ግርማ ካሣ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

”... እነ መለስ ናቸው ሕግ። መለስ የፈለገውን ነገር ሕገ ወጥ ነው ካለ ሕገ ወጥ ነው። ይህን አውቀህ ምኑን ነው ታገል የምትለው? ምኑን ነው በሰላማዊ መንገድ ለውጥ አመጣለሁ የምትለው? እርሱ እኔ በፍጹም ትርጉም ያለው እውነተኛ ለውጥ ለማምጣት የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው ብዬ አላምንም … ጊዜ ማጥፋትና እራስን መሸንገል ካልሆነ በቀር ...” ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ

 

 

 ”... ግን መገፋት ይችላሉ። በርግጥ ምርጫ ሊያጡ ይችላሉ። ምርጫ ለማሳጣት የግድ ጠመንጃ መሆን የለበትም። በተለያዩ መንገድ፣ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች፣ በመካከለኛው ምስራቅ እንዲሁም በሰሜን አፍሪካ እንዳየነው፣ ሕብረተሰቡ በፍጹም አልገዛም ብሎ መሳሪያ ሳይዝ ሊያስገድዳቸው ይችላል። በዚያ መልክ መኬድ አለበት ብዬ አምናለሁ። ግን መገደድ አለባቸው። በስልጣን ላይ ሊቆዩ እንዳማይችሉ ማወቅ አለባቸው። ያ ሲሆን ብቻ ነው ለውጥ የሚመጣው ...”

ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ከኢሳት ጋር ካደረጉት ቃለ-ምልልስ የተወሰደ

 

ከላይ የጠቀስኳቸው፣ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ሁለት አባባሎች፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የግንቦት ሰባት ንቅናቄ መስራችና ሊቀመንበር፣ በቅርቡ ከጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ጋር በኢሳት የዳይስፖራ ቴሌቭዥን ካደረጉት ቃለ ምልልስ የተወሰዱ ናቸው። ሰላማዊ ትግል ጊዜ ማጥፋትና እራስን መሸንገል ነው ባሉበት በዚያው አንደበታቸው፣ ያለ ጠመንጃ ለውጥ ማምጣት ይቻላል ይሉናል ዶ/ር ብርሃኑ።

 

በተለይም የአንድ የፖለቲካ ደርጅት መሪ ሆነን፣ በቴሌቭዥን ቀርበን ትንታኔዎች በምናቀርብበት ጊዜ ምን እንደምንናገር፣ የምንናገረው ነገር ምን ሊያስከትል እንደሚችል ብናገናዝብ ጥሩ ይሆን ነበር ብዬ አስባለሁ።

 

በመጀመሪያ ደረጃ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የሰላማዊ ትግልን፣ ሕውሀት/ኢሕአዴግ ሲፈቅድ ብቻ ከሚደረግ እንቅስቃሴ ጋር ያምታቱት ይመስለኛል። ማህተመ ጋንዲ፣ ሕዝቡን ለነጻነቱ በሚያንቀሳቀሱበት ጊዜ፣ የቅኝ ገዢ እንግሊዞችን ሕግና ትእዛዝ እየጠበቁ አልነበረም። ሰላማዊ የሆነ የእምቢተኝነት ዘመቻዎች ነበር ያደርጉ የነበረው። ሮዛ ፓርክ ለነጮች ብቻ በተፈቀደ የአውቶቢስ መቀመጫ ላይ ሲቀመጡ፣ የባለስልጣናትን ዘረኛ መመሪያና ሕግጋት ሲጥሱ፣ ሰላማዊ ትግል ነው ያደረጉት። በግብጽና በቱኒዚያ የመንግስቶቻቸውን አዋጆች ወደ ጎን አድርገው ዜጎች ሰልፎች ሲወጡ፣ ሰላማዊ ትግል ነው ያደረጉት።

 

ሰላማዊ ትግል በአጭሩ፣ ተኩሶ ሰው መግደልን ያላካተተ፣ ለውጥ ለማምጣት የሚደረግ ማናቸውም አይነት እንቅስቃሴዎችን ያጠቃልላል። ስለዚህ ዶ/ር ብርሃኑ ”በሰላማዊ መንገድ ለውጥ ማምጣት አይቻልም” የሚሉትን አባባል ”አገዛዙ የሚፈቅደውን እንቅስቃሴ ብቻ በማድረግ ለውጥ ማምጣት አይቻልም” በሚለው አባባል ቢያስተካክሉት ጥሩ ሊሆን ይችል ነበር። እንጂ እንዲሁ በደፈናው የተሳሳቱና እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ አስተያየቶችን በመስጠት፣ ሊታገል የተዘጋጀውን ሕዝብ ግራ ማጋባት መልካም ነው አልልም።

 

ያ ብቻ አይደለም።” እኛ አልተሳካልንም፣ እኛ እነዚህና እነዚያን ስህተቶች አድርገን ነበር። ከኛ ተመክሮ ትምህርት ወስድችሁ፣ ከኛ ስህተት ተምራችሁ፣ ትግሉ ወደፊት ግፉት” መባል ሲገባ፣ ”እኛ ሞክረን ሳይሳካለን ስለቀረ፣ እኛ ታግለን ውጤት ማምጣት ስላልቻልን፣ ሌሎች የሚያደርጉት ጥረት አይሳካም” ብሎ መደምደም፣ የሌሎችን ጥረት አሳንሶ ማቅረብ፣ የሽንፈተኝነት መልእክት ማስተላለፍ፣ ሰውን ተስፋ ማስቆረጥ፣ የሚያፈርስ እንጂ የሚገነባና የሚያንጽ አይደለም።

 

ውይይቴን ትንሽ ለጠጥ ላድርገውና ዶ/ር ብርሃኑ ስለ ግብጽና ቱኒዚያ ሲናገሩ ወዳቀረቡት፣ ”ሰላማዊ ትግል አይሰራም” ከሚለው አባባላቸው ጋር በግልጽ ወደሚቃረን ትልቅ ቁም ነገር ልመለስ። የኢትዮጵያ ሕዝብ መሳሪያ ሳይዝ፣ ገዢውን ፓርቲ አስገድዶ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ነው በግልጽ ለማስረዳት የሞከሩት። በጣም ትክክለኛና በሙሉ ልቤ የምደግፈው አባባል ነው። በርግጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ቀና ካለ፣ በምንም ሚዛንና መስፈርት አቶ መለስ የግፍ ቀንበር በእርሱ ላይ ጭነው ሊቀጥሉ አይችሉም።

 

እንግዲህ ትልቁ ጥያቄ ህዝቡ እንዴትና መቼ ነው የሚነሳው የሚለው ነው? ዶ/ር ብርሃኑ ለዚህ መልስ የላቸውም። ከአንድ ሰዓት በላይ የፖለቲካ ትንታኔ ሲሰጡን አንገብጋቢና ወሳኝ እንዲሁም ተግባራዊ ለሆኑ ጥያቄዎች ብዙም የሚሉት አልነበራቸውም። ይህም ምን ያህል የሚያራምዱት ፖለቲካ የከሰረ፣ ከላይ ያማረ በውስጥ ግን ፍሬያማና አቅጥጭ ጠቋሚ የሆነ ፖለቲካ እንዳልሆነ የሚያሳይ ነው።

 

በግብጽና በቱኒዚያ እንዲሁም ሰሞኑን በራሺያ እንቅስቃሴዎች የታዩት፣ በትዊተርና በፌስቡክ ነው። በግብጽ 46%፣ በቱኒዚያ 96% የሚሆነው ሕዝብ የኢንተርኔት አገልግሎት አለው። በግብጽና በቱኒዚያ እንደ አልጃዚራ የመሳሰሉ ከስምንት የሚበልጡ፣ አብዛኛው የአረብ ሕዝብ የሚከታተላቸው የቴለቭዥን ሳተላይቶች አሉ። በቀላሉ በኢንተርኔትን በቴለቭዥን በአጭር ጊዜ ውስጥ ህዝብን ማንቀሳቀስና ማደራጀት ተችሏል።

 

በአገራችን ኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ ከ 0.5 በመቶ በታች ነው። የሳተላይት ዲሽ ያለው ከአንድ በመቶ ያነሰ ነው። በግብጽና በቱኒዚያ የተደረገውን አይነት አደረጃጀትና ቅስቀሳ ማድረግ አስቸጋሪ ነው። ታዲያ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና ድርጅታቸው ግንቦት ሰባት፣ እንዴት አድርገው ነው፣ አሜሪካን አገር ተቀምጠው፣ ሕዝቡን ሊያደራጁ የሚችሉት? እንዴት አድርገው ነው ሕዝቡ እንዲነሳ የሚቀሰቅሱት? ለዚህ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ መልስ ያላቸው አይመስለኝም።

 

ምንም አይነት የተሻለ አማራጭ ሳያቀርቡ፣ አገር ቤት ሰላማዊ ትግል እያደረጉ ያሉ፣ በሰላማዊ ትግል ምክንያት የታሰሩ፣ የተንገላቱ፣ ከሥራ የተባረሩ፣ ትልቅ መከራ የሚደርስባቸው ወገኖቻችን አኩሪ እንቅስቃሴን ”ጊዜ ማጥፋትና እራስን ማታለል ነው ” ማለታቸው የሚያስተዛዝብና የሚያሳዝንም ነው። ከአንድ የተማረ የፖለቲካ መሪ የምንጠብቀው አስተያየት አይደለም።

 

በአገር ቤት በቅርቡ በታላቁ ሩጫ እንዳየነው፣ ሕዝቡ ያለውን ተቃውሞ እያሰማ ነው። ”ሳንፈልጋቸው፤ ሃያ አመታቸው! ” እያለ ነው። በአገር ቤት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በየሳምንቱ የፍኖት ጋዜጣን እያተመ ህዝቡ እንዲያነብ እያደረገ ነው። የፍኖት ጋዜጣ እንዴት ጠንካራና፣ ቀስቃሽ ጽሁፎችን ለአንባቢያን እንደሚያቀርብ አቡጊዳና ኢኤምኤፍ ላይ ሄዳችሁ ማንበብ ትችላላችሁ።

 

የፍትህ ጋዜጣ፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ደግሞ አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ፣ ሳይፈሩ፣ በሚያኮራ መልኩ፣ በድፍረት የገዢውን ፓርቲ አምባገነንነት አጋልጠዋል። በዚህም ምክንያት የአውራምባ ታይምስ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ የፍትህ ጋዜጣ ጸሃፊ ርዮት አለሙ ታስረዋል። በየአብያተ ክርስቲያናቱና ጸሎት ቤቶች ለሰላም ለፍቅር ለአንድነት ይጸለያል። ገዢው ፓርቲ አፋኝ ፖሊሶውቹን እንዲለወጥ፣ ለብሄራዊ እርቅ እንዲዘጋጅ ከውስጥም ከውጭ የተለያዩ ተማጽኖዎችና ይቀርቡለታል፤ ግፊቶች ይደረጉበታል። እነዚህም ሁሉ በአገር ቤት እየተደረጉ ያሉ ወሳኝ የሰላማዊ ትግል አካላቶች ናቸው።

 

ሽብሬ ደሳለኝን፣ አረጋዊ ገብረ ዪሐንስን፣ ቢያንሳ ዳባን እንዲሁም ሕይወታቸውን ያጡ በርካታ ወገኖቻችንን እናስታወስ። ከስድስት ወራት በላይ በጨለማ ቤት ተቀምጣ የስነ ልቦና ቶርቸር የደረሰባትን ብርቱካን ሚደቅሳን፣ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በማእከላዊና በአራቱ ማእዛናት ባሉ የአገራችን እሥር ቤቶች የሚማቅቁትን እናስታውስ። በዚህ በሰላማዊ ትግል ውስጥ ብዙዎች እጅግ ትልቅ ዋጋ እየከፈሉ ነው። እንዲሁ በቀላሉ እንደ እቃ እቃ ጨዋታ ጥለን የምንሄደው ነገር አይደለም። ፈረንጆች እንደሚሉት ”We are in it to the finish” ።

 

በቅንጅት ጊዜ የነበረው እንቅስቃሴ፣ አራቱ የቅንጅት አባል ድርጅቶች ገና በቅጡ ከላይ እስከ ታች ሳይቀናጁ፣ የአመራር አባላቱ ሳይተማመኑና አንድ ሳይሆኑ፣ በቂ የሆነ ድርጅታዊ መዋቅርና ዝግጅት ሳይኖራቸው የተከሰተ እንቅስቃሴ ነበር። መሪዎች ሲታሰሩ፣ ከታች ያለው በተዋቀረ መልኩ ትግሉን ሊመራ አልቻለም። በበቂ ሁኔታ ድርጅታዊ ሥራ አልተሰራምና።

 

ይህ በአሁኑ ወቅት በአገራችን ያለው የሰላማዊ ትግል አሁን ካለበት ደረጃ አልፎ ወደፊት ይገሰግስ ዘንድና በአገር ቤት ያሉ የሰላማዊ የፖለቲካ ድርጅቶች የጠነከረ አመራር መስጠት ይችሉ ዘንድ አቅማቸውን የበለጠ ማጎልበት ይኖርባቸዋል። የጠነከረ እርምጃ ለመውሰድ፣ ገዢው ፓርቲ የሚደነግጋቸውን የአለም አቀፍንም ሆነ የኢትዮጵያን ሕገ መንግስት ለሚሽሩ፣ አፋኝ ውሳኔች ”እምቢ” ብሎ ሕዝቡ እንዲነሳ ለመቀስቀስና ለማታገል ጠንካራ መሆን ያስፈልጋል። ዝግጅት ያስፈልጋል። ድርጅታዊ ሥራ አስቀድሞ መስራት ያስፈልጋል።

 

እንግዲህ ጥያቄው እነዚህ አገር ቤት ያሉ ድርጅቶች፣ ሕዝቡን በስፋት ማንቀሳቀስ ይችሉ ዘንድ እነርሱን መደገፉና ማገዙ ይረዳል? ወይንስ እንደ ዶ/ር ብርሃኑ ”ዋጋ የለውም” ብለን ተስፋ በመቁረጥ አሜሪካንና አውሮፓ ተክለን፣ ከሻእቢያ እግር ስር ተቀምጠን የሌሎች አገራትን ገድል ማውራት?

 

ነገሮችን ከስሜት በፀዳ መልኩ ከሁሉም አቅጣጫዎች ማየት ያለብን ይመስለኛል። እኛ ምንም ሳናደርግ፣ የሌሎችን ትግል ከወዲሁ ማንቋሽሽ እጅግ በጣም ነውር ከመሆኑ የተነሳ አገርንና ሕዝብን የሚጎዳ ነው ብዬ አምናለሁ።

 

አንዳንዶች ”አንተስ ግንቦት ሰባትን ታንቋሽሽ የለም ወይ?” ሊሉ ይችላሉ። ግንቦት ሰባት ትግሉን ለመርዳት የሚያደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች አንቋሽሼ አላውቅም። ለምን ቢባል ምንም አይነት እንቅስቃሴ አለ ብዬ ስለማላምን።

 

”የሰላም ትግል አይሰራም” ያሉን ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ቁምጣ ታጥቀው፣ በባሌ ጫካዎችና በጎንደር ተራራዎች የተነሱትን ፎቶግራፍ ቢያሳዩኝ፣ ከዚያ ሆነው በሳተላይት ስልክ፣ ቃለ መጠይቅ አድርገው የድጋፍ ጥሪ ቢያሰሙ፣ ነቀፌታ ሳይሆን አክብሮት ይኖረኝ ነበር።

 

ዜጎች መሯቸው ለመብታቸው ነፍጥ ቢያነሱ ”ለምን?” ብሎ ለመጠየቅ እኔም ሆነ ማንም የሞራል ብቃት ሊኖረው አይችልም። ሴት ልጆቼ ወይንም ባሌበቴ ሲደፈሩ፣ ቤቴ ሲቃጠል፣ ማንም ወሮበላ እንደፈለገ ሲያስረኝ ሲፈታኝ፣ በቃኝ ብዬ፣ እራሴንና ቤተሰቤን ለመከላከል ነፍጥ ባነሳ ”በርታ” እንጂ ለምን ልባል አይገባም። ብረት አንስተው የግፍ አገዛዝን በቃ የሚሉ ወገኖቻች ላይ በጭራሽ አንዳችም አይነት ጥያቄም ሆነ ቅሬታ የለኝም። ሊኖረኝም አይችልም። ከመረጡ፣ የግፍ አገዛዝን በነፍጥ የመታገል የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሙሉ መብት ነው። እራሳቸው ሕወሃት/ኢሕዴጎች ያደረጉት ይሄንኑ አይደለም እንዴ? እነርሱ ሲያደርጉት ጀግንነት፣ ሌላው ሲያደርገው ሽብርተኝነት የሚሆንበት ምንም ምክንያት የለም።

 

እኔ ያለኝ ትልቁ ችግር፣ ነፍጥ ያነሱ ላይ ሳይሆን፣ ነፍጥ ሳያነሱ ስለነፍጥ ጠዋትና ማታ እያወሩ የሚያሰለቹን ላይ ነው።

 

የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ከተቋቋመ ሶስት አመታት ሆኖታል። ለገዢው ፓርቲ ዜጎችን ለማሰሪያ ምክንያትና ሰበብ ከመሆን ውጭ፣ ግንቦት ሰባት አደረገ የምለው ነገር የለም። አራምደዋለሁ በሚለው ሁለገብ ትግል የተቆጣጠረው አንዲት ቀበሌ፣ የገደለው አንድ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ባለስልጣን የለም ። በግንቦት ሰባት ተደረገ የሚባል፣ የተጨበጠ፣ ጥቅም ያመጣ ቅንጣት የምትሆን ክንዋኔ የለችም። እንዴት ተደርጎ ነው ታዲያ የሌለን እንቅስቃሴ ልንቃወምና ልንተች የምንችለው?

 

በውጭ አገር ተቀምጠን፣ ሃምበርገራችንን እየገመጥን፣ በየዩኒቨርሲቲው እያስተማርን፣ በየአውሮፓና አሜሪካ በሚደረጉ ራስን የሟሟቅ ስብሰባዎች ፑልፒቶችንና ጠረቤዛዎችን እየደበደብን፣ ስለጀግንነት፣ ስለ ጦር፣ ወያኔን ስለመጣል፣ በየዳያስፖራ ቴሌቭዥኖችና ራዲዮኖችን ለሰዓታታ እየለፈፍን፣ በባዶ መፎከራችን ላይ ነው ያለኝ ትልቁ ችግርና ነቀፌታ። አስመሳዮችና ግብዞች ነው እያስመሰለን ያለው። እኛን እያዩ እነ አቶ መለስ ይሰቃሉ እንጂ አይደነግጡም። አንድ ጊዜ አቶ መለስ የተናገሩት ነገር ነበር። ”ስለጠመንጃ ማውራት አንድ ነገር ነው። የባሩዱን ሽታ ማሽተት ሌላ ነገር ነው” ነበር ያሉት።

 

ይህን አይነት ትችት በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ላይ ማቅረቤ፣ ምናልባት የተወሰኑ የፖለቲካ መሪዎችን በጭፍን የሚከተሉና የሚያመልኩ ግለሰቦችንና የድህረ ገጽ ባለቤቶችን ሊያስከፋ ይችል ይሆናል። ነገር ግን የዶ/ር ብርሃኑ በሰላማዊ ትግል እንዲሁም አገር በት ባሉ ሰላማዊ ድርጅቶች ላይ፣ ያነጣጠረው የአደባባይ ጥቃት፣ ምላሽ ማግኘት ስላለበት ነው ብእራችንን ያነሳነው። እውነት በመነጋገር ነገራችንን ፍርጥርጥ በማድረግ፣ የሚበጀኝን ከማይበጀን እየለየን፣ በተቻለ መጠን ወደ አንድ አቅጣጫ ሁላችንም በአንድነት መድረስ የምንችልበትን ሁኔታ እንዲፈጠር ነው ይህ የተጻፈው።

 

በዚህ አጋጣሚ አሳማኝ የተቃውሞ ነጥቦች ከቀረቡልኝ፣ ምንጊዜም ለመታረምና ለመገሰጽ ዝግጁ መሆኔን መግለጽ እወዳለሁ። ”በሰለጠነ፣ ጨዋነት በተሞላበት መልኩ እንወያይ። አንሰዳደብ። ስንዴውን ከእንከርዳዱ እንለይ። እኔ የሰላማዊ ትግል ይሰራል። አገዛዙ በከፈተው በር አልፈን፣ ከሰሙንና ዝግጁ ከሆኑ ከአገዛዙ ጋር ውይይት አድርገን፣ ካልተቻለም የተዘጋውን በር ሰላማዊ በሆነ መንገድ እራሳችን አስከፍተን፣ መሳሪያ ሳንይዝ፣ የሰው ሕይወት ተኩሰን ሳናጠፋ፣ ቦምቦች ሳናፈነዳ፣ አገዛዙን አስገድደን ለውጥ ማምጣት እንችላለን” ባይ ነኝ። ”የሰለማዊ ትግሉ ትልቅ ሥራና ድርጅታዊ ግንባታ ስለሚያስፈልገው፣ ከሕዝቡ ጋር በአገር ቤት ያሉ የሰላማዊ ታጋዮችን እንደግፍ፤ አቅማቸውን እንዲያጎለብቱ ከጎናቸው እንቁም” የሚል ጠንካራ አቋም አለኝ።

 

”አይ ተሳስተሃል” የምባልም ከሆነ፣ ውጤት የሚያመጣ፣ በሕዝባችን ላይ የተዘረጋውን ቀንበር የሚሰብር ማናቸውም አይነት አማራጭ ከቀረቡልኝ ለማዳመጥ ዝግጁ ነኝ። ሰላማዊ ትግልን የምደገፈው፣ ሰላማዊ ትግል ለሚያራምዱ ለአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ያለኝን ሶሊዳሪቲ የምገልጸው፣ አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት ሁኔታ የሚጠቅመው፣ የሚያዋጣው፣ ውጤትም ሊያመጣ የሚችለው እርሱ ብቻ ነው ብዬ ስለማመን ነው፤ እንጂ ከሰላማዊ ትግል ጋር ስለቆረብኩኝ አይደለም።

 

ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ በኤርትራ ጉዳይ ላይ እንዲሁም ስለኦነግ የተናገሩት ሰፊ ሃተታዎች አሉ። በነዚያ ዙሪያ የግሌን አስተያየቶች ይዤ ሌላ ጊዜ እመለሳለሁ። እስከዚያም ለሁላችንም ቸር ይግጠመን!


ግርማ ካሣ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

 

እ.ኤ.አ. ዲሴምበር 20 ቀን 2011 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!