Hillary Clinton at the African Union headquarters in the Ethiopian capital of Addis Ababa,
ታደሰ ብሩ

መለስ ዜናዊን የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ መሪ እንደሆነ አድርጎ በማቅረብ ሥራ ላይ የተሰማሩ የወያኔ ሹማምንትና ካድሬዎች፣ የዩ. ኤስ. አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስ ሂላሪ ክሊንተን በአዲስ አበባ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ያደረጉትን ንግግር እንዴት እንደሰሙት በአእምሮዬ ሳሰላስል ቆይቻለሁ። እናም የክሊንተንን ንግግር ሳነብ አንዳንድ የማውቃቸው የወያኔ ሹማምንት ንግግራቸውን እንዴት እንደሰሙት በምናቤ እየቃኘሁ ነበር።

 

ክሊንተን “በአሁኑ ጊዜ ከሰሃራ በታች ካሉ አገሮች መካከል ከግማሹ በላይ ዲሞክራሲያዊ፣ ህገ መንግስታዊና፣ ባለብዙ ፓርቲ አመራር አስፍነዋል” ሲሉ በምሳሌነት ኢትዮጵያን ይጠራሉ ብለው ወያኔዎች ሰፍ ብለው እንደሚጠብቁ እገምታለሁ። እሳቸው ግን ቦትስዋና፣ ጋናን፣ ታንዛንያ፣ ናይጄሪያ፣ ቤኒን፣ ማላዊ እያሉ ቀጠሉ።

 

በዚህ ጊዜ የወያኔ ሹማምንት “ምን ጉድ ነው? ኢትዮጵያ እሳቸው ዝርዝር ውስጥ የለችም እንዴ? ረስተዋት ይሆን?” እያሉ ሲቁነጠነጡ ይታየኛል። ስለኬኒያ ሲያነሱ “ኬኒያ ከደረሱ ወደ ኢትዮጵያም መዝለቃቸው አይቀርም” በሚል ትንሽ እፎይታ ተሰምቷቸው ነበር ይሆናል። ክሊንተን ግን ይባስ ብለው ከነውጥ ወደ ምርጫ ወደ ተሸጋገሩት ኒጀርና ጉየና አመሩ። ክሊንተን የአፍሪካ ዲሞክራሲ ውዳሴያቸው፣ በምርጫ ተሸንፎ “አልወርድም” ብሎ ያንገራገረ ተሸናፊ ፕሬዚዳንቷ ከተደበቀበት ጉድጓድ ተገዶ ወጥቶ ወደ ወህኒ ወደ በተላከባት ኮት ዲቯር አጠቃለሉ።

 

በስብሰባዎች፣ በሬድዮና በቴሌቪዥን የሚደግሙትን “ዲሞክራሲያችን” በክሊንተን ንግግር ውስጥ ማጣታቸው የወያኔ ሹማምንትን፣ ካድሬዎችንና የወያኔ ጋዜጠኞችን አንጀት የሚበጥስ ነገር ነው።

 

ሚስ ክሊንተን ዲሞክራሲን ለማስፈን የተጉትን አገሮች አሞግሰው ከጨረሱ በኋላ ደግሞ አንባገነኖቹን የሚሸነቁጥ ትችታቸውን አስከተሉ።

 

ነገር ግን ... ይህንን [የዲሞክራሲ] እድገት እያወደስን ባለንበት የአሁኗ ወቅት ላይ እንኳን ሳይቀር ... እጅግ ብዙ የሆኑ የአፍሪካ ህዝቦች ትተዋት ስለሚያልፏት አገራቸው ሳይሆን በስልጣን ላይ ስለሚቆዩበት ጊዜ እርዝማኔ በሚያስጨንቃቸው፤ ለብዙ ዓመታት በስልጣን ላይ በቆዩ ገዚዎች ስር ናቸው። አንዳንዶቹ ይባስ ብለው በዲሞክራሲ እንደሚያምኑ ይናገራሉ - ዲሞክራሲ በራሳቸው የአንድ ወቅት ምርጫ ትርጓሜ።

 

ይህ አካሄድ ግን በአህጉሪቷም ሆነ በውጭ ተቀባይነት እያጣ ነው። በሰሜን አፍሪቃና መካከለኛ ምሥራቅ እየሆነ ያለውን ተመልከቱ። ለዓመታት ድምፃቸው ታፍኖ በአምባነገነን አገዛዞች ስር የነበሩ ህዝቦች አዲስ አመራር እየጠየቁ ነው። ዛሬ አፋቸውን ሞልተው በመናገር መብቶቻቸውን ተግባራዊ እያደረጉ ነው። የሥራ እድሎች በጠበቡበት፤ ጥቂቶች ብቻ በልጽገው ብዙሃኑ እየተጎሳቆለ ባለባቸው አገሮች - በተለይ ወጣቶች - ብሶቶቻቸውን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ለውጦችን በመፈለግ እየገለጹ ነው።

 

መልዕክቶታቸው ለሁላችንም ግልጽ ናቸው! ከእንግዲህ የቀድሞው ዓይነት አገዛዝ ተቀባይነት የለውም። ጊዜው መሪዎች ለህዝባቸው ተጠያቂ የሚሆኑበት ነው። መሪዎች ህዝባቸውን ማክበር ይኖርባቸዋል። ጊዜው መሪዎች የህዝቦቻቸውን መብቶች እንዲያከብሩ፤ የህዝቦቻቸውን ኑሮ እንዲያሻሽሉ ግድ ይላቸዋል። አለበለዚያ ግን መሰናበቻቸው ደርሷል!!!

 

እያንዳንዱ የዓለም አገር ከዚህ የዲሞክራሲ ንቅናቄ መማር ይኖርበታል። በተለይ ደግሞ ስልጣን ላይ የሙጥኝ ያሉ፤ ማናቸውንም ተቃዉሞ እየደፈጠጡ ያሉ፤ በዜጎቻቸው ኪሳራ እራሳቸውን እያከበሩ ያሉ የአፍሪቃ መሪዎች ከዚህ ከአረቦች ታላቅ መነሳሳት ትምህርት መውሰድ አለባቸው። ለእነዚህ ገዢዎች መልዕክታችን ግልጽ ነው። ለዚህ ታሪካዊ ወቅት እራሳችሁን አብቁ! የህዝባችሁን ተስፋና ምኞት አሳኩ! ወጣቶቻችሁ የራሳቸውን እድል እንዲፈጥሩ እርዱ! አለበዚያ ... ህዝባችሁ ነፃነትና መልካም ኑሮ አይገባውም የምትሉ ከሆነ፤ ሁሉንም - ወንዱም ሴቱም - በእኩልነት መኖር እንዳለበት የማታምኑ ከሆነ፤ ዜጎች ተከብረው፣ ሰርተው መኖር የማይችሉ ከሆነ ... እናንተ በተሳሳተ የታሪክ ጎዳና ላይ ናችሁ! ጊዜ ይህን ያሳያችኋል!

 

ምን ጉድ ነው? የ97ቱ የቅንጅት የምርጫ ቅስቀሳ መሰለሳ!!!!

 

ክሊንተን ሁለተኛውን አጀንዳቸውን ጀመሩ - ልማት! “በልማት ኢትዮጵያ ካልተጠራችማ ማን ሊጠራ? በልማት ኢትዮጵያ ካልተወደሰች ማን ሊወደስ ነው?” እያሉ ወያኔዎች ማዳመጣቸውን ቀጥለዋል። ሆኖም ግን አሁንም የተጠበቀው ሳይሆን ቀረ። የክሊንተን የመጀመሪያው ዓረፍተ ነገር ብቻውን እንጥል የሚያስወርድ ሆነ። በዓለም በከፍተኛ ፍጥነት እያደጉ ካሉት አስር አገሮች ውስጥ ስድስቱ ከሰሃራ በታች ይገኛሉ።

 

በአፍሪቃ ውስጥ በኢኮኖሚ እያደገ ያለ አገር ያለ ስለማይመስላቸው ይህ ዓረፍተ ነገር የወያኔ ሹማምንትን በጣም እንደሚያበሳጫቸው እርግጠኛ ነኝ። ለዚያውም ያለ አብዮታዊ ዲሞክራሲ እንዴት ይታደጋል? ይህ ለእነሱ የማይመስል፣ የማይሆን ነገር ነው።

 

ክሊንተን ንግግራቸውን ቀጠሉ። በፍጥነት በማደግ ላይ ያሉትም ቢሆኑም የአንድ ወይም ጥቂት ምርቶች ጥገኛ መሆናቸውን ገለጹ። ወጣቶች ተምረው ሥራ ማግኘት አለመቻላቸውን አወሱ። የቱኒዚያውን ወጣት አስታወሱ። በኢኮኖሚውም መስክ ደህና ውጤት አስመዝግበዋል ያሏቸውን ዛምቢያን፣ ማሊን፣ ጋናንና ሩዋንዳን አወደሱ። አሁንም ኢትዮጵያ በዝርዝራቸው ውስጥ የለችም።

 

ክሊንተን ንግግራቸውን እያገባደዱ ነው። ኢትዮጵያን ፈጽሞ ሳያነሱ ተሰናበቱ እንዳይባል የጤና አገልግሎችን በተመለከተ 30, 000 የጤና ባለሙያዎች በገጠር መሰማራታቸውን አወደሱ፤ በሱዳን የአቤይ ግዛት ላይ ኢትዮጵያ እየተጫወተች ያለውን የገላጋይነት ሚና አደነቁ። ይህችን ብቻ ጣል አድርገው ወደ ሌሎች አናዳጅ ጉዳዮች ሄዱ ...

 

ጋዳፊ!!! ጋዳፊን ብትወዱትም፤ በገንዘብ ቢረዳችሁም መሄጃው ደርሷል አሏቸው። ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉም እንደገና ወደ አረብ አብዮት ተመልሰው መጡ። ወያኔዎች “አይ መከራ! እኚህ ሴትዮ ዛሬ አልቀቁንም!” እንደሚሉ መገመት ቀላል ነው።

 

ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት የአረብ መነሳሳት የአዲስ ነገር መምጣት አብሳሪ ነው። በአረብ አገራት እየጎመራ ያለው ነገር በአፍሪቃም ህዝቦችም ዘንድ ለዲሞክራሲ ባለው ቁርጠኝነት፤ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር፤ የትምህርትና የጤና አገግሎቶች በማስፋፋት ረገድ፤ እና የወጣቶችን ፍላጎቶች ለሟሟላት በሚደረግ ጥረት አማካይነት ስር እየሰደደ ነው።

 

አሉ። የአረቦች አብዮት ወደ አፍሪቃም እየመጣ ነው ማለታቸውም አይደል? ...

 

እኛ እዚህ ካላችሁ አገሮች ሁሉ የሚመጡ ስደተኞችን እንቀበላለን፤ ብዙዎቹ በአሜሪካ የፈጠሩትን ስኬት እናያለን። ያም ሆኖ ግን እዚህ የምሰራውን መልካም ነገር ምነው በራሴ አገር ውስጥ በሰራሁ የማይል አንድም አፍሪካዊ ስደተኛ አላጋጠመኝም። ምናለ በሃገሬ፣ በህዝቤ መካከል፤ በቤተሰቦቼ መካከል፤ የሚበሉትን እየበላሁ፤ የአገሬን አበቦች እያሸተትሁ በኖርኩ የማይል አፍሪቃዊ አታገኙም። እኔ ለአፍሪቃዊያን ይህችን አፍሪቃ ማየት እሻለሁ፤ የወደፊቱ ዓለም እድልም ያለው እዚህ ነውና።

 

ክሊንተን ንግግራቸውን ጨረሱ። የወያኔ ሹማምንት፣ ካድሬዎች እና የወያኔ ጋዜጠኞች ጨሱ!!!!

********

ሂላሪ ክሊተን በዲፕሎማሲ መስክ ባልተለመደ ቀጥተኛነት በመናገራቸው በጣም ረክቻለሁ፤ተደስቻለሁ። መባል ከነበረበት ነገር ውስጥ ቀራቸው የምለው የለኝም። ሁሉንም ብለውታል። የቀረው ነገር ቢኖር ተግባር ብቻ ነው።

 

የተግባር ፓለቲካ ውስብስብነት ደግሞ እረዳለሁ። ስለሆነም ክሊንተን ዛሬ ይኸን ተናገሩና ነገ መለስ ዜናዊን ከጋዳፊ ጋር በእኩል ሚዛን ያስቀምጡታል ብዬ የማምን የዋህ አይደለሁም። በተግባር፣ በአሜሪካ ፓለቲካ ውስጥ ለጊዜው ምንም ለውጥ አናይ ይሆናል።

 

ሆኖም ግን የአምባነገኖች ምሽግ መናድ ጀምሯል። ከአሁን በኋላ መለስ ዜናዊ የአሜሪካ ወዳጅ የሚሆነው ሁነኛ ተለዋጭ እስከሚገኝ ድረስ ብቻ ነው። ለህዝባችን ሁነኛ አማራጭ መፍጠር ያለብን ደግሞ እኛ ነን። ኃላፊነቱ የኛ ነው።

 

ከክሊንተን ንግግር ውስጥ የቀረው ተግባራዊ እርምጃ ነው፤ እሱ ደግሞ የኛ ሥራ ነው።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!