Atsé Yohanesግርማ ካሣ ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

(ሚያዝያ 24 ቀን 2000 ዓ.ም. May 2, 2008)

“ዐፄ ዮሐንስ ይዋሻሉ

መጠጥ አልጠጣም ይላሉ

ሲጠጡ አየናቸው በርግጥ

እራስ የሚያዞር መጠጥ”

 

ይህ ለዐፄ ዮሐንስ አራተኛ የተገጠመ ቅኔ ነበር። ሰሙ፣ ዐፄ ዮሐንስ መጠጥ አልጠጣም እያሉ የሚያሰክር መጠጥ ሲጠጡ እንደሚታዩ የሚገልጽ ሲሆን፤ የቅኔው ዋና መልዕክት - ወርቁ ግን የእኝህን ታላቅ ኢትዮጵያዊ የደም መስዋዕትነት ያሳያል።

 

በቅርቡ የሱዳን ወታደሮች በኢትዮጵያ ድንበር ዘልቀው በመግባት ከተሞቻችንና መንደሮቻችንን እያቃጠሉ እንደሆነ በሠፊው እየተዘገበ ነው። የሱዳን ታጣቂዎች በኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጽሙት እኩይ ተግባር አሁን በኦማር አልበሽር አገዛዝ የተጀመረ አይደለም።

 

ከመቶ ዓመታት በፊት ማህዲስት ደርቡሾች (ሱዳኖች) እስከ ጎንደር ከተማ በመዝለቅ ትልቅ ቃጠሎ እንዳደረሱ ታሪክ ያስተምረናል። በወቅቱ የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር የነበሩት ዐፄ ዮሐንስ አራተኛ ይህን ድንበር ዘለል ጥቃት ለመመከት ወዲያው ነበር ወደ ጎንደር የተሰማሩት። እራሳቸው የሚመሩትን ጦር በማዝመት ማህዲስቶችን በጀግንነት ከኢትዮጵያ ምድር ገፍተው ወደ ሱዳን ድንበር አደረሷቸው።

 

ዐፄ ዮሐንስ፣ ሌላውን አስቀድመው ከኋላ መቅረት ይችሉ ነበር። ነገር ግን “በአገር ጉዳይ ላይ ወደኋላ ማለት የለም” በሚል ቁርጠኝነት ከተራው ወታደር እኩል እፊት ፊት ቀደሙ። ሙሉ ለሙሉ ፍልሚያው ውስጥ ገቡ።

 

ታዲያ የኢትዮጵያ ሠራዊት በድል ወደፊት እየገሰገሰ ባለበት ወቅት ድንገት ከጠላት በተተኮሰ ጥይት ይመቱና ሱዳን ድንበር አካባቢ መተማ ላይ እኝህ ጀግና፣ አንበሳ፣ ታላቅ የኢትዮጵያ ልጅ ለአገራቸው ነፃነትና አንድነት ሲሉ ይወድቃሉ። ዐፄ ቴዎድሮስ በመቅደላ ተራራ ላይ በእንግሊዞች እጅ ላለመማረክ ጥይት ጠጥተው እራሳቸውን በገደሉ ጊዜ ተገጥሞ የነበረውን ግጥም ትንሽ ለውጥ አድርጌ፣

 

”መተማ ሜዳ ላይ ጩኸት በረከተ

የሴቱን አናውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ”

 

ስል የእኝህን ኩሩ ኢትዮጵያዊ ገድል እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ በዚህ አጋጣሚ እዘክረዋለሁ።

 

ከዚያ በኋላ በዐፄ ዮሐንስ መሞት የኢትዮጵያ ሠራዊት ደነገጠ። ማህዲስት ደርቡሾች አይለው መጡ። የዐፄ ዮሐንስን እራስ ቆርጠው በምድራቸው እያዞሩ ነጋሪት አስነፉ።

 

በአሁኑ ወቅትም የሱዳን ታጣቂዎች ያኔ በዐፄ ዮሐንስ ዘመን እንዳደረጉት ሁሉ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት እያደረሱ ነው። በኢትዮጵያ ያሉ መሪዎች ግን የሚመልሱት ምላሽ ያኔ ዐፄ ዮሐንስ ከመለሱት ምላሽ ጋር ሲነጻጸር ሰማይና ምድር የተራራቀውን ያህል የተራራቀ ነው።

 

እስከአሁን ድረስ ኢህአዴግ ሙሉ ለሙሉ ከሚቆጣጠራቸው የመገናኛ ብዙሃን፣ በጎንደር መንደራቸው በሱዳን አሸባሪዎች ስለተቃጠለባቸው ወገኖቻችን የተዘገበ አንዳች ነገር የለም። ከማስታወቂያ ሚኒስቴር ሆነ ከጠቅላይ ሚኒስቱ ጽ/ቤት የወጣ መግለጫ አላነበብንም። በውጭ አገር ባሉ እንደ አይጋ ፎረም (የኢትዮጵያ ራሽ ሊምቦ) እና ኢትዮጵያ ፈርስት የተሰኙ አፍቃሪ ኢህአዴግ ድህረ ገጾች ዘንድም አምስት ሳንቲም አልተጻፈም።

 

የሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤቶች መሪ የነበሩ ሼክ አዌ “በኢትዮጵያ ላይ ጅሃድ አውጃለው” በማለታቸው ብቻ የአገራችንን ሉዓላዊነትና አንድነት ማስጠበቅ አለብን በሚል ሰበብ፣ የኢትዮጵያ ሰራዊት ሱማሌን እንዲወር መደረጉ የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያውያን በታሪካችን ጎሮቤት አገር ወረን አናቅም። እነ አቶ መለስ ዜናዊ አስጀመሩን።

 

ታዲያ በሰፊው እየተዘገበ ያለውን የኢትዮጵያ ዳርድንበር በተመለከተ ከኢህአዴግ ዘንድ ዝምታ ብቻ ነው ያየነው። የሱዳን አሸባሪዎች የሚፈነጩበት አካባቢ የዐፄ ዮሐንስ አስክሬንና የመይሳው ካሳ ዐፄ ቴዎድሮስ እትብት የተቀበረበት፣ ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ ግዛት የነበረ አይደለም እንዴ? ታዲያ ዝምታው ለምንድን ነው? አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም እንደተባለው ሳይሆን እንደማይቀር እገምታለሁ።

 

በሶማሊያ ጦርነት ለማወጅ ሲባል ሲለፈፍብን የነበረው ለ”ኢትዮጵያ አንድነት የመቆርቆሩ ጉዳይ” አሁን ወዴት ነው ያለው? ወይስ የኢትዮጵያ ጥቅም የግለሰብን ጥቅም ከሚያስጠብቅ የውጭ ኃይል ጥቅም ያነሰ ነውን?

 

በፓርላማ ተቀምጠው ‘ተቃዋሚ ነን’ የሚሉ እነ አቶ ልደቱ አያለው እና ዶ/ር በየነ ጴጥሮስን የመሳሰሉ ተቃዋሚዎች እነርሱም ዝምታን የመረጡ ይመስላል። ኢህአዴግን እንዳያኮርፍና በፓርላማ አቶ መለስ ዜናዊ እንዳይወርፏቸው ፈርተው ይሆን? መልሱን ለእነርሱ እተወዋለሁ።

 

ያኔ የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር የነበሩት ጃንሆይ ዐፄ ዮሐንስ አራተኛ፣ ደማቸውን ለኢትዮጵያ ሲያፈሱ የአሁኑ ርዕሰ ብሔር ግን ለኢትዮጵያም ደንታም ያላቸው አይመስልም። የአፋሩ ሱልጣን ኢብራሂም አሰብን በገንዝብ እንደሸጡ ሁሉ በአራት ኪሎ ያሉ መሪዎችም ድንገት ከሱዳን ነዳጅ ለማግኘት፤ ወይንም በሱዳን በትጥቅ ትግል የሚታገሏቸው ካሉ ቦታ እንዳያገኙ ለማከላከል፤ አሊያም በኤርትራ በኩል የባህር በር ስለተዘጋና የበርበራን ወደብ የመጠቀሙ ጉዳይም አስተማማኝ ስላልሆነ የሱዳን ወደብን ለመጠቀም አስበው ይሆን የዳርፉሩን ወንጀለኛ ኦማር አልበሽርን አቅፈው የሚያስተናግዱት? ወይስ ኮሎኔል መንግሥቱ በዚምባብዌ መጠለያ እንዳገኙ በሱዳን የወደፊት መጠለያ ለማዘጋጀት ታስቦ ይሆን?

 

“የኢትዮጵያ ድንበር አልተደፈረም። የሚወራው ወሬ ውሸት ነው” የሚል ማስተባበያ ከኢህአደግ ባለሥልጣናት ሊቀርብ ይችላል። መፍትሄው ግን ቀላል ነው።

 

በሀገራቸው የአንድነት ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያውያን የኢህአዴግን ጥቂት ባለሥልጣናት ማመን ካቆሙ ረዥም ጊዜ ተቆጥሯል። ስለዚህ በአስቸኳይ ገለልተኛ የሆነ ኮሚሽን ተቋቁሙ ከሱዳን በኩል የተፈጸመውን ጥቃት እንዲሁም “ተፈርሞ ለሱዳን ተሰጠ” ስለተባለው የኢትዮጵያ ግዛት መርምሮ ለህዝብ ይፋ እንዲያደርግ እጠይቃለሁ። የኢህአዴግ መሪዎች እውነት ከእነርሱ ዘንድ አለ ብለው የሚያምኑ ከሆነ መርማሪ ኮሚሽኑ ነፃ ያወጣቸዋል።

 

በሀገሩ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የመወሰን መብቱ መረጋገጥ አለበት። የኢትዮጵያ ህዝብ ያልወሰነው ማንኛውም ስምምነት ሆነ ውል ወደፊት ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። አይኖረውምም!!!!!

 

ኦማር አልበሽር ከአማካሪዎቻቸው ጋራ ይሄን ጊዜ “ኢትዮጵያ የሚረባ ሰው የላትም” እያሉ ያፌዙ ይሆናል። ነገር ግን በጋራና በአንድነት ለዚህ ወራሪ ኃይል መልስ የምንሰጥበት፣ ኢትዮጵያ ልጆች እንዳሏት የምናሳውቅበት ጊዜው አሁን ነው። በውጭ አገር፣ በአገር በውስጥ፣ በገጠርና በከተማ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዐፄ ዮሐንሶች እንዳሉና አገርን የሚሸጡ ለጊዜው የተመቻቸው እጅግ በጣም ጥቂቶች እንደሆኑ የምናውጅበት ጊዜው አሁን ነው።

 

በዚህ አጋጣሚ በአራት ኪሎ የሚገዛውን አምባገነን ስርዓት እንደ ምሰሶ ሆናችሁ የምትሸከሙ የኢህአዴግ እንዲሁም የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት አባላት የሆናችሁ ሁሉ፣ ከዝምታ የምትወጡበት ጊዜው አሁን እንደሆነ ላሳስብ እወዳለሁ። እርስ በርስ ከፋፍሎ የተበተባችሁን የእነ አቶ በረከት ስሞዖንና አቦይ ስብሓት ነጋን መረብ በጣጥሳችሁ የጀግናውን የዐፄ ዮሐንስን ኮቴ በመከተል ኢትዮጵያን የማዳን ታሪካዊ አደራ አለባችሁ።

 

እግዚአብሔር አገራችን ኢትዮጵያን ይጠብቃት!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!