ግርማ ካሣ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. 

መግቢያ

ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ከግንቦት ሰባቱ መሪ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር ባደረገው ቃለ-ምልልስ ካነሳቸው ነጥቦች መካከል የኤርትራ ጉዳይ ይገኝበታል። ኤርትራን በተመለከተ ዶ/ር ብርሃኑ ከተናገሩት የምጋራቸው በርካታ ነጥቦች አሉ። በተለይም የኤርትራ ሕዝብ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ትልቅና ስር የሰደደ ታሪካዊ ትስስር እንዳለው፣ በርግጥ በኢትዮጵያ ሕዝብ የተመረጠ ለሕዝብ ፈቃድ ተገዢ የሆነ መንግስት ቢኖር፣ ከኤርትራ ጋር ያለውንም ሆነ ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት በጣም እንደሚቀል በመግልጽ የሰጡትን አስተያየት፣ ምናልባት ከአምባገነኖቹ በስተቀር የማይጋራው ሰው አለ ብዬ አላስብም።

 

 

(በቅድሚያ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ በኢሳት ላደረጉት ቃለ-ምልልስ የሰጠሁትን ክፍል አንድ ጽሁፍ አንብባችሁ የተቃውሞም ሆነ የድጋፍ አስተያየት ለለገሳችሁ ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ። የዶ/ር ብርሃኑ የኢሳት ቃለ መጠይቅ በድረ ገጻቸው ላስተናገዱ ድረ ገጾች በአብዛኛው ጽሁፎቼ ለአንባቢዎቻቸው እንዲያቀርቡ መላኬን እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ)

 

”በኢትዮጵያ ሕዝብ የተመረጠ መንግስት ሲኖር፣ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በኢትዮጵያ ሲፈጠር ለሁሉም ይጠቅማል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ለኤርትራ ይጠቅማል። ለምን ቢባል ኤርትራውያን እና ኢትዮጵያውያን ዋቴቨር የታሪክ ሂደት የፈጠረው ችግር ይኑር፣ ወንድማማቾች ነን ብለን እናምናለን። ከኤርትራዊ ጋር ያልተጋባ፤ ከኤርትራዊ ጋር አብሮ ያልኖረ፤ ብዙ ሰው አላውቅም። ግምሽ ኤርትራ ኢትዮጵያ ውስጥ ካለ ቋንቋ ጋር የሚጋራ ሕዝብ ያለበት ነው። ወደድንም ጠላንም በአንድ መልኩም ሆነ በሌላ የተሳሰርን ነን” ነበር ዶ/ር ብርሃኑ ያሉት።

 

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ያለው ችግር የሕዝቦች ችግር አይደለም። ነገር ግን በአዲስ አበባና በአስመራ የሚገዙ፣ ሕዝብ ያልመረጣቸው አምባገነን ገዢዎች ያመጡት ችግር ነው። አቶ ኢሳያስ እና አቶ መለስ ዜናዊ በኤርትራውያንና በኢትዮጵያውያን መካከል ለተፈጠሩ ችግሮች፣ በባድመ ጦርነት ወቅት ላለቁት በአሥር ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን እልቂት ተጠያቂዎች ናቸው።

 

ሻዕቢያ አሥመራን እንደተቆጣጠረ አዲስ አበባ የሚኖሩ አንዲት ትዬ ገነት የምንላቸው የሃማሴን ሴት፣ አስመራ ሄደው ታዝበው የመጡትን አንድ ታሪክ ላጫውታችሁ። ገና ሬፌረንደም አልተደረገም ነበር። በአዲስ አበባ ቻርተር የተባለው ጸድቆ አቶ መለስ ዜናው ጊዜያዊ ፕሬዘዳንት ነበሩ።

 

በአሥመራ፣ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ አሉ ከሚባሉ የአገር ሽማግሌች ጋር ስብሰባ ያደርጋሉ። ያኔ አቶ መለስና አቶ ኢሳያስ ወዳጅ ነበሩ። (እንደሚወራው ከሆነ አሁንም አቶ መለስ ፈርተው በግልጽ አያወጡትም እንጂ፣ በድብቅ ይገናኛሉ፣ ወዳጅነታቸውንም እንደጠበቁ ነው ይባላል። በተለይም ኦነግ፣ ኦብነግና ግንቦት ሰባት ሁሉም በሻዕቢያ የሚረዱ፣ ሽብርተኞች ሲባሉ፣ ሻዕቢያ በፓርላማ ሽብርተኛ አለመባሉ ለዚህ እንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሳል)

 

በስብሰባው አንድ አረጋዊ አባት ይነሱና ”ልጆቻችን ናችሁ። ታግላችሁ እዚህ በመድረሳችሁ ኮርተንባችሁሃል። ተደስተናል። መድኃኔዓለም ይባርካችሁ” ብለው ምስጋናቸውን ያቀርባሉ። ይቀጥሉና ”አሁን በማሃል አገር ወዳጅ መንግስት ነው ያለው። ነገር ግን ነገ ሌላ መንግስት ቢመጣ ምን ታደርጋላችሁ? ጤፉን ቡናውን ከየት ነው የምታመጡት? እባካችሁ በትንሹም በትልቁም ከመሃሉ ሰው ጋር አታቀያይሙን!” ይላሉ እኝህ አባት። ትዬ ገነት እንደነገሩን፣ እኝህ አባት ከዚያ ጊዜ ጀመሮ ታይተው አያታወቁም። ምን ሊደርስባቸው እንደሚችል እንግዲህ ገምቱ።

 

የሰብዓዊ መብት ከሚረግጥ ጋር እንዴት ሰብዓዊ መብት ማስከበር ይቻላል?

 

ዶ/ር ብርሃኑ የሚመሩት ድርጅት ለሰብአዊ መብት መከበር፣ ለሕግ የበላይነት ለዲሞክራሲ መስፈን እታገላለሁ የሚል ድርጅት ነው። ግንቦት ሰባት በአቶ መለስ አገዛዝ ላይ ጠንካራ ወገዛና ክስ ሲያቀርብ፣ በዋናነት የአቶ መለስ አገዛዝ እያደረሰ ያለውን ፍጹም የሆነ የአፈና ስርዓት በማጋለጥ ነው።

 

ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ከኤርትራ ጋር አብሮ ስለመስራታቸው ጥያቄዎች ሲያቀርብ፣ ዶ/ር ብርሃኑ አንድ ወቅት ኢትዮጵያ ሪቪው አቶ አንዳርጋቸው በአስመራ ጉብኝት እያደረጉ እንደሆነ የዘገበውን ለመካድ፣ በአዲስ ድምጽ ራድዮ ”ግንቦት ሰባት ምንም አይነት ግንኙነት ከሻዕቢያ ጋር የለውም” እንዳሉት፣ ከሻዕቢያ ጋር አብረው እንደማይሰሩ አላስተበበሉም። ከሻዕቢያ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው፣ አብረው እንደሚሰሩ፣ በሻዕቢያ እንደሚረዱና እንደሚደገፉ ዶ/ር ብርሃኑ አልካዱም።

 

ከሻዕቢያ ጋር አብሮ ስለመስራት ከተነሳ በዋናነት የማነሳው፣ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ሳይጠይቅ ያለፈው አንድ ትልቅ ጉዳይ አለ። እርሱም ለዲሞክራሲ እታገላለሁ የሚል ድርጅት እንዴት አድርጎ የዲሞክራሲ ጠላት ከሆነ ቡድን ጋር አብሮ ሊሰራ እንደሚችል ነው።

 

በቺካጎ ከሚገኝ የኢሊኖይ ኢንስቲቱት ቴክኖሎጂ በኮምፒቴሽናል ማቴማቲክስ በPHD የተመረቁ ናቸው። እንደ አብዛኞቻችን ምቾትን መርጠው ኑሯቸውን በአሜሪካን አገር አድርገው መኖር ሲችሉ፣ ወደ ትውልድ ከተማቸው አስመራ ይመለሳሉ። እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በ1990 የአስመራ ዩኒቨርሲቲ አራተኛ የሳይንስ ተማሪ በነበርኩኝ ጊዜ፣ የዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮ ሳይንስ ፋከልቲ ዲን ሆነው ሰርተዋል። ዶ/ር ክፍሉ ገብረእግዚአብሔር ይባላሉ። በግል የማውቃቸው፣ አግባብ ያለኝ፣ በጣም የማከበራቸውና የምወዳቸው ሰው ናቸው።

 

እንደ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ምሁር የሆኑት ዶ/ር ክፍሉ፣ ይኸው ከአስር አመታት በላይ የት እንደሆኑ በማይታወቅ እሥር ቤት እየማቀቁ ነው። እንደውም፣ በወህኒ የደረሰባቸው ስቃይ እጅግ በጣም የከፋ ከመሆኑ የተነሳ፣ በጣም የሚታመሙ እንደሆኑና ሕይወታቸው ሊያልፍ እንደሚችል የሚገልጹ አሳዛኝ ጭምጭምታዎች እየተሰማ ነው። ይህን የሚያደርገው ማን ነው ቢባል፣ ይህን የሚያደርገው የግንቦት ሰባት ድርጅት ወዳጅ የሆነው የኢሳያስ አምባገነን መንግስት ነው።

 

የስዊድን ዜግነት አለው። በምእራብ ስዊድን ጎተንበርግ በምትባል ከተማ ነዋሪ ነበር። ኤርትራ ነጻ ስትወጣ ወደ አስመራ ይመለሳል። ትዳር መስርቶ ልጆች ይወልዳል። ሴቲት የምትባል የመጀመሪያውን ነጻ ጋዜጣ ማውጣት ይጀምራል። ይህ ሰው ዳዊት ይሳእቅ ይባላል። በሻዕቢያ የደህነት አባላት ተይዞ በቁጥጥር ስር እንዲውል ከተደረገ አሥር አመታት አለፉ።

 

ጋዜጠኛ ዳዊት እስከአሁን ድረስ የት እንዳለ አይታወቅም። ከአስመራ የሚመጡ አንዳንድ ዜናዎች እንደሚጠቁሙት በእሥር ቤት ሳይሞት አይቀርም ይባላል። ዳዊት ልክ እንደ ኢትዮጵያዊቷ የዲሞክራሲ ታጋይ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ የአውሮፓ ሕብረት የሚሰጠው የሳካሮቭ የሰላም ሽልማት እጩ ሆኖ የቀረበ ሰው ነው። ይህን ሁሉ ግፍ በጋዜጣኛ ዳዊት ይሳእቅ ላይ እያደረሰ ያለው ማን ነው ቢባል በድጋሚ፣ የግንቦት ሰባት ወዳጅ የሆነው የኢሳያስ አገዛዝ ነው።

 

ቦታና ጊዜ አይበቃም እንጂ ሻዕቢያ በኤርትራውያን ወንድሞቻችን ላይ እየፈጸመ ያለውን እጅግ በጣም አሰቃቂ ግፍ በብዛት መዘርዘር ይቻላል ። ስለሻዕቢያ ግፍ አምንስቲ ኢንተርናሽናል፤ የተባበሩት መንግስታት፣ የአለም አቀፍ ጋዜጠኞች ማሕበር፣ ሂውመን ራይት ዋችን ጨመሮ በርካታ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶ በሰፊው ዘግበውታል። የተለያዩ የኤርትራውያን ድረ ገጾች በኦዲዮ፣ በቪዲዮ፣ በጽሁፍ በኢሳያስ አገዛዝ የደረሱ የተለያዩ ሰቅጣጭ ድርጊቶችን በምስክርነት እያወጡ ነው።

 

እንግዲህ ይህ ሁሉ እየታወቀ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋና ድርጅታቸው እንዴት ከእንደዚህ አይነት ቡድን ጋር አብሮ ለመስራት መወሰናቸው ሕሊና ያለውን ሰው ሁሉ ግራ የሚያጋባ ነው ብዬ አምናለሁ። ሕወሃት/ኢሕአዴግን ወንበዴና ወሮበላ ብለው የሚጠሩት ዶ/ር ብርሃኑ፣ ሻዕቢያን ወዳጅ አድርገው ማቅረባቸው ትንሽ የሚያስኬድ አይመስለኝም። በአንድ በኩል አቶ መለስ ዜናዊ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ለምን አሰሩ ብለን ተቃውሞ እያሰማን፣ በሌላ በኩል ጋዜጠኛ ዳዊት ይሳእቅን እያሰሩ የሚያሰቃዩትን አቶ ኢሳያስን ለማቀፍ እጆቻችን መዘርጋት ምን ይባላላል?

 

እንግዲህ ከግንቦት ሰባት ጋር ካሉኝ መሰረታዊ ልዩነቶች አንዱ ይሄ ነው። ግንቦት ሰባት መርህና አቋም ያለው አይመስለም። እርግጥ ነው ዶክተሩ እንዳሉት ፖለቲካ ኃይማኖት አይደለም። ነገር ግን ፈረንጆች ኮመን ሴንስ የሚሉት ነገር አለ። በአንድ በኩል እዚህ ያሉት ወንድሞቻችንን እያረዳ ያለን ቡድን፣ እዚያ ያሉ ወንድሞቻችን ለማዳን ያግዘናል ብሎ ማለት ሴንስ የሚሰጥ አይደለም። አያስኬደም። በዚህ ብቻ የግንቦት ሰባት ቡድን ለዲሞክራሲና ለሰብአዊ መብት መከብር ያለው ቁርጠኝነት ከጥያቄ ምልክት ውስጥ የሚገባ እንደሆነ እናያለን። በአፍ እንጂ በተግባር ለሰብዓዊ መብት መከበር ግንቦት ሰባት ቦታ እንደማይሰጥ ይህ በግልጽ የሚያሳይ ነው።

 

ባልሳሳት የግንቦት ሰባት መሪዎች የሚያደርጉት ትግል የመነጨው፣ በነአቶ መለስና በነአቶ በረከት ስምኦን ላይ፣ በግለሰብ ደረጃ፣ ካላቸው ቂምና ጥላቻ እንዲሁም እልህ የመነጨ እንጂ በርግጥ ከውስጣቸው የዲሞክራሲ ነገር ከንክኗቸው አይመስለኝም። በጥላቻና በበቀል ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ደግሞ ደጋፊውን ሁሉ ሳይቀር ገደል የሚከት እንጂ ለአገርና ለሕዝብ ዘለቄታ ያለው አስተማማኝ ለውጥ የሚያመጣ አይሆንም።

 

ሕወሃት/ኢሕአዴግ ላይ ካለ ጥላቻ የተነሳ ወደ ሻዕቢያ መዞር ጉዳት እንዳለው፣ በብሬመን ጀርመን አገር የዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት፣ ኢትዮጵያውያን ከኤርትራውያን ጋር ለማቀራረብ፣ በኤርትራ ጉዳይ ጠበብት ከሆኑትንና በኤርትራ ጉዳይ ላይ መጽሃፍ ከጻፉት ከዶ/ር ዳንዔል ክንዴ ጋር የተለያዩ ኮንፈርሳንቾን ያዘጋጁ፣ ፕሮፌሰር ተስፋጽዮን መድሃኔ እንዲህ ሲሉ ነበር ያስቀመጡት፡

 

”አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ምሁራን የኢሕአዴግን መንግስት ከመጥላትና ለማስወገድ ካላቸው ጉጉት የተነሳ፣ ኤርትራንና የኢሳያስን መንግስት በሚመለከት የዋህ ወይም ገራገር የሆነ አቋም ይወስዳሉ። ለምሳሌ የአስመራው መንግስት የመለስን መንግስት ለመጣል የሚረዳቸው ይመስላቸዋል፤ ከዚያም አልፎ የአስመራው መንግስት በኢትዮጵያ አንድነት የሚቆረቆር – እንዲያውም አንዳንዴስ የሁሉቱን አገሮች ፌደራላዊ አንድነትን የሚፈልግ ሆኖ ሲቀርብ ይታለሉለታል። ከመሃከላቸው ኢሳያስ አፈወርቂን በይፋ የሚመርቁም በአንድ ወቅት ብቅ ብለው ነበር። እነዚህ ምሁራን የነዚያ የኢሕአዴግን መንግስት የሚወድሱ ኤርትራውያን ተቃዋሚዎች ኢትዮጵያዊ ቅጂ ናቸው። የኤርትራውያኖቹ ውዳሴ ኢሕአዴግ ለሁለቱ አገሮች ትብብር እንዲያገለግል እንደማያደርገው ሁሉ፣ የኢትዮጵያውያን ሻዕቢያን ማሞገስም አይረዳም። እንዲያውም ዕንቅፋት ይሆናል” [1]

 

የኤርትራ መንግስት የኢትዮጵያን አንድነት ይፈልጋል ወይ?

ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር በተለያዩ አጋጣሚዎች ”ከኦነግ ጋር መነጋገር፣ አብሮም መስራት ያስፈልጋል” በሚል የተለያዩ መድረኮች የተካፈሉ፣ የቀድሞ የኢሕአፓ ከፍተኛ አመራር አባል የነበሩ፣ በኢሊኖይ በሚገኝ የሃርፐር ኮሌጅ የኢኮኖሚ ፕሮፌሰር የሆኑና በጣም የማከብራቸው ወዳጄ ዶ/ር ጌታቸው በጋሻው በቅርቡ ከነኦነግ ጋር አብሮ ስለመስራት በጻፉት ጽሁፍ፣ ስለኤርትራ መንግስት የጠቀሱት ነገር አለ። ኦነግ ከሻዕቢያ ጥገኝነት መውጣት እንዳለበት አትኩረው ያሰመሩት ዶ/ር ጌታቸው ”ኢትዮጵያ ወዳጅ ጎረቤትና አለም አቀፋዊ ድጋፍ የላትም። ከሰሜን በኩል፣ በተጭበረበረ መንገድ ነጻነቷን ከኢትዮጵያ ያወጀችው ኤርትራ (ሻዕቢያ) ኢትዮጵያን በዘላለማዊ ቀውስ ውስጥ ለመጨመር አርፋ የምትተኛ አይደለችም”[2] ሲሉ ነበር ከሻዕቢያ ጋር አብሮ መስራት በኢትዮጵያ ላይ ትልቅ አደጋ እንደሚያመጣ የገለጹት።

 

ከሻዕቢያ ጋር አብሮ ስለመስራት እንደ ኢትዮጵያ ሪቪው ብዙ የዘገበ፣ ብዙ ጥረት ያደረገ አካል አለ ብዬ አላስብም። የድረ ገጹ ዋና አዘጋጅ፣ አስመራ ድረስ በመሄድ ከአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ቃለ መጥይቆችን ያደረገ ሲሆን፣ በርግጥ የኤርትራንም የኢትዮጵያን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ አብሮ መስራት የሚቻልበትን ሁኔታ ለማጤን ሞክሯል።

 

ብዙዎቻችን እንደምናስታውሰው ስድስት ክፍል ያለው፣ ኢትዮጵያ ሪቪው ላይ የወጣ የአቶ ኢሳያስ ቃለ መጠይቅን ተከታትለናል። ኢትዮጱያ ሪቪው በስፋት ጽ/ቤቱ አስመራ የሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር እንቅስቃሴን ለአንባቢያኑ ያቀርብም ነበር። እንደውም በዚያን ወቅት በግንቦት ሰባትና በአርበኞች ግንባር መካከል አንድ አገራዊ ግንባር መፍጠር የሚቻልበት ሁኔታ ላይ ንግግሮች ይደረጉ እንደነበር ሲወራም ሰምቼያለሁ። ሻዕቢያ የኢትዮጵያ ኃይሎችን እንደማይቃወም፣ ከሻዕቢያ ጋር አብሮ መስራት እንደሚቻል ነበር በከረንት አፌር ፓልቶክ ክፍል ዋና ባላቤት በሆነው በፊታውራሪ እንደልቡ፣ በነአቶ ዙውድ አለም ከበደ በመሳሰሉ ሰዎች ሲነገረን የነበረው።

 

ነገር ግን ድንገት ያልተጠበቀ ዱብዳ ወረደ። ሻዕቢያ በዚያ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ከሃያ የሚበልጡ የአርበኞች ግንባር አመራር አባላትን አሰረ። (የት እንደታሰሩ የሚያወቅ ሰው የለም) ከሻዕቢያ ጋር መስራትን ሲያበረታታ የነበረውና ለአንባቢዎቹ እውነትን ለመግልጽ የማይፈራው ኢትዮጵያ ሪቪው፣ ምንም እንኳን ከዚህ በፊት ይደግፈው የነበረ ነገር ቢሆንም፣ ያለውን ሃቅ ፈልቅቆ በማውጣት ኢትዮጵያውያን የጠራ ግንዛቤ እዲያገኙ አደረገ። በሻዕቢያ እየተደረገ ያለውን አሳዛኝ ግፍ አጋለጠ።

 

ወደ 5000 ሺሆች ይጠጋል ተብሎ ይገመት የነበረው የአርበኛው ግንባር ሰራዊት፣ ኢትዮጵያ ሪቪ እንደዘገበው ወደ ሰባ ወረደ። ብዙዎች ድንበር እያቋረጡ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሱ። ብዙ ይወራለት የነበረውና ብዙዎች ተስፋ ያደረጉበት የአርበኞች ግንባር፣ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራ ይዞ፣ የኢትዮጵያን አንድነት አንግቦ የሚንቀሳቅስ በመሆኑ፣ የኢትዮጵያን አንድነት በማይፈልግ ሻዕቢያ ድባቅ ተደረገ።

 

እንግዲህ ዶ/ር ብርሃኑና ድርጅታቸው ግንቦት ሰባት፣ ከኢትዮጵያ ሪቪውና ከአርበኞች ግንባር ለምን ትምህርት ሊወስዱ እንዳልቻሉ ነው አንድ ሌላ ሊገባኝ ያልቻለ ነገር። ”ከኤርትራ ጋር እንሰራለን” ሲሉ፣ እራሳቸውን በሻዕቢያ ቀምሲ ስር ሲያስቀምጡ፣ በአርበኞች ግንባር የደረሰው በነርሱ እንደማይደርስ ምን ማስተማመኛ አላቸው? እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ምንም ማስተማመኛ ያላቸው አይመስለኝም።

 

ግንቦት ሰባት በሻዕቢያ ሲደገፍ በምትኩ ምን ቃል የገባው ነገር አለ?

ሻዕቢያ ግንቦት ሰባትን ሲደግፍ በምትኩ ከግንቦት ሰባት የሚጠብቀው ነገር እንደሚኖር መቼም ማንም ያጠዋል ብዬ አላስብም። ይሄንኑ በተመለከተ ጋዜጣኛ ሲሳይ አጌና ዶ/ር ብርሃኑን ጠይቋል። ለሕዝብ ግልጽ አላደረጉትም እንጂ የግንቦት ሰባት አመራር አባላት ከሻዕቢያ ጋር ሲነጋገሩ የተሰማሙበት አንዳንድ ነጥቦች ይኖራሉ። ሻዕቢያ ከኛ ምንም የሚፈልገው ነገር የለም ብሎ መናገር ትንሽ የኢትዮጵያውያንን የአስተሳሰብ ብስለት መናቅ ይመስለኛል።

 

”በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በሕዝብ የተመረጠ መንግስት ካልሆነ በቀር ማንም መደራደር አይችልም” የሚል አቋም እንዳላቸው ዶ/ር ብርሃኑ ይናገራሉ። ነገር ግን በሻዕቢያ ተረድቶና ተደግፎ ስልጣን የጨበጠው እራሱን ዲሞክራሲያዊና በሕዝብ የተመረጠ አድርጎ የሚቆጠረው፣ ሕወሃት/ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ብዙ ውሳኔዎች እንዳሳለፈ ሁላችንም የምናውቀው ነው። በግንቦት ሰባትና በሻዕቢያ መካከል የሚኖረው ግንኙነት በሕወሃትና በሻዕቢያ መካከል ከነበረው ግንኙነት በምን ሊለይ እንደሚችል ዶ/ር ብርሃኑ ቢዘረዝሩልን መልካም ይሆን ነበር። ሕውሃት ዲሞክራሲን አሰፍናለሁ ሲለን ነበር ያኔ። አሁንም ግንቦት ስባት ዲሞራሲን አሰፋናለሁ እያለን ነው። ያኔም ሕወሃት ከኦነግ ጋር ይነጋገር ነበር። አሁንም ግንቦት ሰባት ከአንድ ኦነግ ሳይሆን ከብዙ ኦነጎች ጋር እየተነጋገረ ነው።

 

ግንቦት ሰባት በሻዕቢያ እስከተደገፈና የሻዕቢያ ጥገኛ እስከሆነ ድረስ፣ ሻዕቢያን ማስቆጣት የሚችል አይመስለኝም። የሻዕቢያን ጥቅም የሚጎዳ፣ ግን የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቅ ነገሮች ላይ አቋም ለመውሰድ ይቸግረዋል። ለምሳሌ እንዲሆን ያህል አንድ ቀላል ነገር ልጠቀስ። ግንቦት ሰባት ኢትዮጵያ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት የሚገልጽ አቋም ሲወስድ ብዙ ጊዜ አንሰማም። ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ሆነም አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የቅንጅት አመራር የነበሩ ጊዜ አሰብ ሰላማዊና ሕጋዊ በሆነ መንገድ የኢትዮጵያ መሆን እንዳለበት አምነውና ተቀብለው ሲናገሩ ነበር። ለምን ቢባል የአሰብ ጉዳይ በቅንጅት ማኒፌስቶ በግልጽ ሰፍሮ ነበርና። በውጭ ጉዳይ ላይ በምርጫ ዘጠና ሰባት ቅንጅትን ወክለው የተከራከሩት ድር ብርሃኑና ነጋና ዶ/ር ያዕቆም ወልደማሪያም ነበር። ዶ/ር ያዕቆብ በቅርቡ አሰብ ለምን የኢትዮጵያ መሆነ እንዳለበት በስፋት የሚተነትን መጽሃፍ አቅርበውልናል። ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ግን፣ አሁን ከቅንጅት ሲወጡ፣ ይህ በኢትዮጵያን ዘንድ አንገብጋቢ የሆነው የአሰብ ጉዳይ ላይ ዝምታን የመረጡ ይመስላል። ኢትዮጵያ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት የመናገር ጉልበትና አቅም ያላቸው አይመስለኝም። ታዲያ ይሄ ምን የይባላል?

 

በሻዕቢያ እየተረዳንም የጠመንጃ ትግል ያዋጠናል ወይ?

እንግዲህ ግንቦት ሰባት ከሻዕቢያ ጋር አብሮ የሚሰራበት አንዱ ምክንያት በትጥቅ ትግል ወይንም የነርሱን ቋንቋ ልጠቀምና ”ወያኔ በሚገባው ቋንቋ ወያኔን ” ለማናገር ነው።

 

እንደሚታወቀው የኢሳያስ አፈወርቂ ቡድን በአለም አቀፍ ደረጃ የተገለለ፣ የተለያዩ እቀባዎች በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክት ቤት የተደረገበት መንግስት ነው። የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ለሻአቢያ ከሰጣቸው ማስጠንቀቂያዎች አንዱ ሻዕቢያ የጎሮቤት አገሮችን ሽምቅ ተዋጊዎች ማሰልጠኑንና መርዳቱንን እንዲያቆም ነው።

 

በመሆኑ ኢሳያስ አፈወርቂ የአለም አቀፍን ሕግ የማክበር ግዴታ ስላለባቸው፣ የአለም አቀፍ ማህበርሰብን ውሳኔ ለማላላት፣ አስመራ ያሉ የኦነጎች፣ የግንቦት ስባት፣ የኦብነግ ወዘተረፈ ጽ/ቤትችን፣ አሉ የሚባሉ የማሰልጠኛ ካምፖችን ለመዝጋት ይገደድ ይሆናል። አስመራ የተከሉ የሕወሃት/ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎች ነን የሚሉ ድርጅቶች በቀለሉ ዜሮ ሊገቡ ነው ማለት ነው።

 

ሻዕቢያ የተባበሩት መንግስታትን ውሳኔ ጥሶ የመለስ አገዛዝን የሚቃወሙ እንደ ግንቦት ስባት ያሉ ድርጅቶች መደገፉን ቢቀጥል ደግሞ፣ ግንቦት ሰባት ከሻዕቢያ ጋር ባለው ግንኙነት የማታ ማታ መመታቱ አይቀሬ ነው። መሳሪያና ድጋፍ የሚያገኘው ከሻዕቢያ ከሆነ፣ ሻዕቢያ ደግሞ በአለም አቀፉ ማህበረሰብ እቀባ ከተመታ፣ ምን አቅም ኖሮት ነው ሌሎችን ሊረዳና ሊደግፍ የሚችለው? ግንቦት ሰባት ከሻዕቢያ ጋር ሆኖ የሚያድርጋቸው ማናቸውም አይነት እንቅስቃሴዎች በአለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚወገዙ ነው የሚሆኑት። በዚህ ሁኔታ እንዴት ተደርጎ ነው በትጥቅ ትግል አይሎ መውጣት የሚቻለው?

 

ሶስተኛ ሊዘነጋ የማይገባው፣ እውን ሊሆን የሚችል አንድ ነገር አለ። ብዙዎች አቶ መለስና አቶ ኢሳያስ ውስጥ ውስጡን ግንኙነት እንዳላቸው ይናገራሉ። ምናልባት ዛሬ የደፈረሰው የሕወሃት/ኢሕአዴግ እና የሻዕቢያ ግንኙነት ነገ በቀላሉ ሊገነባ ይችላል። የታሪክ መጽሃፍት እንደሚያስነብቡን ሻዕቢያ ከዚህ በፊት ኢሕአፓን ይደግፍ ነበር። ኢሕአፓን ከድቶ ነው ወደ ሕወሃት የሄደው ይባላል። ነገም ኦነግ፣ ግንቦት ሰባት ወዘተረፈን ክዶ ከሕወሃት ጋር ቢተቃቀፍ እነ ግንቦት ሰባት የት ሊገቡ ነው?

 

ዶ/ር ጌታቸው በጋሻው በግልጽ እንዳስቀመጡት በኢትዮጵያ ሰላምና ዲሞክራሲ እንዲኖር፣ የኢትዮጵያን አንድነት የሚቀበል ማንኛውም አይነት ድርጅት፣ እራሱን ከሻዕቢያ ጥገኝነት በይፋ ማውጣት ይኖርበታል። ከሻዕቢያ ጋር ያለንን ግንኙነት በጥሰን፣ በሻዕቢያ እየተጎዳና እየታረዳ ካለው የኤርትራ ሕዝብ ጋር ግንኙነታቸን ማጠናከሩ የበሰለና የሚያዋጣ ፖለቲካ ነው። ”በአዲስ አበባም በአስመራም ያሉ ገዢዎች የሕዝብን መብት እንዲያከብሩ ሁሉቱንም እንታገላቸው” እላለሁ።

 

ከኦነግ ጋር እያደረገ ስላለው ውይይት ዶ/ር ብርሃኑ በሰጡት ትንተና እና ከአንባቢያ በቀረቡልኝ አስተያየቶች ዙሪያ ያተኮረ፣ የመጨረሻ ክፍል ሃተታዬን ይዤ እመለሳለሁ። በዚያን ወቅትም የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ቢወስዳቸው ይጠቅማሉ የምላቸውን የመፍትሄ ሃሳቦችንም ይዤ እቀርባለሁ። አላማዬ ግንቦት ሰባትን እና የግንቦት ሰባት አመራር አባላትን ለማጥቃት ወይንም ለማዳከም ሳይሆን፣ የያዙት መንገድ ውጤት እንዳላመጣና የትም እንዳማይደርሱ ለማሳየት፣ በዚህም ምክንያት ቆም ብለው እንዲያስቡና መንገዳቸውን እንዲመርመሩ ለመምከር ነው። እሰከዚያው ለሁላችንም ቸር ይግጠመን።

 

[1] የኢትዮጵያና የኤርትራ ዝምድናና የምሁራኑ ሚና እንዴት ነበር? አሁንስ ምን መሆን አለበት? - ፕ/ር ተስፋጽዮን መድሃኔ

[2] የኢትዮጵያ አንድነት ጥያቄ - ከኦነግና ሌሎች የዘር ድርጅቶች ጋር መነጋገርና መተባበር ለምን ያስፈልጋል? - ጌታቸው በጋሻው


ግርማ ካሣ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. 

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!