ግርማ ካሣ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

ትዝ ይለኛል በጥቅምት ወር 1984 ዓ.ም. አካባቢ ነበር፤ ሁለት ጓደኛምች በቸርችል ጎዳና፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጀርባ በሚገኘው የ”ትግላችን” ኃውልት ጋር ፎቶግራፍ ለመነሳት የቆሙት። (ይህ ኃውልት አሁን ይኑር አይኑር አላውቅም) እነዚህ ወጣቶች፣ የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ምስል የሚታይበትን ኃውልት አክብረው ሳይሆን እዚያ ቦታ ፎቶግራፍ ለመነሳት የቆሙት፤ ከኃውልቱ በስተግራ በኩል መሬቱ ላይ ተተክለው የነበሩ አበባዎች ማርከዋቸው ስለነበር ነው።

 

አረንጓዴ ቢጫ ቀይ አበባዎች መስመሩን በጠበቀ መልኩ ተተክለው የኢትዮጵያ ባንዲራ መሬቱ ላይ የተዘረጋ አስመስለውት ነበር።

 

በወቅቱ ኢትዮጵያዊነት እንደ ወንጀል፣ የኢትዮጵያ ባንዲራ ደግም እንደ ተራ ጨርቅ የሚቆጠርበት አሳዛኝ ወቅት ስለነበረ “ኢትዮጵያዊነታችንን የሚወስድብን ማንም የለም” ሲሉ ነበር ወጣቶቹ በወቅቱ ለነበረውና አሁንም ላለው የነአቶ መለስ/ስብኃት/በረከት አገዛዝ ተቃውሞዋቸውን የገለጹት። ጉዳዩ ከትግላችን ኃውልት ወይንም ከአበባዎቹ ሳይሆን ጉዳዩ ከኢትዮጵያዊነት ጋር ነበር።

 

ትዝ ይለኛል መስከረም 1 ቀን 1984 ዓ.ም.፣ የአበሻ ልብስ ለብሰው፣ አሁንም በቸርቸል ጎዳና ከፒያሳ ወደ ለገሃር ሲራመዱ የነበሩ አምስት ወጣት ወንዶች። መኪና ነጂዎች የመኪናቸውን ክላክስ እየነፉና በመስኮት እጃቸውን እያውለበለቡ፣ እግረኞች ደግሞ ሠላምታ እየሰጡ ለነዚህ አምስት ወጣቶች አክብሮታቸውን እና አድናቆታቸውን ይገልጹ ነበር።

 

ጉዳዩ ከወጣቶቹ ወይንም ከለበሱት የአበሻ ልብስ አልነበረም። ጉዳዩ ወጣቶቹ በለበሱት የአበሻ ልብስ የአንገትና የእጅ ዘርፍ ዙሪያ ተስፍተው በነበሩት - አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ቀለማት ባላቸው ጨርቆች ነበር። ጉዳዩ በወቅቱ ጥቃት ይደርስበት ከነበረው ከ”ኢትዮጵያዊነት” ጋር ነበር።

 

ግንቦት ሰባት 1997 ዓ.ም. በተደረገው ምርጫ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ በታሪኩ ታይቶ የማይታወቅ አስደናቂ ተዓምር ማሳየቱ ይታወሳል። እነ አቶ መለስ ዜናዊ ሥልጣን ከጨበጡ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያዊነትን ሲያጥላሉ፣ ዜጎች ለኢትዮጵያዊነት ሳይሆን ለጎጣቸው ቅድሚያ እንዲሰጡ ሲያደርጉ፣ ኢትዮጵያን እንደ አንዲት ሉዓላዊ አገር ሳይሆን እንደ ተራ ዕቃ ሲቆጥሯትና ሲቆራርጧት ዓመታት አሳልፈዋል።

 

ታዲያ በግንቦት ሰባት 1997 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ሕዝብ ያገኘውን ትንሽ ቀዳዳ በመጠቀም ነበር በማያዳግም ሁኔታ እቅጭ ቅልብጭ ያለውን ድምጹን የሰጠው። ለዓመታት ሲያደነቁረው የነበረውን የዘር ፖለቲካ “እጸየፈዋለሁ” ነው ያለው። በመቱ፣ በጎሬ፣ በአምቦ፣ በድሬዳዋ፣ በጎንደር፣ በጅጅጋ፣ በደብረ ብርሃን፣ በጎባ፣ በደሴ፣ በአዋሳ፣ … በየክልሎቹ በገጠርና በከተማ ኢትዮጵያዊነትን ነበር የመረጠው።

 

በምርጫ ዘጠና ሰባት ሕብረትና ቅንጅት በጋራ አሸናፊ እንደሆኑ ቢታወቅም ጉዳዩ ከቅንጅትም ሆነ ከሕብረት መሪዎች ጋር አልነበረም። ጉዳዩ ከ“ኢትዮጵያዊነት” ጋር ነበር።

 

የግንቦት ሰባቱ ቀን በጎላ መልኩ የሚያስታውሰን የኢህአዴግን መሸነፍ ወይንም የቅንጅትና ሕብረት ማሸነፍ ሳይሆን፤ የኢትዮጵያዊነት ማሸነፍን ነው። ለኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ቦታ የማይሰጥ፣ ኢትዮጵያውያንን በዘርና በኃይማኖት የሚከፋፍልና ኋላ ቀር የሆነ ፖለቲካ በኢትዮጵያ ቦታ እንዳማይኖረው ነው በማያሻማ ሁኔታ ግንቦት ሰባት ያሳየው።

 

መርሳት የሌለብን አንገብጋቢ ቁምነገር አለ። ግንቦት ሰባት የጉዞው መጨረሻ አይደለም። ተሰፋይቱ ምድር ገና አልደረስንም። ጎበዝ የአገሬ ልጅ፣ ፍርሃትንና ተስፋ መቁረጥን ከላያችን ላይ አውልቀን “ይቻላል!” በሚል ቁርጠኝነት አገራችንን ከመፈረካከስ፣ ከድህነት ከበሽታና ከጦርነት እናድን።

 

እኛ ካልተነሳን - ማን? አሁን ካልተነሳን - መቼ? ...

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!