አሁን አደገኛ ሁኔታ ላይ ተደርሷል። ፍትህን ወደ መቃብር ለመክተት በተቀናጀ እና በተደራጀ መልኩ የሚሴረው ሴራ እና የሚሸረበው ተንኮል ስጋና ደም ለብሶ እነሆ ከበር ቆሟል። ከረቡዕ (11/04/2004) ጀምሮ በጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ፤ እንዲሁም በአዘጋጆቹ ሙሉነህ አያሌው እና ኃይለመስቀል በሸዋምየለህ ላይ መፈናፈኛ የሚያሳጣ ክትትል እየተደረገ ሲሆን፣ ይሄ ርዕሰ አንቀጽ እየተዘጋጀም (13/04/2004) የጋዜጣው ቢሮ በክትትል ቀለበት ውስጥ እንደሆነ ነው።

 

 

በዚህም የተነሳ የመሥራት ነፃነትን ብቻ ሳይሆን የመተንፈስ ነፃነትንም በሚያፍን መልክ በአዘጋጆቹ ላይ እየተደረገ ያለው ጫና ፍፁም ሕገ-ወጥ እንደሆነ ለማስገንዘብ እንፈልጋለን። እናም እነዚህ የደህንነት ሠራተኞች በጠራራ ፀሐይ የዜጐችን የመዘዋወር እና በነፃ የማሰብ ሕገ-መንግሥታዊ መብት እንዲያፍኑ የላካቸው አካል ሕገ--መንግሥቱን እየናደው እንደሆነ ህዝብ ሊያውቀው ይገባል። እነዚህ ሰዎች የጋዜጠኛ ኃይለመስቀልን ሲም ካርድ በነጠቁበት ጊዜ የደህንነት ሠራተኞች እንደሆኑ ቃል በቃል ከነገሩት በኋላ ከባድ ማስፈራሪያ ከተከበረው የጋዜጣው ቢሮ በር ላይ አድርሰውበታል።

 

በፍትሕ እምነት ይሄ ሀገር የእናንት /የገዥዎቻችን/ እንደሆነ ሁሉ፤ የእኛም ነው። በእንደዚህ አይነቱ የደህንነት ጫና እና ማስፈራሪያ የምንለውጠው አቋምም ሆነ የምንሰደድበት ሀገር የለም። ሀገራችን ኢትዮጵያ ነችና። ደግመን ደጋግመን እንደምንለው፤ ዛሬም እንላለን በወከባ እና በማስፈራሪያ በሀገሪቱ ቁጥር አንድ ተነባቢ የሆነችው ፍትህ ጋዜጣ የሚያጎነብስ አንገት እንዲኖራት አንፈቅድም። ለስደት የተዘጋጀ ልብ የላታም። ምንጊዜም የህዝብ ድምፅ፣ የህዝብ አንደበት እንደሆነች ትቀጥላለች። ከዚህ በተረፈ አፋኙን የፕሬስ ሕግ ጨምሮ የተለያዩ የወንጀለኛ መቅጫ ሕጎች ስላሉ፣ ጥፋት ካለ በሕግ መጠየቅ እንጂ፤ ለሀገር ደህንነት እና የህዝባችንን (እኛን ጨምሮ) ሠላም ለመጠበቅ የሰለጠኑ የደህንነት ሠራተኞች አላስወጣ አላስገባ እንዲሉን እንዲያደርጉ ማሠማራቱ ዛሬ ምናአልባት ሰማይ አይታረስ … ቢሆን እንኳ ነገ በሕግ ያስጠይቃል። ይህንንም ከታሪክ መማር ብልህነት እንደሆነ በዚህ ሥራ የተሳተፋችው ሁሉ እንድትገነዘቡት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል።

 

እንደሚታወቀው ፍትህ በወጣቶች የምትዘጋጅ ጋዜጣ ነች። በተቃራኒው ደግሞ በዕድሜ ከእኛ ጋር የሚቀራረቡ ወንድም እና እህቶቻችን (የደህንነት ሠራተኞች) ትዕዛዝ እየሰጣችሁ ሥራችንን እንዳንሠራ እንቅፋት መፍጠሩ፤ ጉዳቱ ለሀገርም ጭምር ነው። የሆነ ሆኖ ግን በእነዚህ የዕድሜ አቻዎቻችን ላይ አንዳች ቅሬታ የለንም። ቅሬታችን ለሀገር ጥቅም ሊውሉ የሚገባቸውን የደህንነት ሠራተኞች ሠላማዊ ዜጐችን እንዲያፍኑና እንዲያስፈራሩ በመደቡት ላይ ነው። ይህ በየጊዜው ”ታገልንለት”፣ ”ተሰዋንለት”፣ ... የምትሉትን ሕገ-መንግሥት መናድ ነው። ግልፅና አደገኛ ወንጀል እንደሆነ ልታውቁት ይገባል።

 

ከዚህ ውጪ የመጣውን መከራ ለፕሬስ ህልውና ስንል እስከመጨረሻው እንቀበለዋለን። በእርግጥ ይሄ የእኛ የዓላማ ፅናት ነው። ነገር ግን ቀጣዩ ጊዜ አስፈሪ እና አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ይገባናል። ሆኖም ባመንበት ዓላማ ላይ ቆመን የመጣውን ከመቀበል ውጪ ሌላ አማራጭ እንደማይኖረን ለመንግሥት፣ ለህዝብ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ፍትህን በኢትዮጵያ ከሚገኙ የፕሬስ ውጤቶች በህትመት ብዛት አንደኛ ትሆን ዘንድ ላደረጉ አንባቢዎቻችን ግልፅ ማድረጉ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል። እናም የፍትህ አንገት በአቋም ለውጥ ሊቀለበስ እንደማይችል እና ለስደት የተዘጋጁ እግሮች እንደሌሏት ዛሬም ደግመን ደጋግመን እናረጋግጥላችኋለን።

 

የፍትህ ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!