አትክልት አሰፋ (ከቫንኩቨር ካናዳ)

ዛሬ ጠዋት በጣም ጠዋት 4 ሰእት ከ11

ገበሬው በጉን ለመሸጥ በግ ተራ ገብቷል። በግተራው ገዥና ሻጭ በርከት ብለው ይተራመሳሉ። በጉን ለመሸጥ ከቆመው ገበሬ ጋር የተጠጋው ገዥ ‘ስንት ናት’ ብሎ አንዷን በግ ይጎትትና ወገቧንም ይፈትሻል። በጓ ታስላለች። እንዴ ምንድነው? ይላል ገዥ ገበሬውን እያየ በመደናገጥ። ገበሬው ዝም ይላል። ከእንደገና ወገቧን ያዝ ያደርጋታል፤ ገዥ። አሁንም በጓ ታስላለች ‘ምን ሆና ነው ታስላለችሳ’ ይላል ገዥ። አሁንም ገበሬ ዝም ይላል። “አትናገርም እንዴ ያስላታል፤ አሟታል እንዴ?” ቢለው ገዥው:   “መሆኑ ነዋ” አለ ገበሬው ጋቢውን ተከናንቦና ውሸት ላለመዋሸት ተጨናንቆ። የሚያስላትን በግ ቢችል ሊሸጥ ነበር ሀሳቡ አስተዳደጉ ውሸትን ስላላስተማረው ውሸቱን መቀላመድና አታሎ መሸጥ አልወደደም። እናም በጓን ለገበያ ቀርባለች፤ ግን ግን በጓ በገበያ ላይ አለችም የለችምም።

 

ኢትዮጵያ ስለምትባል ሀገርና ህዝብ ለመጻፍ ብዙ ውጣ ውረድ ወይንም ስለሚጽፉት ነገር መጨነቅ አያሻም። ኢትዮጵያ ውስጥ? በተለይ የሶማሌና የደቡብ ክልል ህዝብ በርሃብ ሲቃ ሲያጣጥር፣ ከብትና አራዊቱ በጠኔ መውደቁ እየተሰማ ስለምን ስለሌላ ይጻፋል?። ሰው በሰውነቱ መኖር ተከልክሎ፣ ለ20 አመት በአንድ ግለሰብ የሚመራ መንግስት በጫንቃው ላይ ተሸክሞ ስለ ምን ሌላ ነገር ይጻፍለታል?። ለምን ተናገርክ? በሚል አሸባሪ ነህ ተብሎ ወህኒ የሚያጉሩት ህዝብ መሀከል ተፈጥሮ እኮ ስለምን ሌላ ነገር ሊጻፍለት ይታሰባል?። አጭበርባሪ ፓትሪያርክና ተጭበርባሪ ህዝብ ተሸክሞ እኮ ምን ታስቦ ስለሌላ ለመጻፍ ሰው ይነሳሳል?። የእምነት አባት አስታራቂ፣ ጠባቂ ባልሆነባት ምድር ላይ ተፈጥሮ ሌላ ምን አሰኝቶ እስኪርቢቶ በወረቀት ላይ ይወርዳል።

 

በዋና ከተማችን አዲስ አበባ በድንገተኛ አደጋ ከትምህርት ቤት ወደ ሆስፒታል የተወሰደ ህጻን ሃኪሞች በሽታ ፍለጋ ሲሯሯጡና ለማያውቁት በሽታ ለቀዶ ጥገና ሲሽቀዳደሙ የልጇን መውደቅ የሰማች እናት ‘በሽታውን አውቀዋለሁ ተውት ለልጄ ምግብ ስጡት ይድናል’ ብላ የተሳቀቀችበትና ለሶስት ልጆቿ በየቀኑ ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ በየተራ ምሳ  እንደምትቋጥርላቸው ገልጻ ህጻኑ ልጅ ‘ትላንትና ምሳውን በተራው የበላ ነው’ በማለቷ ከቀዶ ጥገና ልጇን ያዳነች እናት ባለበት ሀገር ተወልደን ምን ተብሎ ነው ስለሌላ ለመጻፍ የሚሮጠው።

 

አስር የአዲስ አበባ የአንድ ትምህርት ቤት ህጻናት ልጆች ወድቀው ችግሩ የምግብ እጦት እንደሆነ በአደባባይ እየታወቀና ቤተሰቦች እየመሰከሩ “ባልታወቀ በሽታ” ብሎ በቴሌቭዥን በመዋሸት ታላቁን የአዲስ አበባን ርሃብ የሚያስቀይሱ ቱባ ቱባ መሪዎች ባሉባት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ተፈጥሮ ስለ ሌላ ስለምን ለመጻፍ ይሞከራል እናንተዬ?።

 

አሁንም ቀጥል ቀጥል አለኝ ልጨምርበት መሰል። አንድ ኢትዮጵያ ደርሶ የመጣ ወዳጄ በምስክርነት እንዳጫወተኝ ሱማሌ ተራ አካባቢ ባለቤቱ ሱፐር ማርኬት እቃ ለመግዛት ከመኪና በወረደች ሰአት መኪና ውስጥ ሳይወርድ አንድ ሰቅጣጭ ትርኢት ያይ ነበር። አዎ አንድ የኔቢጤ ለማኝ ህጻን ልጅ ባገኛት ገንዘብ እዚያው አካባባቢ ካለች ዳቦ ቤት ሄዶ ዳቦ ይገዛና መግመጥ ይጀምራል። አንዲት በእሱ እድሜ ያለች ሌላ ሴት ህጻን የኔ ቢጤ ተንደርድራ ትመጣና ‘አግምጠኝ’ ‘አግምጠኝ’ በማለት ስትጠጋው ልጁ ዳቦውን በሁለት እጁ ግጥም አድርጎ ይዞ መግመጥ የሚገባት ድረስ በጣቱ ቆንጥጦ ያገምጣታል። እና ለእሱም በተራው ይገምጣል። ዳቦዋ እስክታልቅ በጋራ ተጋመጧት። ይሄንን ችግርን በጋራ የሚያሳልፉ ለማኝ ህጻናት ያሉባትን ምድር በጫንቃ ተሸክሞ ሰው ሁሉ ሀገር ሀገር ከሚል ውጭ  ስለቅንጦት ለመጻፍ ምን ይዳዳዋል።

 

በተጓዳኙ ደግሞ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ፖለቲከኞች በቅንጦት እኔ እበልጥ እኔ በማለት እየተተራመሱ የሚታዩበትን የውጭ ሀገርን ኑሮ ታያላችሁ፡ ልጆቹን የግል ትምህርት ቤት አስገብቶ በተድላ ከመኖር ውጭ ይህ ሁሉ ውጣ ውረድ ምንም የማይመስለው ግለሰብ ሲተራመስ ትመለከታላችሁ። በየቦታው እየተሹለከለከ በሁሉም ቦታ አለሁ እያለ ነገር ግን በሁሉም ቦታ የሌለ ግለሰብ ሲሯሯጥ ትመለከታለህ፣ እኔ በቆፈርኩት ቦይ ካልፈሰስክ የማሪያም ጠላት የሚሉ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን ማየት ናላሽን ያዞረዋል። ለመስራት፣ ለመሮጥ ብሎም የሀገርንና የህዝብን ሮሮ ተሸክመው ከሚንከራተቱ ጥቂት ሰዎች ይልቅ በእጥፍ ድርብ ግዴለሽና ሞራል የለሹ በዝቶ በአይንህ ጥጋጥግ ማየት የተለመደ ነው።

 

ብቻ እነኚህ ሁሉ ትርምሶች ሲተራመሱብኝ እና ሲመላለሱብኝ ነው ድንገት ቫንኩቨር የመጣችልኝ። የኔዋ ቫንኩቨር። ውቧ። ደጓ ቫንኩቨር፣ ግን ግን በደጎችና በእኩዮች የታጨቀችው ሀገር። በቫንኩቨር ሁሉም አለ፤ ግን ሁሉም የለም። የምኖርባትን ቫንኩቨርን በመዳሰስ  ኢትዮጵያንና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን መግለጽ ይቻላል።

 

በውጭ ሀገር ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ስቃይ፣ ድካም፣ ብርታት፣ እንቅፋት፣ ጠብ፣ ፍቅር፣ መተቃቀፍና መገፋፋት ምኑ ቅጡ በቫንሲቲ የሌለ የለም፤ ሁሉም አለ። ግን ግን ሁሉም የለም። በአለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን ኑሮ በቀጭኑ እዚህ ቫንኩቨር ያገኙታል።

 

የሀይማኖት ትርምስ ነው? ምን ችግር አለ እዚህ እኛ ጋር በሽ ነው። ለዚያውም ብዙ የሚያስብል ብዙ የሚያስተዛዝብ፣ ብዙ የሚያጽፍ። ስንቶቹን አየን ጃል። ታላቁንም ታናሹንም ታናሽ፤ ታናሹንም ታላቁንም ታላቅ አድርገው ማየት ይችላሉ። እዚሁ ውቧ፣ ደጓ ቫንኩቨር ውስጥ።

 

እናም በቫንኩቨር ኦርቶዶክስ ሀይማኖት ብትሉ ሁለት፣ ሶስት ምናልባትም አራት፤ ጴንጤ ያሉ እንደሆን አራት ቢበዛ አምስት፣ ሙስሊም ቢሉ የሰሞኑ ጉድ ከተጣራ በቁጥር። ብቻ ምኑ ቅጡ። ሁሉም ሞልቷል። በዝርዝር የሚገባበት።

 

ከሀዲ ታገኛላችሁ በቫንኩቨር ዛሬ ያለውን ነገ የማይደግም ቀላባጅ። ቃሉን ጠባቂም አለ እውነተኛ በማተቡ የጸና እዚሁ ቫንኩቨር ውስጥ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ተምሳሌት መንደር። ቫ.ን.ኩ.ቨ.ር

 

ቫንኩቨር ውብ ከተማ ናት የሌሎቹን ዜጎች ጣጣ ትተን በዚህች በውቧ መንደር ያሉ ኢትዮጵያዊያንን አበጣጥሮ ማየት የግድ ይላል። በፖለቲካ ብትሄዱ ብዙ ጉዳጉዶች አሉ፤ በግለሰቦች ቢጓዙ አ…ቤ….ት የምታዩት ሰብእና፣ የሚመለከቱት ማንነት። ዛሬ ቀይ ነገ ጥቁር ሁሉም አለ ሁሉም። እዚችው ቫንኩቨር። ከነዚያ ከታላላቆቹ ሀገርንና ህዝብን በማገልገል፤ የጥቁርን ማንነት በአደባባይ በማሳየት በእውቀትና በብርታት ከሚታወቁ ታላላቅ እውነቴን ነው እጅግ ታላላቅ ሰዎች እስከ የኔ ቢጤው ታች በጣም ታች እስካለው ጉድ እዚሁ በኔ ከተማ ቫንኩቨር ትመለከታላችሁ። ከደጋጎቹና ከቸሮቹ እስከ ክፉዎቹና እኩዮቹ፣ ከአተራማሾቹ እስከ ተተራማሾቹ፤ ከሩህሩሆቹና ሰውን ከልብ ለመርዳት ከሚፍጨረጨሩት እስከ አስመሳዮቹና ጨካኝ የእናት ጡት ነካሾቹ በቫንኩቨር ትመለከታላችሁ። ለዚያም ነው በቫንኩቨር ሁሉም አለ የምለው ደግሞም አዎ ሁሉም አለ፤ ግን ግን ሁሉም የለም።

 

እናም እኔ ራሴ ውስጧ ስላለሁባት ስለሽቅርቅሯ መንደር ቫንኩቨር ልዘምት ወሰንኩ ውስጡን ለማበራየትና ለመመርመር ግድ አለኝ። በጓዳ ተደብቀው ከሚኖሩት፤ ራሳቸውን በአደባባይ እስከሚረጩት፤ ስራ ለመስራት ከሚደክሙት ተንኮልና ማናለብኝነት አስከሚወጣጥራቸው። ከትጉሀኑ እስከ ስንኩላን ሀሳብ ቀማሪዎች፤ ከአምባ ገነን እስከ ተራ ገነኑ ድረስ ሁሉም አሉ። እዚህ ቫንኩቨር ያሉ ሁሉም ቦታ ቢዞሩ ሊኖሩ የሚችሉ ገጸባህሪያት አሉ በታላቋ ቫንኩቨር። የምጀምረው በሀይማኖትና በፖለቲካ አተራማሾቹና ተተራማሾቹ ነው። የእኔ የህይወት ጥሪ አንድ ነው የማውቀውን በመረጃ ያረጋገጥኩትን እውነት ለናንተ መስጠት። ማቀበል። ልክ ነው ደግሞ ግዴታየ ያ ነው እናም ሁሉንም ያየሁትን የታዘብኩትን እነግራችኋለሁ እና እናንተ ትፈርዳላችሁ።

ሳምንት እቀጥልበታለሁ

አክባሪያችሁ እኔ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ