W/z Azeb Mesfin ወ/ሮ አዜብ መስፍንዘኢትዮጵያ

ቦታው ኒዮርክ ውስጥ ነው። አፓርትመንት ቪላ የሚሉት አይነት ልዩና ትልቅ የእንግዳ ማረፊያ ነው። ከማረፊያ ሳሎን ውስጥ ጠ/ሚ/ር አቶ መለስ ዜናዊ እና በኒዮርክ የተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ቋሚ  አምባሳደር የነበሩት አቶ ፍስሃ ይመር ብቻቸውን ተቀምጠዋል። አቶ ፍሰሃ ለአቶ መለስ ብርቱ ማብራሪያና ሪፖርት እያቀረቡ (ብሪፍ) እያደረጉ ነው።

 

 

በዚህ መካከል የሳሎኑ በር ድንገት ተበርግዶ ተከፈተ። የአቶ መለስ ባለቤት ወ/ሮ አዜብ ነበሩ። ወይዘሮዋ ሁለቱንም ሰላም ሳይሉ እንደተቆጡ በቀጥታ ወደ መኝታ ክፍሉ አመሩ። የመኝታ ክፍሉን በር በርግደው መልሰው ደግሞ በኃይል እስኪጮህ ዘጉት። ወዲያው ሰከንድም ሳይቆዩ ደግሞ እንደገና በርግደው ወጡ። አሁንም በሩን በኃይል አጩኸው ዘጉና ወደ ዋናው በር አመሩ። እዚያም እንደዚያው ኃይል በተቀላቀለበት ሁኔታ በሩን ደረገሙት። አዜብ ሆን ብለው እንዳደረጉት ያስታውቃል። ይህ ሁሉ ሲሆን አቶ መለስ ቀና ብለው የተመለከቱት አንዴ ብቻ ነው። ምንም እንዳልተፈጠረ ሁሉ አቶ ፍሰሃን እንዲቀጥሉ በእጃቸው ምልክት ሰጧቸው።  

 

W/z Azeb Mesfin ወ/ሮ አዜብ መስፍንየወ/ሮ አዜብ ጠባይ ገና ከበረሃው ጊዜ ጀምሮ በአቶ መለስ ጓደኞች ይታወቃል። ለምሳሌ በወያኔዎቹ ወንዶችና ሴቶች መካከል ምንም ዓይነት የጾታ ግንኙነት ክልክል መሆኑ ከቀረ በኋላ አመራር አካላቱ መኝታ ቤት ተዘጋጅቶላቸው ነበር። ወደ በኋላው ላይ፣ አቶ መለስ እና ወ/ሮ አዜብም የራሳቸው መኝታ ቤት ነበራቸው። የአቶ መለስ የቅርብ ጓደኞች፣ በተለይም የፓርቲው የሥራ አስፈጻሚ አባላት፣ ማድረግ ከሚያስጠላቸው ነገር ውስጥ አንዱ፣ ወደ አቶ መለስ መኝታ አካባቢ መሄድ ነበር። ምክንያቱም አዜብ አቶ መለስን ሲያመናጭቁ ማየት አይፈለጉም። የአዜብ ሁኔታ ለግልፍተኞቹ ታጋዮች የሚዋጥ ነገር አይደለም። ስለዚህ አቶ መለስን በግልም ሆነ በሥራ ጉዳይ ከፈለጓቸው ውጭ ቆመው ማስጠራትን ይመርጣሉ እንጂ ወደ ውስጥ አይዘልቁም።

 

“በዚያ ላይ በጣም ነው የምትጮኸው፣ ጩኽቷ ደግሞ ውጭ ድረስ ሁሉ ይሰማል …” ብለዋል ምንጫችን።  

 

በ1970ዎቹ ከቤተሰባቸው ጋር ተሰደው ሱዳን ያደጉት ወ/ሮ አዜብ፣ የኢትጵያዊት እመቤትነትን ወግ ብዙም የሚያውቁ አይመስሉም። ስሜታቸውን በቀላሉ ይገልጻሉ። መቆጣት ካለባቸው ይቆጣሉ። መነጫነጭ ካማራቸውም እንደዚያው ናቸው። ግንኙነት አያስጨንቃቸውም። በዓለም ላይ የሚፈሩት ሰው ያለ አይመስልም። የአቶ መለስ ባለቤት ሰለሆኑ ሳይሆን ድሮም እንደዚሁ ነበሩ ይባላል። ድርጅቱ አቶ መለስን ላለማስከፋት ተሽክሟቸው መኖሩን የሚናገሩ አሉ። ገና በ15 ዓመታቸው ወያኔን በሱዳን ጽሕፈት ቤቱ የተቀላቀሉት “ጓል ጎላ” (አዜብ) ግን ይሄ የተወሳሰበው ነገር አይገባቸውም። አቶ መለስንም የማይፈሩ መሆኑን ለማሳየት ርቀው የሚሄዱትን ያህል አቶ መለስንም የማያስነኩ ነብር መሆናቸውን ያሳዩበት አጋጣሚ ብዙ ይመስላል። አቶ መለስ ይቺን ሚዛን ሳይወዷት አይቀርም። ለምሳሌ ፓርቲያቸው ህወሓት ለሁለት ተከፍሎ አቶ መለስ አደጋ ላይ በወደቁ ጊዜ፣ የተከፈለውን ካድሬ ሁሉ በማስተባበር አቶ መለስን ያዳኑት አራት ሰዎች ናቸው። አቶ ስብሓት ነጋ፣ አቶ  አርከበ እቁባይ፣ አቶ ብሐርሃነ ገ/ክርስቶስ እና ወ/ሮ አዜብ መስፍን ናቸው።

 

አዜብ አቶ መለስ ራሳቸው እስኪገርማቸው ውስጥ ውስጡን ብዙ ሥራ ሠርተዋል። የአዜብ ማንነት በአቶ መለስም ዘንድ ይበልጥ ያንሰራራው ከዚያን ጊዜ በኋላ ነው የሚሉ አሉ። በዚያ ላይ በቅርብ ጓደኞቻቸው ሁሉ ሊፈነገሉ የነበሩ አቶ መለስ የቻሉትን ነገር ሁሉ ወደ ሚያምኑት ሰው ማዞር ነበረባቸው። ከአዜብ በላይ ማን ሊቀርባቸው ይችላል? ስለዚህ አዜብ «ጓል ጎላ» በ8ኛው የህወሓት ድርጅታዊ ጉባኤ ለማዕከላዊ ኮሚቴነት ተመረጡ። የፓርላማም ገብተው ከአቶ መለስ ጎን ተቀመጡ። በፓርላማ ውስጥም የማኀበራዊ ጉዳዮች ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆኑ።

 

የህወሓት ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የኢሕአዴግ ም/ቤት አባል የኤፈርት ምክትል ሥራ አስፈሚ፣ … እየሆኑ ሹመት በሹመት ላይ ተደረበላቸው። ድሮም ሰው የማይፈሩት አዜብ አሁን ደግሞ ጭርሱኑ ሰው የሌለ መሰላቸው። አቶ መለስና አዜብ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰውን ባለመፍራት አንድ ናቸው። በዚህ ግን ቢያንስ አቶ መለስ ይሻላሉ። ቢያንስ አንድ አዜብን ይፈራሉ።  

 

ለምሳሌ ከሁለት ወራት በፊት በመቀሌ የህወሓት የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ነበር። “ስብሰባ ከማለት ግምገማ ብንለው ይሻላል” ብለዋል ምንጫችን። እዚያ ግምገማ ላይ ወ/ሮ አዜብ ስለ ኤፈርት (የለበጣም ቢሆን) የኦዲት ሪፖርት ማቅረብ ነበረባቸው። ለነገሩ ሲጀመር ራሱ ሪፖርቱን ማቅረብ የነበረባቸው አቶ አባዲ ዘሙ ነበሩ። ምክትልነት የማይስማማቸው አዜብ ግን እንዲህ ያለውን እንደማይቀበሉ የታወቀ ነው። ችግሩ እሱ ብቻ ሳይሆን ወ/ሮ አዜብ ባቀረቡት ሪፖርት አቶ አርከበ ዕቁባይን መክሰሳቸው ነው። እንደ አዜብ ሪፖርት፣ ኤፈርት ጥሩ እየሠራ አይደለም። ምክንያቱም “ኤፈርት መውደቅ የጀመረው ከድሮ ጀምሮ ተያያዥ ችግሮች ስለነበሩበት ነው” … እያሉ በመካከሉ የፖለት ቢሮ አባልነት ሳይሆን አዜብነታቸው ስለመጣባቸው፣

 

“እንዲያውም ኤፈርት ሞቷል። ኤፈርትን የገደለው አርከበ ነው” የሚል አገላለጽ ተጠቀሙ።

 

የማይሞተው ኤፈርት መሞቱን ለመግለጽ ሳይሆን አርከበን ለመንካት ሆን ብለው ነው።

ወደ ኋላ ብዙ ተጉዘው፣ ነገር ጎትተው የተናገሩት መሆኑ ግልጽ ነበር።   

ግምገማ ላይ የማይባል ነገር የለም።   

አቶ አርከበ ከንቲባ ከመሆናቸው በፊት የመስፍን ኢንጂነሪንግ እና የኤፈርት ኢንደስትሪው ዘርፍ ሰብሳቢ ነበሩ። ያኔ በእሳቸው አመራር ብዙ ስህተት መፈጸሙን በተደረገ ጥናት መረጋገጡን ነበር አዜብ የገለጹት። ስብሰባውን የሚመሩት አቶ መለስ ዜናዊ ነበሩ። ስለ ጉዳዩ አቶ አርከበ የሚለው ነገር ካለ በማለት ወደ አቶ አርበከ መመልከታቸው አልቀረም። አቶ አርከበም እድሉን እስኪያገኙ ድረስ ለመናገር መቸኮላቸው ያስታውቃል። ብዙ ማብራሪያ ይሰጣሉ የተባሉት አቶ አርከበ ግን ትንሽ ነገር ብቻ ተናግረው ዝም አሉ። ተሳድበው ማለት ይቻላል።   

 

“እኔ” አሉ አቶ አርከበ “ እኔ አሁን ስለቀረበው ኦዲት ሪፖርት ያለኝን አስተያየት መስጠት እችል ነበር። ስለተባለው ነገር መልስ ስለሌለኝ ሳይሆን አንቺ ይሄን ሪፖርት ማዘጋጀትም ሆነ የኔ መልስ ይገባሻል ብዬ ስለማላስብ ነው” ብለው ዝም አሉ።   

 

አቶ መለስ ምንም አስተያየት ሳይሰጡ ወደ ሚቀጥለው ጉዳይ እንሂድ ብለው ስብሰባውን በሌላው ጉዳይ መምራት ቀጠሉ። አቶ መለስ እንዲህ የሚያደርጉት እሳቸውና አዜብ የተለያዩ ሰዎች መሆናቸውን ለማሳየት ነው ብለው የሚያምኑ አሉ። በእፍረት እየተሸማቀቁ ነው የሚሉም ተሰምተዋል። ሌሎች ደግሞ ሆን ብለው ነው እንዲያውም አዜብን በተናገሩላቸው ቁጥር እሳቸው ይበልጥ ይጠቀማሉ ባዮች ናቸው።  ይህ የአቶ መለስ ስትራቴጂ ምናልባት ከአናት ላሉት የወያኔ ባለሥልጣናት እንጂ ታች ላሉ የሠራ አይደለም። ምክንያቱም አዜብን መናገር ቀርቶ ቀና ብሎ ማየት በብዙዎቹ የበታች ባለሥልጣናት ዘንድ የሚታሰብ ነገር አይደለም።

 

“ፓርቲው አሁንም በህይወት አለ። አምባገነንነት አልሰፈነበትም፤ እንኳን አዜብን መለስንም ቢሆን መቃወም ይቻላል …” የሚል ፖለቲካ ለአቶ መለስ ቢሠራም ለእነ አቦይ ስብሓት ነጋ ግን የሠራ አይመስልም። ታች ድረስ ወርደው የገቡበት እየገቡ የፈለጉትን ማስፈጸም የቻሉት ወ/ሮ አዜብ የአቶ ስብሓትን የሥልጣን ቀጠናና ዘዴ ሳይጋፉ አልቀሩም።

 

ወ/ሮ አዜብ እንደ አቶ መለስ በስብሰባ፣ እንግዳ በመቀበልና በመሸኘት ተወጥረው አይውሉም። ነጻ ናቸው። አጃቢ አያስፈልጋቸውም። ብዙ ጊዜ የሚወዷትን “ኢንፊኒቲ” መኪናቸውን፣ ራሳቸው እያሽከረከሩ፣ ከፈለጉት መስሪያ ቤት ከች ይላሉ። ወይንም ስልክ አንስተው የፈለጉትን ይጨርሳሉ። ከተማ መዋል፣ በየቡና ቤቱ፣ በየቢሮው፣ በየግብዣው እየዞሩ ነገር ሲያገነኛኙ የሚውሉት አቶ ስብሓት ነጋ፣ የወ/ሮ አዜብን ስም በየቦታው መስማት ያስጠላቸው ብቻ ሳይሆን፣ ለፓርቲያቸውም አደጋ ነው ብለው ያስባሉ።  ዛሬ የወ/ሮ አዜብ ስም በየቦታው ይነሳል። ኃይለኛ ናቸው፣ ቁጡ ናቸው፣ ግልምጫቸው አይጣል ነው፣ የፈለጉትን ነገር ወዲያው አደራርገው ቶሎ ካልሸኟቸው የተናቁ ይመስላቸዋል። ምንም ነገር አይገባቸውም … ወዘተ ብዙ ይባላል።  

 

“ሰው እስኪ አሁን ከኃ/ማርያም ደሳለኝ ጋር ይጣላል?” ብለዋል አንዱ አቀባያችን።

 

አዜብ ያልተጣሉት ሰው የለም። ከበረከት፣ ከአርከበ፣ ከስብሓት፣ ከአባዲ፣ ከሳሞራ፣ … ወዘተ። የፈለገው ነገር ቢመጣ ከአዜብ ጋር የማይጣሉት ቴዎድሮስ አድኃኖም ብቻ ናቸው ይባላል። አዜብን ለህወሓት ሥራ አስፈጻሚነት የጠቆሟቸው እሳቸው ስለሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ቴዎድሮስ አዜብን እንደ ህጻን አበራርደው መሸኘት ይችላሉ ይባላል። ቴዎድሮስ፣ ከበረሃ ያልመጡ ወያኔነትን ብዙም የማያከሩ፣ አራዳ ቢጤ፣ ልስልስና ተግባቢ ናቸው ይሏቸዋል። ብዙዎቹና በተለይም አድርባዮቹ ግን አዜብ ገና ሳይደርሱባቸው ወደፊት እንዳትቀየመኝ በማለት ውለታ ለመዋል የሚሽቀዳደሙ መሆናቸው ተነግሯል።  

 

“የአዜብን ነገር ከሷ ጋር ብቻ ጨርሱ” የሚመስለው የመለስ አካሄድ፣ ብዙም አሸንፎ ያልወጣ በመሆኑ፣ ወያኔዎቹ ውስጥ ውስጡን በቁጭት እየታኘኩ ይመስላል።

 

“መለስ እንዳሉት በራሳቸው ፈቃድ ከሥልጣን ቢወርዱ፣ ከምንም ነገር በፊት የሚያደርጉት ነገር ቢኖር አዜብን መፍታት ይመስለኛል፣ እኔ ለሱም ቢሆን ሰላም የምትሰጠው አይመስለኝም። ብዙ ነገር ሳታበላሽበት አትቀርም” የሚሉም አስተያየት ሰጪ አጋጥመውናል።

 

 የአቶ መለስ ልጅ ሳትቀር አንዳንዴ ከሰዎች ጋር ሽምግልና እየገባች፣  

 

“የእናቴን ጠባይ ታውቃላችሁ። አዲስ ነገር አይደለም። ስለዚህ ፕሊስ አንደርስታንድ አድርጓት …” እያለች በጭንቀትና ሐፍረት መማጸኗን በእማኝነት የሚያነሱም አሉ።  

 

የአዕምሮ ዕጢ በሽተኛ ሆነው ብራስልስ የሚመላለሱት አቶ መለስ ዜናዊ፣ ራሳቸው ጭምር ያመሷትን የታመሰች አገርና ያወሳሰቡትን ድርጅታቸውን ይዘው፣ ከበሽተኛው ልጃቸውና ከአዋኪዋ ባለቤታቸው ጋር ኑሮን መግፋት ሳያሳስባቸው አይቀርም። እንደ ሻርክ ጥርስ ተከፍቶ የሚጠብቃቸው ህዝባዊ ማዕበልም መምጫው አይታወቅም። ፈልገውትም ሆነ ሳይፈልጉት ከሚያስፈልጉት በላይ ያከማቹት ሥልጣን ግን ከውጭ ተቃዋሚዎች እንጂ ከውስጥ ብል ያዳናቸው አይመስልም።  

 

“አንተስ የራስህ ጉዳይ! ድርጅታችንን ግን ገድለህ መሄድ የለብህም!” ባይ ሆነው የተገኙት አዛውንቱ አቦይ ስብሓት ነጋ፣ ከመሞታቸው በፊት ማስተካከል የፈለጉት ነገር ያለ ይመስላል።

 

የወ/ሮ አዜብ ዝላይም ሆነ የአንድ ሰው (አቶ መለስ) አምባገነንነት ኢትዮጵያ ውስጥ ስለመስፈኑ “ሰዎች ጥያቄ እያነሱ ነው። ይህ ጥያቄ በህወሓት ታጋዮችም ውስጥ ያለ ይመስለኛል” ብለው እስከመናገር መድረሳቸው ይህን አመልካች ይመስላል።  

 

በተለያዩ ስብሰባዎች በወ/ሮ አዜብ ተርብነት የተነደፉት፣ ቆሊያቸውን እየተገፈፉ፣ የተዋረዱት አቶ ስብሓት እያደር ሲያስቡት አንድም እፍረት አንድም ውድቀት ሆኖ ሳይታያቸው አልቀረም።

 

በዚህ የተነሳ ይመስላል፣

“ህወሓትን ከሴት ቀሚስ ነጻ ባላወጣ እኔ ስብሓት አይደለሁም!” የሚለው አባባላቸውን ሰሞኑን መልሰው ማስተጋባት ጀምረዋል።

 

“ድርጅታችንን እናድን” የሚል ዘመቻ የያዙት ስብሓት፣ ወደ ቀድሞ ታጋዮች ሳይቀር ጎራ ማለት መጀመራቸው እየተሰማ ነው።

 

በሰሞኑ አንድ አጋጣሚ ነገር ሽረባም ሆነ ድጋፍ ፍለጋ በመለስ ወደ ተባረሩት የቀድሞ የኢህአዴግ ኤታማዦር ሹሙ ወደ ጄነራል ፃድቃን ወ/ትንሣይ ጎራ ብለው ነበር አሉ።  

 

ስብሓት - ህወሓትን ከሴት ቀሚስ ነጻ ብናወጣ ምን ይመስልሃል?

 

ፃድቃን - ስማ ልንገርህ ህወሓት ነጻ መውጣት ካለበት ለዚህ ሁሉ ምክንያት ከነበረው ከእንዳንተ ዓይነቱ ሰው ነው። ታዲያ እንዴት አድርጌ ነው ችግር ከሆንከው ካንተ ጋር ህወሓትን ነጻ የማወጣው? 

 

ከዚያ በኋላ ምን ተባብለው ይሆን? 

እኛ መቼም በነሱ ዓለም ጨርሶ የለንም።  

ጨቋኝም ተጨቋኝም እነሱ እየሆኑ ነው። አሁንም ላያችን ላይ ሊጠጋገኑ ይታሹብናል።

 


(ይህ ፅሁፍ በዋሽንግተን ዲሲ እና በአካባቢዋ ከሚሰራጭ ጋዜጣ ላይ በቅርቡ ታትሞአል። የጋዜጣው ስም ‘ዘኢትዮጵያ’ ይባላል። የመጣጥፉ ፀሐፊ ማን እንደሆነ በውል አይታወቅም።)

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!