቃሚ ተጽዕኖ ለማድረግ ከዲያስፖራ የሚደረገው ጥረትና ትግል ከምርጫ 2002 ማግስት ጀምሮ አቅጣጫው ተሰበጣጥሯል። በተለይ ሠላማዊ እና ህጋዊ ትግል ላይ እኔ ተስፋ ስላደረኩ፤ ከኢህአዴግ 99.6% ወንበር ማግበስበስ በኋላ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሂደት በጣም ጭጋጋማ፤ ጨለማ፤ ድንግዝግዝና ተስፋ አስቆራጭ ሆኖብኝ ነበር።

 

ሰሞኑን ሲያሳስበኝ የከረመው ግን የሠላማዊ-ታጋዮች ትግላቸው በሁለት ግንባሮች መሆኑ ነው ። አንዱ፤ ኢህአዴግ የሚያደርግባቸው ጫና፣ ወከባ፣ ትንኮሳ እና እንግልት ጋር ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ በሁለገብ ትግል ለመታገል ህብረት ለመፍጠር ከሚሞክሩት ሃይሎች ጋር ነው።

 

ከኢህአዴግ ጋር ያለው ትግል አዲስ ነገር አይደለም። ኢህአዴግን ካለፉት አራት ምርጫዎች ባህሪውን በሚገባ አውቀነዋል። ሠላማዊ ትግል ሚያራምዱ ፓርቲዎች ኢህአዴግን ለማሸነፍ ያልቻሉት ኢህአዴግ ምትሃታዊ ሃይል ኖሮት ሳይሆን ሠላማዊ-ታጋዮች ካላቸው የንዋይ (ገንዘብ) አቅም ደካማነት የተነሳ እንደሆነ ሠላማዊ-ታጋይ ፓርቲዎች ጠቁመዋል።

 

ኢህአዴግ ፓርቲ ነው ከማለት ይልቅ፤ ኢህአዴግ መንግስት ነው ማለት ይቀላል።ኢህአዴግ ጋር የሚታገሉ ፓርቲዎች ከመንግስት ጋር ነው ሚታገሉት፤ ማለትም ከፖሊስ ጋር፣ ከቀበሌ ጋር፣ ከፍርድ ቤቶች ጋር፣ ከምርጫ ቦርድ ጋር፣ ከኤፈርት ጋር፣ ከባለሃብት የኢህአዴግ አባላት ጋር እና ከኢትዮጵያ መከላከያ ጋር ጭምር ነው (በምርጫ 2002 ሰሞን ትግራይ ላይ ዝቅ ብሎ ህዝቡን ለማስፈራራት የበረረው የጦር ጀት አውሮፕላን ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነው)።

 

ኢህአዴግ በጣም ጉልበተኛ ነው! በቅርቡ፤ ካፒታል ኢትዮጵያ እንደዘገበው፤ ኢህአዴግ $120 ሚሊየን ብር ($7.5 ሚሊየን ዶላር) የሚያወጣ ህንጻ ለዋና ጽህፈት ቤትና ለማሰልጠኛ ለማሰራት አቅዷል። ኢህአዴግ በጣም ሃብታም ነው፤ ገንዘቡን ከየት እንዳመጣ ለማንም ተጠያቂ አይደለም (መንግስት ስለሆነ)፤ ማንም ሊጠይቀው የሚችልም አይመስለኝም፤ ሃብታምነቱ ግን ግልጽ ነው። ኢህአዴግ ጎልያድ ነው!

 

ለሠላማዊ-ታጋዮች ጎልያድ አላንስ ብሎ፤ ሰሞኑን የሰማሁት የሁለገብ-ታጋይ ውይይቶች ለሠላማዊ ታጋዮች ሁለተኛ የትግል ግንባር ሆኗል። ከሁለገብ-ታጋዮች ጋር ሠላማዊ-ታጋዮች ጦርነት ይገጥማሉ ብዬ አላስብም፤ በሁለገብ-ታጋዮችና በሠላማዊ-ታጋዮች መካከል ያለው ትግል የረቀቀ ትግል ነው

 

ዲያስፓራ ገንዘብ አለው፤ በአመት ወደ $3 ቢሊዮን ዶላር ዲያስፖራው ወደ ኢትዮጵያ ይልካል። ይሄንን ገንዘብ ኢህአዴግ ለልማት እፈልገዋለሁ ብሎ ተጎምዥቷል፤ ሁለገብ-ታጋዮች ለጥይትና ፈንጅ መግዣ ይፈልጉታል፤ በተጨማሪም ሠላማዊ-ታጋዮች ከዲያስፓራ የገንዘብ ድጋፍ ይፈልጋሉ። ለምሳሌ በምርጫ ‘97 ቅንጅት ወደ $200,000 ዶላር እንደነበራቸው የቅንጅቱ አመራር አባል ሲናገሩ ሰምቻለሁ፤ ይህ ገንዘብ በከፊሉ ከዲያስፖራ የተገኘ ነው።

 

ቅንጅት በሠላማዊ ትግል፤ $200,000 ዶላር ተጠቅሞ፤ ታሪካዊ የሆነ የወንበር ብዛት አሸንፏል (ቅንጅት ምርጫውን ማሸነፉን አለማሸነፉን በዚህ ጽሁፍ መከራከሩ አላማዩ አይደለምና እሱን ልለፈው)። ታዲያ የሁለገብ-ታጋዮች ከዲያስፖራ የሚወስዱትን ገንዘብ ሠላማዊ-ታጋይ ፓርቲዎች የመጠቀም እድል ቢያገኙ ምነው እንደገና ታሪክ በሰራን!? በሁለገብ-ታጋዮችና በሠላማዊ-ታጋዮች መካከል ግጭት የሚሆነው “ማን ከዲያስፖራ በብዛት የገንዘብ ድጋፍ ያግኝ?” የሚለው ጉዳይ ነው። ሁለገብ-ታጋዮች የዲያስፖራውን ስሜት በቀላሉ እንዲያገኙ ምርጫ 2002 ጥሩ ምክንያት ሆኖላቸዋል።

 

ሁለገብ ትግል የተስፋ መ-ቆ-ረ-ጥና የወኔ መ-በ-ጠስ ውጤት ነውና ደጋፊዎቹን አልፈርድባቸውም፤ እንዲያውም ኢህአዴግ ነው ለሁለገብ ትግል በተዘዋዋሪ ነዳጅ ያቀበለው (ነዳጁ “99.6%” ይባላል)። ሆኖም ግን ሁለገብ ትግል ለዜጎች አይጠቅምም፦ ሠላምና መረጋጋትን ያናውጣል፣ ንብረት ያወድማል፣ ባለሃብቶችን (investors) ያስበረግጋል፣ ንጹሃንን ይገላል፤ ያቆስላል፤ አካል ያጎድላል … ወዘተ። ሁለገብ ትግል “የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው” ነው።

 

ታዲያ ምን ይሆን መፍትሄው? መፍትሄው ጎልያድ የሆነውን ኢህአዴግን ተጋፍጠው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታገሉትን ሠላማዊ ታጋዮች በገንዘብ መደገፍ ነው። ይሄ ሃሳብ እንደ ቀጭን ወጥ ለብዙዎች አይስማማም፤ ይገባኛል። ነገር ግን ለሠላማዊ ትግል ስኬታማነት ወሳኙ ሙሉ እና ቋሚ ጽናት ነው። ተስፋ መቁረጥ ግን ሽንፈት ነው። ሠላማዊ ትግልን ከጠመንጃ ትግል የሚለየው አንድ ትልቅ መሰረታዊ ነገር አለ፦ ሠላማዊ ትግል የሚያስገኘው ስልጣን ብቻ ሳይሆን፤ ሠላማዊ ትግል የሚራመድበትና የሚያልፍበት ሂደት በራሱ አገርን፣ ዜጎችን፣ እንዲሁም መጪውን ትውልድ የሚጠቅም የበሰለና ቀና የፖለቲካ ባህል ቀርጾ፣ የፖለቲካ ርስት አፍርቶ ያልፋል እንጂ ደም አፍስሶ፤ ንብረት ደምስሶ አያልፍም።

 

ጎልያድን ለማሸነፍ ትንሹን ዳዊትን መደገፍ አለብን። ጎልያድ የሆነው ኢህአዴግን በሠላማዊ ትግል ለማሸነፍ እንደሚቻል በምርጫ ‘97 ቀምሰነዋል፤አሁንም ይቻላል። ሠላማዊ-ታጋዮች ኢህአዴግን ያለ ዲያስፖራ የገንዘብ ድጋፍ በምርጫ ውድድር ለማሸነፍ አይችሉም። ፖለቲካ ገንዘብ ያስፈልገዋል፤ ለምሳሌ፤ የሬዲዮ ስርጭት ገንዘብ ያስፈልገዋል። ሠላማዊ ታጋዮችን የሚያገለግል አንድ እንኳን ሬዲዮ የለም። ይህን ሬድዮ በመክፈት ሠላማዊ-ታጋዮች ከሚታገሉላቸው ህዝቦች ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያጠናክሩ በማድረግ ድጋፋችንን እንቀጥል።

 

ምርጫ 2002 የበጠሰውን ወኔያችንን ለሠላማዊ-ታጋዮች ሬዲዮ በመክፈት ወኔያችንን እናድስ።

ከሠላማዊ-ታጋዮች ጐን በሙሉ እና ቋሚ ጽናት እንቁም!


ፀሐፊውን ለማግኘት፦ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!