ፊታውራሪ ተክሌ  (ኦታዋ - ካናዳ)

ሲጀምር፡ ሰዎች ምን ይሉታል? አዲሱና ይመር።

ይመር የእግዜር በግ ነው። ይመር የእስልምና እምነት ተከታይ ስለሆነ የኣላህ በግ ነው ብል ይሻላል። የክርስትናው አብርሀም የእስልምናው ኢብራሂም ከሆነ፡ የክርስትናው ይስሀቅ፡ በእስልምናው ውስጥም ይኖራል ብዬ በማሰብ ነው። “እኔ የምልህ፡ አሁን ሰዎቹ የብርቱካንን ግብዣ ተቀብለዋል፡ መጀመሪያ እናንት ለምንም ምክንያት ተቋቋሙ፡ አሁን ግን፡ ቀልዳችሁን ትታችሁ የስፖርት ፌደሬሽኑን ማጠናከሩ አይሻልም እንዴ?” አለኝ ይመር ከሲያትል። በስልክ ነው። “አልገባኝም እስኪ ድገምልኝ” አልኩት። አብራራልኝ። (ይህ ታሪክ እውነት ነው። ስሙ ግን የፈጠራ ነው።)

 

ይመርን ጨምሮ፡ ብዙ ሰዎች፡ የኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስ ማህበረሰብ በሰሜን አሜሪካ (ከዚህ በኋላ “የኢትዮጵያዊነት ውርስ” እየተባለ ይነበብልኝ) http://ethiopianheritagesociety.org/ ፡ ራሱን ለቻለ የተቀደሰ ዓላማ የተቋቋመ ማህበር ሳይሆን፡ በኢትዮጵያዊያን ስፖርትና ባህል ፌደሬሽን በሰሜን አሜሪካ ውስጥ፡ የወ/ት ብርቱካንን ሚደቅሳን የክብር እንግድነት ግብዣ አላግባብ መሰረዝና፡ ፌደሬሽኑ ከአላሙዲን ጋር ያለውን/የነበረውን ቁርኝት ተከትሎ፡ ፌደሬሽኑን ሀሳቡን ለማስለወጥ፡ ወይንም ለአፍራሽነት ወይንም ለስልት ብቻ የተቋቋመ፡ የእልህ ድርጅት አድርገው ወስደውታል። ይሄ አይነቱ አቋም የሚንጸባረቀው ደግሞ እንደይመር አይነት ባሉ ሰዎች ዘንድ ብቻ አይደለም። የአሜሪካን ድምጽ የአማርኛው ዝግጅት ባልደረባ አዲሱ አበበም ተመሳሳይ ጥያቄና ስሜት አለው።

 

የይመርንም የአዲሱንም ስሜት እረዳለሁ። አዲሱ አበበ፡ ለአመታት ሲዘግበው የኖረው ታሪካዊ ድርጅትና ዝግጅት እንዲህ እንደዋዛ እንዲዳከምና እንዲከስም ካለመፈለግ የመነጨ ነው። ይመርም ያዲሱን ያህል ባይሆንም እዚህ ሰሜን አሜሪካ ከዘለቀ ግዜ ጀምሮ አልፎ አልፎ ሲቋደሰው የኖረው የኢትዮጵያዊያን ስፖርት ፌደሬሽን በሰሜን አሜሪካ፡ ሲሆን ሲሆን ስህተቶች ካሉበት እንዲታረምና እንዲቀጥል እንጂ፡ እሱም እንደ አዲሱ አበበ፡ ይሄ አንጋፋ ድርጅት እንዲከስም ስላልፈለገ ነው። ለኔ የሁለቱም ሀሳብና ምኞት ጤናማ ነው። ይሁን እንጂ በዚህ የኢትዮጵያዊነት ውርስ ድርጅትን እንደ ስፖርት ፌደሬሽኑ ስጋት አድርጎ የማየት ስሜት ውስጥ መታረም ያለባቸው መሰረታዊ ስህተቶች አሉ። ስለዚህም፡ የኛ የሆኑም የኛ ያልሆኑም ሰዎች፡ አንደኛ ቀድሞውንም በራሳችን ህይወት ስላልተፈጠርን፡ ሁለተኛ፡ የብርቱካን ግብዣ ስለተመለሰ፡ ሶስተኛም ደግሞ ሰሞኑን ፌደሬሽኑ ከአላሙዲን ጋር ያለው የስፖንሰርሺፕ ወዳጅነት ስለተቋረጠ እና፡ ስፖርት ፌደሬሽኑ መልሶ የህዝበ ስለሆነ፡ ባስቸኳይ የድርጅታችንን የምስረታ ሰነድ ቀዳደን ወደ ቆሻሻ ቅርጫት እንድንጥልና፡ ጓዛችንን ሸክፈን አትላንታ እንድንገባ የሚሰጡትን አስተያየቶችን በተመለከተ፡ ትንሽ ማብራሪያዎችን መስጠት ወደድኩኝ።

 

ድርጅታችን የሚለውን ይበል። ይሄ ማብራሪያ የኔን ሀሳብ ብቻ ነው እንጂ የኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስን ድርጅት አይወክልም። እንደውም ይሄንን ጽሁፍ ብዙዎቹ ድርጅታዊ አጋሮቼ ላይወዱልኝ ይችላል። እንደአባል እስከማውቀው ድረስ፡ የኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስ ማህበረሰብ በሰሜን አሜሪካ አቋም፡ በማናቸውም መልኩ አሉታዊ ወደሆነና ገንቢ ወዳልሆነ ንግግርና አታካራ ውስጥ እንደማይገባ፡ እንዲያውም በዚያ መልኩ የሚመጡትን በቀናነትና በአዎንታዊ መልኩ ማስተናገድና፡ በተቻለ መጠን ከማናቻውም እንካ ሰላንቲያ መራቅ ቢሆንም፡ እኔ ግን ባንድ በኩል በመደራጀት ባምንም፡ በሌላ በኩል ግን አንዳንድ መሰረታዊ መብቶቼን የድርጅት ጣጣ እስረኞችና ታጋቾች ማድረግ ስለማልፈልግ፡ መብትን መሰረት ያደረገ ማፈንገጥ ስለሚያምርብኝ፡ ይሄ ጽሁፍ ሀሳቤን በነጻነት የመግለጽ መብቴን ተጠቅሜ የምጽፈው ጽሁፍ ነው። ስለዚህ ይሄ ጽሁፍ፡ በምንም መልኩ የኔና የኔን ብቻ እንጂ የኢትዮጵያዊነት ውርስ ማህበረብን ሀሳብ አይወክልም።

 

ትንሽ ወደኋላ፡ ታሪክ አይደል?

 

ወደ ፌደሬሽኑ ከመዝለቄ፡ ከዚያም ስለኛ ከማውራቴ በፊት ስለዚህ ሰው ማውራት አለብኝ። የዛሬ አስራዘጠኝ አመት አካባቢ መሰለኝ፡ በወንድሞቼ ቁምጣና፡ በወላጆቼ ቁጣ ዱብ ዱብ በምልበት እድሜ ላይ፡ ይሄ የመከራችንና የጭቅጭቃችን አንዱ ምሰሶ ተወለደ። አላሙዲን። አላሙዲን ሸራተንን ሊገነባ ነው፡ አላሙዲን ስቴዲየም ሊገነባ ነው፤ አላሙዲን እንዲህ ሊያደርግ ነው ሲባል ውስጤ ተስፋ ሲሞላበትና ሲኮራበት ትዝ ያለኛል። አላሙዲን ጻድቅ፡ ከጻድቁ ተክልዬ የላቀ ጻድቅ፡ ያኔ ድቁና ለመቀበል ዘጥ ዘጥ የምልበት ሰዓት ስለነበርና ጽድቅን ሁሉ የምለካው በጳጳሳት ቅድስና በመሆኑ፡ አላሙዲን፡ ከጳጳሳት ሁሉ የጸደቀ ጻድቅ፡ የድህነታችንን ደብዳቤ ሊሰርዝ የመጣ፡ የአምላክ መልእክተኛ ይመስለኝ ነበር። እነሆ ከአመታት በኋላ ግን እየበሰልኩ፡ እንዲሁም በአላሙዲን እየከሰልኩ መምጣት ጀመርኩ። አላሙዲ፡ እኚያ ከድህነት ያወጡናል፡ አገራችንንም እድገት በእድገት፡ ወርቅ በወርቅ ያደርጉልናል ብየ በልጅነት ያሰብኳቸው ሰው፡ ሼህ ሞሀመድ አላሙዲን፡ እነሆ የኢትዮጵያ የጭቆናና የብዝበዛ ምሳሌ ሆኑ። የማይገነቡትን ማጠር፡ ያጠሩትን ማሳደር፡ በለውዝ ዋጋ የገዙትን በወርቅ ዋጋ መቸብቸብና ኢትዮጵያ ሲገቡ የነበራቸውን የአምስት መቶኛ የባለሀብትነት ደረጃ፡ በኢትዮጵያ ሀብት እነሆ ወደ ሀምሳኛ ከፍ አደረጉት። ያ በራሱ ባልከፋ፡ ይለይላችሁ ብለው በንብም መናደፋቸው ነው ያመመን።

 

ስለአላሙዲን ማውራት የዚህ ጽሁፍ ዋንኛ አላማ ባይሆንም፡ ዋንኛው የስፖርት ፌደሬሽኑን ውዝግብ ያጎላው ያላሙዲን ንክኪ ስለሆነ፡ ስለአላሙዲን ተጨማሪ ነገር ማክል ተገቢ ሆኖ ስላገኘሁት ነው። ስለአላሙዲን ሲነገር ከማይመቹኝ አያሌ ነገሮች ውስጥ አንደኛው ይሄ ኢትዮጵያ ላይ ንዋየ መዋእላቸውን የሚያፈሱት በአገራቸው ፍቅር ስለሚቃጠሉ፡ ነገር ግን በኪሳራ፡ ያለትርፍ ነው የሚለው ነው። ይሄ ስህተት ነው። የአላሙዲን አንዱ ድርጅት ብቻ፡ ሚድሮክ፡ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር፡ በ1990 ዓ.ም. በ170 ሚሊዮን ዶላር ከገዛው የለገደምቢ የወርቅ ክምችት ብቻ፡ በአስር አመት ብቻ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ወርቅ ሲሸጥ፡ ያገኘውን 500 ሚሊዮን ዶላር ስንጥቅ ትርፍ  እዚህ ጋር ይመልከቱት። http://www.midroc-ethiotechgroup.com/CEO'S OFFICE (CORPORATE)/NEWS/CEO'S MESSAGES/CEO'S MESSAGES-53-CORPORATE RESPONSIBILITY.htm በዚህ ሁሉ ግዜ ውስጥ፡ ላካባቢው ህዝብ፡ ባስር አመት፡ አስር ሚሊዮን ብር ተወርውሮለታል ይላል የሚድሮክ ድረ-ገጽ። አላሙዲን ኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሰው ስላተረፈው ነው። አለቀ።

 

እንጂ የህንዱ ካራቱሪ ባለቤትም እኮ ትንሽ ቆይቶ እናቴ ከወለጋ ነች ሊል ነው። ወይም ከሀረሪ። ወይም ትንሽ ከፍ ብሎ ከቅድመ-አያቱ ያደርገዋል። እንደውሙ ህንዶች በ19ኛው ክፍለዘመን ከእንግሊዝ ጋር ሆነው አጤ ቴዎድሮስን ሊወጉ ሲመጡ የቀሩ ኢትዮጵያዊ ነን፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ ውስጥ መዋእለ-ንዋይ የማፈሰው በኢትዮጵያዊነቴ ምክንያት ነው ሊል ይችላል። አንድ ሄክታር መሬት በሳምንት 100 ብር ነው፡ የተባለው? ያንን አናይም። ያ ሁሉም ይሁን። ይጠቀሙ። አላሙዲን ይደጉ። ይባስ ብለው፡ የበለጠ ያበሳጨኝ ግን፡ እኚህ ሰው እኛን ካሰደደ ስርአት ጋር ቆመው አገሪቱን የሚወጉ፡ የኛንም ስደት የሚያራዝሙ ንብ መሆናቸው ነው። ኢህአዴግ የምርጫ አርማ የሆነውን ንብ ለብሰው ሲሰለፉና ምን ታመጣላችሁ ሲሉን ኖሩ። ይሄን ለምን አነሳሁት? ምንስ ይጠቅመናል?

 

ፌዴሬሽኑ ኛ ነው፡ ሁሉም የኛ ነው፡ ግን የኛ እስከሆነ ድረስ ብቻ ነው

 

የኢትዮጵያዊያን ስፖርት ፌደሬሽን በሰሜን አሜሪካ፡ ኳስ የሚጠለዝበት፡ የስፖርት ብቻ ድርጅት ቢሆን ግድ የለኝም። ለኔ ፌደሬሽኑ ስፖርት ብቻ አይደለም። ከስፖርትም በላይ ነበር። እንጂ ለኳስ ለኳስማ እነ ቼልሲ፡ እነ ማንቼ፡ እነ አርሶናል፡ እነ ማድሪድ አሉልን፡ እነ ባርሳ አሉ። ፈደሬሽኑ የአንድነትም ምሳሌ ነበር። ይሄ የአንድነት ምሳሌ ደግሞ አንድነታችንን ሊሸረሽሩ የሚችሉና እኛን ያሰደዱንን  ሀይሎችን ማራቅ አለበት የሚል ጽኑ እምነት አለኝ። እንደእኚህ ያለ የጭቆና ምሳሌ የሆኑ ሰውና ድርጅታቸው፡ የስደተኛው ነው የሚባለውን የስፖርት ፌደሬሽን የውሳኔ ማእከል ከሆኑ፡ ፌደሬሽኑ የኔ መሆኑ ያቆማል። ግልጽ ነው። የተወሳሰበ አይደለም። በዚህ ሰሞን ይፋ የወጡት ደብዳቤዎች የአላሙዲንን ስንከራከርበት የቆየነውን ጣልቃ ገብነት ቁልጭ አድርገው ስለሚያሳዩ በሳቸው ጣልቃ ገብነት ላይ ብዙ የምንከራከር አይመስለኝም።[1]

 

አላሙዲንን ይሁን እንባ ጠባቂያቸው አብነት ገብረመስቀል፡ ሀብት ላፈሩበት ስርአት አዳሪዎች ናቸወ። ፌረዴሽኑም ከነዚህ ሰዎች ጋር ከተዋዋለና የእነሱ የክብር አባልነት ሳያንስ፡ እነሱን ሊያስከፋ ይችላል ብሎ በዴሞክራሲያዊ ስርአት የተወሰነ ውሳኔ ኢዴሞክራሲአዊ በሆነ መንገድ ከሻረ፡ እነሱን ያገኛል፡ እኛን ግን ያጣል ማለት ነው። ለዚህም ነው፡ ባንድ በኩል ፖለቲካ ውስጥ የለንበትም እያሉ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህን አሁን አገራችን ውስጥ ያለው ኢፍትሀዊ አገዛዝ የፈጠራቸውን በዝባዦች ጭኖ ለመጓዝ ሲሞክር፡ የብርቱካን ጉዳይ ተጨማሪ ሆኖ የመጣው። ለኔ፡ ለፊታውራሪ ተክሌ፡ ወደታች እንደማስረዳው፡ አንድነታችንን የሚፈታተን ከሆነ ብርቱካንም በእግር ኳስ መድረኩ ላይ ባትጋበዝ ግድ የለኝም። ነገር ግን ያ የሚወሰነው የነአላሙዲን ፊት በማየት መሆን የለበትም። በዚህ ኢትዮጵያዊያን 28 አመት ደክመው ባቆሙት የራሳችን ድርጅት ውስጥ፡ የታየው ያ አይነት ብልሹና ኢፍትሀዊ አሰራር፡ ለኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስ ድርጅት በፍጥነት መመስረት የራሱን አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ባይካድም፡ “የለም እኛ ብቻ ነን ኢትዮጵያን እንድንወክል የተሰየምን የሚል ኢህአዴጋዊ ሀይል” ካልመጣ በስተቀር፡ ማንም ኢትዮጵያዊነትን መሰረት አድርጎ ድርጅትና ማህበር፡ እድርምና እቁብ ሊመሰረት ይችላል። ያ ድርጅት፡ መገምገም ያለበት በተቋቋመበት አላማ፡ በሚሰራውና በማይሰራው ስራው እንጂ፡ የሱ መፈጠር በሌሎች ቀድመው በተፈጠሩ ድርጅቶች ላይ በሚኖረው አንድምታ አይደለም። አስኪ አስቡት፡ ኢህአፓ ግንቦት ሰባት ለምን ተቋቋመ ብሎ ሲቆጣ። ወይንም መኢአድ፡ ኢዴፓን ለምን ተፈጠረ ብሎ ሲናደድ። ወይንም መድሀኔዓለም ቅዱስ ገብርኤል ለምለ ተቋቋመ ብሎ አዙን ልቀቁኝ ሲል። በኢትዮጵያ ጉዳያ ላይ ማንም ሞኖፖሊ ያለው ድረጅትም የለም። ይሄ ኢህአዴጋዊ አስተሳሰብ ነው። እኔ ብቻ ነኝ አውራ፡ ከኔ በቀር ይህቺ አገር ትጠፋለች፡ ብሎ ያለ ያው ኢህአዴግ ነው።

 

እንደማብራሪያ፡ እንድታውቁት ያህል

 

አንደኛ ነገር፡ ብዙዎቹ የኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስ ማህበረሰብ መስራቾች ከሀገራቸው በስደት ርቀው የሚገኙ ሰዎች እንደመሆናቸው መጠን፡ በአገራቸው ያለው ኢሰብአዊ አገዛዝ ያሳስባቸዋል። ስለዚህም ማንም ስደተኛውን ኢትዮጵያዊ የሚወክል ድርጅት የስደተኛውን ስሜት ማንጸባረቅ አለበት ብለው ቢያምኑና፡ ስፖርት ፌደሬሽኑም ይሁን ሌሎች ድርጅቶች ከዚያ በተቃራኒ ከተጓዙ፡ ያንን ተቃውመው ቢነሱ፡ ያ ማንም የማይነካው መብታቸው ነው። ባንድ በኩል ያ ቁጣ የሚመነጨው፡ የስፖርት ፌደሬሽኑ ትናንተም የኛ ነበር፤ ዛሬም የኛ ነው ከሚል መሰረታዊ አስተሳሰብ ነው። ነገር ግን የስፖርትም ይሁን የትውፊት ማህበረሰብ የኛ ሆኖ የሚቀጥለው፡ አንድ መሰረታዊ ቅድመ ሁኔታ ከተጠበቀ ነው። ይኸውም “ድርጅቱ የኛ ነው” የሚሉትን ሰዎች ስሜትና እምነት እስካንጸባረቀ ድረስ ብቻ ነው። ከዚያ በተረፈ ግን፡ ባንድ በኩል ከፖለቲካ ውጪ ነን እያሉ በሌላ በኩል ግን፡ ስልጣን የያዙ የፖለቲካ ሀይሎችን ጥቅምና ክብር፡ እንዲሁም ጥበቃ፡ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለማስጠበቅ የሚተጋ ከሆነ፡ ያንን ድርጅት መቆጣቱና በተለያዩ መልኩ መኮርኮም ሳይሆን፡ ዝም ብሎ ማለፉ ነው ሀጢያቱ።

 

ይሄ አስተሳሰብ፡ ለስፖርት ፌደሬሽኑ ብቻ ሳይሆን፡ ለማናቸውም ህዝባዊ ድርጅቶች የሚሰራ፡ ኢትዮጵያ ካለው አገዛዝ ጋር ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚነት በተሰለፉትም ላይ የሚሰራ ነው። ለምሳሌ እኔ በግሌ የብርቱካን በሀይማኖትም ይሁን በባህል ድርጅቶች ውስጥ በክብር እንግድነት መጋበዝ አይመቸኝም። ስለዚህ ብርቱካን በክብር እንግድነት ስትጋበዝ፡ ጠቋሚውን ሰው ተንኮለኛና ነገረኛ አድርጌ ነው የተመለከትኩት። ምክንያቱም ብርቱካንን የምናውቃት በፖለቲከኛነት ነው። ብርቱካን እንደዳኛ ስዬ ላይ በወሰነችው ውሳኔ ብትደነቅም፡ ብትወደስም፡ የዳንነት ህይወቷ ብዙም አይማርከንም። ብርቱካን ብትታሰረም፡ ብትጎበኘንም እንደፖለቲከኛ ነው እንጂ እንደአርቲስት ወይንም እንደ ስፖርተኛ አይደለምና የክብር እንግድነት ግብዣዋ ጭቅችቅ መፍጠሩ አያስደንቅም። ነገር ግን መጽሀፈ ቁልቁሉ ብዙሀን ይመውኡ እንዳለው፡ የብዙሀኑ ውሳኔ የሰሷ በክብር እንግድነት መጋበዝ ከሆነ፡ የስፖርት ፌደሬሽኑም ይሁን ሌሎች ፡ የስደተኛው ድርጅቶች ብርቱካንን አይደለም፡ መለስንም አናመጣልን ካሉ፡ ለመቀበል መዘጋጀት አለብንና፡ የብርቱካን ግብዣ መጋበዝ ባይማርከንም፡ የብርቱካን መጋበዝ ግን ፍትሀዊ ባልሆነ መንገድ ሲቀለበስ፡ የመጀመሪያው የቅልበሳው ተቃዋሚ እኔ ነኝ። ምክንያቱም፡ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ፡ ወይንም ቦርድ ውሳኔ ብርቱካን ትምጣ ሆኖ ሳለ፡ የለም እነአብነት ገብረመስቀልን እነ አላሙዲንን ወይንም ሌሎች ስውር የበላይ ጠባቂዎችን ያስከኮርፍብናል ተብሎ የብዙሀኑ ውሳኔ የሚሻር ከሆነ፡ ያ ውሳኔ ፍትሀዊ አይደለም። ወኔን ይፈታተናል። ዘራፍ ያሰኛል። የዚህ አይነት አሰራር ኢትዮጵያ ውስጥ የተለመደ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን፡ “ይሄ አሜሪካ ነው” ይላሉ ፈረንጆቹ። ወይንም ካናዳ። ስለዚህ ይሄንን አሰራር ተቃውመው የሚነሱ ሁሉ የግድ ጠላት ናቸው ማለት አይደለም። ወዳጆችም ነው። ሚዛናዊና አስተዋይ ወዳጆች።

 

ሌላን ድርጅት ለመቃወም ሲባል ብቻ ሌላ ድርጅት ማቋቋም ገንዘብም ግዜም ይበላል። ለዚያውም በዚህ ገንዘብና ጊዜ ወርቅ በሆኑበት ሰሜን አሜሪካ። እልህና ቁጭት አንድ ታሳቢ ነጥቦች ሊሆኑ ይችላሉ። ብቻቸውን ግን የትም አያደርሱም። ስለዚህ ተጨማሪ መሰረታዊ የምስረታ ዓላማና ፋይዳ መኖር አለበት ማለት ነው። የኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስ ማህበረሰብም፡ በዚያ ሰሞን በነሀሴ በብርቱካን መጋበዝ ጉዳይ ላይ የተፈጠረው ጭቅጭቅ እንደተጨማሪ ነዳጅ ቢያቀጣጥለውም፡ ቀድሞም ቢሆን፡ የኢትዮጵያዊነት መሸርሸር፡ የኢትዮጵያዊነት መተርተር፡ የኢትዮጵያዊነት መሸበር፡ የኢትዮጵያዊነት፡ መቀበር፡ የኢትዮጵያዊነት መጭበርበር፡ የኢትዮጵያዊነት መሰበር፡ ባሳሰባቸውና ውስጣቸውን ሲበላቸው በቆየ ሰዎች ጠንሳሽነት፡ ቋሚ ለሆነ፡ ኢትዮጵያዊነትን ለሚያራምድ ዓላማ የተመሰረት ድርጅት እንጂ፡ በነሀሴ የተፈጠረን ጸብ በመስከረም ለመቋጨት የተጠነሰሰ ሴራ አይደለም። እነሆ ለምንም ይመስረት ለምንም፡ የዚህ ድርጅት መፈጠር በስፖርት ፌደሬሽኑም ይሁን በሌሎች አካባቢዎች የራሱ የሆነ አዎንታዊ ተጽእኖ ፈጥሯል። ቢያንስ የስፖርት ፌደሬሽኑ ቤተሰቦች፡ ፌደሬሽኑ 28 አመት ከተኛበት እግር ኳስ ብቻ ወጥቶ፡ ዘንድሮ ሌሎች እንደ ሩጫ ያሉ ባህላዊ ጫዋታዎችንና፡ ዝግጅቶችን እንዲያካትት ሆኗል። የብርቱካን ውሳኔ እንዲመለስ፡ የአላሙዲን ተጽእኖም እንዲቀነጠስ ሆኗል። ሸራተንም ቀስ ብሎ ከድረ-ገፁ ላይ ይነሳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ማንም ይያዘው ማን፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ መጨከን ግን ይከብደኛል። እሱ ይቀመጥ። የሆነ ሆኖ፡ የኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስ ድርጅቱ መመስረት፡ ለፌደሬሽኑም ህልውናና አቋም መጥራት የራሱ የሆኑ አዎንታዊ አስተዋጽኦዎች አምጥቷል፡ እንጂ እንደ ተቀናቃኝ ድርጅት መታየት የለበትም።

 

የኢትዮጵያዊነት ውርስ ድርጅት ሌላ፡ ስፖርት ፌደሬሽኑ ሌላ፡ አንዱ ለስፖርት አንዱ ለትውፊት

 

ሶስተኛና ከላይኛው የሚቀጥለው፡ ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለየቅል እንዲሉ፡ (እርግጠኛ ነን፡ ማነው ዱባ ማነውስ ቅል የሚሉ አይጠፉም)፤ የኢትዮጵያዊነትን ትውፊት ለማስጠበቅ የተቋቋመው የውርስ ድርጅት፡ የተቋቋመበት ዓላማና የሚሸፍናቸው የዝግጅት አይነቶች ከስፖርት ፌደሬሽኑ ዝግጅቶች የሰማይና የምድር ያልህ የተራራቁ ናቸው ባልልም፡ የዱባና የቅል ያህል የተለያዩ ናቸው። ምናልባት ከውርስና ቅርስ ማህበረሰቡ ምስረታ ጋር በተያያዘ ከሚቀርቡት ትችቶች ወደ እውነት የተጠጋውና አጥጋቢ መልስ ያልተሰጠበት፡ የቀኑ መደራረብ ሳይሆን መቀራረብ ጉዳይ ነው። እሱም ቢሆን፡ የሚደራረበው ባንድ ቀን፡ የሚቀራረበው ባንድ ሳምንት ነው። እኛ እሁድ ዲሲ ስንዘጋ፡ ስፖርት ፌደሬሽኑ አርብ አትላንታ ይከፍታል። ቢደራረብም እንኩዋን፡ የኛ ዓላማ ምን ይሁን ምን በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውን ዘንድሮ አትላንታ፡ ለከርሞ ደግሞ ሎስ አንጀለስ፡ ከዚያም ወደ ዳላስ ቢሄዱ፡ ዘወትርም ቢሆን እዚያው ዲሲና አካባቢው የሚቀመጡ፡ አያሌ ኢትዮጵያዊያን አሉ። እኛ ያለምነው ያንን ቀሪውንና ኗሪውን የዲሲና አካባቢው፡ እንዲሁም የሰሜን አሜሪካ ኢትዮጵያዊ መሰረት አድርገን ከአገራችን ውጪ እንደ አገር እንደ አድባር የሚያገለግል ተቋም መገንባት ይመስለናል። እንጂ ልንሻማ ያሰብነው ገበያም ይሁን አዝመራ የለም። የኔ ቢጤ ትርፍራፊውን ነው ያሰብነው። ዋና ዋናው ወደ አትላንታ ይሄዳል። ስለዚህ አትላንታ በዲሲ፡ ጅማ ባዲሳባ፡ ወይም አዲሳባ በናዝሬት፡ ወይንም ድሬዳዋ ባስመራ መቀየም የለበትም። አይ የኔ ነገር፡ አስመራ ለካ ኢትዮጵያ አይደለችም።

 

የኢትዮጵያዊነት ውርስ ድርጅት አላማዎች አያሌ ናቸው። ይሄ ሰብሳቢ ያጣው ህዝባችን፡ ባመት አንዴ ብቻ ሳይሆን አመቱን ሙሉ የሚገናኝበት፡ የሚሰባሰብበት፡ በያዘው የፖለቲካ አቋምና በሀይማኖቱ፡ በብሄሩና በቀለሙ ሳይለይ የሚመካከርበት፡ ኢትዮጵያዊነቱን የሚያከብርበት፡ የህዝብ “ኤምባሲ” ያስፈልገዋል። እንደምረዳው ከሆነ፡ የውርስ ድርጅቱ የተቋቋምንበት ዓላማ ራሱን የቻለ ሰፊና ግዙፍ ነው። ስፖርት ፌደረሽኑ በያመቱ ከከተማ ከተማ ይዘዋወራል። ያ ጥሩ ነው። ግን ደግሞ ቋሚ የኢትዮጵያዊነት ማእከል ቢኖረን መልካም ነው። ስለዚህ አንዱ የዚህ አዲስ ድርጅት ዓላማ በዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ ቋሚ የኢትዮጵያዊነት ማእከል መገንባት ነው። ዛሬ ለሰርግና ለፓርቲ፡ ለድግስና ለለቅሶ፡ ለቀብርና ለስብሰባ በየወሩ በየግዜው ለአዳራሽ የምንከፍለው ኪራይ የትናየት ነው። ዛሬ ኢትዮጵያዊያን የጥበብ ሰዎች በተመጣጠኝ ዋጋ ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡባቸው የራሳችን አዳራሾች የሉንም። ሽሻና በርጫ ቤት ማንም ነጋዴ ሊከፍተው ይችላል። ነገር ግን፡ ዛሬ ወጣቶቻች የሚገናኙበት፡ ልምድ የሚለዋወጡበት፡ ግጥም የሚአነቡበት፡ ሀሁ የሚቆጥሩበት፡ ያለፈውና መጪው እንዲሁም የዘመኑ የሚገናኝበት የማህበረሰብ ማእከል የለንም። ሲያትል ገንብቷል። ኤድመንተን ራሱ ገንብቷል። ዲሲ ግን አንብቷል ቢባል ይሻላል። ቻይናዎቹ አላቸው። ህንዶቹም አላቸው። ትሪንዳድና ቶቤጎ አንኩዋን አላቸው። እና ግን የለንም። ስለዚህ ህልማችን ያንን መገንባት ነው።

 

ሀያ ስምንት አመት ኢትዮጵያዊያንን ማገናኘትና ማገልገል ትልቅ ድል ቢሆንም፡ በራሱ ግን መጨረሻ አይደለም። ስለዚህ እኔ የውርስ ድርጅቱን ፌደሬሽኑን ለማገዝ እንደመጣ ገንቢ ድርጅት እንጂ፡ በፌደሬሽኑ ላይ እንደመጣ መአት መታየት የለበትም ባይ ነኝ። ፌደሬሽኑ ሩጫ አልነበረውም። ፌደሬሽኑ የስእልና የጥበብ ኤግዚቢሽን አልነበረውም። ፌዴሬሽኑ ለተለያዩ የፖለቲካና የንግድ ድርጅቶች የመገናኛ መድረክን ቢፈጥርም፡ ከእግር ኳስና ሙዚቃ ዝግጅቱ ባሻገር፡ በራሱ የሚያዘጋጃቸው ባህላዊ፡ ታሪካዊና ማህበረሰባዊ ዝግጅቶች የሉም። እኛ ፌደሬሽኑ ያልሸፈናቸውን ዝግጅቶች ነው የምንሸፍነው። ከፌደሬሽኑ ለመተካከል አንችልም። ይሄ ናይጄሪያ ብሪታኒያ ላይ ለመድረስ እንደምታደርገው ሩጫ ነው የሚሆነው። ሌላ ሀያ አመትም አይበቃንም። የእግር ኳስ ስፖርት ዋንኛ ጉዳያችን አይደለም። ባህልና ኪነጥበብ፡ ፈጠራና ቅርስ፡ ክብርና ወጣት፡ አገርና ውርስ ናቸው ዋንኛዎቹ ዝግጅቶቻችን። ስለዚህ ይሄ የኛን ማህበረሰብ እንደ ጸረ-ፌደሬሽን አድርጎ ማየት አግባብ አይደለም። በኢትዮጵያዊነት ውርስ ድርጅት መምጣት የሚፈርስ ወይንም የሚንገዳገድ ፌደሬሽን ካለ፡ ያ ካህያ ቆዳ የተሰራ ቤት ነው ማለት ነው። ምክንያቱም ጅብ የጮኸ እለት የሚፈራርሰው፡ ከአህያ ቆዳ የተሰራ ቤት ብቻ ነውና።

 

እንደ ማጠቃለያ፡

 

ከዚያ በተረፈ ግን፡ አንድ ነገር መካድ የለበትም። አሁንም ቢሆን እኔ በግሌ፡ ፌደሬሽኑ ንብን ደረቱ ላይ ለጥፌ ልጓዝ ቢል ዝም አልልም። ለዚህ ነው የዛሬ ሶስት አመት፡ የስፖርት ፌደሬሽኑ በዋሽንግተን ዲሲ፡ 25ኛ አመት የምስረታ በዓሉን ሲያከብር፡ ለምንድነው ከኚያ የኢትዮጵያን ሀብት በለውዝ ዋጋ አጋብሰው ከሚበዘብዙ፡ ያም ይሁን፡ እንደገና ኢህአዴግን ምረጡ ብለው ባደባባይ ከሚዘምሩ፡ እንደገናም፡ ባለፈው ሰሞን አንዱ የፌደሬሽኑ የቦርድ አባል እንደተናገረው፡ “በደም ገንዘብ” ከበለጸጉ ሰው ጋር የምትዳሩት ብለን ስንጠይቅ፡ “የለም እኛ ሰውየውን የምናውቃቸው በለጋስነታቸውና ባገር ወዳድነታቸው እንጂ በፖለቲከኛነታቸው አይደለም” የሚል መልስ ሲሰጠን፡ እነሆ በራሳቸው አንደበት፡ ሼህ አላሙዲን “እኔ ኢህአዴግ እንድሆን ያጠመቀኝ” ብለው የተናገሩበትን ቪዲዮ እነዚህ ድረ-ገጾች ላይ ላይ የለቀቅነው። http://www.ethiopianreview.com/content/5532 ወይንም http://www.youtube.com/watch?v=XzjJQZ9Rqxc&feature=related ላይ። ወይንም እዚህ ላይ፤ http://www.youtube.com/watch?v=3Gd2Kg6CCZU&feature=related ይመልከቱ።

 

እነሆ አትላንታም ዲሲም የኛ ነው። እንግዲህ፡ ነገሮች እየተስተካከሉ መምሰላቸው መልካም ነው። ገበያውም መድረኩም ህዝቡም ሜዳዉም ለሁላችንም በቂ ነው። በስፖርት ፌደሬሽኑ ውስጥ ሆነው፡ ሌሎችን እንደ ጸረ-ፌደሬሽን አድርገው ከመወንጀል ይልቅ ራሳቸውን በመመርመር በቁርጠኝነት የታገሉትንና የሚታገሉትን ሳላደንቃቸው አላልፍም። መሰሽ ቀላል ነው። ብልጠትም ነው። እዚያው ሆኖ መጋፈጥ ጀግንነት ነው። ለዚህ ነው እስክንድር ነጋን የምወደውና የማደንቀው። እንደኔ ብልጥና ጮሌ አይደለም። ግን ጀግና ነው። ስለዚህ እዚያው ውስጥ ሆነው ፌዴሬሽኑን ለማጥራት የተጉትን አደንቃለሁ። እቀናባቸዋለሁም። ግን ደግሞ የሚመስለንን ይዘን መጓዝም የዚህ የምንኖርበት ምእራብ አለም ልዩ ገጽታ፡ አገራችን ያጣነውና የተሰደድነው ትልቅ መብት ነው። ስለዚህ ሰው የመሰለው ይከተለን። ያልመሰለውም የመሰለውን ይያዝ። የኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስ ድርጅት በራሱ ነው እንጂ መመዘንና መመንዘር ያለበት፡ በንጽጽርና ከሌላ ድርጅት ጋር ተያይዞ መተርጎም የለበትም። እኛ እኛ ነን። እነሱም እነሱ ናቸው። ግን ሁላችንም እናን ነን። በሉ፡ መጀመሪያ ዲሲ እንገናኝ። ከአርብ ጁላይ 1 እስከ እሁድ ጁላይ 3 በጆርጅ ታውን ዩኒቨርስቲ ሁለገብ ስቴዲየም፤ http://ethiopianheritagesociety.org/ ። ከዚያ አትላንታ እንገናኝ፡ ከጁላይ 3 እስከ 9 መሰለን። http://www.esfna.net/። ከዚአ በፊት ግን በዚህ ሳምንት ሌላም አለ፡ ሲልቨር ስፕሪንግ፡ http://colesville.patch.com/events/ethiopian-festival

ፊታውራሪ ተክሌ፡ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!