ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ለዴንቨርና አካባቢዋ ምእመናን በሙሉ  

ሰው ወደ ቤተክርስቲያን የሚሄደው ፈጣሪውንና አምላኩን ለማመስገንና ለመማጸን ከእለት እለት ባርኮና ቀድሶ በሰላምና በደስታ እንዲያደርሰው የቀደመውን ኃጢአቱን በማስታዎስና በመናዘዝ የወደፊት ህይወቱ እንዲስተካከልለት ከአምላኩ ጋር ቃል ኪዳን የሚግባባበት እውነተኛ የህይወት መገኛ ቤት ሲሆን አምላክ በወደደና በፈቀደ መጠን እንደ እምነታችን ብቃት ችግራችን ለአባታችን በህብረትም ይሁን በተናጠል የምናቀርብበት የማይታየውን አምላክ በእምነት አብሮን ከእኛ ጋር በመሆን እለት ከእለት ጉዞአችን እንድናስተካክልና ቀሪውን ሁሉ በህይወታችን ዘመን ለመፈጸም እንዲያስችለን ቃልኪዳን የምንግባባበት በክርስቶስ ኢየሱስ ተመስርታ በቀደምት አባቶቻችን ጸንታ ለእኛ የተላለፈችልን የህይወታችን መገኛ የሆነችውን ቤት በአክብሮትና በትህተና በተሰበረ ልብ ፈጣሪን ለማምለክ ነው።

 ወደዚህ ቅዱስ ስፍራ የምናደርገው ጉዞ የህንጻውን ውበት የግቢውን ማማር ተመልክተን ሣይሆን አብ አካላዊ ቃል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በማምለክና ከመስቀሉም ስር ለመምበርከክ ሲሆን አዳኝም ገዳይም፤ ሰጭም ነሽም፤ ሸዋሚም ሻሪም የሆነውን አምላክ በመሻት ነው።  ሁለትም ሶስትም ሆናችሁ በስሜ በተሰበሰባችሁ ጊዜ እኔ በመካከላችሁ እገኛለሁ ባለው አምላካዊ ቃል መሰረት ክብሩን በጎነቱን ቸርነቱን ፍቅሩን መሃሪነቱንና አዳኝነቱን እለት ከእለት ለማወደስና ለመቀደስ ዘለዓለማዊነቱንና ይቅርባይነቱን በመተማመን በአለችን አጭር የኮንትራት ዘመን እራሳችን በመንፈስ ቅዱስ ግብር አዋርደን በቤቱ ለመኖር እንድንበቃ ጸጋ በረከቱን እንዲያድለን ለመማጸን ነው።

 

ታዲያ ይህ ሆኖ እያለ በቤተክርስቲያናችን ዙሪያ አንዳንድ የክርስቲያን ታናናሾች ተሰግስገው የሚሰሩትን እኩይ ተግባር ስንመለከት ከየት ተነስተው ወዴት እንደሚደርሱ መገመት ባያዳግትም ለጊዜው እኛ ሰዎች ስጋ ለባሾች ነንና ቅር መሰኘታችን አይቀሬ ነው። የአባቶች መንገላታት፤ የምእመናን መገፋት፤ የእምነታችን መቦርቦር፤ የቤተክርስቲያኒቱ ልጆች ተገቢዉን ግልጋሎትም ሆነ እርዳታ አቅማቸው በፈቀደ መሰረት ለእናት ቤተክርስቲያናቸው እንዳይለግሉ ከሰይጣን ተልኮ ባላነሰ  በቤተክርስቲያናችን ዙሪያ ሲፈጸሙ ይስተዋላሉ። 

 

ብዙዎች አባቶችም ሆኑ ምእመናን ነገሮችን በአንክሮ ቢመለከቷቸውም በተወሰኑ በእጣት በሚቆጠሩ ግለሰብ የቦርድ አባላትና ሌሎች ጥቂት በሆኑ የእግዚአብሄርን ቃልም ሆነ ሃይማኖታቸውን ጠንቅቀው በማያውቁ ግለሰቦች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ኢመንፈሳዊ ተግባራትን ሲያካሂዱ መታየቱ ከወዴት እንደሚያደርሳቸው ወደፊት የምንመለከተው ይሆናል፡፡ ቀደም ሲል ምእመናንን አንተ ከዚህ ሃገር ነህ፤ አንቺ ከዚህ ወገን ነሺ፤ ባለአገሮች ወዘተ በማለት አንድ አምላክ አንድ አምሳል ያለውን ምእመን እነርሱን በሚያመቻቸውና በሚስማማቸው መንገድ በመከፋፈል ድሮ የዚህ ካህን ደጋፊ ነህ በመቀጠልም ደግሞ የዚህ መንደር ተወላጅ ነህ ከዚያ መንደር ተወላጅ ጋር ለመኖር ከተፈለገ የመንደሩን የመኖሪያ ቪዛ ፈቃድ ማግኘት በቅድሚያ ያስፈልጋል በማለት በቤተክርስቲያን ዙሪያ ምእመናን እርስ በእረሳቸው በኑፋቄ ላይ እንዲወድቁ አንድ ሆኖ አንድ ያደረገንን አመላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን በተገቢው መንገድና በተገቢው ቦታ እንዳናመልከው ሲከላከሉ ይታያሉ። እግዚአብሄር ግን መእመናኑንና ቤተክርስቲያንን አንድ አድርጎ አጽንቶ ለዘለዓለም ያኖራቸዋል።

 

ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰው ስጋውን የቆረሰው  በመስቀል ላይ ተቸንክሮ ኤሎሄ ኤሎሄ አሎሄ ላማ ሰበቅታኒ (አመላኬ አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ ) እያለ በጎልጎታ ቀራንዮ አደባበይ ላይ የዋለው ለተወሰኑ ገለሰቦች ብቻ በመንደርም ሆነ በጎጥ ንጹሁን ምእመን ለሚከፋፍሉ ተልካሾችና ዝምታን ገንዘብ አድርገው ለተቀመጡ ተመዳቢዎች ሳይሆን ለመላው የዓለም ህዝብ መሆኑን ዘንግተው የእግዚአብሄርን ስምና ተግባር መሳቂያና መሳለቂያ ማድረጋቸው እውነተኛ ክርስቲያን በጎችንም ለተኩላ ማስነጠቃቸው ገሚሱም ምእመን ቤተክርስቲያን ሂጀ የእነርሱን ክፋትና ተንኮል ሰምቸና ተመልክቸ ከምመለስ እግዚአብሄርን ከቤቴ ብማጸነው የበለጠ ይጠቅመኛል በማለት ቤተክርስቲያን ሂዶ እግዚአብሔርን ከማገልገልም ሆነ እነርሱም በቤተክርስቲያናቸው ከመገልገል እራሳቸውን የአራቁትን ምእመን የሁላችንም ቤት ይቁጠረው።

 

በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቶዋህዶ ቤተክርስቲያን እምነትና ስርአት ላይ ተመስርተው ያላደጉ የማያውቁትን ደረጃውን ያልጠበቀ ንግግርን የሚናገሩ እለት ከእለት የሚያሳዩት መሃይማዊ የእምነት ዲቃላነት እጅጉን ቤተክርስቲያንንና በውስጧ ለዘመናት ጸንተው የኖሩትን እውነተኛ ምእመናንን አሳዝኖአል። እኔም በክርስቲያንነቴ ይህንን እንድል ከአስገደዱኝ ሁኔታዎች ከብዙ በጥቂቱ መጥሰቀስ ተገቢ ሆኖ በማገኘቴ በመጠኑም ቢሆን ጉዳዩን ማንሳቱ የአልገባን ምእመን ካለን ሁኔታዎችን ተረድተን ጸሎታችን ሁሉ ምድርን ያለ ካስማ፤ ሰማያትን ያለ ባላ የሚታየውንና የማይታየውን ሁሉ ለፈጠረ ለዘለዓለማዊ አምላክ እለት ከእለት እንድንማጸን የእርሱ መልካም ፈቃድ እንዲሆንልን መለመን እንደሚገባን ሲሆን ማንኛችንም ቢሆን በሃይማኖታችን ላይ የመጣውን አስጠያፊ ተግባር በጸሎትም ሆነ  ሌሎች አማራጮችን በመጠቀም አንድ ክርስቲያን ለእምነቱ ማድረግ የሚገባውን ነገር ሁሉ ማድረግ ግዴታችን መሆኑን ተገንዝበን በግሩፕ ሳይሆን በአንድነት፤ ስለ እውነት በመቆም ይህን ብናገር እገሌ ይቀየመኛል በማለት ለምድራዊ ሰው ክብር ሳይሆን ለዘለአለማዊ አምላክ ክብር በመቆም የእግዚአብሄር ቁጣም ሆነ መቅሰፍት በእኛና በልጅ ልጆቻችን ላይ እንዳይተላለፍ ከወዲሁ መመከትና መከላከል ይኖርብናል።

 

በመሆኑም ቀደም ሲል ከእምነታችን ውጭ የሆኑትን የነጭ ታጣቂ ጠባቂዎች በቤተክርስቲያን ዙሪያ በማሰማራት አንዳንድ የቤተክርስቲያኒቱ የቦርድ አባላት ሆን ብለው የፈጠሩትን ግርግር እንዲያባብሱላቸው ምእመናንንም ሆነ ከምእመናን አብራክ የተገኙ ለጋ ህጻናት በአእመሯቸው ላይ መጥፎ መንፈስ ተዋህዷቸው እንዲያድጉ ምእመናን ለቤተክርስቲያናቸው ህንጻ ሞርጌጅ (Mortgage) መሸፈኛም ሆነ ለልዩ ልዩ መንፈሳዊ አገልግሎት ስራ ማስፈጸሚያ እንዲውል በእምነት የዋጡትን ገንዘብ ያለ አግባብ ለውጭ ታጣቂ ሃይላት በመክፈል ምእመናን በዚህ የኑሮ ውድነት ዘመን  ከልጆቻቸው አፍ መልቅቀው ለተቀደሰው የእግዚአብሄር ቤት እንዲውል ያደረጉትንና በእየሳምንቱ አውደ ምህረት ላይ በመውጣት በሰለቸና በገነተረ አቀራረብ ዘዴ የገንዘብ አዋጡ መልእክት በማስተላለፍ በተዋጣው ገንዘብ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የአባቶቻቸውን እምነት፤ ባህል፤ ወግና ልምድ እንዲያጡ  ከፍተኛ ግፊት ሲያደርጉና በተግባርም እየተረጎሙና እያስተረጎሙ ስለመሆኑ የቤተክርስቲያኒቱ ምእመናን ከሊቅ እስከ ደቂቅ ምስክሮች ናቸው።  ይህ ጉዳይም ለቤተክርስቲያናችንና ለምእመናኑ ትልቅ ሊድን የማይችል የአእምሮ ነቀርሳ ጥሎ ማለፉ አንድና ሁለት የለውም በተለይም በለጋ ህጻናት ልጆቻችን የወደፊት የሃይማኖት እጣ ፈንታ ምን እንደሚመስል ስመለከተው ሆድ ይብሰኛል። 

 

ይህ በዚህ እንዳለ ሰሞኑን በዚች በዳግማዊት ቅድስት ግሸን ማርያም ቤተክርስቲያን ዙሪያ በእነዚሁ ተመራጭ የቦርድ አባላት ከግላዊ ስጋዊ ስሜት አኳያ የተላለፈውን ውሳኔና በተግባርም እየተደረገ ያለው አስነዋሪና እርካሽ ተግባር ጥቂት ማለት እወዳለሁ፡፡ 

 

እለቱ እሁድ እኔም እንደ አባቶቸ ለአለፉት ቀናት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የሰራሁትን ሃጢአት ለአምላኬ ለመናዘዝ ያለፈውን ይቅር እንዲለኝ የሚመጣውን ጊዜ ክፉ ከመስራትና አምላኬን ከማስቀየም እንዲጠብቀኝ ያመራሁበት እለተ ሰንበት ነበር።  ቅዳሴው በሙሉ መንፈስም ይሁን በጥርጣሬ መንፈስ መቸም እንበለው ተቀድሶ ተጨረሰ።  በለጋ ህጻናት አንደበት  ዘማርያንና ለእግዚአብሄር ሳይሆን መንፈሳቸው ለሰዎች ለመታየት በተገራ አንዳንድ የሰንበት ትምህርት ቤት እህት ዘማርያን እንደ ጥንቱ መንፈስ ቅዱስ የተላበሰ ውዳሴ ባይቀርብም ከበሮዎቹ ሲመቱ አፋቸው ሲንቀሳቀሱ ተስተዋሉ።  የእለቱን ስብከት በተመለከተ በሌላ ሰአት እንመለስበታለን። እናንተ ስለሰላም ትሰብካላችሁ ሰላም ግን ከእናንተ እርቃለች ይል የለ።  ከዚህ በመቀጠል አንድ የቦርድ ተወከይ ነኝ ባይ ከታች ተነስቶ ወንዶችንና ሴቶችን የሚከፍለውን ጠባብ ወሽመጥ መንገድ ይዞ ወደ ምስራቅ አቅጣጫ በመምጣት አውደ ምህረቱን ተቆጣጠረው፡፡  እንደምን አደራችሁ ምእመናን አለ መረጋጋትና ማስተዋል በጎደለው መንፈስ እየናጠጠ።  በእርግጥ ማንኛቸውም የቦርደ አባላት አውደ ምህረት ላይ ወጥተው የማይዋሹት ነገር ቢኖር እንደምን አደራችሁ የሚለውን ቃል ብቻ ነው። የሰዓት አቆጣጠሩን እነርሱ እንደፈለጉት ጥዋቱን ምሽት፤ ሌሊቱን ቀን፤ ማድረግ ስለማይችሉ ብቻ። በሌላ መንገድ ግን ሁሉም ተመረጮች ተንኮልና ክፋት ከመሞላት ውጭ የሚመሳሰሉበት መንገድ እንደለለ እሙን ነው።

 

ታዲያ ይህ በዚህ እንዳለ በወቅቱ ቤተ ክርስቲያን አውደ ምህረት ላይ ቆሞ ካስተላለፋቸው የውሸት መልእክቶች እንደምሳሌና በብሉይም ይሁን በሃዲስ ዘመናት በቤተመቅደስም ይሁን በቤተክርስቲያን ላይ ታይቶና ተሰምቶ እንዲሁም ተደርጎ የማይታወቅ ለጀሮ ባዳ ለአይን እንገዳ የቤተክርስቲያንን ትዎፊትና እምነት የሚጻረር ሃዋርያው ቅዱስ ጳዉሎስ በመልእክቱ የአምልኮት መልእክት አላቸው ሃይሉን ግን ይክዱታል እንዳለው ሲያዳምጡት የሚሰቀጥጥ ወሬ ይዞ ብቅ አለ።  ምእመናንም ዛሬ ደግሞ ከማያልቅበት የውሸት ጎተራ ውስጥ ምን ይዞ ይቀርብ ይሆን በማለት አይን ለአይን በስሜት ይናበቡ ጀመር፡፡ የፕሮገራሙን ፍጻሜም ከአምላካቸው ጋር እስከ ቅዳሴ መውጫ ድረስ በካህኑ ጸሎት ለማሳረግ ሲጠባበቁ ለነበሩት ምእመናን አንድ አዲስ መልእክት ብልጭ አደረገ። የተጨፈኑ ላሞኛችሁ ዘይቤውንም ቀጠለ። በአለፈው ሳምንት በገለጽነው መሰረት አለ ሊቁ የቤተክርስቲያናችን ተቆርቋሪ፤ ለቤተክርስቲያናችን ደህንነት ሲባል ዘጠኝ ሰርቡላንስ ቪድዮ ካሜራዎችን በቤተክርስቲያኑ ውጭም ሆነ ውስጥ በማስቀመጥ ላይ እንገኛለን። ለዚህ ስራ ማስፈጸሚያ የሚውል ገንዘብ ምንጊዜም ቢሆን ከእናንተ ስለምንፈልግ እናንት የእኛ እርጥብ ፎጣ ማለት ናችሁ።

 

እርጥብ ፎጣ እንደሚታወቀው ውሃ ይነከራል ይጨመቃል አሁንም ይነከራል ይጨመቃል ስለዚህ እናንተም ከዚያ ፎጣ ያነሰ አስተወጽኦ እንደማታደርጉ እርግጠኛ ነኝ በማለት የተከበረውን ምእመን እንደ አንድ የምግብ ቤት የእጅ ቆሻሻ መጥረጊያ ፎጣ በመቁጠር ለንግድ ቤታቸው ለሚፈልጉት ካሜራ ምእመናን በቤተክርስቲያናቸው ውስጥ ሲጸልዩ ለመቆጣጠር ያመች ዘንድ ዘጠኙ የቦርድ አባላት በነፍስ ወከፍ እያንዳንዳቸው አንዳንድ ሰርቡላንስ ካሜራ እንዲደርሳቸው ለእኩይ ተግባራቸው ማስፈጸሚያ ያመቸው ዘንድ የወሰደው ጥቅስ ሲስተዋል አለማወቁን ብቻ ሳይሆን ከንቱነቱን ያመለክታል። ጥቅሱም እግዚአብሔር ቤትን ካልሰራ ሰራተኞች ሁሉ በከንቱ ይደክማሉ።

 

እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ ጠባቂዎች ሁሉ በከንቱ ይተጋሉ የሚለውን ነበር፡፡ መዝ 126 ከቁጥር 1 እርግጥ ነው ይህ ቃል በትክክል በመጽሃፍ ቅዱሳችን ውስጥ ሙሉ በሙሉ ይገኛል። እኛም የምናመልከውና የምንከተለው አምላክ ይህን እንደሚያደርግልን ተራዳኢ መላእክትንም ሳይቀር እንደሚልክልን ለደቂቃም ቢሆን ጥርጥር የለንም። ጥሩ አባባል። እንኳንስ እኛ የአንዲት የኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆች ይቅርና ሌሎችም የዓለም ክርስቲያን ወገኖቻችን ይህን ቃል በአንክሮ ይቀበሉታል፡፡ ይልቁንስ እኛማ ኢትዮጵያዊ መልኩን ነብር ዥንጉርጉርነቱን ይቀይራልን የተባለልን ዜጎች አይደለነምን ምንም እንኳ ያን ያህል የተትረፈረፈ ገንዘብ ባይኖረንም በእምነታችን ከአምላካችን ጋር የአለን ግንኙነት ሲወርድ ሲዋረድ እስከ አለንበት ጊዜ ድረስ እግዚአብሔር አምላክ ለነቢያት ለጻድቃን ለሰማእታት ለሃዋርያትና ለደናግል ከሙሴ ዘመንና ከዚያም በፊት የሰጠውን ቃልኪዳን ያለአጠፈብን ቢሆንም ቅሉ ሁሉን የፈጠረ የአብርሃሙ ሥላሴ መልካም ፈቃድ ሆኖ ለዚች እለት አብቅቶናል። የሚያሳዝነው ነገር ቢኖር የተጠቀመው ጥቅስ በተግባር ሊፈጽም ከአሰበውና በመፈጸም ላይ ካለው እኩይ ተግባር ጋር አለመዘመዱ ነው። እግዘ.አብሄር ሃገርንና ቤትን የሚጠብቅና የሚሰራ መሆኑን ካረጋገጠ ለምን ሰርቡላነስ ቪዲዮ ካሜራ በቤተክርስተያን ውስጥ ማስቀመጥ እንዳስፈለገ ሊገባኝ አልቻለም።  

 

በመሰረቱ ሰርቡላን ቪዲዮ ካሜራ የሳይንስ ግኝት ሲሆን በዘመናችን የሚያገለግለውም በአንዳንድ መስሪያቤቶችና የንግድ ተቋማት ውስጥ ግለሰቦች ህገወጥ ተግባራትን ለመፈጸም ድንገት ቢሞክሩ ለመቆጣጠር በስጋዊ ምኞት አስገዳጅነት ተነሳስተው ችግር አንዳይፈጥሩ ለመከታተል ያመች ዘንድ ነው። ይህም ሲባል ካሜራዎች የሚተከሉት በእምነተ ተቋማት ላይ ሳይሆን በቁማር መጫዎቻ ቦታዎች፤ በትራፊክ መስቀለኛ መንገድ ማቋረጫ መስመሮች፤ በታላላቅ የንግድ ቤቶችና በሌሎችም ስፍራዎች ሲሆን የቤተክርስቲያን ካሜራ ግን እምነት ለአለው ሰው ሆነ የሃይማኖት አባት የእግዘአብሄር አይን ብቻ ነው። ምእመናን ወደ ቤተክርስቲያን የሚጎርፉት ንግድ በመነገድ የስጋዊ ፈቀዳቸውን ለመፈጸም ቁማር ለመቆመር የአንድን ሰው ገንዘብ ያለምንም ድካም አሟጦ ለመውሰድ ሳይሆን ከእግዚአበሄር ዘንድ የሃጢአት ስረይትን ለማግኘትና ዘለዓለማዊ ህይወትን ገነዘብ ለማድረግ ነው። ማንንም ቢሆን ሰውን ሰው ጠብቆ የሚያድነው ሃይል የለም። ሃይሉና ጠባቂው መመኪያውና አሌንታው እርሱ እግዚአብሄር ብቻ ነው። እግዚአብሔር ደግሞ ልጆቹን የሚያስተውልበት ዓይን አጥቶ እረዳት እንዲሆነው የቦርዶችን ዓይን አይፈልግም። በእርግጥ አንድ ነገርን ከእኔም  ከእናንተም ሊፈልግ ይችላል። እርሱም አይናችን ሳይሆን ልባችን እንድንከፍትለት።  እመን ትድናለህ ነውና።

 

ስለሆነም በሌሎች የሃይማኖታችን ተመሳሳይ አብያተክርስተያናት ለምሳሌ እንደ አርመን ኦርቶዶክስ፤ ገሪክ ኦርቶዶክስ፤ የሶርያ ኦርቶዶክስ፤ የራሻ ኦርቶዶክስ እና የሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን በመሳሰሉት በብዙ ብሌን የሚቆጠር መተኪያ የሌላቸው ሃብትና ንብረት እንዲሁም ቅርስ በቤተክርስቲያናቸው ውስጥ ይዘው በሚገኙት ሃይማኖታዊ ተቋማት እንኳ የአምላካቸውን ጠባቂነት ዘንግተው በሃብታቸው ተመክተው በእራሳቸው ሃይል ለመጠቀም ምእመናንን ከእግዚአብሄር ልጅነትና ከቤቱ የሚያስወጣ የእግዚአብሔርንም መኖርና አለመኖር ኑፈቄ ውስጥ የሚጥል የሃያ አራት ሰዓት ካሜራ ጥበቃ ቀርቶ የአንዲት ሴኮንድ እንኳ ጥበቃ ለማካሄድ እራሳቸውን በትእቢት ተሞልተው ለዲያቢሎስ አሳልፈው አልሰጡም። ሃይማኖታችን ቀደምትነት ያለው እንጅ ከኋላ የተገኘ አልነበረም። ህዝባችንም ህዝበ እግዚአብሄር፤ ሃገራችንም ሃገረ እግዚአብሄር፤ የተባሉት ለዚህም አይደለ። (ስትጸልዪ እንደ ገብዞች አትሁኑ ለሰዎች ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማእዘን ቆመው  መጸለይን ይወዳሉና።  እውነት እላችኋለሁ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።

አንተ ግን ስትጸልይ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያውንም ዘግተህ በስውር ለአለው አባትህ ጸልይ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል። ማቴ፤ ምዕራፍ 6 ቁጥር 5-7 የሚለውን አባታዊ ቃል ተዘንግቶ እነርሱ እራሳቸው አንደ ግብዞች ግማሽ ቅዳሴ ላይ ሆነ ቅዳሴ ሊያበቃ ሲል በምእመናን መካከል እንደ አይጥ እየተንሸራሸሩ ምእመናን መነፈሳዊ ግንኙነታቸውን ከአምላካቸው ጋር እንዳያደርጉ የመንፈስ ቅዱስ  ትስስራቸውን ለማቋረጥ መንገዱን መዝጋታቸው አልበቃቸው ብሎ ይባስ ብሎ ብዙ አባቶችና እናቶች ተምበርክከውም ሆነ ተሸፋፍነው እያለቀሱ፤ ደረታቸውን እየደቁ፤ በሙሉ ስሜት እንዳይጸልዩ ሃጢአታቸውን እንዳይናዘዙ በቤተክርስቲያናችን ዘንድ ተቀባይነት የሌለው የአርዮስአውያንና የግብዝነት ስራ ሲፈጽሙ መስተዋሉ ለቤተክርስቲያናችን ጥቅም ሳይሆን ጉዳት፤ ደህንነት ሳይሆን ችግር፤ በጎ ነገር ሳይሆን ነቀርሳ፤ ሁልጊዜ ምእመናን ለጸሎት ወደ ቤተክርስቲያን በመጡ ጊዜ ወደ ላይ  አንጋጠው ፈጣሪያቸውን ሲማጸኑ  በዘጠኙ ቦርድ አባላትቁጥር ልክ የተተከሉትን ዘጠኝ ሰርቡላነስ ካሜራዎች አንዲያመልኳቸው ሆን ብለው ማስቀመጣቸው ናቡከ ደነጾር በዘመኑ አሰርቶት ከነበረው የጣኦት ምስል የሚበልጥ እና በስውር የሚያየውን አምላክ በግልጽ መክፈሉን በጭራሽ ክደው መሆኑን ለመረዳት ያስችላል፡ እግዚአብሔር አምላካችን አኮ የፈጠራት ዓለም በመዳፉ አትሞላም እርሷን ለመጠበቅና ለመመልከት ሌላ ሰው በዘመኑ በቤተክርሰቲያናችን በኃይማኖታችን ላይ እንደሚቀልዱት ተራ የቦርድ አባላት የእግዚአብሄርን ቤት ለመገንባት ሳይሆን በትእቢትና በእልህ ተነሳስተው ለማፍረስ የህዝቡ እረኛ እግዚአበሄር ሳይሆን እኛ ነን ብለው በድፍረት እንደሚፈጽሙት ሳይሆን እግዚአብሄር ሁሉን ነገር መመልከት እንደሚችል ሌላ እረዳት ዓይን እንደማያስፈልገው ቅዱስ ቃሉ ያስረዳናል። እንዲህ ሲል፤

 

እግዚአብሔር ከሰማይ ተመለከተየሰውን ልጆች ሁሉ አየከማደሪያው ቦታ ሆኖበምድር ወደሚኖሩ ሁሉ ተመለከተእርሱ ብቻውን ልባቸውን የሰራስራቸውን የሚያስተውል።  መዝ፡ 32 ቁጥር 13 ዘጠኙ የቤተክርስቲያኒቱ ቦርድ አባላት ስማችሁን ለመጥቀስ ብዙም አልቸኩልበትም ሆኖም ግን እባካችሁን ተለመኑን ሁላችንም ቢሆን በእግዚአብሄር ዘንድ ኢምንት ነን አምላክ ስራችን ሁሉ ያስተውላል።  ሞት ቢዘገይ የረሳን እንዳይመስለን እንጠንቀቅ። 

 

ሌላው ትልቁና አስቸጋሪው የካሜራው በቤተክርስቲያኒቱ መደቀን ታሪካዊነቷንና ሉዓላዊነቷን ሃይማኖቷን እምነቷን ሚስጢራተ ቤተክርስቲያናትን ጠብቃ የቆየችን ቤተክርስቲያን ሃያ አራት ሰዓት የሚሰራ ካሜራ በተራ መሃይምናንና ካሜራውን ባስቀመጡት ኢኦርቶዶክስአውያን የደህንነት ሰራተኞች ( Security workers) በመቅደስም ውስጥ ሆነ በውጭ የሚገኙ ሚስጥራተ ቤተክርስቲያን ምን እንደሚመስሉ በግልጽ የአለም ህዝብ እንዲመለከቷቸውና ቤተክርስቲያኒቱን መሳቂያና መሳለቂያ እንዲሁም መዘባበቻ እንድትሆን በዘመኑ ግራኝ አህመድ በቤተክርስቲያናችን ላይ  ከአደረሰው እርካሽ የጥፋት ተግባር የማይተናነስና ፍንትው አድርገው ለማሳየት የኮንትራት ስምምነት መፈራረማቸው ብቻ ሳይሆን እነርሱም እራሳቸው ዲያቆናት እንኳ ሊነኳቸውም ሆነ ሊመለከቱአቸው የማይገቡና ክልክል የሆኑትን ነግሮች ሁሉ በማን አለብኝ ስሜት በመነሳሳት ጉዳዩ ለማይመለከታቸውን ግለሰቦች ለማሳወቅ መራወጣቸው ለቤተክርስቲያናችን መዕመን መቅሰፍት እንዲወርድ ከማድረግ ውጭ አልፎም የአለም ህዝብ በፈተና ለይ እንዲወድቅና በረከት እንዲርቀው መገፋፋታቸው እሙን ነው።

 

በተለይም የቤተክርስቲያኒቱ ጉዳይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ የሚመለከታቸው የሃገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ተብየ ይህ ድርጊት ሲካሄድ ነገሮችን ሁሉ በሉ ግፉበት አበጃችሁ እያሉ ቡራኬ እየሰጡ መቅሰፍት እንዲነግስ በረከት እንዲጎድል የዳዊታቸው ማህደር በመንፈስ ቀዱስ ሃይል ሳይሆን በገንዘብ ( ዶላር) ሃይል እንዲሞላ ለሃይማኖታቸው ሳይሆን ለእለት ሆዳቸው የቆሙ ስለመሆኑ ወርቅ በእሳት እንደሚፈተን እርሳቸውም በተለያዩ ፈተናወች ይህ ነው ብለን የማንገምተው ፈተና ውስጥ ገብተው በተለያዩ ቦታዎች ችግር ላይ መውደቃቸው የአደባባይ ሚስጢር ስለመሆኑ ዋቢ የማያሻው ጉዳይ ነው፡፡ ሁሉን ቢናገሩት ሆድ ባዶ ይቀራል ይባል የለ።

 

ይህ አልበቃቸው ብሎ በምእመናንና በቦርዶች መካከል ሰላም ጠፍቶ በምእመናንና በምእመናን መካከል ሰላም ደፍርሶ እርሳቸዉም ሆኑ በዚች ቤተክርስቲያን ዙሪያ የሚገኙ ካህናት ችግሩን እየተመለከቱ በስብሰባ መካከል የሃሳብ አለመግባባት ሲከሰት በመካከል ቁጭ ብለዉ እየሰሙና ዘጠኙ የቦርድ አባላት በዲክታተርነት የአራመዱትን ኢኦርቶዶክሳዊ የስብሰባ አመራር ባርከው በመክፈት ምእመናን በነጻነት ሃሳባቸውን እንዳይገልጡ በታጠቁ ሃይላት ተከበው ኢመንፈሳዊ ተግባር ሲደርስባቸውና በኋላም ቢሆን እነዚህ የዲክታተር ቦርድ ጥርቅሞች ንጹሁን ክርስቲያን በእራሳቸው ጉዳይ በእራሳቸው ቤተክርስቲያን ውስጥ ችግሮቻቸውን አንስተው እንዳይወያዩ ከሶስት ጊዜ ያለአነሰ ፖሊስ ተጠርቶ እየመጣ ሲመለስ እየተመለከቱ አንዳንድ ምእመናን እንኳ ሳይቀሩ ተነስተው አባቴ እርሶ በመካከላችን ተገኝተው እንደዚህ አይነት ኢኦርቶዶክሳዊ ስራ ሲሰራ ዝም ብለው ይመለከታሉ ከእርሶ እኛ ባናውቅ የካህን ወጉን ያድርጉ እባኮት ተነስተው አባታዊ ተግሳጸወትን ያስተላልፉ ተብለው ቢለመኑ ምንም አይነት እነቅስቃሴ ሳያሳዩ ቅራኔው ከትንሽ ወደ ከፍተኛ ደረጃ እንዲደርስ ዋንኛ ተጠያቂ በመሆን ከእሳት ላይ ቤንዚን የአርከፈከፉ አባት ስለመሆናቸው ሰው ቀርቶ ሰይጣን የምስክርነት ቃሉን መስጠት ይችላል።

 

በመጨረሻም ሰዓት ቢሆን የሰጡት የማሳረጊያ ጸሎት በሰላም አስጀምረህ በሰላም ለአስፈጸምከን አምላክ ክብር ምስጋና ይገባሃል ማለታቸው የሰው ደም ፈሶ ባለማየታቸው በእርሳቸው ዘንድ ያሁሉ የምእመናን ለቅሶ፤ የሰኩሪቲ ግርግር፤ የፖሊሶች መውጣትና መግባት የቱን ያህል እንዳስደሰታቸውና ለገንዘብ እንደተገዙ በአደባባይ ሊያስመሰክሩ ችለዋል።  በእግዚአብሄር ቤት ውስጥ እርሱን እንድናገለግል ተሹመን በውስጡ የሚስተካከሉ ነገሮችን በአንክሮ ሳይሆን በቸለልተኝነት ስሜት የምንመለከት ከሆነ ነገሮች ሁሉ እየገፉ ሲሄዱ በሰውም ሆነ በእግዚአብሄር ፊት ከተጠያቂነት የማናመልጥ መሆኑን ከወዲሁ መገንዘብ ይኖርብናል።  በመሆኑም ብጹእ አባታችን አቡነ ሣዊሮስ ለቤተክርስቲያኒቱ የአሳዩት ጥሩ ስነምግባር ሲመዝን እያደር እየቀለለና ምእመናንም ሆነ ቤተክርስቲኒቱን በአጠቃላይ ፈተና ላይ የሚጥል ስለመሆኑ ጥርጥር የለውም።

 

በእርገጥ ይህ የሚያመለክተው እርሳቸው ለዚህ ትልቅ መንፈሳዊ ተልኮ ብቁ እንዳልሆኑ ስለሆነ ምንአለባት ከእርሳቸው አቅምና ተፈጠሮ ጋር ይህ መንፈሳዊ ሹመት ጎን ለጎን ስለማይሄድ እኛም ደግሞ ልጆቻቸው ችግራቸውን ግልጽ በሆነ መልኩ ልንረዳ ያልቻልን በመሆኑ በእኛና በእርሳቸው መካከል የሰማይና የምድር ርቀት የሚያክል ልዩነት እንዳለ እርሳቸው እራሳቸውም ሳይረዱት የቀሩት ነገር ያለ አይመስለኝም። በእርሶ አባትነት በእኛ ልጅነት መካከል የአለውን ልዩነት ለማጥበብ ከተፈለገ ለቦርዶች ሳይሆን ለሚያወድሱትና ለሚቀድሱበት ቤተክርስቲያን ሲሉ እራሰዎን ለአምላክ ዝቅ አድርገው ምእመናንን ብቻ ሳይሆን እርሰዎም ስጋ ወደሙ ሲፈትቱም ሆነ ሲያቀብሉ ሲቀበሉ የተተከሉት ካሜራዎች እንደሚያዩዎት ተገነዝበው እነዚህ ካሜራዎች ተነስተው ቤተክርስቲያናችን የጥንቱና የጥዋቱ የአባቶቻችን ቤተክርስቲያን እንድትሆን ቢጥሩና ሌሎችንም ኢመንፈሳዊ ተግባራት በሙሉ እንዲስተካኩ የበኩለዎትን አስተዋጽኦ ቢያደርጉ እርሰዎም ሆኑ መእመኑ በአጠቃላይ በንስሃ የምንመለስበትን መንገድ ቢፈጥሩ የነነዌን ህዝብ ከጥፋት ዮናስን ልኮ የመለሰ አምላክ እንደሚታረቀን አልጠራጠርም እያልኩ ለጊዜው በዚች ጽሁፍ የምሰነባበተው  

 

ከዴንቨር ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን ምእመናን አንዱ            

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ