ፕሮፌሠር ዳንኤል ክንዴ ከማርች 25 እስከ 27 ቀን 2011 እ.ኤ.አ. በካሊፎርኒያ ሳንሆዜ በተካሄደው በሦስተኛው የኢትዮጵያና የኤርትራ ወዳጅነት ጉባዔ ላይ ”የኢትዮጵያንና የኤርትራን ሕዝብ የሚያስተሳስሩ ቋሚ ሠንሰለቶች” በሚል ርዕስ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበው ነበር። ይህንን ጥናታዊ ጽሑፉ ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ የላኩልን ሲሆን፣ በዚህ አጋጣሚ ምስጋናችንን ለፕ/ር ዳንኤል እያቀረብን፤ ምንም ሳንጨምርና ሳንቀንስ እንደወረደ አቅርበነዋል። መልካም ንባብ!! 

የኢትዮጵያንና የኤርትራን ሕዝብ የሚያስተሳሥሩ ቋሚ ሠንሰለቶች

በፕሮፌሠር ዳንኤል ክንዴ

በሦስተኛው የኢትዮጵያና የኤርትራ ወዳጅነት ጉባዔ የቀረበ

ሳንሆዜ፣ ካሊፎርኒያ

March 25-27, 2011

መልሶ የማሳተም፣ የመተርጐም፣ የማባዛት ወይንም የመቅዳት መብቱ የደራሲው ነው።

 

ክቡራትና ክቡራን:-

እንደምታውቁት ሁሉ፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ በብዙ መንገድ የተሳሰረ ነው። በጅኦግራፊ፣ በዘርና በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በባሕል፣ በታሪክና በኢኮኖሚ መያያዝ ብቻ ሳይሆን መከራንም ደስታንም አብሮ ሲካፈል የኖረ ሕዝብ ነው። በሁለቱ አገሮች ተከፍለው እንዲኖሩ የተገደዱትን አፋሮችን፣ አሳውርታዎችን፣ ትግሬዎችን፣ አገዎችን፣ ኩናማዎችንና ሌሎችንም መገንዘብ ብቻ በቂ ማስረጃ ነው። ጣሊያኖች ባይመጡ ኖሮ፣ ሃማሴን፣ ሠራየ፣ አኮለጉዛይና ሌላው የቀረው ክፍል ኤርትራ የሚባል ስም አይሰጠውም ነበር።

 

በልማዳዊ ታሪክ አጻጻፍ በኩል ብንሔድ፣ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ የተገነባው ቀይ ባሕርን አቋርጠው በኢትዮጵያ መሬት ላይ ሰፍረው በነበሩ ሳባውያን ዓረቦች ዕርዳታ ነው ይባላል። እንዲያውም የአንድ ሥልጣኔ የሚዛን መድፊያ መለኪያዎች ከሆኑት ውስጥ የሚከተሉትን ሳባውያን ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስተምረዋል ተብሎ ተጽፏል። የእርሻ ሞፈርና ቀንበር፣ የከብት ዕርባታ፣ የወንዝ ግድብ ሥራ፣ ማዕከላዊ መንግሥት ማቋቋም፣ ሃይማኖት፣ የጽሑፍ ፊደላትን መፍጠር፣ የቤቶችንና የሃውልቶችን አሠራር ጥበብ ማወቅ፣ ብረት ማቅለጥ፣ መዳብና ወርቅን አቅልጦ የመገበያያ ገንዘብ መሥራት፣ የመርከብ ሥራ፣ ልዩ ልዩ የሆኑ የጦር መሣሪያዎችን ለመሥራት መቻል፤ ይኸ ሁሉ ተዳምሮ ከውጭ የመጣ ጥበብና እውቀት ነው ተብሏል።

 

እንዲህ ያለ ልማዳዊ ታሪክ የተጻፈው በስማ በለው፣ በይሆናል፣ ወይንም ሳይሆን አይቀርም በሚል ግምታዊ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተ ነው። “ሳይሆን አይቀርምን” ምን አመጣው? ብላችሁ ብትጠይቁ መልሱ ከባድ አይደለም። ታሪኩን የጻፉት ፈረንጆች ናቸው። ሁሉም ታሪክ ጸሐፊዎች አንድ ዓይነት አመለካከት ወይም አስተያየት የላቸውም። ቢሆንም ብዙዎቹ ከግብፅ በስተቀር አፍሪካኖች የገነቡት የዳበረ ሥልጣኔ አለ ብለው አያምኑም። ዓረቦችን በኢትዮጵያ ሥልጣኔ ላይ ያስገቡበት ምክንያት ኢትዮጵያዊያን ካለውጭ ዕርዳታና አመራር እንዲህ ያለ በከፍተኛ ደረጃ ላይ የዳበረና የረቀቀ ሥልጣኔ ለመገንባት ችሎታውም ብቃቱም የላቸውም ከሚል የተሳሳተ ግንዛቤ የመነጨ ነው።

 

ክቡራትና ክብራን፡-

ለዚህ የተሳሳተ የታሪክ አጻጻፍ ምንጭ ከሆኑት ሰዎች ውስጥ ሁለቱን ብቻ እንመልከት፤ (1) በ17ኛው ምዕተ ዓመት የነበረ JOB LUDOLF (1624-1704) የሚባል 25 ቋንቋዎች የሚችል ጀርመናዊ ምሁር ነበር። እርሱም አባ ጐርጐርዮስ ከሚባል ኢትዮጵያዊ የቤተ ክህነት ሰው ግዕዝና አማረኛን ተማረ። ኢትዮጵያ ግን ሄዶ ምንም ዓይነት ጥናት አላደረገም። ታሪኩንም የጻፈው በቋንቋ ችሎታው በመጠቀም ብቻ ነበር። (2) ከ77 ዓመት በፊት የሞተ CONTI ROSSINI (1872-1949) የሚባል ጣሊያን በግዕዝ፣ ትግረ፣ ትግረኛ፣ አማረኛ፣ አርጐባ፣ ጉራጊኛንና አደሬን አብጠርጥሮ የሚያውቅ ምሁር ነበር። በሞያ በኩል ብንሄድ ሁለቱም ታሪክ ጸሐፊዎች የተካኑት በቋንቋ ብቻ ነበር። ታሪክ ለመጻፍ ግን ቋንቋ ብቻ በቂ አይደለም። ሌሎች ሞያው የሚጠይቃቸው ሞያዎች አሉ።

 

እነዚህ ምሑራን የኢትዮጵያን ታሪክና ሥልጣኔ ከዓረብች ጋር ያዛመድት በሚከተሉት ሦስት ምክንያቶች ነበር። (1) ግዕዝ፣ ትግረ፣ ትግረኛ፣ አማረኛ፣ አርጐባ፣ ጉራጌኛ እና አደርኛ የሚባሉ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ከዕብራይስጥ፣ ከሲርያክ እና ከዓረበኛ ጋር በጣም ቀረቤታ ያላቸው ቋንቋዎች በመሆናቸው፣ (2) ንጉሥ ኤዛና ከ1700 ዓመት በፊት አክሱም ላይ ባቆመው ኃውልት ራሱን ንጉሠ ኢትዮጵያ ማለቱ ብቻ ሳይሆን፣ የሳባ፣ የሳልሂን፣ የሂምያርና የራይዳን ንጉሥ ብሎ መሰየሙ፣ (3) አንዳንድ የዓረቦች ታሪካዊ ቅርሶች ሰሜን ኢትዮጵያ ውስጥ በመገኘታቸው ነበር።

 

ከእነርሱ በኋላ የመጡት ታሪክ ጸሐፊዎች፤ ለምሳሌ ፈረንሳዊው JEAN DORESSE, እንግሊዞቹ SPENCER TRIMINGHAM እና EDWARD ULLENDORFF ከላይ የቀረበውን ሁሉ ጥያቄ ውስጥ ሳያስገቡ አሜን ብለው ተቀብለው SEMITIC ETHIOPIA እያሉ በሰፊው ጽፈዋል።

 

የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ሁሉ፣ አንድ ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ ይማራል። በዚህ ላይ ክርክር የለም። ሆኖም SEMITIC የሆኑ ቋንቋዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በመኖራቸው ብቻ፣ እንዲሁም አንዳንድ የዓረብ አገሮች በኤዛና ቁጥጥር ሥር ስለነበሩና አንዳንድ የዓረብ ታሪካዊ ቅርሶች ኢትዮጵያ ውስጥ በመገኘታቸው ብቻ ተነሳስተው የኢትዮጵያ ሥልጣኔ በዓረቦች ዕርዳታ የተገነባ ነው ብሎ በቂ ማስረጃ ሳይዙ አቋም መውሰዱ በአሠራር በኩል ብዙ ተቀባይነት የለውም።

 

ስለሆነም፣ ፈረንሳዊዋ JACQUELINE PIRENNE, A.J. DREWES ከኒዘርላንድስ፣ RUDOLFF FATTOVICH ከጣሊያን፣ ROGER SCHNIDER ከፈረንሳይ፣ GROVER HUDSON ከአሜሪካ፣ DAVID APPLEYARD ከእንግሊዝ፣ ብዙ ዓመታት የወሰደ ጥናት ካደረጉ በኋላ JOB LUDOLF እና CONTI ROSSINI የደረሱበትን መደምደሚያ ውድቅ አድርገውታል።

(1) ዓረቦች ከአገራቸው በብዛት ፈልሰው ወጥተው ኢትዮጵያ ውስጥ ለመኖራቸው ታሪካዊ ማረጋገጫ የለም።

(2) SEMITIC የሚባሉ ቋንቋዎች በጠቅላላ ኢትዮጵያ ውስጥ ተወልደውና ዳብረው ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ተዛመቱ እንጂ ከመካከለኛው ምሥራቅ ወደ ኢትዮጵያ አልመጡም።

(3) የኢትዮጵያ ሥልጣኔ በኢትዮጵያ ሕዝብ የተገነባ እንጂ በውጭ እጅ እንዳልሆነ እላይ ስማቸው የተጠቀሰው ምሑራን ሰፋ አድርገው ጽፈዋል።

 

ክቡራንና ክቡራት፡-

ይኸ ሁሉ ሃተታ ከአርዕስቱ ጋር ምን ግንኙነት አለው? ብላችሁ ብትጠይቁ አይገርመኝም። ታሪክ ጸሐፊዎች የሰሜን ኢትዮጵያን ሕዝብ ኤርትራውያንንም ጨምሮ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጣም የተለየ አድርገው ነው የሚያቀርቡት። ይኸ ግን ስህተት ነው። መጠነኛ የሆነ ጥናት እንኳ ብናደርግ ጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በልዩ ልዩ መንገድ የተያያዘና የተሳሰረ ሆኖ እናገኘዋለን።

አንዱን ኢትዮጵያዊ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ለመለየት ከተቻለ በቋንቋ ብቻ ነው። ቋንቋም ቢሆን ብቻውን መለያ ሊሆን አይችልም። የግለሰቦችን ማንነት በቋንቋ ብቻ ለመወሰን አይቻልም። አብረው መሄድ ያለባቸው ተጨማሪ የሆኑ እንደ ታሪክ፣ ኢኮኖሚ፣ ባሕልና አስተዳደር የመሳሰሉት መስፈርቶች ይገኛሉ። በልዩ ልዩ ምክንያቶች ሰዎች ከቦታ ቦታ ይዘዋወራሉ፤ ጋብቻ አለ፣ አገር መለወጥ አለ። ይህ ሁሉ አብሮ መታየት ይኖርበታል። አገርን ለመገንባት ቋንቋ ብቻ በቂ አይደለም። “ሰዎች እራሳቸውን በራሳችው ይለኩና ከራሳቸው ጋር ሲወዳደሩ ዕድገቱ የት ላይ ነው?”

 

 

Ethiopia provinces

 

 

ምንም ዓይነት ጥናት ሳይደረግ ፋሽስት ሙሶሊኒ ለብልሃቱ ያዘጋጀውን ካርታ በመቅዳት የኢትዮጵያን ሕዝብ በቋንቋ ከፋፍሎ ፌዴሬሽን ብሎ ማውራቱ ቀና ያልሆነ ሥራ አለመሆኑ ሕዝብ ያውቃል። በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የተጣለውን የከፋፍለህ ግዛ (APARTHEID) ሥርዓት በዓዋጅ መሠረዝና የነበሩትን ክፍላተ ሀገራት መልሶ በፌዴሬሽን የማዋቀሩ ተግባር ቢታስብበት ይመስለኛል።

 

በቋንቋ ብቻ ሕዝብን አንድ ለማድረግ የሚቻል ቢሆን ኖሮ ሶማሊያ ተገነጣጥላ አትጠፋም ነበር። ዘጠኙ SPANISH ቋንቋ የሚናገሩ የደቡብ አሜሪካ አገሮች አንድ በሆኑ ነበር። እንዲሁም አሥራ ስምንት የሚሆኑት ዓረብኛ ተናጋሪ አገሮች አንድ መንግሥት ባቋቋሙ ነበር። ጀርመንና ኦስትሪያ እንዲሁም አሜሪካና ካናዳ አንድ አገር መሆን ይገባቸው ነበር።

 

አንጋፋው የእንግሊዝ ፈላስፋ በርትራንድ ራስል እንዳለው “ብሔርተኝነት” እኛ እና እነርሱ የሚል፤ አንድን ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ ጋር የሚያጋጭና የሚያራርቅ የ19ኛው ክፈለ ዘመን ያመጣው ታሪካዊ በሽታ ነው።

 

የዛሬ 62 ዓመት ኤርትራውያን ኤርትራውያን አልነበሩም። ሃማሴን፣ ወይንም ሠራዬ፣ ወይንም አኰሎጉዛይ፣ ወይም ሌላ ነበሩ። ኦሮሞዎችም እንዲሁ ኦሮሞ አልነበሩም። ቦረና፣ ጉጅ፣ ሜጫና ቱሉማ ነበሩ። አማራ የሚባለውም ስም ክርስቲያን የሆኑ ሰዎች መጠሪያ ሲሆን፣ ይኸም ወሎ ክፍለ ሀገር ውስጥ በበሽሎና በወለቃ ወንዞች መካከል በሚገኝ ቦታ ላይ ይኖሩ የነበር ሰዎች መጠሪያ ነበር። ዛሬም ቢሆን አማራ ለሚባሉ ሰዎች አማራነት ትርጉም የለውም። ባለፉት 700 ዓመታት በጠቅላላው በኢትዮጵያ ክፍላተ ሃገራት ተሰባጥረው ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ተጋብተውና ተዋልደው ስለኖሩ ከአማራነት ይልቅ ጐንደሬነት፣ ባሌነት፣ ሐረሬነት፣ ጐሬነት፣ ምንጃርነት፣ ጐጃሜነት፣ መንዜነት፣ ወሎየነት … ወ.ዘ.ተ. ለእነርሱ ትርጉም አለው።

 

ብዙዎች ኤርትራውያንና ኢትዮጵያውያን “ከዘር” ይልቅ እራሳቸውን የሚያዛምዱትና የሚያቆራኙት ከተወለዱበት ወረዳ፣ ወይም አውራጃ ወይም ከክፍለ ሀገር ጋር ነው። እኔ ሃማሴን ነኝ፣ እኔ የጅማ ልጅ ነኝ፣ እኔ የሐረር ልጅ ነኝ፣ ኦሮሞ ከሆነ ደግሞ ጄሌ ወለጋ ነኝ እንዲህ ነው እያሉ ያደጉት። ወያነ በሕዝብ በኩል ምንም ዓይነት ተቀባይነት ስለሌለው እራሱን በሥልጣን ላይ ለማቆየት የሚችለው ሕዝብን በመከፋፈልና ያልነበረ ቅራኔ በመፍጠር ብቻ ስለሆነ፤ ከታሪኩና ከባሕሉ ጋር የማይሄድ “የዘር” ፖለቲካ ከውጭ አምጥቶ በሕዝብ ጫንቃ ላይ ጥሎ ይገኛል።

 

የዓለም ሕዝብ በአህጉር ደረጃ በፖለቲካና በኢኮኖሚ እየተዋሃደ በሚሄድበት ዘመን ጊዜው ያመጣቸው ሁሉን እናውቃለን የሚሉ የፖለቲካ ሰዎች ተነሳስተው የኢትዮጵያን ሕዝብ በቋንቋ ከፋፍለው APARTHEID (ተለያይቶ መኖር) ክልል አቋቁመው ሰው እፈለገበት ቦታ መኖር፣ መሥራት፣ መነገድ፣ ማረስ፣ መምረጥና መመረጥ አለመቻሉ የማሰብ ችሎታቸው ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ፍንጭ ይሰጣል። በቋንቋ አሜሪካንን እናደራጅ ቢባል 311 ክፍለ ሃገራት አቋቁሞ በ311 ቋንቋዎች ማስተዳደር ብቻ ሳይሆን በተጨማሪም MATHEMATICS, PHYSICS, እና CHEMISTRY ማስተማር ያስፈልጋል ማለት ነው። ኢትዮጵያም ዘመኑ ያመጣቸው ባለሥልጣኖች አሜሪካ እንኳ ለማድረግ ያልሞከረውን ድርጊት እኛ እናደርገዋለን ብለው ተነስተዋል። አቅም ቢኖርማ ጥሩ ነበር። እራሳችንን እንኳ ለመመገብ የማንችል አገር እንደሆንን ዓለም በሙሉ ያውቃል። በየዓመቱ ከእህል ልመና መውጣቱ እንኳ ትልቅ ተግባር ነበር። አገሪቱ ውስጥ ያለው ትምህርት ውድቀቱና ጥራት ማጣቱም አንዱና ዋናው ምክንያት ደግሞ ይኸው ነው።

 

ክቡራትና ክቡራን፡-

ታሪክን የፖለቲካቸው መሣሪያ አድርገው እንደሚጽፉት አንዳንድ ሰዎች ሳይሆን፤ ኢትዮጵያ በአፄ ምኒልክ ዘመን የተፈጠረች አገር አይደለችም። ከአፄ ምኒልክ በፊትና በኋላ የመጡት መሪዎች ኢትዮጵያዊ የሆነውን ሕዝብ አንድነቱን ለማስጠበቅና የኢትዮጵያ ግዛት የነበረውን መሬት ለማስመለስ ከፍተኛ ትግል አድርገዋል። አክሱምን፣ ላሊበላንና ጐንደርን ማዕከል ያደረገ የኢትዮጵያ ታሪክ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ አሁን ያለችውን ኢትዮጵያን ያቋቋሟት ታላቁና ጀግናው ንጉሥ ዓምደ ጽዮን(1313-1342) ናቸው። ቤጃዎችን ከኤርትራ መሬት አስወጥተው፣ ዳህላክንና ምፅዋን ከዓረቦች ነፃ አድርገው ከዳህላክ እስከ ባሌ፣ ከወለጋ እስከ ዘይላ ድረስ ያለውን አገር አንድ አድርገው “ንጉሠ-ኢትዮጵያ” እያሉ አገሩን የመሩ ንጉሥ ነበሩ።

 

ንጉሥ ይስሐቅ (1414-1429) ሁለት ጊዜ ምፅዋን ከዓረቦች ወረራ ነፃ ያወጡ፣ ዘይላን እንደገና የኢትዮጵያ ወደብ ያደረጉ፣ ወላሞን፣ ሲዳሞን፣ ሐረርን፣ ከፋንና እናርያን የኢትዮጵያ አካል ያደረጉ መሪ ነበሩ።

 

አፄ ዘርያዕቆብ (1434-1468) ሦስት መጻሕፍት የጻፉ፣ ሦስቱን እህቶቻቸውን የክፍለ ሃገራት አስተዳዳሪዎች አድርገው የሾሙ፣ በ1445 ዓ. ም. አዳልን፣ ድዋሮን እና ኦጋዴንን የኢትዮጵያ አካል ያደረጉ፣ በ1447 ዓ.ም. ሞቃዲሾን ለኢትዮጵያ ወደብ ያደረጉ፣ ሃማሴንን ሠራዬን፣ አከሉጉዛይንና ትግራይን አንድ አድርገው በባሕረ ነጋሽ እንዲተዳደሩ ያደረጉ ታላቅ ንጉሥ ነበሩ።

 

ንጉሥ ሠርፀ ድንግል (1563-1597) በበኩላቸው የወራሪውን የኦቶማን ቱርክ ጦር ለመቋቋም ሰሜን ኢትዮጵያ ከመዝመታቸው በፊት በ1577 ዓ. ም. ሐረር ላይ ትልቅ ድል የተጎናጸፉ፣ ከ1578 ዓ. ም. ጀምሮ ቱርኮችን ከዳህላክ በስተቀር በጦር ሜዳ እያሸነፉ ከትግራይና ከኤርትራ ጥርግ አድርገው ያስወጡ፣ ከጐንደር ከወሰዱትም ጦር ብዙውን ወታደር አገሩን እንዲጠብቅ በማለት ሃማሴን ላይ ሠፍሮ እንዲኖር ያደረጉ ናቸው።

 

በንጉሣውያን ቤተሰብ በኩል ብንሄድ ደግሞ በ17ኛው መቶ ዓመት ተስፋጽዮን አቴሽሞን የሃማሴን አገረ ገዥ አድርገው የሾሙት የአፄ ፋሲል አባት ንጉሥ ሱስንዮስ(1607-1632) ሲሆኑ፣ እርሳቸውም የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትተው ካቶሊክ ሆነው ነበር። የካቶሊክ ሃይማኖት በቤተ መንግሥት አካባቢ ሥር እንዲይዝ ለማድረግና ለማስፋፋት ይረዳ ዘንድ የሮማው ጳጳስ ግሪጎሪ 10ኛው (1621-1623) ዘሊንዳ የምትባል ቆንጆ ልጃገረድ ለንግሡ ሚስት እንድትሆን ልከዋት ነበር። ዘሊንዳ ALEXANDRIA ስትደርስ ሱስንዮስ ሞተዋል። (የሴትዮዋን ስም እስከ ምንጩ (EMML7334 folio 43V) የላኩልኝ አንጋፋው ምሑር ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ስለሆኑ በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናቸው እወዳለሁ)

 

በእርሳቸው ፋንታ የነገሡት ልጃቸው አፄ ፋሲል ስለነበሩ፤ የዘሊንዳን መምጣት ሲሰሙ ALEXANDRIA ድረስ ሰዎች ልከው ጐንደር ድረስ አስመጧት። አፄ ፋሲልም በቁንጅናዋ ተማርከው ወደ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አስጠምቀው ስሟን ዘሊሃ አስብለው አገቧት። በጋብቻውም አምስት ሴት ልጆች ተወለዱ። አንደኛዋ ልጃቸው እመቤት ሰብለ ወንጌል የተዳረችው ለፀዓ ዘጋ ባላባት የሃማሴን አገረ ገዥ ለዓብሱሉስ ነበር። ከዚህም ጋብቻ እያሱ የሚባል ልጅ ተወልዶ ባሕረ ነጋሽ ሆኖ ለብዙ ዓመታት አገሩን ያስተዳድር ነበር።

 

ሠራዬ ብንሄድ ደግሞ የአረዛ ባላባቶች እነ ራስ ኪዳነ ማርያም እና እነ ደጃዝማች ላይኔ ከአፄ ፋሲል የሚወለዱት በእመቤት ሰብለወንጌል በኩል ነው። የአፄ ፋሲል ሁለተኛ ልጃቸው የተዳረችው ተምቤን ሲሆን፣ አንድንድ ታሪክ ጸሐፊዎች አፄ ዮሐንስ ትውልዳቸውን ከአፄ ፋሲል የሚቆጥሩት በዚህ ጋብቻ ምክያት ነው ይላሉ።

 

ወደ ሌላ አርዕስት ብንሄድ፤ ከዓረቦች፣ ከኦቶማን ቱርኮች፣ ከግብፆች፣ ከሱዳኖችና ከጣሊያኖችጋር የተደረጉ ጦርነቶች ሁሉ አብዛኛዎቹ የተካሄዱት አሁን ኤርትራ በሚባለው መሬት ላይ ነበር። በ640 ዓ.ም. ዳህላክ ላይ፣ በ854 ዓ.ም. ምፅዋ ላይ፣ በ1335 ዓ.ም. ምፅዋ ላይ፣ በ1557 ድባርዋ ላይ፣ በ1875 እና በ1876 ጉንደትና ጉራዕ ላይ፣ በ1877 ሰዓቲና ዓይለት ላይ፣ በ1880 ስንሂት ላይ፣ በ1885 ኩፊት ላይ፣ እና በ1887 ዶጋሌ ላይ ነበር።

 

ከእነዚህ ጦርነቶች ሦስት ሁኔታዎችን እንረዳለን። (1) ኢትዮጵያን ለማንበርከክ የሚመጣው ወራሪ ኃይል በመጀመሪያ የሚተናነቀው ከኤርትራ ሕዝብ ጋር ነበር፤ (2) ኤርትራ ለኢትዮጵያ ዓይን፣ መስኮትና በር መሆኗን፤ (3) ኢትዮጵያና ኤርትራ ተወያይተውና ተግባብተው ቢተባበሩ የሚመጣውን ጠላት ሁሉ መቋቋም ብቻ ሳይሆን፣ ለወደፊትም በልማትና በዕድገት በኩል ብዙ ተግባሮችን አከናውነው የነበራቸውን ታላቅነትና ከበሬታ ሊያስመልሱ ይችላሉ።

 

ዘመናት አልፈው ጣሊያኖችም ከኤርትራና ከኢትዮጵያ ተባረው እንግሊዞች በገቡበት ወቅት ዓልዓዛር ተስፋ ሚካኤል የሚባል ስመ ጥሩ ኤርትራዊ ጋዜጠኛ በERITREAN WEEKLY NEWS ላይ ሕዳር 2 ቀን 1944 ዓ. ም. በኤርትራ ምሁራን ስም ለእንግሊዞች ከጻፈላቸው ደብዳቤ በከፊልም ቢሆን ላካፍላችሁ፤“WE ERITREANS BEG BRITAIN TO RESTORE OUR ANCIENT UNITY WITH ETHIOPIA, AS SHE PROMISED US IN 1941. ALL ERITREANS KNOW THAT ETHIOPIA IS OUR MOTHERLAND. EVERY ANNUAL FEAST OF ETHIOPIA BELONGS ALSO TO US. WE CELEBRATE THE SAME RELIGIOUS FESTIVALS AS IN ETHIOPIA, AND DURING FEASTS, ETHIOPIAN FLAGS ARE DISPLAYED AND ETHIOPIAN PATRIOTIC SONGS ARE SUNG. WHEN WAR BROKE OUT BETWEEN ETHIOPIA AND ITALY IN 1935, THOUSANDS OF ERITREANS SACRIFICED THEMSELVES FOR THEIR MOTHERLAND AND FOUGHT SIDE BY SIDE WITH THEIR ETHIOPIAN BROTHERS.” ፌዴሬሽኑ መጣ ፌዴሬሽኑ ፈረሰ፤ ሠላሳ ዓመት ሙሉ ሕዝብ ተሰቃየ፤ ሰው ሞተ፣ አንዳንዱም አካለ ስንኩል ሆነ፣ ንብረት ወደመ፣ ብዙውም አገሩን ለቅቆ ወጣ፣ ይኸ ሁሉ ፈተና በኤርትራ ሕዝብ ላይ ብቻ ያነጣጠረ እንዳልነበረ ሁላችሁም ታውቃላችሁ። ግፉም፣ ጭቆናውም፣ በደሉም፣ ግድያውም አሁንም በተባባሰ መንገድ ቀጥሏል። በነበረው የተዛባ አመለካከት ላይ ሌሎቹም ድርጊቶችና የተዛቡ አመለካከቶች ሲፈጠሩ፣ የባሱ የጭቆናና የብዝበዛ ድርጊቶችም እየተካሄዱ ነው።

 

ይህ የጀመርነው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ጤናማ የሆነ ሂደት እንዲኖረው ነገሮችን በጥሞና እየተወያየን እንቆቅልሾችን እየፈታን እንደምንሄድ ተስፋ አለኝ። ምሑራዊ ክርክር ጤናማ ነው። ለሰላም፣ ለልማትና ዕድገት ቁልፍ የሆነ መሣሪያ ነው። ኤርትራ ነፃነቷን አግኝታ ያለ ኢትዮጵያ ለመኖር እችላለሁ ብላ መነሣቷን መረዳት እንችላለን። ኢትዮጵያም በበኩሏ ያለ ኤርትራ ለመኖር እንደምትችል መገንዘብ ችለናል። ቢሆንም ትብብር አስፈላጊ ነው። እንኳንስ ለኤርትራና ለኢትዮጵያ ቀርቶ ለማንም አገር ከጐረቤት ጋር መተባበር ይጠቅማል። የአውሮፓ፣ የኤሽያና የሌሎች አህጉር አገሮች በትብብር የት ደረጃ ላይ እንደደረሱ መገንዘብ አያዳግትም።

 

ኢትዮጵያና ኤርትራ የነፃነት ምልክት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ያውለብልቡ እንጂ ከድህነትና ከልመና ገና ነፃ አልወጡም። ብቻቸውን ሆነው የትም አይደርሱም። ከጅቡቲ፣ ሶማሊላንድ፣ ፑንትላንድና ከሶማሊያ ጋር በዲፕሎማሲና በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በንግድና በልማት፣ እንዲሁም በመከላከያ ዘርፎች መተባበር ይኖርባቸዋል። ለዚህ ሁሉ ተግባር አስተማማኝ መሠረት የሚሆነው፣ የኢትዮጵያና የኤርትራ በፌዴሬሽን መተሳሠር ነው። ይህንን ለማድረግ ይቻል ዘንድ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከመምጣቱ በፊት የነበሩትን ክፍላተ ሃገራት መልሶ በፌዴሬሽን ማዋቀር ተገቢ ይመስለናል።

 

ሁናቴው በዛሬው መልኩ ሊቀጥል አይችልም። ለውጥ ይመጣል። ለውጡ ግን የሰላም፣ የዕድገት፣ የእኩልነትና የአንድነት ኃይሎች የትብብር ውጤት መሆን ይኖርበታል።

 

ልማትን በተመለከተ አንዳንድ ጥናቶችን አድርጌያለሁ። የጥናቱ አስኳል የሚያተኩረው (1) እነዚህ አገሮች ለምን መተባበር እንዳለባቸው? (2) እንዴትስ ሊተባበሩ ይችላሉ? (3) በትብብሩስ ምን ያህል ለመጠቀም ይችላሉ? የሚል ነው።

 

ጥናቱን እንዳሳተምኩ በየቦታው እየተዘዋወርኩ ለአፍሪካ ቀንድ COMMUNITIES አቀርባለሁ። ስለትብብር ፕሮጀክቶች አሁንም ቢሆን ሰፋ አድርጌ መናገር እችላለሁ። ሆኖም መድረኩ አይደለም፣ የሌሎች ተናጋሪዎችንም ጊዜ መውሰድ ስለሚሆንብኝ እዚሁ ላይ አቆማለሁ።

በጥሞና ስለአዳመጣችሁኝ አመሰግናለሁ!!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ