Prof. Mesfin Woldemariamመስፍን ወልደማርያም (ፕ/ር) ግንቦት 2000

በጥንቶቹ መሣፍንት ዘመን፣ የአንድ ቡድን የሥራ መሪ ሆኜ ወደ ጎሐጽዮን ኼጄ ነበረ። የማላውቃቸው የወረዳው አስተዳዳሪ የሆኑ አንድ ባላምባራስ፣ መኪና ውስጥ ተቀምጬ ከሰው ጋር ስነጋገር አዩኝና አልወደዱልኝም። “ማነው ይኼ፣ ምንድነው የምታነጋግረው፣ …” እያሉ ሰውየውን ሲቆጡ፣ ከመኪና ወረድኩና ማንነቴን ገለጽኩላቸው፤ ደብዳቤም አሳየኋቸው። ከምመራው ቡድን ውስጥ አንድ አሜሪካዊ አይተዋልና መሪው እኔ ነኝ ስላቸው በጣም ተናደዱ። “ይኼ ደፋር! ፈረንጅ እያለ መሪው እኔ ነኝ ይላል?!” ብለው ወደ ፖሊሱ ዞሩና “ውሰደው፤ እሰርልኝ!” አሉት።

 

ፖሊሱ ግራ ገባውና ያለ ደብዳቤ አላስርም አለ። ምን ችግር አለ፣ ወረቀት እንዲመጣላቸው አዘዙና ባቡር መንገድ ላይ ቁጭ ብለው ጻፉለት፤ ፖሊሱ ይዞኝ ኼደ፤ አንድ ቀን አደርሁ። እንግዲህ ይኼ ሕግ ነው ወይስ ጉልበተኛነት ነው፤ ጉልበት የሆነላቸው ፖሊስ ነው እንጂ እሳቸውማ በጉልበት ለእኔ አይበቁም ነበር። በኢትዮጵያ ሰውን ማሰር እንዲህ ቀላል ነበር አሁንም ነው። የጉልበት መግለጫ ከመሆን በቀር ሌላ ዓላማ የለውም።

 

ይህ አጉል የጉልበት መግለጫ አንዱ የባሕል መሠረት ሆኖ በጣም ስለተዋሃደን፣ አብሮን የተፈጠረ ይመስላል፤ የሚያስረው መንግሥት ወይም ፍርድ ቤት ብቻ አይደለም፤ ወላጆችም ያስራሉ፤ ጌቶችም ያስራሉ፤ ማንም ሹም ነኝ ባይ ያስራል። በደርግ ዘመን ቀበሌው ሁሉ እንደፈለገው ማሰር ስለጀመረ ቀበሌዎች ሰው እንዳያስሩ የሚል ትዕዛዝ ተላልፎላቸው ነበር። ማሰር የጥፋት ውጤት ሳይሆን፣ ልዩ ደስታን የሚሰጥ የጉልበት መግለጫ ነው። የጉልበት መግለጫው መሠረቱ ከባድ የሚያቃዥ ፍርሃትና ስጋት ነው። በጥንት ዘመን የሥልጣን ተቀናቃኝ ይሆናሉ ተብለው የሚፈሩት የነገሥታት ልጆች በየተራራው ላይ ወህኒ ቤት ውስጥ፣ ያለምንም ጥፋት ይኖሩ እንደነበሩ እናውቃለን። እንዲያውም በዘመናችን የልጅ ኢያሱ ወንዶች ልጆች ሁሉ፣ በሚያሳዝን ሁኔታ ውስጥ በግዞት ሲኖሩ አይተናል። አሳፋሪ የፍርሃት ባሕል ነው፤ ገና አልለቀቀንም።

 

በመሠረቱ መታሰር ቅጣት ነው፣ አንዳንዴ መታገት ይባላል። የሚያስረው ወይም የሚያግተው ማን ነው? የሚታሠረው ወይም የሚታገተውስ ማን ነው? ያለምንም ጥርጥር ለማገት ወይም ለማሰር ጉልበት ያስፈልጋል፤ ያለምንም ጥርጥር የሚታሰረው ወይም የሚታገተው ሰው የጉልበተኞቹ ዓይን ያረፈበት መሆን አለበት።

 

ከሕግ ጋር ምንም ዝምድና የለውምና በማገቱ እንጀምር። በአሜሪካና በኢጣሊያ ብዙ የወንጀል ድርጅቶች አሉ። በጉልበታቸው ከመንግሥት ጋር የሚፎካከሩ ናቸው። ያልገበረላቸውን እንኳን ማገትና ማሰቃየት እስከ መግደልም ይደርሳሉ። በጣም ሀብታሞች ስለሆኑም ፖሊሶችንም ሆነ ዳኞችን በገንዘብ እየገዙ፣ ተግባራቸውን በትክክል እንዳይፈጽሙ ያደርጋሉ። እነዚህ የወንጀል ድርጅቶች፣ ከሕግ በላይ ሆነው፣ በራሳቸው ኃይል ለራሳቸው ጥቅም የሚሠሩ ናቸው። ስለዚህም የእነዚህ የወንጀል ድርጅቶች ተግባር በመሠረቱ ፀረ-ማኅበረሰብና ፀረ-ሕግ መሆኑን እናውቃለንና ሰዎችን በማገታቸው አንደነቅም ይሆናል።

 

ማኅበረሰቡ በተደራጀበትና መንግሥት ባለበት አገርስ ሰዎች የሚታሠሩት እንዴት ነው? አንድ ሰው ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ከተያዘ፣ ለጊዜው በመደበኛ ፖሊስ ይያዝና ይታሠራል። ሆኖም ከ48 ሰዓታት በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ ፖሊስ እስረኛውን ለፍርድ ቤት ማቅረብ አለበት። ፍርድ ቤት ጉዳዩን ተመልክቶ ለመወሰን ሁለት ምርጫዎች አሉት። አንዱ የታገተውን ሰው በዋስ መልቀቅ፣ ሁለተኛው ደግሞ ታስሮ እንዲቆይ ትዕዛዝ መስጠት።

 

የሚታገቱት ወይም የሚታሠሩት ሰዎች ዓይን ያረፈባቸው ሊሆኑ ይችላሉ ብያለሁ፤ እነዚህ ሰዎች ከጥፋት የሚቆጠርባቸው (ወንጀላቸው አልልም) የሌላውን ሰው ቀልብ መሳባቸው ብቻ ሊሆን ይችላል። “ጅብ የሚጠራባቸው” ሀብታቸው ሊሆን ይችላል፤ ዝናቸውም ሊሆን ይችላል። ዘፋኝ በዘፈኑ ሲታሰር አይተናል። ሰልጥነናል ስንል በዚህ ረገድ የአፄ ቴዎድሮስን ያህል፣ የመቻል ብቃት አናሳይም፤ በየኼዱበት እየተከተለች ከነዘርዘራቸው በግጥም ስትሰድባቸው የነበረችውን አዝማሪ አልነኩዋትም። በዘመናችን ዘፋኝ ብቻ ሳይሆን ዘፈንም ሲታሰር አይተናል። በባሕላችን ሃሳባቸውን የመግለጽ ነፃነት የተፈቀደላቸው አዝማሪዎች፣ አልቃሾችና እረኞች ነበሩ ሲባል ሰምቻለሁ። መንገዳችን ወደ ኋላ ሆነና ፈረንጆች ቀደሙን።

 

ለመሆኑ የማያጠራጥር ተጨባጭ ማስረጃ ሳይገኝ ሰውን ማሰር ምን ይባላል? ሰዎችን ካሠሩ በኋላ ምርመራ ምን ማለት ነው፣ አስር ዓመትና ከዚያም በላይ ከታሠሩ በኋላ ፍርድ ቤት ወይ በነፃ የሚያሰናብታቸው ወይም ደግሞ ያንኑ በእስር ላይ የቆዩበትን ያህል ጊዜ እስራት ሲፈርድባቸው ምን ይባላል።

 

በጣም የሚደንቀው ነገር ደግሞ፣ እስር ቤቶች በውጭ እርዳታ የሚደጎሙ መሆናቸው ነው፤ አለዚያማ እስረኛው በችጋርና በበሽታ ያልቅ ነበር። ሆኖም ትንሽም ቢሆን ለእስር ቤቶች የሚወጣው የሕዝብ ገንዘብ፣ ለዚህች ደኸ አገር ጉዳትን የሚያስከትል ነውና የዋስትና መብት የሚጠበቅ ቢሆን ከብዙ ወጪ እንድናለን። እስር ቤቱን ለሟሟቅ ተዘጋጅተው፣ ክረምቱን በዚያ ለማሳለፍ የሚገቡት “ደንበኞች” የሚባሉት ይበቃሉ። የሁለት ሺህ ዓመታት በዓል ጊዜ ሳያልፍ፣ የማሰርን ባሕል ከላያችን እናራግፈው፤ ከእሱም ጋር ፍርሃታችንንና ስጋታችንን ለመጋፈጥ መንፈሳዊ ወኔ እናዳብራለን።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ